Sunday, March 3, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሀብቱንና ትርፉን እያሳደገ የቀጠለው አዋሽ ባንክ

ተዛማጅ ፅሁፎች

አዋሽ ባንክ በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ለመገንባት ለጠየቀው ቦታ የሊዝ ክፍያ ፈጽሞ ጊዜያዊ ካርታ መረከቡና በ2015 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 9.8 ቢሊዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ፡፡ 

ባንኩ ለዋና መሥሪያ ቤቱ ሕንፃ ግንባታ የጠየቀው ቦታ ዋቢ ሸበሌ ሆቴል ፊት ለፊት የሚገኘውን የፌዴራል ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ኤጀንሲ ሲጠቀምበት የነበረው ቦታ ሲሆን፣ ቦታው እንደሚሰጠው ከተገለጸለት በኋላ ካርታ ሳይሰጠው ከሁለት ዓመታት በላይ ቆይቶ ነበር፡፡ ባለፈው ሳምንት ግን ለቦታው የተጠየቀውን የሊዝ ክፍያ በመክፈል ጊዜያዊ ካርታ በማግኘት ቦታውን በእጁ ማስገባት መቻሉን ባለፈው ቅዳሜ ኅዳር 15 ቀን የባንኩ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተገልጿል፡፡

የአዋሽ ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ጉሬ ኩምሳ ለጠቅላላ ጉባዔው አባላት ‹‹ሰበር ዜና›› ብለው እንደገለጹት፣ ለዋናው መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ የሚሆነውን ቦታ በጊዜያዊነት ፈቃድ ያገኙት ከጠቅላላ ጉባዔው መካሄድ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ነው፡፡

የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር በዕለቱ ቀድሞ በተዘጋጀው ሪፖርታቸው ላይ ‹‹የወደፊት የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታውን አስመልክቶ ባንኩ ከአዲስ አበባ አስተዳደር ጋር ግንኙነት በማድረግ የመገንቢያ ቦታ የተፈቀደልን ቢሆንም መሬቱን በእጃችን ላይ ለማስገባት ሌት ተቀን እየለፋን እንገኛለን፤›› ብለዋል፡፡

አያይዘውም በአሁኑ ወቅትም ቦታው ላይ የነበሩ ቤቶች እየፈረሱ ስለሆነ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሊዝ ፈርመን የቦታው ካርታ ይሰጠናል ብለን እየተጠባበቅን እንገኛለን›› በማለት ቀድሞ የተዘጋጁበትን ሪፖርት አቅርበው ነበር፡፡ ሆኖም ሪፖርቱ ከተዘጋጀ በኋላ አዲስ ሰበር ዜና አለን በማለት ለዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ አስተዳደሩ ጊዜያዊ ካርታ እንደሰጣቸው አስታውቀዋል፡፡

ይህንንም ‹‹በመጨረሻው ሰዓት በደረሰን መረጃ በትናንትናው ዕለት ሙሉ በሙሉ ሊዝ ከፍለን ጊዜያዊ ካርታ የተሰጠን ሲሆን ጊዜያዊውን ካርታ በቅርብ ቀን የምንቀበል ይሆናል›› በማለት መረጃውን ለጠቅላላ ጉባዔው ገልጸዋል፡፡

አዋሽ ባንክ ለሕንፃ መገንቢያው ከአስተዳደሩ ጊዜያዊ ካርታ ያገኘበት ቦታ የአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች በመባል የሚታወቀው ተቋም ሲገለገልበት የቆየ ሲሆን ቦታው ለአዋሽ መፈቀዱ ከተረጋገጠ በኋላ ኢንተርፕራይዙ ቦታውን እንደለቀቀ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በቦታው ላይ የነበሩ ግንባታዎችም እየፈረሱ መሆኑም ታውቋል፡፡

ባንኩ ይህንን ቦታ ለማግኘት ጥያቄ ካቀረበ ዓመታት የቆየ ቢሆንም አሁን ግን ቦታውን ስለማግኘቱ እርግጠኛ መሆን በመቻሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ አዲሱን የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ ለመጀመር ወደሚያስችለው ሥራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ባንኩ ስለሚገነባው አዲስ ሕንፃ ከዚህ ቀደም ከሪፖርተር ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት የአዋሽ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፀሐይ ሽፈራው በአዲስ አበባ የሚገነቡት ሕንፃ የአዋሽ ባንክ በሚመጥን ደረጃ የሚገባ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡ ይህም በአዲስ አበባ ከተማ ረዥሙን ሕንፃ ሊገነባ እንደሚችል የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡

አዋሽ ባንክ በኢትዮጵያ ከግል ባንኮች የመጀመርያ የሚባለውን የራሱን ሕንፃ ከእህት ኩባንያው አዋሽ ኢንሹራንስ ጋር የገነባው ከ20 ዓመታት በፊት ሲሆን ይህ ሕንፃ አሁን ካለው የባንኩ ዕድገት ጋር የማይመጣጠንና የዋና መሥሪያ ቤቱን ሥራ በተበታተነ ቦታ እንዲሠራ ያስገደደው በመሆኑ አዲሱን ሕንፃ በቶሎ ለማስጀመር ፍላጎት ያለው መሆኑ ታውቋል፡፡

ባንኩ አሁን የሚጠቀምበትን ሕንፃ በወቅቱ ቫርኔሮ በተባለው ተቋራጭ በ340 ሚሊዮን ብር ያስገነባው እንደነበር አይዘነጋም፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ አዋሽ ባንክ በተጠናቀቀው የ2015 የሒሳብ ዓመትም ከአገሪቱ የግል ባንኮች ቀዳሚ የሚያደርገውን ከፍተኛ ትርፍ ማትረፉን አስታውቋል፡፡ በቅዳሜው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ባንኩ ከታክስ በፊት 9.8 ቢሊዮን ብር ከታክስ በኋላ ደግሞ 7.2 ቢሊዮን ብር እንዳተረፈ ያስታወቁት የቦርድ ሊቀመንበሩ ይህም ከታክስ በፊት ያስመዘገበው የትርፍ መጠን በ2.3 ቢሊዮን ብር ወይም በ31 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑ አለው፡፡

ይህ የትርፍ መጠን በአገሪቱ የግል ባንኮች ታሪክ ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ በትርፍ ሆነ በእሴት፣ በተቀማጭ ገንዘብና በሌሎች አፈጻጸሞቹ አሁንም ቀዳሚ ሆኖ እንዲቀጥል እንደቻለው የቦርድ ሊቀመንበሩ በሪፖርታቸው ውስጥ በተለያየ መንገድ ጠቅሰዋል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ያገኘው የተጣራ ትርፍም አንድ ሺሕ ብር ዋጋ ያለው አንድ አክሲዮን 577 ብድር የትርፍ ድርሻ አስገኝቷል፡፡ በ2014 የሒሳብ ዓመት ባንኩ አንድ አክሲዮን ያስገኘለት የትርፍ ድርሻ ክፍፍል መጠን 570 ብር በመሆኑ በ2015 ያገኘው ብልጫ እንዳለው አመላክቷል፡፡

ባንኩ የ2015 የሒሳብ ዓመት የተቀማጭ ገንዘቡ መጠኑን በ23 በመቶ በማሳደግ ወይም በ35.4 ቢሊዮን ብር ጭማሪ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ በመቻሉ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑ 187.4 ቢሊዮን ብር ሊደርስ ችሏል፡፡

ባንኩ የደረሰበት የተቀማጭ ገንዘብ መጠን በባንኩም ሆነ በአገሪቱ የግል ባንኮች ታሪክ ከፍተኛ የሚባል ስለመሆኑም ተጠቅሷል፡፡ ባንኩ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የሰጠው የብድር መጠንም በ22.3 በመቶ አድጓል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ብቻ 40.9 ቢሊዮን ብር አዲስ ብድር የሰጠው አዋሽ ባንክ ይህም አጠቃላይ የብድር ክምችቱን ከ162 ቢሊዮን ብር በላይ አድርሶታል፡፡ ከሰጠው ብድር ውስጥ ከፍተኛውን መጠን የያዘው የአገር ውስጥ ንግድ ንግድና አገልግሎት ሲሆን ከተሰጠው ጠቅላላ ብድር 24 በመቶን ድርሻ ይይዛል፡፡ የባንኩ የሀብት መጠን ወደ ሩብ ትሪሊዮን የተጠጋ ሲሆን ከቀዳሚው ዓመት በ40.9 በመቶ ዕድገት ያሳየ ሆኗል፡፡

አዋሽ ባንክ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ የሀብት መጠኑን እያሳደገባቸው ካሉ ኢንቨስትመንቶቹ ውስጥ አንዱ በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች የoነባቸውና እየገነባቸው ያሉ ሕንፃዎች ናቸው፡፡ እስካሁንም በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ከ15 በላይ የራሱ ሕንፃዎችን ገንብቶ አጠናቋል፡፡

በቅርቡ አጠናቆ ለሥራ ዝግጁ ካደረጋቸው ሕንፃዎች መካከል በባሌሮቢ ባለአራት ወለል ሕንፃ፣ አንዱ ነው፡፡ በአሰላ እየተገነባ ያለው ባለአምስት ወለል ሕንፃም እየተናቀቀ ነው ተብሏል፡፡

ሕንፃዎቹ ሌላ በድሬዳዋ፣ በአምቦ፣ በወሊሶ፣ በአሶሳ፣ በቦንግ፣ በቡራዩ በቢሾፍቱና በየቡ ከተሞች ለሚገነባቸው አዳዲስ ሕንፃዎች የስትራክቸራል ዲዛይኖችን ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እየገነባቸው ካሉ ሕንፃዎች ቡልቡላ ሕንፃ የሚል መጠሪያ ያለው ባለ G+13 ሕንፃ ግንባታ ሥራ ተቋርጦ ቆይቷል፡፡ የቦርድ ሊቀመንበሩ በቅዳሜው ሪፖርታቸው የቡልቡላ ሕንፃ ከተቋራጩ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ሥራው የቆመ ቢሆንም ግንባታውን ለማስቀጠል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ከፍተኛ አፈጻጸም ያገኘበትና ከሌሎች የግል ባንኮች አንፃር ሲታይ በልዩነት የሚጠቀሙ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ ሲሆን፣ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ባንኩ ከተለያዩ የውጭ ምንዛሪ ግኝቶቹ ከ1.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ያገኘ ሲሆን ይህ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከቀዳሚው ዓመት ከ250 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዕድገት የታየበት እንደሆነ ታውቋል፡፡

የባንኩ አጠቃላይ የሀብት መጠን 24 ቢሊዮን ብር በላይ የደረሰ ሲሆን የተከፈለ ካፒታልም ከ42 በመቶ በላይ ጭማሪ በማሳየት 15 ቢሊዮን ብር ማድረስ ችሏል፡፡ ይህ የተከለ ካፒታል መጠንም በኢንዱስትሪው ከግል ባንኮች ከፍተኛው በመሆን የሚጠቀስ ነው፡፡ አዋሽ ባንክ ዓመታዊ ገቢ መጠንም ከፍተኛ የሚባል ዕድገት ያስመገበበት ዓመት ነው፡፡ በሪፖርቱ እንደተመለከተውም በዓመቱ ውስጥ ያገኘው ጠቅላላ ገቢ 28.8 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህ ገቢ ከቀዳሚው ዓመት በ8.2 ቢሊዮን ብር ወይም በ40 በመቶ አድጓል፡፡

ዓመታዊ ወጪውም በ44 በመቶ ስለመጨመሩና የዓመቱ አጠቃላይ ወጪው 19.1 ቢሊዮን ብር ሲሆን ይህም ከቀዳሚው ዓመት የ5.9 ቢሊዮን ብር ጭማሪ ማሳየቱም ታውቋል፡፡

አዋሽ ባንክ ከ1983 ወዲህ በኢትዮጵያ የመጀመርያው የግል ባንክ በመሆን ሥራ የጀመረ ሲሆን በ2017 ዓ.ም. 30ኛ ዓመቱን ለማክበር በመዘግጀት ላይ ነው፡፡

ባንኩ በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ ከ875 በላይ ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን የሠራተኞቹም ቁጥር ከ20 ሺሕ በላይ ደርሷል፡፡ የባንኩ ጠቅላላ ባለአክሲዮኖችም ከ6,500 በላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች