Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሥራችን ላይ እንቅፋት ፈጥሮብናል›› አቶ ያዕቆብ ወልደ ሥላሴ፣ የሮያል ፎም ስፕሪንግ ፍራሽና የፕላስቲክ ውጤቶች ማምረቻ የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢትዮጵያ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል በኢንቨስትመንት ዘርፉ የተሰማሩ ተቋሞችን መደገፍ የግድ እንደሚል ይታመናል፡፡ መንግሥት ሊያደርግ ከሚችለው ድጋፍ አንዱ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን ማሳደግና ለውጭ ምንዛሪ ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ ዘርፎችን ማጠናከር ይገኝበታል፡፡ በኢንቨስትመንት ዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት በውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዳይፈተኑ መንግሥት ትልቁን ድርሻ መወጣት ቢኖርበትም፣ ችግሩ በሁሉም ዘርፍ የተሰማሩትን እየፈተነ ይገኛል፡፡  በችግሩ ከተነኩ ተቋማት አንዱ ሮያል ፎም ነው፡፡ ሮያል ፎም ይህንን ችግር ለማለፍ ምርቶቹን ወደ ተለያዩ አፍሪካ አገሮች እየላከ ይገኛል፡፡ በዋናነት ፍራሽ፣ ፈርኒቸር፣ ቡና፣ የቅባት እህልና ሌሎች ምርቶችን በማምረት ለአገሪቱ ኢኮኖሚ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው፡፡ አቶ ያዕቆብ ወለደ ሥላሴ የድርጅቱ የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው፡፡ የድርጅቱን ሥራ በተመለከተ ተመስገን ተጋፋው አነጋግሯቸዋል፡፡

‹‹የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሥራችን ላይ እንቅፋት ፈጥሮብናል›› አቶ ያዕቆብ ወልደ ሥላሴ፣ የሮያል ፎም ስፕሪንግ ፍራሽና የፕላስቲክ ውጤቶች ማምረቻ የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ሪፖርተር፡- ሮያል ፎም ስፕሪንግ ፍራሽና የፕላስቲክ ውጤቶች ማምረቻ ድርጅት እንዴት ተመሠረተ?

አቶ ያዕቆብ፡- ሮያል ፎም ግሩፕ ወደ ኮርፖሬት ግሩፕ ከመምጣቱ በፊት በ2002 ዓ.ም. የተመሠረተ አገር በቀል ኢንቨስትመንት ነው፡፡ ከተመሠረተ ከአሥራ አምስት ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ድርጅት መሥራች አቶ ኢዮብ ንጉሤ ናቸው፡፡ ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ ከፎምና ከቤት ዕቃዎች (ፈርኒቸር) ምርት በተጨማሪ፣ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ውስጥ በመሠማራት አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል፡፡ በተለይ ቡናና የቅባት እህሎችን ወደ ውጭ አገር በመላክ፣ የራሱን አስተዋጽኦ እያበረተከ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሮያል ፎም ሪል ስቴት፣ ኮንስትራክሽን፣ ሆቴል፣ ጨርቃ ጨርቅ እንዲሁም አውቶሞቲቪ ኢንዱስትሪው ውስጥ በመሰማራት የውጭ ምንዛሪን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ላይ ይገኛል፡፡ ከ700 በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት የራሱን ድርሻ መወጣት ችሏል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመወዳደር ምርቶቹን በተለፈገው ልክ በማምረት ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ማድረግ ችሏል፡፡  

ሪፖርተር፡- ድርጅታችሁ ምን ዓይነተ አገልግሎትን እየሰጠ ነው?

አቶ ያዕቆብ፡- ድርጅቱ በዋናነት የትኩረት አቅጣጫውን አድርጎ የሚሠራው በማምረት ዘርፍ በመሰማራት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በርካታ አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል፡፡ ሮያል ፎም ያመረታቸውን ምርቶች አገር ውስጥ ከመሸጥ በተጨማሪ ወደ ተለያዩ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ምርቶቹን እየላከ ይገኛል፡፡ በቅርቡም የፍራሽና የቤት ዕቃ ምርቶቹን ለመላክ ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡ የፍራሽ ምርቶችንም ከአዲስ አበባ ውጪ በኦሮሚያና በድሬዳዋ ፋብሪካ በመክፈት ተደራሽ እያደረገ ይገኛል፡፡ በተለይ ጥራት ያለው ምርት በማምረት የማኅበረሰቡን ፍላጎት ለማሟላት የበኩሉን ጥረት እያደረገ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ድርጅታችሁ ከተቋቋመ አሥራ አምስት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ሥራችሁ ላይ ምን ዓይነት ችግር ገጥሟችኋል?

አቶ ያዕቆብ፡- በኢንዱስትሪው ውስጥ በርካታ ችግሮች ይኖራሉ፡፡ ለአብነት ያህል ብናይ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ገጥሞናል፡፡ ድርጅቱ የአብዛኛውን ጥሬ ዕቃ የሚያመጣው ከውጭ ነው፡፡ በመሆኑም የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሥራችን ላይ እንቅፋት ፈጥሮብናል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ድርጅቱ ምርቶቹን በአገር አቀፍ ደረጃ ለማስፋፋት ቢፈልግም የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግር ሆኖብናል፡፡ ከውጭ ምንዛሪ ባሻገር ድርጅቱ በሚሠራባቸው ቦታዎች ንቁ የማኅበረሰብ ተሳትፎ አለው፡፡ ይህም ከመንግሥት በኩል በቂ የሆነ ድጋፍ እንዲያገኝ አስችሎታል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ምርቶችን ወደ ውጭ አገር ለመላክ ጥራት አንዱና ዋነኛው መሥፈርት ስለሆነ፣ ድርጅቱ ይህንን ተግባራዊ እያደረገ መገኘቱ ከውጭ ምንዛሪ ውጪ ያሉ ችግሮችን እንድንቋቋም እየረዳን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅታችሁ ከሌሎች ተቋሞች ጋር ቅንጅት ፈጥሮ እየሠራ ይገኛል፡፡ ሥራችሁ ምን ይመስላል?

አቶ ያዕቆብ፡- እንደ ማኅበር የራሳችን የሆነ አሠራር ተግባራዊ እናደርጋለን፡፡ በተለይም ከመንግሥታዊ ተቋማት ጋር ቅንጅት በመፍጠር ከ150 በላይ ሕፃናትንና አረጋውያንን በየወሩ የምንደግፍበት መርሐ ግብር እያከናወንን እንገኛለን፡፡ ተቋሙ ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ በቋሚነት ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል የተቋሙ ድርጅቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ውስጥ ለውስጥ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎችን በማከናወን የበኩላችንን እየተወጣን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት ምን ዓይነት ድጋፍ አድርጎላችኋል?

አቶ ያዕቆብ፡-  መንግሥት ለዘርፉ ብዙ ድጋፎችን እያደረገልን ይገኛል፡፡ በተለይ ወደ አገር ውስጥ ለምናስገባቸው ማሽነሪዎች የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎችን እየሰጠን ይገኛል፡፡ ለማምረቻም የሚሆኑ ቦታዎችን በምንጠይቅበት ጊዜ ተገቢውን ምላሽ እየሰጠን ነው ማለት ይቻላል፡፡ በተሰጠን ቦታ በርካታ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ ፋብሪካዎችን በመገንባት የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራን እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- በቀጣይ ምን ለመሥራት አስባችኋል?

አቶ ያዕቆብ፡- በቀጣይ ሮያል ፎም ከሚሰጣቸው አገልግሎቶቹ በተጨማሪ በአዋሳና በአዳማ ፋብሪካዎችን ለማቋቋም ዕቅድ ይዘን እየሠራን እንገኛለን፡፡ በሐዋሳ ከተማ ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች መገጣጠሚያ ፋብሪካ ለመገንባት እየሠራን ነው፡፡  በአዳማ ኢንዱስትሪ ዞን ከመንግሥት ሼዶችን በመውሰድ ከ600 በላይ ማሽነሪዎችን በመትከል የካልሲ ማምረቻ ፋብሪካ ለመትከል ዕቅድ ይዘናል፡፡ ሮያል ፎምና ፈርኒቸር ምርቶችን ወደ ተለያዩ የአፍሪካ አገሮች በመላክ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለማስቀረት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያም ያለውን ስምና ዝና ለማስፋት አርቲስትና የኢቢኤስ ቲቪ የፕሮግራም አቅራቢ ሉላ ገዙን የተቋሙ ብራንድ አምባሳደር አድርጎ ሾሟታል፡፡ ይህም ሹመት ለቀጣይ አራት ዓመታት የሚቀጥል ይሆናል፡፡  

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እስከ ግለሰቦች የሚደርሰው ወገን ፈንድ

ወገን ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ሕጋዊ ዕውቅና በማግኘት ከኢትዮጵያና ከተለያዩ አገሮች ልገሳን ለማሰባሰብ ‹‹ወገን ፈንድ›› የሚባል የበይነ መረብ (ኦንላይን) የድጋፍ ማሰባሰቢያ ድረ...

ግዴታን መሠረት ያደረገ የጤና መድኅን ሥርዓት

የኢትዮጵያ ጤና መድኅን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ማኅበረሰብ አቀፍና የማኅበራዊ ጤና መድኅን ሥርዓቶችን መሠረት አድርጎም ይሠራል፡፡ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ሥርዓት በኢመደበኛ...

የመሠረተ ልማት ተደራሽነት የሚፈልገው የግብርና ትራንስፎርሜሽን

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ተቋም አርሶ አደሩን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በማድረግ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚውን የማሳደግ ዓላማ ይዞ የተመሠረተ ነው፡፡ ተቋሙ የግብርናውን ዘርፍ ሊያሳድጉ የሚችሉ ጥናቶችን...