Monday, February 26, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

‹‹የኦጋዴን የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት ብዙ ሰው የሚመላለስበትና የሚተራመስበት ሆኗል›› የማዕድን ሚኒስቴር

ተዛማጅ ፅሁፎች

  •  የማዕድን ፈቃድ አየር በአየር ሽያጭ መንሰራፋቱና የማዕድን ፖሊስ መቋቋሙ ተገልጿል

የኦጋዴን የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት ላይ በዙ ሰዎች ይመላለሳሉ፣ ይተራመሳሉ እንጂ የተፈጥሮ ሀብቱን ማምረት አልተቻለም ሲሉ የማዕድን ሚኒስትሩ ተናገሩ።

የሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸማቸውን ሰኞ ኅዳር 17 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረቡት የማዕድን ሚኒስትሩ ሀብታሙ ተገኝ (ኢንጂነር)፣ በሶማሌ ክልል ኦጋዴን ዞን የተገኘው የተፈጥሮ ጋዝ ተመርቶ አገሪቱ ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻለች አስረድተዋል።

‹‹የኦጋዴን የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት ብዙ ሰው የሚመላልስበትና የሚተራመስበት ሆኗል፣ ነገር ግን ምንም ምርት ማምረት አልተቻለም›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ‹የፈለገውን ይፍጅ እንጂ ለትክክለኛውና አቅም ላለው ኩባንያ ነው መስጠት የሚገባን ብለን ወስነናል፤›› ሲሉም ተደምጠዋል።

የፕሮጀክቱን መረጃዎችና እውነታዎች ለማረጋገጥ፣ ሥጋቶችና የንግድ አዋጭነቱን ለመገምገም እንኳ በመቸገር ስድስት ወር እንደፈጀ፣ ብዙ ውይይቶችን ከብዙ የመንግሥት ተቋማት ጋር በማድረግ በአሁኑ ወቅት ግን እንደተጠናቀቀ ተናግረዋል።

የተፈጥሮ ጋዝ የዩሪያ ማዳበሪያ ፍላጎትን በአገር ውስጥ ለማምረትና ለማሟላት የሚያስችል ቢሆንም ኢንቨስትመንቱ ከ1.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚፈጅ የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ነገር ግን መንግሥት የፈጀውን ፈጅቶ እንዲፈጸም አቅጣጫ ማስቀመጡን ተናግረዋል።

በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች በተለይም በግልና በመንግሥት አጋርነት ለመተግበር ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ፣ ነገር ግን ከሁሉ በፊት የተፈጥሮ ጋዝን ማምረት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

የተፈጥሮ ጋዝ በሶማሌ ክልል ኦጋዴን ዞን ካሉብና ኢላላ በተባሉ አካባቢዎች ከተገኘ ከ15 ዓመታት በላይ የተቆጠረ ሲሆን፣ የተፈጥሮ ጋዝ መኖሩን ያረጋገጠው ፔትሮናስ የተባለው የማሌዢያ ኩባንያ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ኩባንያ በዚሁ አካባቢ የነዳጅ ክምችት መኖሩን የሚጠቁሙ ፍንጮች በመመልከቱ የተፈጥሮ ጋዙን ማውጣት በማዘግየት ነዳጅ ፍላጋው ላይ በርካታ ሚሊዮን ዶላሮችን ካፈሰሰ በኋላ ሳይሳካለት ከአካባቢው ለቆ ወጥቷል።

ይህንን ተከትሎም መንግሥት ፔትሮ ትራንስ ለተባለ የቻይና ኩባንያ የተፈጥሮ ጋዝ እንዲያወጣ ፈቃድ የሰጠ ቢሆንም፣ ኩባንያው ለዓመታት ከቆየ በኋላ በቂ ፋይናንስ ማግኘት ባለመቻሉ ውሉ ተቋርጦ ፈቃዱ ተነጥቋል።

በመቀጠል የገባው ፖሊ ጂሲኤል የተባለ የቻይና ኩባንያ ሲሆን፣ ኩባንያው የተፈጥሮ ጋዙን ለማምረትና ወደ ጂቡቲ ወደብ የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያ ለመዘርጋት የተለያዩ ስምምነቶች ማድረጉን ካስነገረ በኋላ ትኩረቱን ቀይሮ ነዳጅ ፍለጋ ላይ በመሰማራቱ የተፈጥሮ ጋዝ ማምረት አልተቻለም።

ይህ የቻይና ኩባንያ እ.ኤ.አ. በ2018 በኦጋዴን ዞን ነዳጅ ማግኘቱን መግለጹና ይህንንም መረጃ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳይቀር በደስታ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል። ነገር ግን ኩባንያው የተፈጥሮ ጋዙንም ሆኑ አገኘሁ ያለውን ነዳጅ ሳያመርት ውሉ ተቋርጧል።

ተገኘ የተባለው ነዳጅ ከምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ማብራሪያ እንዲሰጡ በምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አባላት የተጠየቁት የማዕድን ሚኒስትሩ ሀብታሙ ተገኝ (ኢንጂነር)፣ ‹‹የኦጋዴን የነዳጅ ሀብት መጠን ግልጽ አይደለም፤›› ብለዋል።

‹‹ኩባንያው ያወቀው የነዳጅ ሀብት መጠን ምን ያህል እንደሆነ ዝርዝሩን እናያለን፣ ነገር ግን ያለ ማዕድን ሚኒስቴር ፈቃደ ነዳጅ ማውጣት እንደማይቻል ቋሚ ኮሚቴው እንዲረዳ እንፈልጋለን፤›› ብለዋል።

የማዕድን ሥራ ላይ ተሰማርተው የማያውቁና አቅም የሌላቸው የውጭና የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ጭምር የማዕድን ፍለጋ ፈቃድ በማውጣት ክምችት ያለባቸውን አካባቢዎች የመያዝና የመቀራመት ሥራ ተንሰራፍቶ መቆየቱንም አስረድተዋል።

በዚህም አማካይነት ምንም ሳይሠሩ የተሰጣቸውን የማዕድን ፈቃድ በአየር ላይ የመሻሻጥ ሥራ ላይ ተስማርተው እንደነበር የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ‹‹በፖታሽ ማዕድን ላይ የታየው ይህ ችግር ነው›› እንደ አንድ ማሳያ ጠቅሰዋል።

የፖታሽ ማዕድን ፍለጋና የማምረት ፈቃድ ወስደው በአፋር ክልል ተስማርተው የነበሩ ኩባንያዎች የማዕድን ፈቃድ አየር ላይ መገበያየታቸውና በኋላም መንግሥት ለሽያጩ ዕውቅና ባለመስጠቱ በዓለም አቀፍ የግልግል ፍርድ ቤት መንግሥት ላይ ክስ የመሠረቱ ኩባንያዎች መኖራቸውን ሪፖርተር ከዚህ ቀደም መዘገቡ ይታወሳል። ከእነዚህ ኩባንያዎች መካከል አንዱ አይሲኤል የተባለ የአስራኤል ኩባንያ ተጠቃሽ ነው።

‹‹አሁን ይህንን ያልተገባ አካሄድ በማስቆም አቅምና በዘርፉ ልምድ ላላቸው ኩባንያዎች ብቻ ፈቃድ እንዲሰጥ ማድረግ ጀምረናል›› ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት የማዕድን ዘርፉን በዋነኝነት እየፈተኑ የሚገኙት የኮንትሮባንድ ንግድና የፀጥታ ችግሮች መሆናቸውን የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ችግሩን ለመፍታትም የማዕድን ፖሊስ ለማቋቋም በመንግሥት ደረጃ መወሰኑን ተናግረዋል።

ይህንን ዘርፍ ከፀጥታ ሥጋትና ከኮንትሮባንድ ለመጠበቅ የማዕድን ፖሊስ ማቋቋም አስፈላጊነት ታምኖበት በዚህ ላይ ብቻ የሚሠራ የማዕድን ፖሊስ ለመመሥረት ከፌዴራል ፖሊስ ጋር የዝግጅት ሥራዎች መጀራቸውን ገልጸዋል።

‹‹በደርግ ሥርዓት ወቅት የማዕድን ፖሊስ የሚባል ነበር፡፡ ነገር ግን የማዕድን ዘርፍ ብዙም አስፈላጊ አይደለም የሚል እምነት በወቅቱ በመፈጠሩ ነው የፈረሰው›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ በአሁኑ ወቅት ግን ይህንን አደረጃጀት መመለስ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ተናግረዋል።

ይህ የፖሊስ አደረጃጀት በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች የሚሰማራ ሳይሆን በዋና ዋና የማዕድን ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግም ገልጸዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች