Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየሕዝብ ጉዳዮች ከዳኝነት ክፍያ ነፃ ካልሆኑ ዜጎች ፍትሕ የማግኘት መብታቸውን ያጣሉ ተባለ

የሕዝብ ጉዳዮች ከዳኝነት ክፍያ ነፃ ካልሆኑ ዜጎች ፍትሕ የማግኘት መብታቸውን ያጣሉ ተባለ

ቀን:

  • ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤቱታ ቀርቧል

በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተዘጋጅቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው፣ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ክፍያን ለመወሰን በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ተካቶ የቀረበው፣ የሕዝብ ጥቅም ለማስከበር ለፍርድ ቤት የሚቀርቡ ክርክሮች (ጉዳዮች) ከክፍያ ነፃ እንዲሆኑ የሚደነግግ አንቀጽ የማይካተትና ክፍያ የሚፈጸምባቸው ከሆነ፣ ዜጎች በሕገ መንግሥቱ ያገኙትን ፍትሕ የማግኘት (Access to Justice) መብትne የሚያሳጣ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ለሕዝብ ጥቅም ተብሎ ፍርድ ቤት የሚቀርብ ሙግት የግለሰቦችን ጥቅም ለማስከበር እንደሚቀርብ መደበኛ ክርክር ተቆጥሮ, የዳኝነት ሊከፈልበት እንደማይገባ ‹‹ቁም ለአካባቢ›› “Defend the Environment” የተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለጠቅላይ ፍርድ ቤትና ለሌሎችም የሚመለከታቸው ተቋማት አቤቱታ አቅርቧል፡፡

ረቂቅ ደንቡ አንቀጽ 5(1) የተደነገገው፣ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ለሚሰጡት አገልግሎት የዜጎችን ፍትሕ የማግኘት መሠረታዊ መብትን ‹‹በማይጋፋ መልኩ›› ተመጣጣኝ የሆነ የዳኝነት ክፍያ እንዲያስከፍሉ፣ የሚለው ድንጋጌ፣ የደንቡን ዓላማዎች ለማሳካት ከዋና ዋናዎቹ መሣሪያዎች መካከል አንዱ ለሕዝብ ጥቅም ተብሎ በፍርድ ቤት የሚቀርበው ክርክር፣ የግለሰቦችን ጥቅም ለማስከበር እንደሚቀርበው መደበኛ ክርክር ተቆጥሮ የዳኝነት እንዲከፈልበት የሚያስገድድ መሆኑን አብራርቷል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከረቂቅ ደንቡ ዓላማ አንፃር፣ ዜጎች ፍትሕ የማግኘት መብታቸውን ለመጠቀም ዕድሉን በመነፈጋቸው፣ የሌሎችን የሕግ ድጋፍ የሚፈልጉ ዜጎችን የሚጎዳና ለዜጎች መብቶች መከበር ዕውቀትና ልምዳቸውን ለማበርከት ዝግጁ የሆኑ የሕዝብ ጥቅም ተሟጋቾችን የማያበረታታና የሚያሸሽ መሆኑን ድርጅቱ በደብዳቤው አብራርቷል፡፡

ከሕግ ማዕቀፍ ረገድ ለሕዝብ ጥቅም ተብሎ የሚቀርቡ ክርክሮች (Public Interest Litigation) ከፍትሐ ብሔር ጉዳዮች የሚመደቡ በመሆናቸው፣ የጉዳዩን ልዩ ባህሪ ከግምት የሚያስገባ የተለየ የሥነ ሥርዓት ሕግ ባለመኖሩ፣ መደበኛው የሕግ ሥነ ሥርዓት ሕግ ተፈጻሚ እየሆነ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ በመሆኑም አንዳንድ የግል ጉዳይ ወይም የሌላውን ግለሰብ ጥቅም ለማስጠበቅ፣ የፍትሐ ብሔር ጉዳይ ይዞ ፍርድ ቤት ከሚሄድ ወኪል የሚጠበቀው ከፍተኛ ትጋትና ሌሎች ጫናዎችን በባለጉዳዮች ላይ የሚጥለው መደበኛው የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ፣ ከራሳቸው አልፈው ለሌላው ሰው ጥቅም ለሚሠሩ የሕዝብ ጥቅም ተሟጋቾች ላይም ጫና እያሳረፈ ነው፡፡ በአገሪቱ ባለው ተጨባጭ ሁኔት የሕዝብ ጥቅም ለማስከበር ክርክሮችን ፍርድ ቤት ይዘው የሚሄዱ የሕዝብ ጥቅም ተሟጋቾች (Public Interest Litigator) የፍርድ ቤት የዳኝነት ክፍያ፣ የምስክሮች፣ የሰነዶች ትርጉም፣ የጽሕፈት፣ በፍርድ ቤት የሚታዘዙ የተለያዩ ኪሳራዎችና ሌሎች ወጪዎችን እንዲከፍሉ መደረጉ ተገቢ አለመሆኑን ድርጅቱ ገልጿል፡፡ በተጨማሪም ባለሙያዎቹ በተለያዩ ምክንያቶች የፍርድ ቤት ቀጠሮ ሲያመልጣቸው (ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የሚደረገው ክርክር ቀጠሮ) የግል ጉዳያቸው እንደሆነ በማሰብ፣ የያዙት ጉዳይ ልዩ ባህሪ ከግምት ውስጥ ሳይገባ መደበኛው ፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ተፈጻሚ መደረጉ ተገቢ አለመሆኑንም አክሏል፡፡

በረቂቅ ደንቡ መካተት የሚገባቸውና ለሕዝብ ጥቅም አጋዥ የሚሆኑ ድንጋጌዎች ካልተካተቱ፣ በሕግ ዘርፍ ዕውቀትና ልምድ ኖሯቸው በበጎ ፈቃደኝነት ሕዝብን ለማገልገል ፍላጎት ያላቸውን በርካታ ባለሙያዎች እንዲሸሹ የሚያደርግ መሆኑንም ድርጅቱ አብራርቷል፡፡

ከዳኝነት ክፍያ ጋር በተገናኘ አገሮች እንደየራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ በሕዝብ ጥቅም ላይ ለሚቀርቡ ክርክሮች ተሟጋቾች ባደላ መልኩ፣ የተለያዩ መንገዶችን የሚከተሉ መሆኑን በርካታ ጥናቶችና ልምዶች እንደሚያሳዩ የጠቆመው ቁም ለአካባቢ ድርጅት፣ የሕዝብን ጥቅም ለማስከበር የሚቀርቡ ክርክሮችን ከዳኝነት ክፍያ ሙሉ በሙሉ ነፃ ማድረግ፣ ከፊሉን መቀነስ፣ በክርክሩ ውጤት ላላመጡና ለሕዝብ ጥቅም ተሟጋቾች ማበረታቻዎችን መስጠት መሆኑን አስረድቷል፡፡

በመሆኑም ረቂቅ ደንቡን ያዘጋጀው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትና ደንቡን የሚያፀድቀው የሕዝብ ተወከዮች ምክር ቤት፣ የጉዳዩን አስፈላጊነት በመገንዘብና ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ የሕዝብን ጥቅም ለማስከበር ፍርድ ቤት የሚቀርቡ ጉዳዮችን (Public Interest Litigation) ከዳኝነት ክፍየ ነፃ የሚያደርጉና ለሕዝብ ጥቅም ተሟጋቾች ላይ ያለውን ጫና በመቀነስ፣ የዜጎችን ፍትሕ የማግኘት ዕድል የሚያሰፉ ድንጋጌዎች እንዲካተቱበት ጠይቋል፡፡

በረቂቅ ደንቡ እንደተገለጸው፣ ከዝቅተኛው የክስ ገንዘብ መጠን 20 ሺሕ ብር የዳኝነት አሥር በመቶ ጀምሮ፣ ከከፍተኛው የክስ ገንዘብ መጠን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ሲሆን፣ አንድ በመቶ የዳኝነት እንደሚከፈል የደነገገው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ክፍያን ለመወሰን የወጣው ረቂቅ ደንብ በፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 55(1) ድንጋጌ መሠረት በ23 አንቀጾች ተዘጋጅቶ በ2015 ዓ.ም. ተዘጋጅቶ ለውይይት የቀረበ ረቂቅ ደንብ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...