Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናወርቅ እንዲያመርቱ ፈቃድ ከተሰጣቸው 13 ኩባንያዎች ሁለቱ ብቻ ሥራ መጀመራቸው ተነገረ

ወርቅ እንዲያመርቱ ፈቃድ ከተሰጣቸው 13 ኩባንያዎች ሁለቱ ብቻ ሥራ መጀመራቸው ተነገረ

ቀን:

በፌዴራል ደረጃ ፈቃድ ከተሰጣቸው 13 የማዕድን ኩባንያዎች ውስጥ በ2016 ዓ.ም. ሩብ ዓመት ሁለቱ ብቻ እያመረቱ መሆናቸውን፣ ቀሪዎቹ 11 ኩባንያዎች በስድስት ወራት ውስጥ ወደ ሥራ ካልገቡ ዕርምጃ እንደሚወሰድባቸው የማዕድን ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ ይህንን ያስታወቀው ኅዳር 17 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የ2016 በጀት ዓመት የሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ሲያቀርብ ነው፡፡

የ2016 በጀት ዓመት ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለቋሚ ኮሚቴው ያቀረቡት የማዕድን ሚኒስትሩ ሀብታሙ ተገኝ (ኢንጂነር)፣ ወርቅ እንዲያመርቱ ፈቃድ የተሰጣቸው 13 ኩባንያዎች ቢሆኑም፣ ያመረቱት ሚድሮክ ጎልድና ስቴላ የማዕድን አውጪ ኩባንያዎች ብቻ ናቸው ብለዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከሁለቱ የወርቅ አምራች ኩባንያዎች የተሻለ አፈጻጸም ያለው ሚድሮክ ጎልድ መሆኑንና በመቀጠል ስቴላ የተሰኘው ማዕድን ኩባንያ እንደሆነ ገልጸው፣ የተቀሩት ግን በሩብ ዓመቱ ለማዕከላዊ ገበያ ምንም ወርቅ እንዳላቀረቡ አስረድተዋል፡፡

የማዕድን ሚኒስቴር በ2016 በጀት ዓመት ከከፍተኛ ወርቅ አምራች ኩባንያዎች 996.1 ኪሎ ግራም ወርቅ ለማግኘት ዕቅድ ቢኖውም፣  719.6 ኪሎ ግራም ወይም 72.2 በመቶ ብቻ እንደተገኘና ለዚህም ትልቁን ድርሻ የያዘው ሚድሮክ ጎልድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንደ ሀብታሙ (ኢንጂነር) ገለጻ፣ የተቀሩት ማዕድን አውጪዎች በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ውስጥ ወደ ምርት ካልገቡ ፈቃዳቸው ላይ ዕርምጃ ይወሰዳል፡፡

በኢትዮጵያ ፈቃድ አግኝተው ከሚንቀሳቀሱ 13 የማዕድን ኩባንያዎች በዓመት 17 ቶን ወርቅ ማምረት እንደሚቻል ሚኒስትሩ ለቋሚ ኮሚቴው አስረድተዋል፡፡

ፈቃድ ከተሰጣቸው 11 ኩባንያዎች አብዛኛዎቹ ዝግጅት ላይ እንደሆኑ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

ከሚድሮክ ጎልድና ከስቴላ ከፍተኛ የወርቅ አምራቾች ውጪ ያሉት ኩባንያዎች የፀጥታ ችግር ባሉባቸው አካባቢዎች መሰማራታቸውን ተናግረዋል፡፡

በሩብ ዓመቱ ክልሎች ከሚያስተዳድሯቸው አነስተኛና ባህላዊ ወርቅ አምራቾች የተገኘው 22 በመቶ ብቻ መሆኑን በሪፖርታቸው ያወሱት ሚኒስትሩ፣ ከፍተኛ የወርቅ ምርት ሲያስገኙ የነበሩ ባህላዊ አምራቾች ማሽቆልቆላቸውን አክለዋል፡፡ ይህም የሚያሳየው ፈቃድ ሰጪው አካል (ክልሎች) በሚያስተዳድሯቸው አምራቾች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባቸው የሚያመለክት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ኦሮሚያ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ትግራይ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ወርቅ የሚገኝባቸው አካባቢዎች ተብለው መለየታቸውን፣ ይሁን እንጂ በቅርቡ በተደረገው ዳሰሳ በሌሎች ክልሎች ወርቅ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በከፍተኛ ሁኔታ ወርቅ ሲያመርት የነበረው የኦሮሚያ ክልል እንደነበር፣ ነገር ግን የ2016 በጀት ዓመት የሩብ ዓመት አፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የተሻለ የወርቅ ምርት ያቀረበው ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መሆኑን፣ ከዚያ ቀጥሎም የተሻለ አፈጻጸም ያለው ጋምቤላ ክልል እንደሆነ ገልጸዋል፡

በትግራይ ክልል ኢዛና ወርቅ አምራች ኩባንያ አንዱ መሆኑን፣ በፌዴራል መንግሥት ዕገዛ ተደርጎለት እስከሚቀጥለው ታኅሳስ ወር ድረስ ወደ ምርት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ በሩብ ዓመቱ ከትግራይ ክልል የተገኘ ምንም ዓይነት ወርቅ የለም ብለዋል፡፡

በ2016 በጀት ዓመት በወርቅ፣ በታንታለም፣ በሊቲየምና በሌሎች ማዕድናት ለማግኘት የታቀደው የውጭ ምንዛሪ 512 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን፣ በሩብ ዓመቱ ደግሞ 112 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል ተብሏል፡፡ ይሁን እንጂ በሩበ ዓመቱ ከታቀደው አኳያ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ፈቃድ ያገኙ የማዕድን አምራቾች በሙሉ አቅማቸው ካመረቱ በዓመት 1.1 ቢሊዮን ዶላርና በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት 11 ቢሊዮን ዶላር ማግኘት እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡  

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አማረች በካሎ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ ከማዕድን ሀብት የተሻለ ገቢ ማግኘት እንድትችል በዘርፉ የሚስተዋሉ ብልሹ አሠራሮች ሊቀረፉ ይገባል ብለዋል።

መንግሥት የኢኮኖሚ ዕድገቱን ለማሳካት አምስት የስትራቴጂ ዕቅዶች ነድፎ እየሠራባቸው ከሚገኙ ዘርፎች አንዱ የማዕድን ዘርፉ በመሆኑ፣ የሚስተዋሉ  ችግሮች ሊቀረፉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የማዕድን ዘርፍ ውስብስብ ፍላጎቶች ያሉበት በመሆኑ ኮንትሮባንድና ብልሹ አሠራሮችን ጨምሮ ሌሎች ችግሮች ላይ ተገቢው ቁጥጥርና ክትትል የማድረግ  ተገቢነትን ሰብሳቢዋ አስረድተዋል፡፡ 

በሌላ በኩል በማዕድናት መረጃ አያያዝ፣ በዘርፉ ስለተፈጠረው የሥራ ዕድል፣ በማዕድን ምርመራና ፈቃድ አሰጣጥ፣ እንዲሁም ማዕድናት ባሉባቸው  አካባቢዎች   የመሠረት ልማት ግንባታ ውስንነትና በመሳሰሉት ላይ ትኩረት ተደርጎ ሊሠራ እንደሚገባ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...