Friday, March 1, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ድጋፍና ተቃውሞ እኩል ይስተናገዱ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ለመንግሥት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የመብት መከበር ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች ተፈጥሯዊም ሆኑ ሕጋዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ጥያቄው የቀረበለት መንግሥትም ባለበት ኃላፊነት መሠረት ተገቢውን ምላሽ የመስጠት ሕጋዊ ግዴታ አለበት፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግን ለመብቶች መከበር የሚቀርብ ጥያቄም ሆነ ምላሹ ተመጣጣኝ ስለማይሆን፣ ብዙ ጊዜ ችግሮች እየተፈጠሩ በርካታ ጉዳቶች ይደርሳሉ፡፡ ለመንግሥት የሚቀርበው ጥያቄ ሕጋዊና ሰላማዊ መሆን ሲጠበቅበት፣ ምላሹም በዚህ መሠረት ሊሆን ይገባዋል፡፡ ነገር ግን ለመብት ጥያቄ ሲቀርብ በተቀባዩ በኩል ጤናማ ዕይታ ስለማይኖር ከጭቅጭቅ በዘለለ፣ ለግጭት የሚዳርጉ አጋጣሚዎች እየበዙ ብዙዎች ተጎድተዋል፡፡ መንግሥት ለሚያከናውናቸው ተግባራቱ የሚደረግለትን ድጋፍ በከፍተኛ ደስታ እንደሚቀበል ሁሉ፣ ተቃውሞ ሲቀርብበት በሠለጠነ መንገድ በማስተናገድ ኃላፊነቱን መወጣት ይጠበቅበታል፡፡ ድጋፍና ተቃውሞ በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ እየቀረቡ ዴሞክራሲያዊ ባህል እንዲያብብ ማድረግ የመንግሥት ተቀዳሚ ኃላፊነት ነው፡፡ ዜጎችም ሆኑ የፖለቲካ ሥራ ላይ የተሰማሩም ዴሞክራሲ እንዲያብብ የሚፈለግባቸውን ኃላፊነት መወጣት አለባቸው፡፡

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ለረዥም ጊዜ የመጣበት መንገድ አባጣና ጎርባጣ በመሆኑ ምክንያት፣ በስክነት ተነጋግሮ ልዩነትን ማጥበብ ወይም የኃይል ዕርምጃን አማራጭ አለማድረግ እያቃተ ነው፡፡ በተለይ መንግሥት በርካታ ኃላፊነቶች የተጫኑበት ትልቅ ተቋም እንደ መሆኑ መጠን፣ በግራም ሆነ በቀኝ ለሚቀርቡለት ጥያቄዎች በከፍተኛ ጥንቃቄ እንደ ቅደም ተከተላቸው ምላሽ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ ከመንግሥት ምላሽ የሚፈልጉ ወገኖችም ጥያቄም ሆነ ተቃውሞ ሲኖራቸው ከምንም ነገር በላይ ለሕጋዊነት ቅድሚያ መስጠት አለባቸው፡፡ በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ ተነጋግሮ ችግሮችን የመፍታት ባህል የሌለበት አገር ውስጥ፣ ዓላማን በኃይል ብቻ ለማስፈጸም የተኬደባቸው መንገዶች በሙሉ ከጥፋት በስተቀር ልማት አላመጡም፡፡ አልፎ አልፎ ሕዝባዊ ትዕይንቶች ወይም መድረኮች ሲኖሩ መንግሥት ድጋፍ ብቻ ሳይሆን፣ ተቃውሞን በፀጋ ለማስተናገድ ራሱን ዝግጁ ማድረግ አለበት፡፡ ድጋፍ የሚያስደስተውን ያህል ተቃውሞ ቢመር እንኳ እንደ ሕዝብ ስሜት መለኪያ መጠቀም ያሻል፡፡ በስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች፣ በአደባባይ ሁነቶች ወይም በሌላ ሥፍራ ዜጎች ቁጣ ሲያሰሙ ትዕግሥተኛ መሆን ይገባል፡፡

እርግጥ ነው የፖለቲካ ባህሉ በጣም ኋላቀርና ደካማ በመሆኑ ምክንያት ብስለት የጎደላቸው ግለሰቦች በሐሳብ መሞገት ስለማይችሉ፣ ስድብና ማንጓጠጥ ላይ ስለሚያተኩሩ እነሱን ምሳሌ ማድረግ አይገባም፡፡ እንዲያውም እንዲህ ዓይነቶቹ ብስለት የሌላቸው ግለሰቦች ከስህተታቸው እንዲማሩ፣ እያሳደዱ ከማሰር ይልቅ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ምሥሎቻቸውንና ስድቦቻቸውን በማጋለጥ ማሳፈር ይቀላል፡፡ በሌላ በኩል ጠንካራ ትችትና ተቃውሞ ለሚያቀርቡት ደግሞ አሳማኝና ሥልጡን ምላሽ በመስጠት ብስለትን ማሳየት ከመንግሥት የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመግለጽ የሚያስቸግሩ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች በመደበኛው ሚዲያና በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ዘርዝረው ከሚያቀርቡ በተጨማሪ፣ በአደባባይ ሁነቶች ከቁጣ በተጨማሪ በቀልድና በምፀት የሚያቀርቡ ስላሉ ድምፃቸውን ማዳመጥ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ውጪ ለምን ተቃውሞ አቀረባችሁ ብሎ ሰዎችን ማሰርና ማንገላታት፣ በሕዝብ ድምፅ ተመርጬ ሥልጣን ይዣለሁ ከሚባል ገዥ ፓርቲም ሆነ መንግሥት አይጠበቅም፡፡ ሰሞኑን ከታላቁ ሩጫ ተቃውሞና ሽርደዳ ጋር በተገናኘ የታሰሩ ሰዎችን በመፍታት፣ የመንግሥትነትን ወግና ባህሪ ማሳየት የግድ መሆን አለበት፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ቀደም ሲል ከሚታወቁ የመንግሥት ተግባራት አንደኛው ሕዝብ የሚለውን ለማወቅ የተለያዩ ዘዴዎችን መጠቀም ነው፡፡ እንደ አካባቢው ነባራዊ ሁኔታ የሕዝብን ስሜት ለመለካት እረኞች፣ አዝማሪዎች፣ ነጭ ለባሾችና የመሳሰሉት ያገለግሉ ነበር፡፡ መንግሥት በቀጥታ መረጃ ከሚያገኝባቸው ዘዴዎች ውጪ የጎንዮሽ መረጃዎችን በማሰባሰብ የሕዝቡን ስሜት ይለካል፣ በተገኙ መረጃዎች ላይ በመመሥረትም አስፈላጊውን ዕርምጃ ይወስዳል፡፡ በዚህ ዘመን ሕዝብ ውስጥ የሚብላሉ በርካታ ጥያቄዎች ምን እንደሆኑ መንግሥት በሚገባ ያውቃል፡፡ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችና በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ብዙ ርዕሰ ጉዳዮች ስለሚነሱ፣ መንግሥት ለሕዝብ ጠቃሚ ናቸው የሚላቸውን ውሳኔዎች ለማሳለፍ የሚረዱት ላይ ቢያተኩር በርካታ ችግሮች ይቃለላሉ፡፡ በተለያዩ መንገዶች የሚቀርቡ አስተያየቶችን ወይም ጥያቄዎችን ለሥርዓቱ ጠላት ከሆኑ ወገኖች የሚሰነዘሩ ናቸው በማለት በደፈናው ከማጣጠል በፊት፣ የትኞቹ ለአገር ሰላምና ዕድገት ሲባል ምላሽ ቢያገኙ ይጠቅማሉ በማለት በስክነት ማጤን የመንግሥት ባለሥልጣናት ኃላፊነት ነው፡፡ ከማይረባ ድጋፍ በሰላ ትችት የሚቀርብ ተቃውሞ ጥቅም እንዳለው መዘንጋት አይገባም፡፡

የተለያዩ ማኅበራዊ መሠረቶችን እንወክላለን ብለው የተመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎችም፣ አባላቶቻቸውም ሆኑ ደጋፊዎቻቸው ከጭፍን ስሜታዊነት ተላቀው ምክንያታዊ እንዲሆኑ ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ትልቁ ችግር በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ርዕዮተ ዓለማዊ ግንዛቤም ሆነ የመወያየት ባህል እጥረት ነው፡፡ ይህ ችግር የተፎካካሪ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን የገዥው ብልፅግና ፓርቲ አባላት ጭምር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የፓርቲያቸውን ፕሮግራምና ደንብ፣ በሥራ ላይ ያለውን ሕገ መንግሥት፣ የተለያዩ ሕግጋቶችን፣ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በቅጡ ሳይረዱ እንደ ቦይ ውኃ በተቀደደላቸው የሚነጉዱ ብዙ ናቸው፡፡ የፓርቲ መሪዎችን ንግግር እንደ በቀቀን ማስተጋባትና መፈክሮችን እንደ ወረዱ ማነብነብ የፖለቲካ ሥራ የሚመስላቸው በርካቶች ናቸው፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ አሳሪና ቆላፊ አስተሳሰብ መውጣት የሚቻለው የፖለቲካ ዕውቀትን በማሳደግ ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ተግቶ መማር፣ ማንበብ፣ መወያየትና መመራመር የግድ ነው፡፡ የፓርቲ ዓላማን ማስፈጸም የሚቻለው ከሌሎች ተሽሎ በመገኘት ነው፡፡ ድጋፍና ተቃውሞ ሲያስፈልግም በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ድምዳሜ ላይ በቀላሉ ለመድረስ ያግዛል፡፡

አገር እያስተዳደረ ያለው ገዥው ብልፅግና ፓርቲ አባላቱንና ደጋፊዎቹን ከአጃቢነት በማላቀቅ፣ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በሚገባ መወጣት እንዲችሉ ያብቃቸው፡፡ ለፓርቲያቸው ያላቸው ቀናዒነት መገለጽ ያለበት ሕዝብን በማገልገል እንጂ፣ ተቃዋሚ ነው ብለው የሚያስቡትን ሁሉ በጅምላ ባልታረሙ ቃላት በማንጓጠጥ አይደለም፡፡ የፓርቲና የመንግሥት ሥራቸውን በአግባቡ መወጣት ቢችሉ እኮ ሌሎች በተቃውሞ አደባባይ አይወጡም ነበር፡፡ ነገር ግን በብዙ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ መልካም አስተዳደር እንዳይኖር፣ ብልሹ አሠራሮች እንዲንሰራፉ፣ ጉቦ መቀበል የተለመደ ሥራ እንዲሆንና ሕዝብ የሚያስመርሩ ድርጊቶች እንዲበዙ በማድረግ ቁጣና ተቃውሞ እንዲቀሰቀስ ምክንያት መሆናቸው የታወቀ ነው፡፡ በእንዲህ ዓይነቶቹ የሚደገፍ መንግሥት ጥላቻ ቢያተርፍ ሊደንቅ አይገባም፡፡ በተፎካካሪ ፓርቲዎች አባላትና ደጋፊዎች ዘንድም ከመጠን ያለፉ አሳዛኝ ድርጊቶች ይፈጸማሉ፡፡ ምክንያታዊ ሆኖ ከመሞገት ይልቅ የግለሰቦችን ሰብዕና ማራከስ፣ ስድብ፣ አሉባልታና ሐሜት ላይ የተሰማሩ በርካቶች ናቸው፡፡ በተለይ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ውስጥ መሽገው ለመስማት የሚዘገንኑ መረጃዎችንና አሉባልታዎችን የሚያሠራጩ በመብዛታቸው፣ ለአገር ሰላምና ዕድገት ሊኖር የሚገባው መቀራረብ እየጠፋ መጨካከን እየበዛ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ መቀጠል ስለማይቻል ድጋፍም ሆነ ተቃውሞ ልክ ይኑራቸው፡፡ መንግሥትም ድጋፍና ተቃውሞን እኩል ያስተናግድ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...

የጋራ ድላችን!

ከፒያሳ ወደ ቄራ ልንጓዝ ነው። ለበርካታ ደቂቃዎች ሠልፍ ይዘን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ታላቁ የዓድዋ ድል ሲዘከር የጀግኖቹ የሞራል ልዕልና አይዘንጋ!

የታላቁ ዓድዋ ድል 128ኛ ዓመት ክብረ በዓል ሲዘከር፣ ለአገርና ለሕዝብ ክብር የሚመጥኑ ተግባራት ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ በዓድዋ ከወራሪው ኮሎኒያሊስት ኃይል ጋር ተፋልመው ከትውልድ ወደ...

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...

የበራሪው የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ቅርሶችን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተረከበ

በቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት (1967-1983) ዘመን የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ የየካቲት 1966 1ኛ ደረጃ ኒሻን ተሸላሚ የነበሩ የአየር ኃይል ጀት አብራሪው የብርጋዴር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ...