Sunday, March 3, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለፕላንና ልማት ሚኒስቴር የተላከው የአቪዬሽን ፖሊሲ ምላሽ እየተጠበቀ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በናርዶስ ዮሴፍ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ላለፉት ሰባት ዓመታት በረቂቅ ደረጃ ከባለድርሻ አካላት ውይይት ሲያደርግበት የቆየውን የኢትዮጵያ አቪዬሽን ፖሊሲ፣ በ2015 ዓ.ም. መጨረሻ ወደ ፕላንና ልማት ሚኒስቴር ልኮ ምላሽ እየተጠባበቀ መሆኑ ተሰምቷል፡፡

ፖሊሲው በአጠቃላይ ትኩረት ካደረገባቸው ጉዳዮች መካከል የአቪዬሽን ከባቢያዊ ኩነቶች፣ ለኢንዱስትሪው ጥንቃቄ የሚያሻቸው ጉዳዩችና የደኅንነት ጉዳዮች ተጠቃሽ መሆናቸው ተነግሯል።

የአውሮፕላን ማረፊያ ማስፋፊያዎች ኢንቨስትመንት፣ በዓለም አቀፍ መዳረሻዎች ስምምነትና ማስፋፊያ የግሉ ዘርፍ ተጠቃሚነት፣ እንዲሁም በተለያዩ የመንግሥት ድርጅቶች ሥር ተበታትነው ያሉ ከአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ጋር የተያያዙ አሠራሮችና የፈቃድ አሰጣጥ ሒደቶችም በአቪዬሽን ፖሊሲው ውስጥ ወጥ ሆነው ተካተዋል ተብሏል።

በዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) ትኩረት ተሰጥቶት አኔክስ 16 የሚል መመርያ ሥራ ላይ የዋለበትን፣ በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ስትራቴጂካዊ ግቦች ተብለው ከተያዙ አምስት ዋና ጉዳዮች አንዱ ነው በተባለው በአቪዬሽን የከባቢያዊ ኩነቶች ጥበቃ በተመለከተ፣ በፖሊሲው አራት ዋና ዋና ጉዳዩች እንደተካተቱበት ለማወቅ ተችሏል።

በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ከዚህ ቀደም በአቪዬሽን ከባቢያዊ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳዩች ቡድን መሪ የነበሩትና አሁን የአየር ትራንስፖርት ልማት ዳይሬክተር አቶ ተሰማ አዳሙ፣ ‹‹የአውሮፕላኖች የካርቦን ልቀት መጠን፣ የግሪን ሐውስ፣ የድምፅ ብክለት፣ እንዲሁም አንድ አገር ወደ ሌላ አገር በሚያበራቸው አውሮፕላኖች የሚያመነጨው የአየር ካርቦን መጠን በዓለም አቀፉ ተቋም ከተቀመጠው የሚፈቀድ መጠን በላይ ከሆነ፣ የገንዘብ ክፍያ የሚፈጽምባቸውን አሠራሮችንም ሁሉ የተመለከተ ደረጃዎች (Standards) አካቶ ፖሊሲው ውስጥ ተቀምጧል፤›› ሲሉ ለሪፖርተር ተናግረዋል።

አቶ ተሰማ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ከዚህ ቀደም ለረዥም ጊዜ በአቪዬሽን ከባቢ ሁኔታ ጥበቃ ላይ ስላልሠራ፣ በፖሊሲው ላይ በዝርዝር እንዳልቀረበ አስታውሰው፣ ‹‹አሁን ግን በዓለም አቀፍ አቪዬሽን ቅድሚያ ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ስለሆነ፣ በመንግሥት እንደ አንድ የፖሊሲ አቅጣጫ እንዲታይ ተወስኗል፤›› ብለዋል።

ፖሊሲውን የማፅደቅ ሒደቱ ገና ቢሆንም አገር አቀፍ የአቪዬሽን ከባቢያዊ ሁኔታ ጥበቃ ኮሚቴ በትራንስፖርት ሚኒስቴር አማካይነት መቋቋሙም ተገልጿል። ‹‹በፖሊሲው ውስጥ በጥቅል ቢቀመጥም የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዝርዝር የድርጊት ዕቅዶችን ይዞ ወደ ሥራ ገብቷል፤›› ሲሉም አክለዋል።

ከኤርፖርት ማስፋፊያ፣ ከመዳረሻ ስምምነቶችና ከኤርፖርት ልማት ስምምነቶች ጋር በተያያዘ ፖሊሲው ስላካተታቸው ይዘቶች ለሪፖርተር ማብራሪያ የሰጡት የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢኮኖሚክ ሬጉሌሽንና ስትራቴጂካዊ አመራር ዳይሬክተር አቶ ጎሳዬ ፋንታ በበኩላቸው፣ ‹‹በጥቅሉ ፖሊሲው የግሉን ኢንቨስትመንት ተሳታፊነት ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረቶች አድርጓል፤›› ብለዋል።

እንደ አቶ ጎሳዬ ገለጻ፣ ፖሊሲው ስለኤርፖርት ማስፋፊያ የሚጠቅስባቸው ክፍሎች መነሻ በሥራ ላይ ያለው የተሻሻለው የኢንቨስትመንት አዋጅ ነው። የኢንቨስትመንት አዋጁ ከዚህ ቀደም ያልነበረና በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ጥገና ዘርፍ ኢትዮጵያዊ የሆነ የግል ባለሀብት በዘርፉ ገብቶ መሥራት እንዲችል መፍቀዱ ተጠቅሷል። የአገር ውስጥ በረራ አገልግሎት ለማቅረብም የውጭ አገር ዜጎች ከኢትዮጵያውያን ጋር በጋራ በመሆን ኢንቨስት ማድረግ እንደሚችሉ ተደንግጓል።

አቶ ጎሳዬ፣ ‹‹ለምሳሌ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከመንግሥት ብቸኛ ባለቤትነት ወጥቶ ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ኢንቨስተር ጋር የአክሲዮን ድርሻ ኖሮት በጋራ የመሥራት ፈቃድ ይሰጠኝ ካለ፣ በኢንቨስትመንት አዋጁ መሠረት እንሰጠዋለን፤›› ያሉ ሲሆን፣ ‹‹እንዲህ ያሉ በኢንቨስትመንት አዋጁ ሥር ያሉ በሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የሚተገበሩ የሥራ ድርሻዎችን በፖሊሲው ውስጥ አካተናቸዋል፤›› ብለዋል።

ረቂቅ ፖሊሲው ውስጥ የተካተተው ሌላኛው ጉዳይ የአየር መዳረሻዎች አገልግሎት ስምምነትን የሚመለከተው ነው። ይህ የስምምነት ዓይነት በውጭ አገሮች የሚገኙ አየር መንገዶች መዳረሻቸውን በኢትዮጵያ ለማድረግ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድም በውጭ አገሮች መዳረሻውን ማድረግ የሚያስችል ዓለም አቀፍ ውል ነው ተብሏል፡፡ አገልግሎቱ በቀን፣ በሳምንት፣ በወር ይህን ያህል ጊዜ ይህ አገር ይህ ከተማ መዳረሻ ይሆናል ተብሎ ዝርዝር ተጠቅሶ ቀርቦ የሚፈጸም ነው።

‹‹አሁን ባለው ሁኔታ የመንግሥት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብቻ ነው፣ የአየር መዳረሻ አገልግሎት ስምምነት መጠቀም የሚችለው፤›› ያሉት አቶ ጎሳዬ፣ ‹‹ረቂቅ ፖሊሲው ውስጥ የግሉ ዘርፍም ከመንግሥት ጋር አብሮ መሥራት የሚችልባቸው የኢንቨስትመንት ሁኔታዎች ተቀምጠዋል። የግል የአቪዬሽን ድርጅቶች ከመንግሥት ጋር ተቀናጅተው ኢንቨስት እንዲያደርጉና በስምምነት የዓለም አቀፍ መዳረሻዎች አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን የሚያስችላቸው ዕድል በፖሊሲው ተካቷል፤›› ሲሉ አብራርተዋል።

በአሁን ወቅት በአገሪቱ ባለ የግል አቪዬሽን ድርጅቶችን በግሉ ዘርፍ አቪዬሽን ድርጅቶች ማልማት ጥያቄ ጉዳይም በረቂቅ ፖሊሲው ምላሽ ያገኛል ተብሏል። አሁን ባለው አሠራር የአየር መንገዶች ግንባታ ፈቃድ በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ስር ኮድ ተሰጥቶት ፈቃድ እየተሰጠ መሆኑን አቶ ጎሳዬ የገለጹ ሲሆን፣ ‹‹ይህንንም ወደ አቪዬሽን ባለሥልጣን የሚያካትት ወጥ አሠራር የሚያስገባ ረቂቅ ፖሊሲ ነው ለፕላንና ልማት ሚኒስቴር የቀረበው፤›› ብለዋል።

በአገሪቱ 19 ባለአንድ መስመር ትንንሽ አውሮፕላን ማረፊያዎች (Air Strips) እንዳሉ የተገለጸ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ቀብሪደሃር፣ ደምቢዶሎ፣ ድሬዳዋ፣ ቦኮ፣ ኮምቦልቻ ያሉት ወደ ሙሉ አውሮፕላን ማረፊያነት እንዲያድጉ በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ውሳኔ ተላልፎ ግንባታቸው እየተከናወነ መሆኑ ተገልጿል።

ሌሎችም አውሮፕላን ማረፊያዎች በወላይታ ሶዶ፣ በጎንደር፣ በቦረና፣ በሚዛን ቴፒ፣ በጎሬና በመቱ ግንባታ መጀመሩ ሲገለጽ አቶ ጎሳዬም፣ ‹‹ባለው የአገሪቱ ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ ምክንያት ግንባታው በሚፈለገው ፍጥነት እየተካሄደ አይደለም፣ ለምሳሌ በነቀምት ተጫራች አላገኘንም፤›› ሲሉ ተናግረዋል።

የባለሥልጣኑ የኢኮኖሚክ ሬጉሌሽንና ስትራቴጂካዊ አመራር ዳይሬክተር በግሉ ዘርፍ ስለሚደረጉ ትንንሽ አውሮፕላን ማረፊያዎች ልማት በሰጡት ማብራሪያ በአሁኑ ወቅት ፈቃድ ወስዶ በግንባታ ሒደት ላይ ያለው የአቪዬሽን ድርጅት አንድ ብቻ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የግሉ ዘርፍ በመሰል የአውሮፕላን ማረፊያዎች ልማት ላይ እንዲሳተፍ የሚጠየቀው የተለየ ቅድመ ሁኔታም እንደሌለ ገልጸዋል። አቶ ጎሳዬ፣ ‹‹አንድ የግል ኢንቨስተር የአቪዬሽን ድርጅት ለመክፈት ባለሥልጣኑን ፈቃድ ሲጠይቅ ሥራውን ከጀመረ ከዓመት በኋላ የሚመለስለት 2.5 ሚሊዮን ብር በዝግ አካውንት እንዲያስገባ እንጠይቀዋለን። የግል ትንሽ ኤርፖርት ለማልማት ሲጠይቅ ግን የምናመሳክርበት የሥራ ልምድ ስለሌለ ይህን ካለመጣህ ፈቃድ አንሰጥህም የምንለው አስገዳጅ ቅድመ ሁኔታ የለንም። አቅሙ አለኝ ልሥራ ብሎ የሚጠይቅ ሲመጣ ፈቃዱን እንሰጣለን፤›› ብለዋል።

ከግል አየር መንገዶች በተደጋጋሚ የሚቀርበውን ‹‹የጥገና ሥፍራ የለንም›› አቤቱታ በተመለከተ፣ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ጥናት አድርጎ ሁለት አማራጮችን አቅርቦላቸዋል ተብሏል።

አቶ ጎሳዬ፣ ‹‹አብዛኞቹ ድርጅቶች በየግላቸው ቦሌ ኤርፖርት የጥገና ሥፍራ እንዲሰጣቸው ይፈልጋሉ፤›› ብለው፣ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ‹‹ቦሌ በማኅበር ተደራጅታችሁ በጋራ የጥገና ሥፍራ መክፈት ትችላላችሁ›› የሚል ምላሽ ተሰጥቷቸዋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ሁለተኛው አማራጭ ቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) ያለው በደርግ ወቅት የተሠራ የአውሮፕላኖች መጠገኛ የሚሆን ሥፍራ በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ተመቻችቷል የተባለ ሲሆን፣ በጊዜያዊነት ግን ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ለጥገና አገልግሎት ተገቢ የሆነ ዋጋ ተደራድሮ የማስጠገን አማራጭ እንደቀረበላቸው ተገልጿል።

ለዘርፈ ብዙው የኢትዮጵያ አቪዬሽን ወቅታዊ ጥያቄዎችና ወደፊት ምን መሆን አለበት የሚል የአቅጣጫ መሻቶች ቋሚ ምላሽ ይገኝበታል የተባለው ፖሊሲ፣ ወደ ፕላንና ልማት ሚኒስቴር የተላከው በ2015 ዓ.ም. መሆኑን፣ የኢኮኖሚክ ሬጉሌሽንና ስትራቴጂካዊ አመራር ዳይሬክተር አቶ ጎሳዬ አስታውሰው፣ ‹‹ምላሻቸውን እየጠበቅን ነው፣ እሺም እምቢም ሊባል ይችላል፤›› ሲሉ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በረቂቅ ፖሊሲው ላይ ስለሚሰጡ ውሳኔዎች አስተያየት መስጠት እንደሚያዳግተው ገልጸዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች