Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

መግቢያ

በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲመጡ አፈሳ በአፈሳ የተገኘ የመንግሥት ድጋፍ፣ በፖለቲካ አያያዝ ስህተቶች የሕወሓት/ኢሕአዴግ የአገዛዝ ዕዳዎች ቆስቋሽ እያገኙ የሕዝብን ኑሮ በሚያናጉ ብዙ የግጭቶችና የጥቃት መልኮች ሲገለጡ ቆይተዋል፡፡ እነዚህ ችግሮቻችን እንደ ብርካቴያቸውና ጥንካሬያቸው የሚያስከፍሉት ዋጋም እየተለዋወጠ ዛሬ የደረስንበት ምዕራፍ ላይ ደርሰናል፡፡ የመንግሥት ተቀባይነትም እየተሸራረፈ ሲያንስ፣ እንደገና ደግሞ ሲጠገን፣ ከመጠገንም በላይ ሲታደስ፣ እንደገና ደግሞ ሲከሳ ዓይተናል፡፡ እንዲህ በሚንገጫገጭ ግን አቅጣጫው ባልተቀለበሰ የሕዝብ ድጋፍ ደመና ውስጥ የሚሆነው እየሆነ የሰሜኑን ጣጣ ከሞላ ጎደል ተወጣን፡፡ ከእንግዲህ የሚቀረን ጎላ ያለ ችግር ኦሮሚያ አካባቢ ያለው ነው ስንል፣ የአማራ አካባቢ ቀውስ ተጨመረ፡፡ ሁለቱን እንደምን አቃለን ይሆን የአገራችንን ሰላም ሙሉ በማድረግ ቀልባችንን በግስጋሴ ትግል ላይ ማሰባሰብ የምንችለው የሚል ራስ ምታት ውስጥ ባለንበት ጊዜ፣ የወደብ ነገር ምነው ዝምታ በዛበት የሚል ዱብ ዕዳ ከመንግሥት ብቅ አለ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ነገሮች ከመንግሥት በኩል ሕዝብ ውስጥ ግርታ በሚፈጥሩበት አኳኋን መምጣታቸው ለምን እንደሚደጋገም አይገባኝም፡፡ ሕዝብን መምራት በዚህ ጉዳይ መወያየት ሊፈራ አይገባም ከማለት በላይ ነው፡፡ የጎረቤት ወደብን በገንዘብ መጠቀም ጥሪት አንካች መሆኑ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ተራ ግንዛቤ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ ኢትዮጵያ ታሪካዊ የወደብ ባለመብትነት ጥያቄ ያላት የመሆኑም ነገር ብዙ የተለፈለፈበት ጉዳይ ነው፡፡ መንግሥት ለዝዞ የቆየውን የባህር በር ጉዳይ ለሕዝብ ሲያነሳው የተጀማመሩ ጥረቶችን ተመርኩዞ ቢሆን ሕዝብ ውዥንብር ውስጥ አይገባም ነበር፡፡ የኢትዮጵያ የተሻጋሪ ውኃዎች አስተዋፅኦ፣ የቀይ ባህር ጂኦ ፖለቲካዊ ጥቅሟ፣ የባህር በር መብቷና በሰጥቶ መቀበል ስምምነት ወደብ የማግኘቱ ሁሉ ጉዳይ መወያያ ሆኖ ሲመጣ ግቢና ደጅ በሌለው መልክ ሁሉም እንዳሻው እየፈተፈተው ይገኛል፡፡ ጠብ ለማዋለድ ከተጠቀሙበት ውጭ በአገር ተቆርቋሪነት አድማስ ውስጥ የተካሄዱት የሚዲያ ውይይቶች እንኳ ጥንቃቄና አቅጣጫ ማጣት ታይቶባቸዋል፡፡ በአመዛኙ የመንግሥት አቋም በሚሰለቅበት ‹‹ሐሳብ ላይ›› በሚል የዋልታ ቴሌቪዥን ዝግጅት ውስጥ እንኳ ስለኤርትራና ስለአሰብ አሸኛኘታችን፣ ስለአልጀርሱ አንካሳ ስምምነታችን፣ ደካማ መከራከሪያና ተከራካሪነት ይዘን ወደ ግልግል ዳኝነት ስለሄድንበት ገመናችን ተነስቶ የተብሰለሰለ ውይይት ተካሂዶ ነበር፡፡ በክስ መብትን ለማስከበር ስላለው ዕድል ሁሉ ብዙ ተብሏል፡፡ መንግሥት አቅጣጫ ያላስያዘው ጉዳይ ብዙ ቦታ ቢረግጥና ነገር አለ ይሆን የሚል ጥርጥሬ ቢፈጥር አይገርምም፡፡ እንዲህ ያለው እዚያም እዚያም የሚረግጥ የሚዲያ ጫጫታ የጎረቤታሞቹን አገሮች የተማመነ ግንኙነት መጥቀሙ ያጠያይቃል፡፡ በመንግሥት ተቀባይነት ረገድ በአንድ ጎን የተፈጠረ ቀዳዳ፣ መላ ኅብረተሰብ የእኔ የሚለው ሌላ ጉዳይ በማንሳት ሊጣፍ እንደሚችል ይታወቃል፡፡ የዚህ ዓይነት ፍላጎት ኖሮም ከሆነ ሐሳብን ለውዥንብር እንደማይመች አድርጎ ከማቅረብ ጋር አይጣላም፡፡ ጥቅማችን የተጎዳው ባለመለፍለፋችን ነው? መለፍለፍ ዛሬ ለጥቅማችን ይበጃል? በኋላ እመለስበታለሁ፡፡

 ከሁሉ በፊት፣ አገራችን አሁን ያላት የሰላም ችግር ራሱን በራሱ እያባዛ የኑሮ ውድነትን በመታገል ጥረታችን ላይ፣ በመልሶ ማቋቋም/በመልሶ ግንባታችን ላይና በውጭ ግንኙነታችን ላይ የሚያስከትለው መጥፎ ተፅዕኖ የማይናቅ ነው፡፡ እየተሻሻለ የመጣው ከምዕራባውያን ያለን ግንኙነት ተመልሶ ወጥመድ ውስጥ እንዳይገባም ያስፈራል፡፡ እናም፣ የኃይል ዕርምጃ እየወሰዱ የሰላም አማራጭ ዝግ አለመሆኑን ከማሳወቅ ባለፈ፣ ሰላምን በሰላማዊ መንገድ በማምጣት ቁርጠኝነት መታከት የሌለበት ጥረት ማድረግ ግዳችን ይመስለኛል፡፡ በወታደራዊ ድል የመጠናቀቅ ጫፍ ላይ ደርሶ የነበረውን የሰሜኑን ጦርነት በድርድር ለመደምደም እንዳልቸገረን ሁሉ፣ ዛሬም ውጤታማ ድርድር ለማድረግ የሚሆን አንጀት የሚቸግረን አይመስለኝም፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ዕገዛን ሳንሻም፣ የኢትዮጵያ አንድነትና የአገሪቱ የፀጥታ ኃይሎች ብቸኛ ሕጋዊ ታጣቂነት ለድርድር በማይቀርብበት ሁኔታ ውስጥ፣ ሰላምን ለመጨበጥ ሲባል ሊጣስና ሊቋደስ የሚችለውን ሁሉ እስከ ማድረግ ቸር በሆነ ቁርጠኝነት ውጤታማ ድርድር የማድረግ አቅሙ ያለን ይመስለኛል፡፡

በአንገብጋቢው የሰላም ጉዳያችን ላይ ራሳችን ለራሳችን መፍትሔ መሆን ከቻልን፣ በውስጣዊ ኅብረታችንና በአገራዊ የውስጥ ተግባሮቻችን መቃናት ረገድ የምንፈጥረው አዎንታዊ መነቃቃትና ሙቀት ቀላል አይሆንም፡፡ ከራሳችን አልፎም፣ ኢትዮጵያ በቀጣናዋ ውስጥ ያላት ተሰሚነትና ተከባሪነት ይጨምራል፡፡ ጎረቤቶቿ ራሳቸው በራሳቸው ተቃዋሚዎቻቸውን ባካተተ ድርድርና ፖለቲካዊ መላ ለአገራቸው መፍትሔ እንዲሆኑ (በነውጥ ከመዳፋት እንዲያመልጡ) አርዓያ መሆንም ትችላለች፡፡ በዚህ ረገድ እስከ ማማከርና እስከ ማቀራረብ ድረስ ጠቃሚነቷ ሊፈለግም ይችላል፡፡ የብቻና የጋራ ጥቅሞችን ማሰናሰልን እየጠየቀ በመጣው ቀጣናዊ ደኅንነትና ግስጋሴ ላይ የምታቀርበው ሐሳብም የመሰማት ዋጋው ይጨምራል፡፡

በዚህ አተያይ ውስጥ ሆኜ፣ ዛሬ የቀጣናችን የህልውና ደኅንነትና ግስጋሴ በሚሻው ግንዛቤና ተግባር ውስጥ የኢትዮ-ኤርትራን የብቻ ተራክቦ የሚያስተውል የውይይት መንደርደሪያ አቀርባለሁ፡፡

የኢትዮ ኤርትራ ልሂቃን ቢወያዩበት የሚጠቅም ፈር

አጠቃላይ የዕይታ ግቢ

የምድራችን ለሕይወት ምቹ ሆኖ መቀጠል የሰው ልጅ አኗኗሩን እንዲያርቅ ግድ እያለ ቢሆንም፣ የሰው ልጅ በአግባቡ አኗኗሩን ማረም አልተቻለውም፡፡ በሌላ ፈርጅ በጥቂት ኃያላን አገሮች ፍላጎትና ቁጥጥር ውስጥ የቆየው ዓለም አቀፋዊ ትድድር፣ እስከ ዛሬ በሚያደርጋቸው የእውነታዎች አገማገሙ፣ በውሳኔዎች አሰጣጡ፣ በዕርምጃዎች አወሳሰዱ፣ ከዕርዳታና ከብድር ጋር በሚዳበሉ ትዕዛዛቱ ሁሉ ሰላምና መረጋጋት ከማምጣት ይልቅ በአያሌው ምስቅልቅልን የሚያባዛ ሆኖ ከስሯል፡፡ በዚህም ምክንያት በሥርዓቱ የተማረረውና መውጫ ማምለጫ የሚሻው እየተበራከተ ሄዷል፡፡ መበራከት ብቻ አይደለም፣ ያረጀውንና የከሰረውን ዓለም አቀፋዊ መዋቅር የመቀየር ትግሉም ከተጀመረ ዋል አደር ብሏል፡፡

እስካሁን የታየው ትግል የተቆላለፉትን የምድርን ጤናማ ሆኖ መቀጠልን፣ የሰውን ልጅ በሕይወት የመኖር ጉዳይንና የዓለም ትድድርን ፍትሐዊ የማድረግ ጥያቄዎችን አንድ ላይ አሰናስሎ የሸረበ የመፍትሔ ፈር ለመቅድድ አልቻለም፡፡ ይሁን እንጂ ግንኙነታቸው ደንገዝገዝ ያለ ግን ተመጋጋቢነት ያላቸው ትግሎች በብዙ ጉጥ እየተካሄዱ ነው፡፡ በአንድ ጎን የምድር ብክለትንና ሙቀትን የመቀነስ/የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ጩኸትና ትግል አለ፡፡ በሌላ ጎን የዓለም አቀፍ ተቋማትን ኢፍትሐዊ አወካከልና አወሳሰን ከእነ ቡልዶዘራዊ ጫናዎቹ የሚቃወምና እንዲስተካከል የሚጠይቅ ጩኸት አለ፡፡ በጩኸትና ትግሎቹ ውስጥ ያለው ሠልፍ ከደሃ አገሮች እስከ ኃያላን/ዲታ አገሮች ያሉበት ነውና፣ በትግሉ ውስጥ አላፈናፍን እያለ የመጣውን ምዕራባዊ ጎራ (የዶላር-ዮሮ የበላይነትን) ሰብሮ የመውጣትና ሌላ አማራጭ ከምዕራባውያኑ በተሻለ አለዝቦ የመፍጠርና ብሶተኛ አገሮችን የመሳብ ቋጠሮም እየተፈለቀቀ ነው፡፡ በምዕራባዊው ጎራ ውስጥ ሌላ ልዝብ ምዕራባዊ ጎራ የመፍጠር ፍላጎትም ይልወሰወሳል፡፡ ይህኛው ጎራ በአግባቡ ያልተፈለቀቀ ፈራ ተባ በሚል የመፈላቀቅ ሒደት ውስጥ ገና ያለ ግን ከምዕራብ አውሮፓ እስከ ኢንዶ ፓስፊክ እስያ ድረስ ሸሪክ ያለው ነው፡፡ የዚህ መጪ ምዕራባዊ ጎራ እስያዊ ሸሪክ ከምዕራብ እያፈነገጠ ካለው የጎራ ሥሪት ጋርም ያልተላቀቀ ጉድኝት አለው፡፡ ከምዕራብ ባፈነገጠው የጎራ ሥሪት ውስጥም ምዕራብ ቀመሶች አሉ፡፡ በቀላል አነጋገር መጣን መጣን በሚሉት ጎራዎች ውስጥ የምዕራባዊነትም የምሥራቃዊነትም መዘናነቅ አለ፡፡ 

ከመጠጠር ይልቅ ድፍርስነትና ዋዣቃነት (ለየላቸው ሲባል መተሻሸት፣ ቀና አሉ ሲባል ማቀርቀር) በሚንፀባረቅበት የአሁኑ የጎራዎች ሽግሽግና አፈላቀቅ ውስጥ በደሃና ታዳጊ አገሮች በኩል ያሉት አቋሞች በሦስት መልክ የሚገለጹ ናቸው፡፡ ከሁሉም ጋር ለስላሳ ግንኙነት የመፍጠር ፍላጎት አንዱ ነው፡፡ በነባር ወዳጅነት ውስጥ ሆኖ የነገሮችን አካሄድ አድፍጦ መጠበቅ ሌላው ነው፡፡ በነባር ጎራ ውስጥ ላሳለፉት ጥቃት አዲስ መጡን ጎራ መከታ/ብሶት መወጫ ቢሆነኝ ብሎ መፍጨርጨር ሦስተኛው ዝንባሌ ነው፡፡ ይህንን በመሰሉት ዝንባሌዎች ውስጥ የአፍሪካና የምሥራቅ አፍሪካ አገሮችም አሉበት፡፡

በዚህ ራመድ ገተር የማለት መፍተልተል ባለበት ያላበቃ የጎራዎች የሽግሽግ ሁኔታ ውስጥ ሆነውም ነባርና አዲስ መጥ ኃያላኑና ዲታ አገሮች የጥቅም አጀቦችን የመሻማት ሚናቸውን አልረሱም፡፡ አንዱ ሁነኛ የሽሚያ ሥፍራ አፍሪካና የአፍሪካ ቀንድ ዙሪያ ነው፡፡ ቀደም ብሎ ‹‹የጋራ መድረክ›› በሚል ዘይቤ ጀምሮ ‹‹አጋርነት›› የሚል ቃል እስከ መጠቀም የደረሰው ከጊዜ ጊዜ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ጃፓን፣ አሜሪካ፣ ፈረንሣይ፣ አውሮፓ ከአፍሪካ ጋር የሚያካሂዱት የ‹ጉድኝት› ስብሰባ የዚሁ መገለጫ ነው፡፡ የተሿሚዎቹ አገሮች መሪዎችና የውጭ ጉዳይ መልዕክተኞች የሚያደርጓቸው ከፍትጊያ ሙቀት ጋር የተገናዘቡ የአፍሪካ ጉብኝቶችም የሽሚያው ነፀብራቆች ናቸው፡፡ በቅርቡ የእንግሊዝ ንጉሥ በኬንያ ያደረገው ጉብኝትና በቅኝ ዘመን ስለተፈጸመ በደል ያቀረበው የይቅርታ ጥያቄ ጥሬ ጉብኝትና ፀፀት ብቻም አልነበረም፣ ለሽሚያ ትግሉ መልህቅ የመጣል/የማጥበቅ ዓላማም ሳይኖርበት አልቀረም፡፡ የሳዑዲና የአፍሪካ ጉባዔም አፍሪካ ላይ የሚያማትሩት አገሮች ቁጥር ገና ሊጨምር እንደሚችል የሚጠቁም ነው፡፡ በእነ ኒጀርና ማሊ ግድም የታየውም የፈረንሣይን ሠራዊት ውጡ የማለት ድፍረትም፣ ሌጣ ድፍረት አይደለም፡፡ ሌላ ፊት በሩቅም ሆነ በቅርበት ያስተዋለ ነው፡፡ ልዕለ ኃያላዊ የመገፋፋት ትግሉ፣ በግልጽም (ማዶ ለማዶ በተለያየ መልክ እየተዋጉም እየተቃቀፉም) ሆነ ሥውር በሥውር እየተካሄደ ነው፡፡ በአፍሪካ ጠረፋማ አገሮች ከህንድ ውቅያኖስ እስከ ቀይ ባህር የጦር ጣቢያም ሆነ የወደብ ጣቢያ ተኮናትሮ እግር የመትከል ሽሚያው ክምችት እየጨመረ የመጣው በንግድ መስመር ጥቅም ምክንያት ብቻ ሳይሆን፣ በአመዛኙ እንዲያውም የአፍሪካን የየብስና የባህር/የውቅያኖስ የተፈጥሮ ሀብት ዒላማ ያደረገ ነው፡፡ በባብኤል መንደብ በኩል አድርጎ ወደ ስዊዝ ቦይ ከሚያመራው መስመር ራስጌ ሌላ የንግድ መስመር ቢዘረጋ እንኳ የግርጌው ሽሚያ ጭር የማይለው ለዚህ ነው፡፡

አፍሪካ ላይ ባተኮረ ዓላማ ውስጥ ነባር የጥቅም ድርሻን እንዳለ የማቆየት/የማሳደግ ፍላጎት እንዳለ ሁሉ፣ ነባሩን ባለ ጥቅም ተጋፍቶ የራስን ጥቅም የመተካት/የማስፋፋት ፍላጎት ሁሉ ይስለከለካል፡፡ አፍሪካ በዘራፊ ንግድና በባሪያ ንግድ የተቦጠቦጠችበት፣ ቀጥሎም በቀጥተኛ ቅኝ የተሰለቀጠችበት ታሪክ የተፈጸመው ኋላቀርነቷ አጋልጧትና ጠረፎቿ የጥቃት ማኮብኮቢያ እየሆኑ ነበር፡፡ ዛሬም በአፍሪካ ቀንድ ዙሪያም ሆነ በሌሎች የጠረፍ አካባቢዎችና የመሀል አገሮች ውስጥ ኃያላን አገሮች ጦር ጣቢያ እስከ መክፈት፣ እግራቸውን አስገብተው የሚገኙት በአፍሪካ የግስጋሴ አቅም ማነስ ምክንያት ነው፡፡ ትርምስ፣ ሽብር፣ አለመረጋጋት የሚመላላስባቸው አካባቢዎች ደግሞ ከሌላው ይበልጥ ለውጭ ኃይል ጣልቃ ገብነትና ጣቢያነት በአቅም የለሽነታቸው ምክንያት ይጋለጣሉ፣ የአፍሪካ ቀንድ የአሁኑ ሁኔታ የዚሁ ውጤት ነው፡፡ ብዙ መገለልና መጠመድን ያየችው ኤርትራ አነሰም በዛ ለኃያላን ጣቢያነት ሳትንበረከክ እስካሁን መቆየቷ የሚደንቅ ነው፡፡

ክርንን፣ ማዕቀብን፣ ወታደራዊ ዕገዛን፣ የፍንቀላ ተንኮልን፣ እርጥባንና ብድርን እንደሚሻቸው ብቅ ጥልቅ እያደረጉ ታዛዣቸውና መጠቀሚያቸው እንደሚያደርጉን ሁሉ፣ እኛም በፊናችን በእነሱ የሽሚያ ፉክክርና ቅራኔዎች ውስጥ ለእኛ በሚበጅ ብልህነት መሹለክለክ፣ ዛቻና ጥፍራቸውን እያገረምን ግስጋሴያችንንና ትስስራችንን ማጠንከር ይጠበቅብናል፡፡  የተረጋጉ አገሮች ሆኖ የመቀጠል ከባድ ፈተና፣ ብልህና የተጋገዘ መፍጨርጨርን ከመቼውም ይበልጥ ዛሬ እየጠየቀን ነው፡፡ ይህም በአፍሪካ አኅጉራዊ ኅብረት ደረጃ ከመተጋገዝ አንስቶ በየክፍለ ቀጣናችን የአንድ አገር ያህል በሆነ መዋቅር አገራዊ ጥቅሞቻችንን፣ ደኅንነታችንንና ግስጋሴያችንን ማስተዋልና ማስተሳሰርን ሁሉ የሚፈልግ ነው፡፡ በዚያ ዓይነት የዕይታና የተግባር ግቢ ካልሆነ በቀር የእያንዳንዱ አገር የየብቻ ፍር ፍር የትም አይደርስም፡፡ በእዚያ ዓይነት ግቢ ውስጥ ተገብቶ የሚካሄደው የማደግ ጥረት እንኳ አበሰኛ እንደሚሆን (በጥባጭ፣ አጋጪ፣ አፋራሽ እንደማያጣው) ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

በአፍሪካ ደረጃም በቀጣናና በአገር ደረጃ፣ ዝምታ ብልጠትም ጅልነትም ሊሆን የሚችልበት ሥፍራና ጊዜ አለ፡፡ ‹‹አሁን በአፍሪካ አገሮች በተለይም በስተምሥራቅ እየታየ ያለው ከበባ አፍሪካን ለሌላ ዙር ስልቀጣ የሚዳርግ ነው!›› የሚል አኅጉራዊ ውሳኔ አሳልፈን ልፍላፎ ብንጀምር አፍሪካን ከአደጋ አናተርፍም፡፡ የአፍሪካ ጉዳት ካለመለፍለፍ የመጣ እንዳለመሆኑ በመለፍለፍ አይቃለልም፡፡ በድህነት፣ በቀውሶችና በጥገኛ አድራጊ የጥቅም ክሮች የተተበተብን እንደ መሆናችን የልፍላፎ ትብብራችን ከጤዛ የራቀ ዕድሜ አይኖረውም፡፡ ጅል ልፍላፎ የሚያስከትለው ውጤት ከአፍሪካ ጥቅም የሚሹትን ኃይሎች ሳትዘናጉ ከፋፍሉን የሚል ንቃት ከመስጠት አይዘልም፡፡ በዚህ ነጥብ ውስጥ እየተባለ ያለው እንለጎም ሳይሆን፣ የሰምና የወርቅ ጨዋታን እንወቅበት ነው፡፡ እነ ሳዑዲም ሆኑ እነ ቻይና ከአፍሪካ ጋር ስለ‹አጋርነት›፣ ስለ‹ጋራ ጥቅም›፣ የአፍሪካ ልማትን ስለ‹ማገዝ› ወዘተ፣ ወዘተ. ሲያወሩ ኩልል ስላሉ ፍላጎቶቻቸው እየተናገሩ አይደለም፡፡ በእኛም በኩል የሚፈለግብን በዚሁ ዘይቤ እየተወዳጀንና እየተግባባን፣ ሰነካክለውን ያሉ የሶሲዮ ኢኮኖሚና የፖለቲካ ችግሮች ለማቃለል መጠበብ ነው፡፡

መጠበባችን አረረም መረረም እንደ አንድ አገር እያሰቡ መተጋገዝንም የሚፈልግ ነው፡፡ የአፍሪካ ቀንድ የግስጋሴ ዕጣም ከዚህ ውጪ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ የጥቅሞች መከበርና የግስጋሴ ዕድልም የዚሁ ቀጣናዊ ዕጣ አካል ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የኢትዮ-ኤርትራ ተጣጥሞ ለመገስገስ መቻል፣ በብልህ የተባበረ ልማት እንደ ቀጣና የመትረፍ አካል ነው፡፡ እንደ እዚያም ሆኖ የኤርትራና ኢትዮጵያ ጉዳይ ከሌሎቹ አባል ጎረቤቶች ጋር በአንድ ከመታየት ያለፈ የብቻ ታሪክና ባህርይም አለው፡፡ አጠቃላይ ቀጣናው የዘመዳም ማኅበረሰቦች ረዥም ታሪክ ያለበት ቢሆንም፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ የዝምድና ታሪክ ደግሞ በልዩ ዓይን ለመታየት የሚበቃ ነው፡፡

ከዋናው የቀጣናዊ ትስስር ግቢ ሳልወጣና በዚሁ ዕይታ እየተመራሁ (ለቀጣናዊ የተሳሰረ ግስጋሴ የሚኖረው የኢትዮ ኤርትራ ገንቢ ሚና በማይፋረስበት አኳኋን) ኢትዮ-ኤርትራ ያላቸውን የብቻ ሥፍራ እንደሚከተለው እደረድራለሁ [ነጥቦች ከአሁኑ የዓለማችንና የቀጣናችን ወቅታዊ እውነታ ከተረዳኋቸው ግንዛቤዎችና በ2003 ተጽፎ በበይነ መረብ ላይ ከተለቀቀ ‹‹ኢትዮጵያና ኤርትራ የቅኝ ወጥመድን የሰበረ ነፃነትን መኖር ይፈልጉ ይሆን?›› ከሚል ጽሑፍ (በስተኋላ ታሪክ ወህኒያችን ወይስ መማሪያችን? በሚል ያልታተመ መጽሐፍ ውስጥ ተካትቶ ከተሠራጨ) ጽሑፍ  የተጨመቁ ናቸው]፡፡

 • ኢትዮጵያ ወደብ ያጣችበትና ኤርትራ ቅኝ የወደቀችበት ታሪክ፣ ኤርትራን ካካተተው ረዥሙ የኢትዮጵያ ታሪክ ጋር ሲተያይ ሚጢጢ ጊዜን የሚሸፍን፣ ኢትዮጵያን የመቀነስና ከባህር ማዶ ግንኙነት የማፈን ትንቅንቅ አንድ መገለጫ ነው፡፡ እናም፣ በምንም መመዘኛ የኢትዮጵያን ታሪካዊ የወደብ መብት ለመሰረዝ መከራከሪያ ለመሆን አይበቃም፡፡ ፍትሐዊ የሆነ ህሊና ያለው ማንኛውም ልሂቅ ይህንን ለማስተዋል ይችላል ተብሎ ተስፋ ይደረጋል፡፡
 • ኤርትራ ቅኝ በተያዘችበት ጊዜ ሁሉ፣ ቀሪዋ ኢትዮጵያ ለኤርትራ ተወላጆች የማይንጓለሉባት አገራቸው ሆና እነሱም አገራችን ብለው የኖሩባት—የለፉላት—የተዋደቁላት አገር ነች፡፡ ለዚህም በኢትዮጵያ የተጋድሎ ታሪክም ውስጥ ሆነ በኢትዮጵያ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ታሪክ ውስጥ በቂ ምስክርነት አለ፡፡
 • ኢትዮጵያን ሙሉ ለሙሉ ለመዋጥ የሞከረችው ፋሽስት ጣሊያን ድል ተመትታ ከኢትዮ-ኤርትራ ምድር በተነቀለችበት ጊዜ፣ በኤርትራ ሰዎች ውስጥ የኤርትራን ነፃ አገር መሆን ፈላጊዎች እንደነበሩ ሁሉ ከኢትዮጵያ ጋር መዋሀድም በሀቅ የነበረ ፍላጎት ነበር፡፡ የኢትዮጵያም አካሌ ነች ባይነትና የባህር በር ታሪካዊ መብት አፍጥጦ ነበር፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራን በፌዴሬሽን መቀላቀል የቋጨው ውሳኔም የዘፈቀደ ውሳኔ ሳይሆን፣ ይፋተጉ የነበሩ ታሪካዊ መሠረት ያላቸው ፍላጎቶችን ያቻቻለ ነበር፡፡
 • በስተኋላ፣ የፌዴሬሽኑ መፍረስ ትልቅ ታሪካዊ ጥፋት ነበር፡፡ ይህንን ለማሳመን በጊዜው የሙሉ ቅልቅል እውነተኛ ፍላጎት ነበር ወይስ በሴራና በጥቅም ድለላ የተከናወነ ነበር የሚል ውዝግብ ውስጥ መግባት አያስፈልግም፡፡ ኤርትራ ውስጥ ብልጭ ብሎ ወደ ነበረው የዴሞክራሲ ሽታ ኢትዮጵያ በመሄድ ፋንታ፣ ኤርትራን ኢትዮጵያ ውስጥ ወደ ነበረው የንጉሥ ፍፁማዊ ሥልጣን ማንሸራተት በራሱ፣ የኤርትራና የኢትዮጵያን የፖለቲካ ዕድገት የጎዳ፣ በሁለቱ ዘመዳም ሕዝቦች ዘላቂ ጥቅም ላይ ጠንቅ የተከለ ነበር፡፡ እናም ለሓርነት ትግል መቀስቀስ ምክንያት ለመሆን የሚያንስ አልነበረም፡፡ ዴሞክራሲ ናፋቂ የንቃተ ህሊና አቅም ኖሮ ቢሆን ኖሮ ከኢትዮጵያ በኩልም ጠንካራ ተቃውሞ ሊገጥመው በተገባ ነበር፡፡ ውሎ ሲያድር ቢያንስ በውጭ ባሉ የኢትዮጵያ ልጆች ዘንድ፣ የፌዴሬሽንን መመለስ የሚወተውት እንቅስቃሴ አለመደረጉም የጎዳ ጉድለት ነበር፡፡
 • የኤርትራን ከኢትዮጵያ መነጠል የማይዋልል የማዕዘን ድንጋይ ለማስያዝ የኤርትራ ሓርነት ታጋዮች ምኒልክ ሸጦናል/የኢትዮጵያ አካል መሆንም ሌላ የቅኝ ተገዥነት ምዕራፍ ነው የሚሉ ቅያሜዎችን በትግሉ ዘመን አጎልብተዋል፡፡ ተነጥሎ በኢንዱስትሪ የተመነደገች አገር የማልማት ህልሙም አብሮ ነበር፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ውስጥ እያደገ የመጣው የኢትዮጵያ የለውጥ ፖለቲካም የኢትዮ ኤርትራን ጉዳይ በተመለከተ ረቺና የጠራ መፍትሔ ማፍራት (አለመቻል) በድክመቱ ነበር፡፡ የ1966 ዓ.ም. አብዮት በኢትዮጵያ ሲመጣ፣ በኢትዮጵያም በኤርትራም በኩል የነበረ ተራማጅ ነኝ ባይ ፖለቲካ፣ በሁለት በኩል የነበረውን ደም መፋሰስ የሚያስወግድ መፍትሔ ማፍለቅ አልቻለም፡፡ ደርግ ከተቋቋመ በኋላም ከደርግ በኩልም ሆነ ከሓርነት ታጋዮቹ በኩል ሊገፋ የማይችል የመፍትሔ መላ (መስዋዕትነቱ እየበረታና ትንቅንቁ እየተራዘመ ሲመጣ እንኳ) ከአንደኛቸውም ሊመጣ አልቻለም፡፡ የ30 ዓመታት የደም ግብር የዚህ ሁሉ ውጤት ነው፡፡
 • 1983 ዓ.ም. ግንቦት ደርግ ወድቆ ሕወሓት/ኢሕአዴግና ሻዕቢያ በባለድልነት ድርሻ፣ ድርሻ ይዘው ሥልጣን ላይ የወጡበት ጊዜ፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ ዕጣ ፈንታ የተያያዘ መሆኑን ለማስተዋልና ለመቀበል ዕድል የሰጠ ነበር፡፡ ሁለቱም ግን የሁለቱን አገሮችና ሕዝቦች ጥቅም ያቻቻለ መፍትሔ ላይ ከመሥራት ይልቅ ኢትዮጵያን የግዳይ ሲሳይ ባስመሰሉ ተግባራት ላይ ናውዘው ነበር፡፡ ከሕወሓት/ኢሕአዴግ ገዥነት በፊት የነበሩት መንግሥታት፣ ጥፋት የማረም ፖለቲካዊ ተግባር ያልታያቸውና ወታደራዊ ‹‹መፍትሔ›› ላይ የተገተሩ ነበሩ፡፡ የኢሕአዴግና የኤርትራ ሐርነት ግንባር የድል አድራጊነት ምዕራፍ ግን፣ ኢትዮጵያ አገራዊ ጥቅሟን በአግባቡ የሚያስከብር መንግሥታዊ ኃይል ጎድሏት ያነከሰችበት ጊዜ ነበር፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዘው የመጡት የአፋሮች ጥያቄና ትግል መታፈንና መደቆስ፣ እንዲሁም ፌዘኛው ሪፈረንደም የዚሁ ነፀብራቆች ናቸው፡፡ እነዚህ ከጥፋት የማይሻሉ ድርጊቶች፣ ከ1990 እስከ 1991 ዓ.ም. ጦርነት፣ በጦርነቱም ሕዝብን መጠቃቂያ ማድረግ፣  የጦርነቱ አጨራረስ ይዞት የመጣው አንካሳ ስምምነትና ከዚያ በኋላ የቀጠለው መተነኳኮል ሁሉ የሁለቱን አገሮች ዘላቂ ጥቅሞች የጎዱ ነበር፡፡
 • ያ ሁሉ አልፎ ዛሬ የምንገኝበት ጊዜ ሁለቱ አገሮች በነገሮች አያያዛቸው ምን ያህል የግስጋሴ ዕድላቸውንና ጥቅማቸውን እንዳጎሳቆሉ ለልሂቃኑም ለሕዝቦቻቸውም ወለል አድርጎ አሳይቷል፡፡ ኢትዮጵያ ውስን የኢኮኖሚ ዕርምጃ ብታሳይም የወደብ አገልግሎት ክፍያ ምን ያህል ጥሪት አንካች እንደሆነ በደንብ ቀምሳለች፡፡ ከቀይ ባህር ጂኦ ፖለቲካዊ ሥፍራ ሳይርቁ መራቅም፣ ምን ያህል ጥቅም የማስከበር አቅም እንደሚያሳጣ በደንብ ተገንዝባለች፡፡ በኤርትራ በኩልም ቅዠቶች ተንነው እውነታ ኩልል ብላለች፡፡ ኤርትራ ጂኦ ፖለቲካዊ ተሰሚነቷ ኮስሷል፡፡ የቀዘቀዘ ልማቷ  በፈታኝ ጥያቄዎች ተወጥሯል፡፡ ጭር ያሉ ወደቦች ታቅፎ በልማት እጥረት መቆራመድን መቀጠል፣ ጠረፍና ወደቦቿን ለኃያላን እያኮናተሩ ኪራይ ቃራሚ ወደ መሆን ጥገኝነት መንከባለል፣ አለዚያም ነፃ አገርነቷ በተከበረበት አኳኋን ከኢትዮጵያና ከቀሪ ጎረቤቶቿ ጋር ተሳስሮ መመንደግ፣ እነዚህ ጥያቄዎች አፍጥጠዋል፡፡
 • የሁለቱም አገሮች የጋራ ጥቅሞች እንዲህ ባፈጠጡበት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ፣ ግስጋሴን ባልጠቀሙ አሮጌ ቅያሜዎች ውስጥ ገብቶ ክርክር መዘርጋት አሮጌ ጉዳይ ላይ ጊዜ ማባከን ነው፡፡ ማንኛችንም በምኒልክና በኃይለ ሥላሴ ዘመን ውስጥ አንኖርም፡፡ የምንኖረው ዛሬና ነገ ውስጥ ነው፡፡ ዛሬ የምንሻው ግስጋሴና ለማንም የማይሽቆጠቆጥ የአቅም ጥንካሬ የሚጠይቀን ጥያቄ፣ ከነፃነት ጋር በተግባባ ትስስር አንድ ላይ መሥራት ያስፈልገናል አያስፈልገንም? የሚል ነው፡፡ የጥያቄው መልስ በነባራዊው የእውነታ መሬት ላይ በጉድፍ ሳይሸፈን ይታያል፡፡ የግብዝነት ጉድፍ ያለው የሰዎች ህሊና ውስጥ ነው፡፡ እውነታን ለመቀበል ገታራ በመሆን፡፡
 • የዛሬ ኢትዮጵያውያን ከጎረቤት ዘመድ ጋር የሚፈጠር ልል ኅብረትን የመዘርጠጥ ፍላጎት ከቶም የሌላቸውና ከዚህ በፊት በሆነውም የሚቆጩ እንደሆኑ ሁሉ፣ የዛሬ የኤርትራ ሰዎችም ከትናንቶቹ በበለጠ ስክነት፣ የጋራ ታሪካችንን በሚዛናዊ ህሊና ገምግመው የኢትዮጵያ የወደብ መብት አለኝ ባይነት ፍትሐዊ ጥያቄ መሆኑንና ከ1983 ዓ.ም. ግንቦት ወደ እዚህ በነበረ የተዛባ የሁለት ቤት ግንኙነት የሁለቱን ዘመዳም ሕዝቦች ጥቅም የጎዱ ስህተቶች እንደተሠሩ ማስተዋል ሊቸግራቸው አይገባም፡፡
 • ኤርትራና ኢትዮጵያ ከትስስር ርቀው አሁን በሚገኙበት የዝም ዝም ሁኔታ ውስጥ መቀጠል ለሁለቱም ጉዳት ነው፡፡ በዝም ዝም ታስሮ ላለመቆየት የሚያደርጉት ዕርምጃ ፍሬያማ የሚሆነውም ዓይነተኛ እንቆቅልሻቸውን በደንብ ካወቁት ነው፡፡ የጂቡቲ ወደብን ስትጠቀሙ ወጪ እንደምታወጡ ሁሉ የእኔንም ወደቦች በዚያው መልክ ተጠቀሙ ብትል ኤርትራ ኢትዮጵያውያን እንደ ጥቃት ነው የሚቆጥሩት፣ ምክንያቱም ከበስተጀርባ የወደብ መብት ጥያቄ ስላላቸው፡፡ ኢትዮጵያ የኤርትራ ወደቦችን ከመጠቀም ብትቆጠብ (ቁጥብነቷ ከሌላ ጎረቤት ወደብ እንደ ይዞታ አልምቶ የመጠቀም ዕድል ከማግኘት ጋር የተያያዘ ቢሆን እንኳ)፣ ኤርትራውያን ላይ የሚፈጠረው ስሜት በውድድር ከመበለጥ አልፎ የሚሄድና የጥቃት ያህል ቅሬታ ሊያሳድር የሚችል ነው፡፡ ምክንያቱም፣ ከዛሬ በስተጀርባ ከጉርብትናና ከሕዝብ ተመሳሳይነት ባሻገር፣ የአንድ አገር ልጅነት ያህል የሆነ ረዥም የሥጋ ዝምድናና የጋራ እህል ውኃ ታሪክ ስላለ፡፡ ይኼው ባለ ብዙ ፈርጅ የረዥም ዘመን ዝምድና አሰብንና ምፅዋን የመፆም ሙከራን ለኢትዮጵያ የገዛ ቤተሰብን የመበደል ነውር ያደርግባታልና፣ ሌላ ጥሩ አማራጭ ብታገኝ እንኳ ኤርትራውያን ያንኑ ያህል ጥሩ ዕድል እንዲያመቻቹ ማሳሰብ ለኢትዮጵያ የዝምድና ኃላፊነቷ ነው፡፡ ኤርትራ በመግባባት አንዱን ወደብ ለኢትዮጵያ የተወችበት ወይም ሌላ ወደብ በኤርትራ ጠረፍ አልምታ እንድትጠቀም የፈቀደችበት ውል (በረዥም ጊዜ ኪራይ/በጥቅም ልዋጭ) ቢኖርና ከዚያ ወዲያ ኢትዮጵያ አፍንጫሽን ላሺ የሚል መሳይ የቸለልታ ግንኙነት ቢከጅላት፣ በገዛ ሥጋ ዘመድ ማጅራት ላይ ካራ ከማሳረፍ በላይ በገዛ ብሔራዊ ጥቅሟ ላይ ካራ የማሳረፍ ጉደኛነት ይሆንባታል፡፡ መሸካከር ለሁለቱ አገሮች ጥቅሞች ጠንቅ ነው፡፡
 • እንዲህ ማድረግ እንዲህ ያለ ውጤት ይኖረዋል እየተባለ ከላይ የተቀመጠው ነገር ሁሉ ከመደረጉ በፊት የሚያስከትለው ውጤት የታወቀ ሆኖ ነው፡፡ አንዳንድ ሰው አጉል ጥንቆላ አድርጎ ሊያቀለውም ይችል ይሆናል፡፡ ‹‹ጥንቆላው›› ግን የቅርብ ታሪከኛ ምስክር አለው፡፡ ዓብይ አህመድ አስመራ የገቡበት የመጀመሪያው የዕርቅ መክፈቻ ትዕይንት በተፈጸመ ጊዜ አስመራ በነበረው አቀባበል የታየው ገደብ ባጣ ዕንባ፣ መተቃቀፍ/መሳሳምና እልልታ የተሞላ መነፋፈቅ፣ እንዲሁም ከኤርትራ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ ትዕይንቱን በቴሌቪዥን እያስተዋሉ የተካሄደው የደስታ ለቅሶ፣ በቤተሰብ መሀል መኮራረፍ/አለመጠቃቀም/ጀርባ መሰጣጣት መብት ሳይሆን መጎዳዳት መሆኑን የተናገረ ነው፡፡ የሁለቱ አገሮች ልሂቃንና መሪዎች አስተዋይነት ካላቸው ይህንን ልብ ይበሉ!!
 • ከላይ የተደረደሩት የጥፋት ምናልባቶች የተመዘኑት ከዝምድና ጥግ ብቻ ነው፡፡ የሰመረና የጠነከረ ግንኙነት፣ ለሁለቱም አገሮች የዝምድና ብቻ ጉዳይ ግን አይደለም፡፡ የቀዘቀዘ ግንኙነት፣ ‹‹በየፀበላችን ተከባብረን እንኑር›› መባባል የጋራ ጂኦ ፖለቲካዊ ጥቅምን ማጥቃትና ማስጠቃትም ነው፡፡ የዚህ ጂኦ ፖለቲካዊ ጥቅም መጠበቅ የእነሱ ጥንካሬና ትብብር ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ አሁን እየተፈለቀቀ በመጣው የዓለማችን አዲስ ውስብስብ እውነታ ውስጥ፣ የሁለቱ መተባበርና የጂኦ ፖለቲካ ጥቅማቸውን ለማስከበር የመቻል ጉዳይ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናቸው ትብብብርና ጥቅም አካል ነው፡፡ ሁለቱ በተናጠልም ሆነ በጋራ የሚሠሩትን ሥራ በዚህ ቀጣናዊ ግቢ ውስጥ ሆነው መመዘን ይገባቸዋል፡፡ ይህንን እስከ ሳቱ ድረስ የራሳቸውን ጥቅም ለሚያቆስል ስህተት ይጋለጣሉ፡፡
 • ከዚህ ነጥብ አኳያ፣ የቀይ ባህር ፎረም ውስጥ ኢትዮጵያ መግባት አለባት ብሎ መከራከር የኤርትራም ሁነኛ የጥቅም ኃላፊነት ነው፡፡ ይህ ጥቅም ዛሬ ባይታይ ውሎ አድሮ መታየቱ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ኤርትራ ጥቅሟ የሚሟላው በአፍሪካ ቀንድ ትምምን ውስጥ ነው፡፡ ቁርጥ ባለ አነጋገር የኤርትራም ሆነ የኢትዮጵያ የቀይ ባህር ጥቅም መከበር፣ ከቀይ ባህር ፎረም አባልነት በበለጠ አፍሪካዊና ቀንዳዊ የኅብረት አቅምንና ተገንነትን ይሻል፡፡
 • አሁን በኢትዮጵያ ልሂቃን አካባቢ ሄድ መለስ እያለ የሚሰማውን የወደብ መብትን በክስ ለማስከበር የሚያስችል ዓለም አቀፋዊ የሕግና የልምድ ድጋፍ አለ የሚል ነገር፣ ከላይኞቹ ነጥቦች አኳያ እንመዝነው፡፡ ወደ ክስ መሄድ በቀላል ተፅዕኖው የሁለቱን አገሮች ግንኙነትና መተጋገዝ የማቀዝቀዝ ጠንቅ አለው፡፡ የክሱ ውጤትም ይቅረብ ይራቅ አይታወቅም፡፡ በክስ መርታት ቢመጣም ወደቡን ማግኘቱና አግኝቶም በሰላም ለመጠቀም መቻሉ ሌላ ትግል ሊሆን ይችላል፡፡ እዚያ ከመደረሱ በፊት፣ የክስ መጀመር በራሱ፣ የሁለቱን አገሮች መሸካከርና የቀንዱን ቀጣና መታወክ ጥቅማችን የሚሉ ኃይሎች ፌሽታቸው እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ሁለቱን አገሮች ለማናቆር ተንኮል እንዲያደሩ ያነቃቃቸዋል፡፡ ሊደራ የሚችለው ተንኮል ደግሞ የዘመዳሞቹን የውስጥ ሰላም እስከ መበጥበጥ ድረስ ርዝማኔ የማግኘት ምናልባት ያዘለም ነው፡፡  ለዚህ ሁሉ አደጋ ተጋልጠውና የሚቆስሉትንም ያህል ቆስለው ዘመዳሞቹ አገሮች ልብ እስኪገዙ ድረስ፣ የቀይ ባህር ጂኦ ፖለቲካዊ ጥቅማቸውና ቀጣናዊ የህልውና ደኅንነታቸው ቆሞ አይጠብቃቸውም፡፡ በሁለቱ መሸካከር-መናቆር-መበጣበጥ የቀጣናቸውንም ጥቅምና ሰላም ያስጠቃሉ፡፡ የዓለማችን ውስብስብና ተለዋዋጭ ሁኔታ በቀይ ባህርና በህንድ ውቅያኖስ አካባቢ አገሮች ላይ እየተጋፋ ያለው የጥቅም ሽሚያ፣ የአካባቢው አገሮች ተጋግዘው ጥቅማቸውን የማስከበር አቅም እንዳይኖራቸው አድርጎ ከመከፋፈል፣ በውዳቂ ጥቅም ከማደንዘዝና የአገሮችን ድህነትና መመሳቀል እንዲራዘም ከማድረግ የማይመለስም መዳፍ ነው፡፡ በተንኮልና በመሸንገያ ሳይበለጡ ይህንን ፈተና በአሸናፊነት አልፎ ለመሄድ፣ የአፍሪካ ቀንድ ጎረቤታሞች ጉርብትናቸውን በተሳሰረ የልማት ገመድ ለመተብተብ መፍጠን ዋነኛ ዋስትናቸው ነው፡፡ ፈጥነው በልማት ከተወሳሰቡ፣ ነባራዊ የልማት ውስብስቡ በራሱ የማይከሽፍ ቀጣናዊ የጋራ ትድድር የመፍጠር ሁነኛ አቅምና ደኅንነታቸውን የሚጠብቅ መከታ ይሆናል፡፡ በዚህ ነጥብ ላይ ጫጫታ ሳይሻ በተግባር የሚተጋ መግባባት ቀጣናችን ይፈለግበታል፡፡
 • በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያ መንግሥትና ልሂቃኑ፣ የኤርትራ መንግሥትና ልሂቃኑ መግባባት ለሁለቱ አገሮች መፍትሔ አስፈላጊ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጣዊ የሰላም ችግሯን ማቃለሏ ለኤርትራም ለቀጣናውም ጥቅም መቃናት አስፈላጊ እንደሆነ ሁሉ የኤርትራም ሰላም ሆኖ መቀጠል ለኢትዮጵያና ለቀንዱ አስፈላጊ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በምዕራብ አገሮች ግድምና በእስራኤል ውስጥ ተከሰተ የተባለው ለየአገሮቹ የፀጥታ ኃይሎች እንኳ ያልተበገረ ድብድብ ኤርትራ ውስጥ አመፅ ነክ ትርምስ እንዳይወልድ ያስፈራራል፡፡ የዛሬው የዓለማችን ሁኔታ፣ የበረሃ ትጥቅ ትግልንም ሆነ የከተማ አመፅንና ወታደራዊ ግልበጣን ከትርምስ አዙሪት ጋር የሚደረግ አደገኛ መዳራት እያደረገው ነው፡፡ በቀውሱ ውስጥ ብቅ ያሉ ቡድኖች ላይ እየተለጠፉ ከትርምስ መባባስና መራዘም አትራፊ ለመሆን የሚሠሩ ምን ያህል ኃይሎች በውጭ እንዳሉም በቅርባችን ያሉ ቀውሶች እያሳዩን ነው፡፡ እናም ኢትዮጵያና ኤርትራ ከእነ ልሂቃኖቻቸው፣ ከሌሎችና ከራሳቸው የኪሳራ ልምድ የመማር አቅም እንዳላቸው ለሕዝባቸውም ለአፍሪካም ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡፡
 • ኤርትራውያንና ኢትዮጵያውያን ዝምድናቸውን የሚያጠናክርና የቀጣናቸውን ትስስር የሚጠቅም፣ ያልዘገየ የጋራ መፍትሔ ላይ እስከሚደርሱ ድረስም በዝምድና አይለገምምና ከምፅዋና ከአሰብ ቢያንስ አንዳቸው በዘመድ ዋጋ ወደ ሥራ እንዲገቡ በማድረግ መጠቃቀም የጋራ ኃላፊነታቸው ነው፡፡

ይህንን የውይይት መነሻ ሐሳብ ሳቀርብ ለኢትዮጵያም ለኤርትራም ወገኖቼ ያለብኝን ኃላፊነት እንደመወጣት ነው የምቆጥረው፡፡ በሁለቱ አገሮች ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ልሂቃንም ስለ‹ጦርነት አደጋ›፣ ስለ‹ተስፋፊነት›፣ ወዘተ እያወሩ የሁለቱን አገሮች መናቆርና የአፍሪካ ቀንድ አገሮችን መከፋፈል ለሚሹ ፍላጎቶች ተቀጥላ ከመሆን ወጥተው፣ በጋራ ወገንተኝነት መንፈስ ለውይይት የቀረበውን ጽሑፍ አንኳር ነጥቦች አስተውለው ወደ መተሳሰብ እንዲመጡ ጥሪ አቀርባለሁ፡፡ በተለይ የሁለቱ አገሮች ምሁራን በጥናት መክረውና ሰልቀው ለሁለቱ አገሮች ፖለቲከኞችና መንግሥታት የሚበጅ መግባቢያ እንዲያቀርቡ ጉጉቴና ተስፋዬ ነው፡፡ 

ስኬት ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ሕዝቦች!

ስኬት ለአፍሪካ ቀንድ ሕዝቦችና ለመላው አፍሪካ!!!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...