Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

ቀን:

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና ዘረፋ የሚፈጽሙ ጫኝና አውራጆች መኖራቸው በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል፡፡ በተለይ የጋራ መኖርያ ቤቶች፣ ሪልስቴቶችና የማኅበር ቤቶች በብዛት የሚገኙባቸው እንደ ቡልቡላ፣ ኃይሌ ጋርመንት እንዲሁም ቱሉዲምቱ አካባቢዎች ከጫኝና አውራጅ ቡድኖች ጋር በተያያዘ ተደጋጋሚ ምሬቶችን መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡

ጫኝና አውራጅ በኅብረተሰብ ላይ ይፈጽሙት የነበረውን እንግልትና ሥቃይ ለመፍታት አዲስ አደረጃጀት ተግባራዊ ማድረጉን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

ቢሮው ችግሩን እፈታለሁ ብሎ ወደ ሥራ ቢገባም፣ የጫኝና አውራጅ ነገር ለብዙዎች ፈታኝ ነው፡፡ ንግግር ሳይሆን ጉልበትና ማስፈራራት የታከለበት መሆኑም ተጠቃሚዎችን ስጋት ላይ የሚጥል ሆኗል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሥጋቱ ካደረባቸው መካከል ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ይገኙበታል፡፡ ወ/ሮ መዓዛ ከዚህ በፊት ከሃና ማርያም ተከራይተው ከሚኖሩበት ቤት ጋርመንት አካባቢ በሚገኘው ኦሮሚያ ኮንዶሚኒየም ቤት ቀይረው ሲገቡ ራሳቸውን በቡድን አደራጅተናል በሚሉ ጫኝና አውራጅ ሰዎች ከፍተኛ እንግልት እንደደረሰባቸው ይናገራሉ፡፡

በተለይ ልጅ ይዞ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ ቤት መቀየር በራሱ አሰልቺ እንደሆነ የሚናገሩት ወ/ሮ መዓዛ፣ ከአንድም ሁለት ጊዜ ቤት ሲቀይሩ ‘ዕቃውን እኛ ነን የምናወርደው’ ከሚሉ ቡድኖች ጋር ግብ ግብ ውስጥ መግባታቸውን ያስታውሳሉ፡፡

የኑሮ ውድነት፣ የቤት ኪራይ እንዲሁም የልጆች ትምህርት ቤት ክፍያ በራሱ ከፍተኛ ወጭ የሚጠይቅ ነው የሚሉት እኚህ እናት፣ ሃና ማርያም አካባቢ ተከራይተው ከሚኖሩበት ቤት ወጥተው ኦሮሚያ ኮንዶሚኒየም ሲገቡ፣ የቤት ዕቃዎችን ለማውረድ 20 ሺሕ ብር መጠየቃቸውን ለሪፖርተር ያስረዳሉ፡፡

ከሁሉም በላይ ጋርመንት አካባቢ በሚገኘውና ኦሮሚያ ኮንዶሚኒየም በሚል በሚታወቀው ስፍራ ተደራጅተው የሚገኙ ጫኝና አውራጅ ነን የሚሉ ቡድኖች የሚጠይቁት ገንዘብ የማይቀመስ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ከዚህ በፊትም ‘እኛ ነን የምናወርደው፣ ሌላ ሰው አያወርድም’ በሚል ከፀጥታ አካላት ጋር ጭምር መጋጨታቸውን ይናገራሉ፡፡

በቅርቡ መንግሥት ያወጣው መመርያ ተግባራዊ ከሆነ ከተለያየ ቦታ ቤት ቀይረው ወደ ሌላ ሥፍራ የሚገቡ የማኅበረሰብ ክፍሎች ዕፎይታን ያገኛሉ የሚሉት ወ/ሮ መአዛ፣ ይኼ ካልሆነ ተመሳሳይ ችግር በከተማዋ ይቀጥላል ሲሉ አክለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ እንደ ልባቸው የሚፈነጩ ጫኝና አውራጆች መበርከታቸውን የተናገሩት እኚህ እናት፣ በከተማዋ በተለያዩ ቦታዎች ቀላልም ሆነ ከባድ ዕቃዎችን ለማውረድ የሚጠይቁት ገንዘብ ከፍተኛ መሆኑን ለሪፖርተር ይገልጻሉ፡፡

በከተማዋ የሚገኙ አብዛኛው ጫኝና አውራጆች የሚፈጽሙት ተግባር አንድ ዓይነት መሆኑን፣ ብዙ ጊዜ የጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ የሚኖሩና ቤት የሚሠሩ ነዋሪዎች የችግሩ ገፈት ቀማሽ እንደሚሆኑ ያስረዳሉ፡፡

በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ምን ያህል ጫኝና አውራጆች አሉ ሕጋዊነታቸውስ ምን ይመስላል? የሚለውን ኅብረተሰቡ ስለማያውቅና ሕጋዊ ሕጋዊ ያልሆኑት ስለማይታወቁ ችግሩ ሊከሰት መቻሉንና ከዚህ በፊትም ጋርመንት አካባቢ በዚህ ችግር ምክንያት ሰው መሞቱን አስታውሰዋል፡፡

የችግሩ ገፈት ቀማሽ ከሆኑት አቶ ሙሉጌታ ታዬ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በከተማዋ በጫኝና አውራጆች ሥራ ላይ የተሰማሩ ቡድኖችን መንግሥት በተገቢው መንገድ መቆጣጠር ይኖርበታል፡፡

ከዚህ በፊት ከአምስት ጊዜ በላይ ቤት ሲቀይሩ ጫኝና አውራጆች በሆኑ ቡድኖች ከፍተኛ ገንዘብ መጠየቃቸውን የተናገሩት አቶ ሙሉጌታ፣ መንግሥት በዚህ ያክል ገንዘብ ብቻ አውርዱ የሚል የዋጋ ተመን ማውጣት ይኖርበታል ብለዋል፡፡

አብዛኛው ጫኝና አውራጆች በራሳቸው ፍላጎት እያስከፈሉ መሆኑን ገልጸው፣ በከተማዋም በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ ነጋዴዎች ጭምር ዕቃዎችን ለማውረድ ከጫኝና አውራጆች ጋር ጭቅጭቅ ውስጥ ሲገቡ ማየታቸውን ይናገራሉ፡፡

ከዚህ ቀደም በርካታ ሰዎች ከኖሩበት ቤት ወደ ሌላ ቤት ለመቀየር ቢፈልጉ ጫኝና አውራጅ የሚጠይቁት ወጭ እንዲሁም ባህሪያቸው ኃይል የታከለበት መሆኑ ያሳስባቸው እንደነበር፣ አሁን ላይ ግን መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ መመርያ ማውጣቱ መልካም እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

ይሁን እንጂ መመርያውም ወጥቶ ምን ያህል ተግባራዊ ይሆናል የሚለው ሥጋት እንደፈጠረባቸው፣ ለዕቃ ማጓጓዣ ከሚሆን የትራንስፖርት ወጪ በተጨማሪ ለጫኝና አውራጆች የሚደረገው የክፍያ ሥርዓት አግባብ እንዳልሆነ ጠቁመዋል፡፡

‘በግዴታ እኛ ነን የምናወርደው’ የሚሉ ጫኝና አውራጆች በከተማዋ መብዛታቸውንና በዚህም የተነሳ ሕገወጥ አሠራር መስፋፋቱን አክለዋል፡፡

ከሁሉም በላይ ከቦታ ቦታ ቤት መቀያየር በራሱ አሰልቺ መሆኑን፣ እሳቸውም ሆኑ ጓደኞቻቸው ጫኝና አውራጆችን ፍራቻ ቤት ሲቀይሩ የቤት ዕቃዎቻቸውን በሌሊት ማስገባታቸውን አስታውሰዋል፡፡

በተለያየ ጊዜም ቤት ሲቀይሩ ከጫኝና አውራጅ ብቻ ከ15 ሺሕ ብር በላይ መጠየቃቸውን፣ የያዙትንም ዕቃ በራሳቸው ወገን ለማስገባት ቢፈልጉም አይቻልም እንደተባሉ ይናገራሉ፡፡

በወቅቱ ከጫኝና አውራጆች ጋር ፀብ ደረጃ ላይ መዳረሳቸውን የተናገሩት አቶ ሙሉጌታ አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች ፀቡን ለማብረድ ፀጥታ አስከባሪዎችን ቢጠሩም የፀጥታ አካላት ለጫኝና አውራጆች ድጋፍ መስጠታቸውን ለሪፖርተር ይገልጻሉ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላምና የፀጥታ ቢሮ በጥቅምት 2016 ዓ.ም. ማብቂያ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ጫኝና አውራጆች ለሕዝብ የምሬት ምንጭ ሆነው በተለያዩ ሕገወጥ ተግባራትን ሲፈጽሙ ቆይተዋል፡፡

በመዲናዋ የሚገኙ ጫኝና አውራጅ ከማኅበረሰቡ አቅም በላይ ክፍያ በመጠየቅና የኅብረተሰቡን የፀጥታ ሥጋት በመሆን ምሬት መፍጠራቸውንም የቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

በዚህ መሠረት ይህንን አሠራር ለማዘመን ማኅበራት እንዲደራጁ መደረጉን ጠቅሰው፣ ጫኝና አውራጆችን መልሶ የማደራጀት ሥራው ከአራት ወራት በፊት ለአዲስ አበባ ከተማ የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ተሰጥቶት ሲሠራ መቆየቱን መናገራቸው ይታወቃል፡፡

በአደረጃጀቱ መሠረት 4‚829 አባላትን የያዙ 399 ጫኝና አውራጅ ማኅበራት በአዲስ መልክ ተቋቁመዋል፡፡

ማኅበራቱ ሕግና መመርያ ተከትለው እንዲሠሩ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላምና ፀጥታ ቢሮ በኩል አዲስ መተዳደሪያ ደንብ ተዘጋጅቶም በፍትሕ ሚኒስቴር አማካይነት መፅደቁ ይታወሳል፡፡

በደምቡም የጫኝና አውራጅ ማኅበራት ሥልጣንና ኃላፊነት የተገለጸ ሲሆን፣ ለእያንዳንዱ ለሚወርድና ለሚጫን ዕቃ ዓይነት የዋጋ ተመን ወጥቶለታል፡፡

በዚህ መሠረት አዲስ በተዘጋጀው ደንብ ዙሪያ ለጫኝና አውራጅ ማኅበራቱ አባላት በቂ ሥልጠናዎች እንደሚሰጥ ወ/ሮ ሊዲያ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት እነዚህ ማኅበራት ሥምሪት ይሰጣቸው የነበረው በሥራ ዕድል ፈጠራ ኢንተርፕራይዝ ቢሮ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ማኅበራቱን ከማደራጀት ጀምሮ አጠቃላይ አካሄዳቸውን በመገምገም ሥምሪት የሚሰጥበት አሠራር መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ከዚህ ቀድሞ የነበረው መመርያ ጫኝና አውራጅ ማኅበራት ሌሎችን ወክለው አሊያም ቀጥረው ማሠራት ይፈቅድ እንደነበር፣ በተሻሻለው አዲሱ መመርያ ጫኝና አውራጆች በውክልናም ሆነ ቀጥረው ማሠራት እንደማይችሉና ለሚጭኑትና ለሚያወርዱት ዕቃ ሙሉ ኃላፊነት የሚወስዱ መሆኑን የቢሮው መረጃ ያሳያል፡፡

በአዲሱ አደረጃጀት ጫኝና አወራጆች ጥሩ ሥነ ምግባር ያላቸው፣ ማኅበረሰቡን ሲያገለግሉ የነበሩና በበጎ ፈቃድ ሥራዎች የተሳተፉ እንዲሁም በሰላም መጠበቅ ዙሪያ ጉልህ ሚና ለነበራቸው ቅድሚያ መሰጠቱ ተገልጿል፡፡

ሪፖርተርም ለጫኝና አውራጆች የወጣው የዋጋ ተመን ምን ያህል ነው? ተደራጅተው የማይሠሩ ጫኝና አውራጆችን ለመቆጣጠር ምን ይደረጋል? የወጣው መመርያስ ለምን ያህል ጊዜ ተግባራዊ ይደረጋልና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ለመጠየቅ ጥረት ቢያደርግም ከተቋሙ በኩል ምላሽ ሳያገኝ ቀርቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...