Friday, March 1, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ

ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር እንወያይ፣ ዝምታ ፈፅሞ አይጠቅመንምና፡፡ ዝምታን ሰብረን ስለአገራችን ጉዳይ እንወያይ፣ አትወያዩ የሚለን ካለ ያበደ መሆን አለበትና መድኃኒት ይፈለግለት። ስለአገር ጉዳይ በብርቱ መነጋገር ያስፈልገናል፡፡

ወገኖቼ ነባር ታሪካችን፣ የአንድነት ዓርማችን፣ የኅብረት ኃይላችንና የመተማመን መርሐችን ሲጠፋ፣ ወገን ከወገን ሲጣላና ሲፋለጥ ዝምታው ምንድነው? የፍርኃት ማቅ ለብሰን እንደ ባዕድ ዳር ቁጭ ብለን ወሬ ስናዳምቅ መታየቱ ለአዕምሮአችን ሰላም ይሰጠን ይሆን? ልብ በሉ “የሞተው ወንድምሽ የገደለው ባልሽ፣ ሐዘን ቅጥ አጣ ከቤትሽ አልወጣ” ያለችውን ኢትዮጵያዊት አስተዋይ ሙሾ አውራጅ እናስታውስ፡፡ መፍትሔ ለመፈለግም ሁላችንም በአንድነት እንነሳ እንጂ ምንድነው ዝምታው? ምንም እንኳ “ዝም አይነቅዝም” ቢባልም፣ ለሁሉም ጊዜና ቦታ አለውና እንደ ሁኔታው እንጠቀምበት፡፡

ዛሬ ወንድም ከወንድሙ እህት ከእህቷ የጎሪጥ እንዲተያዩ ያደረገንን ተውሳካዊ መንፈስ የራቀውና የሰይጣን መፈንጫ የሆነብንን ጉዳይ ተቀምጠን በመወያየት መፍታት፣ ማስተካከልና መስመር ማስያዝ ለምን ይሆን የቸገረን? ነባሩ የሽምግልናው ወግና ታሪካችን ምነው ጠፋ? ሽማግሌዎች ከአገር ውስጥ ጠፍተው ነው? ወይስ በሠለጠነ መንገድ የግጭት አፈታት (Conflict Resolution) ብለው ፈረንጆች ከእኛ የቀዱትን ለእኛው መልሰው ሊያውሱን በቃጣቸው የኩረጃ መንገድ ተሠልፈን? ሁሌም የራሳችንን የናቅንና የሰውን የምንሻ ይመስል የእኛኑ ወግ ከሌሎች ለመዋስ ስንሯሯጥ አባት ሽማግሌዎች በዝምታ እያዩ ነው። ለምን?

ሁሉን አዋቂው አዲሱ ትውልድ እነ ፕሮፌሰር እነ ዶክተር መሆናቸው ነው። የሚገርመው እነ ዶክተር እነ ፕሮፌሰር ትናንትን ያላዩ፣ ባህልና ወጋቸውን የማያውቁ፣ የታሪክ ግንዛቤን ያልቋጠሩ ግን የተሰየሙባቸውን የዕለት ሁኔታዎች ይዘው የሚከንፉና ጊዜም የሚያጥራቸው፣ ለዕለት ጉዳያቸው የሚሯሯጡ በመሆናቸው ጊዜያቸውን ለዚያ እንዲጠቀሙ ፈቀድን፡፡ ነገር ግን የወግና የማዕረግ ጉዳያችንን ለአገር ሽማግሌዎች ብንተውና ሁሉንም ከመሠረቱ ቢያግዙንና ሰላምን ቢያመላክቱን የመከባበር ወጋችንን ቁምነገር ላይ ብናውል ይከፋ ይሆን?

ወገኖቼ መማር መልካም ሆኖ ሳለ መሠረቱን እየጣለ በመሄዱ ለአገር ለወገን ከመጥቀም ይልቅ፣ የሌሎች መልዕክተኛ እንዳንሆን እንጠንቀቅ።                                                                                             ከጥንት ከ17ኛው ክፍለ ዘመን ጀምራ በኢንዱስትሪና በቴክኖሎጂ የተራመደችው እንግሊዝ ያጠመደችብን ወጥመድ ውስጥ ገብተን በከንቱ እንኩራራለን፡፡ ራሳችንን ችለን ከመራመድ ይልቅ የእሷን ባህልና ቋንቋን ይዘን ስንውተረተር፣ ከቴክኖሎጂዋና ከኢንዱስትሪዋ ከመቅሰም ይልቅ በአለባበሷና በአነጋገሯ እንወጠራለን፡፡ እንግሊዝ ግን የማለያየት ጥበብ ስትረጭብን፣ የማከፋፈል ዘይቤዋን ስትሸርብብን እኛ ሞኞቹ እያለን የሌለን፣ አዋቂ መስለን የዋሆች፣ ከንቱ መልዕክት አስተላላፊዎችና ያለንን ንብረት ከመጠቀም ይልቅ ለእሷና ለፈጠረቻቸው አዲሶቹ ልጆቿ በማዘጋጀት፣ እሷና ልጆቿ በቀየሱልን መስመር የልመና ኮረጆ ይዘን ስንቀላውጥ ምኞቷን እያሟላን እዚህ ደረስን። ዋ የእኛ ነገር፡፡

እንግሊዝና አዲሶቹ ልጆቿ ባዘጋጁልን መንገድ ወንድም ከወንድሙ፣ እህት ከእህቷ በተቃራኒ መንገድ እየተጓዝን ነው፡፡ አልፈን ተርፈን በቀዬ እየተለያየን ለመበታተንና የእሷን ምኞት ለመሙላት እየተጋደልን ነው። ይህ ይሆን ዕውቀት? የጥንቶቹ ኢትዮጵያውያን አቡጊዳንና ፊደለ ሐዋሪያትን ብቻ ተምረው አገሬን አላስደፍርም ብለው ያቆዩልንን አገር እኛ የነቃንና የበቃን፣ የተማርን ምሁራን ተብዬዎች በቀዬ፣ በዘርና በሃይማኖት ተለያይተን በእነሱ ቅያስ ብቻ መድረሻቸውን ምንም ሳንጠራጠር ስናከናውንላቸው አይገርምም? ተው ወገኖቼ ወደ ልቦናችን እንመለስ፡፡

አሁን 101 ዓመታትን ያስቆጠረው የቀድሞ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሔንሪ ኪሲንጀር፣ ገና ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ደረጃ ከመድረሱ በፊት እ.ኤ.አ. በ1972 ያዘጋጀልን ዕቅድ ዛሬ ሠርቶለት በሕይወት እያለ ለማየት መብቃቱ አይገርምም? ያለውም የአፍሪካን ቀንድ መበጥበጥ መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በየቀዬው፣ በየባህሉና በየዘሩ ሲፋተግ አገሪቱ እንዳይሆን ትሆንና ያኔ ነው የእኛ ምኞት የሚሳካው ብሎ የተነበየው እነሆ ዛሬ በመድረስ ላይ ይመስላልና ጎበዝ ከእንቅልፋችን እንንቃ፡፡ ወንድም ከወንድሙ እህት ከእህቷ ከመተራረብ ተቆጥበን ወደ ሰላም እንመለስ፡፡ ፀብና ጥላቻ ለማናችንም አይጠቅመንምና። ልብ እንግዛ፣ ለኢንዱስትሪና ለቴክኖሎጂ እንሽቀዳደም። በብድርና በልመና የተሠሩትን ሕንፃዎች፣ መንገዶች፣ ድልድዮችን፣ አብያተ ክርስቲያናትንና መስጊዶችን ማጥፋት ለማን ይሆን የሚበጀው? እባካችሁ ወደ ልቦናችን እንመለስ።                                                                                                                                                

ዛሬ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ወደ ትምህርት ቤት ከመሄድ ይልቅ የመንደር አሟሟቂ ሆነዋል፡፡ ለምን? ሰላም ጠፍቶ ነዋ፡፡ በሰላም ወጥቶ መግባት ባለመቻሉ መንገዱ ስለተዘጋባቸው ነው። ልጆቹን በጉጉት ያሳደገ ቤተሰብ ነገ ልጄ ምን ሊሆን ነው/ልትሆን ነው እያለ የመንፈስ ጭንቀት ይይዘዋል፡፡ በኑሮ ውድነት ያለው መከራና ሥቃይ ይታወቃል፡፡ ወላጅ ልጄ በሚቀጥለው ቀን ምን ይሆን የሚገጥመው የሚል ጭንቀት ውስጥ ገብቶ በሐሳብ ባህር ውስጥ ሲዋኝ ውሎ ማደሩ የጊዜው እውነት ሆኗል። ልጆቹም የሚጠብቃቸው ሁኔታ ከአገር ሸክምነት አልፎ መከራ የመሆን ጎዳናው እየሰፋ ነው። ሌብነትን፣ ነፍሰ ገዳይነትን፣ ቀማኛና ዘራፊነትን ፈልገውት ሳይሆን ተገድደው መሆኑንም መገንዘብ ያለብን ጉዳይ ነውና ይታሰብበት፡፡

መሪዎቻችንም ወደ ሽምግልናው ፊታችሁን አዙሩ፡፡ ሁሌም ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ለአገር ለወገን ሲባል መሸነፍንም ማስተናገድ እንዳለም እወቁ፡፡ ሁሌም አሸናፊ መሆን አይቻልምና። የወገንን ምክር መስማት ያስመሠግናል እንጂ አያስወቅስም፡፡ “መካር የሌለው ንጉሥ ያለ አንድ ዓመት አይነግሥ” የሚለውንም የአበውን ብሂልም አስተውሉ። የፖለቲካ ሥልጣን ለራስ መበልፀጊያ ሳይሆን አገርን ለማሻሻል፣ ወገንን ለማስተማርና ለማንቃት መሆን አለበት እንጂ፣ እንዲያው የሰነፎችና የወሬኞች መሰባሰቢያ መሆን የለበትም፡፡ ይህንንም ባየሁትና ባጠናሁት የባዕድ አገር ምሳሌ ላስረዳ፡፡

ለምሳሌ በአሜሪካና በእንግሊዝ እንዲያው ዘው ተብሎ ወደ ፖለቲካ አይገባም፡፡ ለምን? ዕውቀትን አዳብሮ፣ ለወገን በቂ አስተዋጽኦ ለማበርከት አያስችልምና ነው። መጀመሪያ ራሱን ችሎ፣ ቤተሰቡን አስተዳድሮ ውጤት ያመጣና የወገኑን ችግርና መከራ ምን እንደሆነ በሚገባ ያወቀ፣ ከነበሩት በተሻለ አገሩንና ወገኑን በተለየ መንገድ የሚረዳ፣ አገሩን በበለጠ በዓለም ፊት ቅድሚያ የማሰጠት ብልኃት እንዳለው ተናግሮ ምረጡኝ በማለት ሕዝብ ፊት ይቀርባል፡፡ ከዚያ በፊት ግን ያሳለፋቸውን ውጣ ውረዶች አመላክቶ በልበ ሙሉነት በመነሳት፣ ከሚመለከታቸው የፖለቲካ ባልደረቦቹ ጋርም ይመካከራል፡፡ እነሱም በአዎንታ የአንተ ዕውቀት ለዚህ ቦታ ተገቢነት አለው ግባበት ሲሉት ዕድሉን ለመሞከር ይወዳደርና ይመረጣል፡፡ ካልተመረጠም የተሻለው ሰው በቦታው ይገባበትና ለመላው አገሬው የተሻለ ውጤት ሊያመጣ ይችላል፡፡ ካልቻለም ያ የመጀመሪያው ሰው ለሁለተኛ ጊዜ ተወዳድሮ ካሸነፈ ያንን የተመኘውን አስተዋጽኦ ያበረክታል።

በእኛ አገር ግን ምኑንም ሳያይና ሳያበረክት ሁኔታውና ጊዜ ስላመቸው ብቻ ሥልጣን ይዞ የራሱን ኑሮ የማስተካከል ዓይነት ሲሠራ ነው እስከ ዛሬ የምናየው። ይህ አባባል ዋና መሪዎችን አይመለከትም፡፡ ማለትም መሪዎች የሚመረጡት መጀመሪያ በፓርቲያቸው ተጠቁመው ያንን ካለፉ በኋላ የመላውን ሕዝብ ድምፅ በማግኘት ነው፡፡ በገንዘብ ኃይል፣ በቲፎዞ ብዛትና በማጭበርበር መሰል አሠራሮች በተቀላቀሉበት ሁኔታ ይመረጡና ችሎታቸውና የአስተዳደር ዘይቤአቸው ጉዱ የሚወጣው በኋላ ነው። ለዚህም የዶናልድ ትራምፕን የአስተዳደር ውጤት ማየት በቂ ነው፡፡ የአሜሪካ ጥሩ ጎኑ የበላዩ በአፉ ይለፍልፍ እንጂ በራሱ የሚወስነው ነገር ስለሌለ እምብዛም አገሩን አይጎዳም።

አንደኛ አማካሪዎች የተከበሩና ከመሪው በላይ ዕውቀት ያላቸው ስለሆኑ ምክራቸው ተሰሚነት አለው፡፡ ሁለተኛ ውሳኔ ከመተላለፉ በፊት የኮንግረሱን አዎንታ ማግኘት፣ የሴኔቱን ፍላጎት ማካተትና እጅግም የከፋ ሆኖ ከተገኘ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን (ሱፕሪም ኮርት) ስሜት አዳምጦ ወደ ውሳኔ ይገባል እንጂ እንደ አፍሪካ በአንድ ሰው ፈቃድ ሁሉም ነገር አይከናወንም። እኛ ከእነሱ የወረስነው አለባበስን፣ አመጋገብንና በቋንቋቸው መመፃደቅን በመሆኑ ለአገር ልማት አልተጠቀምንበትም። 

ከጎዳና ላይ ልመና ተወግዶና ሠርቶ መኖር ያለበት ሥራ ማግኘት ሳይችል፣ ወጣቷ ወገናችን ሕፃን አዝላ ዳቦ እየለመነች፣ ትምህርት ቤት ሄዶ መማር የሚገባው ሕፃን አባባ ዳቦ ግዙልኝ እያለ ለዳቦ ልመና ሲሽቀዳደም፣ ሌላም ሌላም ብዙ ችግሮች አሉብን። ይህንን ሁሉ ጉድ ተሸክመንና ይህም አልበቃ ብሎ በጦርነት ወገናችን ሲታመስ፣ ለዚህ እንኳ ተመካክረን መፍቴሔ ማምጣት አቅቶናል፡፡ የአፍሪካ የውኃ ማማ በተባለችው አገራችን በዋና ከተማችን ውስጥ ጫብሱ ተንሰራፍቶ (ጫብሱ ማለት ውኃ በሌለበት አካባቢ በእየ ሦስቱ ቀናት ውኃ ለሚጠጡ ከብቶች የተሰየመ የኦሮምኛ የሦስት ቀናት ድርቅ ማለት ነው)፣ ይህንን እንኳ አስተካክለን ወገናችንን ሳንረዳ “ነፃነት” እያልን ስንራኮት ማየቱ አያሳፍረን ይሆን? ይህ ካላሳፈረንና ካላሳዘነን ምን ያሳዝነን ይሆን? ነፃነትስ ቢሆን ማን ከማን ነው ነፃ የሚወጣው? እርግጥ ነው አሁን ያለውን አስተዳደር ስለማልፈልግ እኔ የተሻለ ማስተዳደር እችላለሁ ብሎ መወዳደር፣ ያ ካልተቻለ የሚቻልበትን መነገድ መሻት እንጂ የባዕዳን መልዕክተኛ በመሆን የወገንን ደም በከንቱ ማፍሰስ ለማንም የማይበጅ ተውሳካዊ አስተሳሰብ ነውና ወደ ልቦናችን እንመለስ፡፡

ለዘመናት ተፋቅሮና ተዋዶ የነበረን ወገን ለማለያየት እሽቅድምድሙ ለምን ይሆን? አሸምቀው ሊያለያዩን ከ18ኛው ክፍለ ዘመን ጀምረው ሲቋምጡ ለነበሩት እንግሊዝና ፈረንሣይ መንገድ እየከፈትን ይሆን? ያኔ ትሪጎኖሜትሪና አልጀብራ ያላጣኑ አባቶቻችን ከዚህ ጥፋ ብለው አሸምቆ የገባውን ናፔርን (አፄ ቴዎድሮስን ለመዋጋት የመጣው የእንግሊዝ ጦር መሪ) ለፈረሱ ውኃና ሳር ነፍገው፣ ለወታደሩ ስንቅ ነስተው ማባረራቸውን ታሪክ ይነግረናል፡፡ ዛሬ ግን ሠለጠንን ባዮች ተማርን የምንል የእዚህ ትውልድ አባላት ለሥልጣን ስንል ወገንን ከወገን ስናፋጅ፣ ከኢትዮጵያ በኋላ የተፈጠሩት እንግሊዝን ጨምሮ ሌሎች ሊያጠፉን ሲሽቀዳደሙ ምን እያደረግን ይሆን? ወገኖቼ “ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ” እንዳይሆን እንንቃ፡፡ የዕርቅ መንገድ ፈልገን ሰላምን እናምጣ። የዛሬ ድሎት ለነገ ልጆቻችን ሐዘን እንዳይሆን፣ ሁሌም አገር የለሽ ስደተኛ ሆነው እንዳይቀሩ፣ የዘመኑም ወጣት ለስደት ተዳርጎ የባህር ዓሳ እራት ከመሆን እንዲተርፍ ይታሰብበት።

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ግለ ሕይወታቸውንና የጉዞ ታሪካቸውን የከተቡበት ‹‹ከባቹማ እስከ ቨርጂኒያ›› በሚል ርዕስ ለአንባቢያን ያቀረቡት መጽሐፍ ደራሲ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው assefadefris@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles