Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅየኅዳር በሽታ

የኅዳር በሽታ

ቀን:

በ1911 ዓ.ም. የበሽታ መቅሰፍት በኢትዮጵያ ወርዶ ብዙ ሰው አለቀ፡፡ በሽታው አዲስ አበባ ደርሶ በጣም የታወቀው በኅዳር ወር ስለሆነ በሕዝብ ቃል ‹‹የኅዳር በሽታ›› የሚል ስም ወጣለት፡፡ ፈረንጆች ግን የበሽታውን ስም ግሪፕ ብለውታል፡፡ በአገራችንም አንዳንድ ሰዎች ‹‹ቸነፈር›› ብለውት ነበር። በሽታው ቀደም ብሎ አውሮፓ ላይ በዓለም ጦርነት ምክንያት ስለተነሳና ብዙ ሰው ስለፈጀ ይኸው ወሬ ከመስከረም ጀምሮ ተሰምቶ ነበር። ወደ አገራችንም በነፋስ ተዛምቶ መጣና ከጥቅምት ጀምሮ ጥቂት በጥቂት በአንዳንድ ሰው ቤት መግባትና መጣል ጀመረ፡፡ በኅዳር ወር ግን አብዛኛውን ሰው ስለነደፈው ከተማው ተጨነቀ፡፡ በሽታው እንደ ሣልና እንደ ጉንፋን አድርጎ ይጀምርና በበሽተኛው ላይ ትኩሳት ያወርድበታል፡፡ ከዚያም ሌላ ያስለቅሳል፣ ነስር ያስነስራል፣ ተቅማጥና ውጋት ያስከትላል፣ አንዳንዱንም አዕምሮውን ያሳጣዋል፡፡ እንዲህ እያደረገ በሦስት በአራት ቀን ይገድለዋል፡፡ ከአራት ቀን ያለፈ በሽተኛ ግን ከሞት ማፋረሱ ነው፡፡ ሆኖም ከግርሻ መጠንቀቅ ነበረበት፡፡ አንዳንድ ሥፍራ ቤተሰቡ በሙሉ ይታመም ስለነበረ፣ አስታማሚ በማጣት በረሃብና በውኃ ጥም ብዙ ሰው ተጎዳ፡፡ ስለዚህ በአዲስ አበባ በየቀኑ ሁለት ሦስት መቶ ከዚህም በላይ ይሞት ጀመር። በአንድ መቃብርም ሁለቱን ሦስቱን ሬሳ እስከመቅበር ተደረሰ፡፡ አንዳንዶም ሰዎች ሬሳ ተሸካሚ በመታጣት በየግቢያቸው ውስጥ ቀበሩዋቸው፡፡ አፍላው በሽታ ከኅዳር 7 እስከ 20 ለአሥራ አራት ቀን ያህል ነበር፡፡ በተለይም ኅዳር 12 ቀን የኅዳር ሚካኤል ዕለት ብዙ ሰው ሞተ፡፡ ከመኳንንት ከንቲባ ወሰኔ ዛማኔል በዚሁ ቀን ሞቶ አዲስ አበባ ሥላሴ ተቀበረ፡፡ ከካህናትም አዲስ አስተማሪው አለቃ ተገኝ ሞቶ አራዳ ጊዮርጊስ ተቀበረ፡፡ ይህ ሰው የመምህር ወልደ ጊዮርጊስ ደቀመዝሙር የነበረው ነው፡፡ በዚያ ሰሞን መቃብር የሚቆፍርና ሬሳ ተሸክሞ የሚወስድ ሰው ለማግኘት ችግር ሆነ፡፡ በቤተሰቡ ውስጥ ከበሽታ ያመለጡ ሲገኙ ሁለት ሰዎች ሬሳ ተሸክመው እየወሰዱ ይቀብራሉ፡፡ ባል የሚስቱን አባት የልጁን ሬሳ እየተሸከመ ወስዶ ቀበረ፡፡ ደግሞ አንዱ መቃብር ይቆፍርና ሬሳ ለማምጣት ወደ ቤቱ ሄዶ ሬሳ ይዞ ሲመለስ ሌላው ቀብሮበት ያገኘዋል፡፡ ቤተሰቡ በሙሉ በታመመበት ሥፍራ ብዙዎች በየቤታቸው እየሞቱ አውሬ በላቸው፡፡ ለጉዳይ ወደ አዲስ አበባ የመጣ እንግዳም እየታመመ መግቢያ አጥቶ በየመንገዱ እየወደቀ አውሬ በላው፡፡ የኔታ ወልደ ጊዮርጊስ በሰፈራቸው በጉለሌ ክፍል በየቤቱ እየዞሩ ለበሽተኞችና ለገመምተኞች እንጀራና ውኃ ሲያድሉ ሰነበቱ፡፡ በእግዚአብሔር ቸርነት ከበሽታው አምልጠን ነበርና እኔንና ጎጃሜ ኃይለ ማርያምን ውኃ በገንቦ እያሸከሙ እሳቸው ቁራሽ እንጀራ ይዘው ይሄዱና ከደጃፍ ሲደርሱ እኛን ከውጪ አስቀርተው ውኃውንና ቁራሹን ይዘው ይገቡ ነበር፡፡ እኛን ማስቀረታቸው በሽታው እንዳይዘን ስላሰቡልን ነው፡፡ በሌላም ሥፍራ የዚህ ዓይነት ትሩፋት የሠሩ መንፈሳውያን ሰዎች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ መሴ ሴዴርኩዊስት የተባሉ ሽማግሌ (የስዊድን ሚሲዮን አስተማሪ) በየሰፈሩ እየዞሩ ለበሽተኞች እህልና ውኃ መድኃኒትም በመስጠት ላይ ሳሉ ከጥቂት ቀን በኋላ በዚሁ በሽታ ታመሙና ሞተው ጉለሌ ተቀብረዋል፡፡ በዚያ ወራት የተቆፈሩት መቃብሮች ጥልቀት ስላልነበራቸው አንዳንዱን መቃብር አውሬ ይተናኮለው ጀመር። ከመቃብሮች የሚወጣው ‹‹ሚክሮብ›› እንደገና በሽታ ያስነሳል ተብሎ ስለተሠጋ ማዘጋጃ ቤት ኖራ እያስበጠበጠ በየመቃብሩ ላይ አስረጨበት፡፡ በዚያም ሳቢያ በየቤተክርስቲያኑ ሁሉ መቃብሩን ቢያስቆጥረው እስከ ስምንት ሺሕ ደረሰ፡፡ ይህም በየመንደሩ የተቀበረውና በየስርቻው የወደቀው ሳይጨመር ነው፡፡ አዲስ አበባ ላይ የሞተው የሕዝብ ቁጥር ዘጠኝ ሺሕ ይሆናል ተብሎ ተገመተ፡፡ የኅዳር በሽታ (ግሪፕ) በአዲስ አበባ ብቻ አልተወሰነም ወደ ባላገር ተላልፎ ብዙ ሰው ፈጅቷል፡፡ ሆኖም በባላገር የአዲስ አበባን ያህል አልጠነከረም፡፡ በዚህ በሽታ በመላው ኢትዮጵያ የሞተው የሕዝብ ቁጥር እስከ አርባ ሺሕ ይገመታል፡፡

(መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ፣ የሃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ የዘመን ታሪክ ትዝታዬ ካየሁትና ከሰማሁት ከ1896-1922)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...