Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅየአንድ አፈር አፈሮች

የአንድ አፈር አፈሮች

ቀን:

ፍቅራችንን ድንበር ወሰን ላይገድበው፣

ሁለት ክልል ላይመጥነው፣

መገዳደል ፍትሕ ላይሆነው፣

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በሽንፈትህ እሰይ ላልል፣

በሽንፈቴ እፎይ ላትል፣

ከቂም በቀር ፍቅር ላይበቅል፣

ልጅህ በእጄ ለምን ይሙት?

ልጄስ በእጅህ ለምን ትሙት?

እኔና አንተኮ የአንድ እናት ልጆች፣

ወንድማማቾች፣

የአንድ አፈር አፈሮች፣

ርስት አፈሩማ ይቅርም ከወደዚ ይሂድም ወደዚያ፣

ያውነው የኢትዮጵያ አንድ አፈር መጠሪያ፣

ወዲያ ካለው የቀድሞዋ፣

ወዲህ ካለው የስካሁንዋ፣

ግዳይ ጥዬ በልጅህ ደም በጀግንነት ላልጠራ፣

ግዳይ ጥለህ በልጄ ደም ላትፎክር ላታቅራራ፣

ወንድም ገድለው ላይፎክሩ፣

ጀብዱ ሠርተው ላይኩራሩ፣

የሐዘን ሙሾ ልዘምሩ፣

እንደ ማህተብ የእምነት ክር ፍቅር ድሩ ላይበጠስ፣

በሐዘናችን ላትዘፍኑ በሞታቹ ላንደንስ፣

ስውር አይሁን ነጭ ሴራው ደስ አይበለው የጠላት ነብስ፣

ልጅህ አይሙት በልጄ ጣት

ልጄም አይሙት በልጅህ ቀስት፣

እኔና አንተኮ ከዘመናት በፊት፣

በታሪክ በሃይማኖት፣

በባህል በትውፊት፣

በደስታ በችግር፣

ስም የሌሽ ስመጥር፣

በጋሻና በጦር፣

ጀብደኛ ባላገር፣

የአንድ አያቶች ዘር፣

የሁለት አፈር ሰፈር፣

ስምየለሽ በጥጋብ፣

ስመጥር በረሀብ፣

እያሉ ሲተቹህ እያሉ ሲተቹን፣

በሙጫ ስድብ አጣብቀውን፣

ሲተቹህ መተቸት ሲተቹን መተቸት፣

እንዳለ ስናውቀው እንዳለ ስታውቁት፣

በአንድ እናት ተወልደን፣

በሁለት አባት አድገን፣

አንድ ውኃ ተራጭተን፣

አንድ አፈር አቡክተን፣

ቃታ ስንሳሳብ እሺ ላይለው ልብህ ደስ ላይለው ልቤን፣

እኮ እንዴት እኔና አንተ ዛሬ እንዲህ እንጫከን?

እኔና አንተኮ የአንድ እናት ልጆች፣

ወንድምና እህቶች፣

የአንድ አፈር አፈሮች፣

እናም ወንድም ስማኝ ልስማህ

ደስ አይበለው ነገር ሰሪ አንተን ከእኔ ፀብ ሲያቃባ፣

እንዘምር ባንድ እንዝለል ወሰን አይኑር የደም ካባ፣

በሞትህ ደስ ላይለኝ ውስጥ ልቤ እዥ ሊያነባ፣

የእናቱን ልጅ ልጄ ገድሎ ላያሰማ ጉሮወሸባ፣

ፍቅር እንጂ ግድባችን ወሰን አይኑር የደም ካባ፣

ይልቅስ ልንገርህ፣

ኩራቴ ኩራትህ፣

ታሪኬ ታሪክህ፣

የሚያመፃድቀኝ የሚያመፃድቅህ፣

የኔም የአባቴ ነው ያንተም የአባትህ፣

ከቢዘን ባስቀድስ፣

ከግሸን ብትሰልስ፣

ባክሱም ብትኮራ፣

ብሸልል ባስመራ፣

ያንተ አባት አባቴ፣

አባቴ አባትህ፣

የሚያመፃድቀኝ የሚያመፃድቅህ፣

ታሪኬ ታሪክህ፣

መሆኑን ስናውቀው መሆኑን ስታውቁት፣

በደምና ባጥንት፣

በሥጋ በጅማት፣

በታሪክ በትውፊት፣

መንታ ናቸው ሲሉን፣

እኮ እንዴት እኔና አንተ ዛሬ እንዲህ እንጫከን?

በብቀላ ፀፀት በቀር፣

ወንድም ጥሎ ላይፎክር፣

ጀግና ተብሎ ሜዳይ ላይኖር፣

በእናቴ ልጅ በመጨከን እሺ ላይለኝ የልቤ በር፣

ወንድ ልጄን ግዳይ ጥለህ ላይፈታ የደምህ ስር፣

ካንድ ደብር አድገን፣

በአንድ አስቀድሰን፣

አንድ ዳዊት ደግመን፣

ካንድ መስጊድ ኖረን፣

በአንድ ሰላት አድገን፣

አንድ ቁርአን ቀርተን፣

እኮ እንዴት እኔና አንተ ዛሬ እንዲህ እንጫከን?

ለጉዳትህ ተሰውቼ፣

ላንተ ክብር ብዙ ሞቼ፣

ስላንተ ነፃነት ካገርህ ደሜ አለ፣

በናቅፋ ተራሮች እቅፍ የታዘለ፣

መጎዳቴን እምቢ ብለህ፣

ስለክብሬ ተሰውተህ፣

የሰጠህኝ ክቡር ደምህ፣

ያንተም አጽም አድዋ አለ፣

ለኢትዮጵያ ነፃነት ስለኔ የዋለ፣

መንታ ናቸው ሲሉን፣

ፍቅር ናቸው ሲሉን፣

እያወቁት ልቦናችን፣

ሁለት ክልል ላይመጥነን፣

ድንበር ወሰን ላይገድበን፣

መገዳደል ፍትሕ ላይሆነን፣

በሽንፈትህ ስንዘምር በለው ያሉህ ሊታዘቡን፣

ነጭ ሴራ ወጣው ሊሉን፣

ሥጋ ክንድህ ሲደማብህ፣

ልቦናችን ሊያዝንብን፣

በዓለም ዜና ድላችንን ደምጥማት ነው ብለው ሊሉን፣

ልጅህ በጄ ለምን ይሙት?

ልጄም በእጅህ ለምን ትሙት?

ስማኝ ወገን ደስ አይበለው ነገር ሠሪ አንተን ከእኔ ፀብ ሲያቃባ፣

ስውር አይሁን ነጭ ሴራው የሸረበው የሞት ደባ፣

እንዘምር ባንድ እንዝለል ወሰን አይኑር የደም ካባ፣

እናም በሞቱት ሞት፣

እኔና አንተ አንሙት፣

እኔና አንተማ የአንድ እናት ልጆች፣

የአንድ አፈር አፈሮች፡፡

  • ገጣሚ ኤፍሬም ስዩም
spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...