Friday, March 1, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኅብረት ባንክ የተጣራ 2.3 ቢሊዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኅብረት ባንክ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ከግብር በፊት ያገኘውን ትርፍ በ62.84 በመቶ በማሳደግ 2.3 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡

ባንኩ ባለፈው ሐሙስ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ሳምራዊት ጌታመሳይ (ኢንጂነር)፣ ባንኩ ከግብር በፊትና ከመጠባበቂያ ተቀናሽ በኋላ 3.06 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን፣ ያስመዘገበ ይህም ከቀዳሚው ዓመት የ1.18 ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

የባንኩ ዓመታዊ ሪፖርት ደግሞ በሒሳብ ዓመቱ ከግብር በኋላ 2.3 ቢሊዮን ብር ትርፍ መገኘቱንና ይህም በ2014 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በኋላ ተገኝቶ ከነበረው ትርፍ ጋር ሲመሳከር በ1.2 ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ያስረዳል፡፡

ኅብረት ባንክ በሒሳብ ዓመቱ ያገኘውን ትርፍ ተመርኩዞ ‹‹ከግብርና ከሌሎች ተቀናሾች በኋላ የባንኩ ትርፍና ኪሳራ ተመልክቶ 1.29 ቢሊዮን ብር ለባለአክሲዮኖች እንዲከፋፈል ወስኗል፡፡ ይህ የትርፍ ክፍፍል መጠን በቀዳሚው ዓመት እንዲከፋፈል ከተደረገው 877.21 ሚሊዮን ብር አንጻር 415 ሚሊዮን ብር ጭማሪ ያለው መሆኑ ታውቋል፡፡

ባንኩ ከወለድ ነፃ አገልግሎቱ ደግሞ የተጣራ 113.1 ሚሊዮን ብር ማትረፉን ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡ በ2014 የሒሳብ ዓመት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ከታክስ በፊት አግኝቶት የነበረው ትርፍ 54.6 ሚሊዮን ብር ከመሆኑ አንፃር በ2015 ያስመገበው ትርፍ ከ150 በመቶ በላይ ብልጫ እንደነበረው ያመላክታል፡፡ ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ያገኘው አጠቃላይ የትርፍ መጠን አንድ አክሲዮን ያስገኘው ትርፍ 50.72 በመቶ እንዲሆን አስችሏል፡፡ በቀዳሚው ዓመት አንድ አክሲዮን ያስገኘው ትርፍ 26.47 በመቶ ስለነበር የሒሳብ ዓመቱ ትርፍ ለባንኩ ባለአክሲዮኖች የተሻለ የትርፍ ድርሻ አስገኝቷል፡፡

የባንኩ ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ በሒሳብ ዓመቱ ጠቅላላ የባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከቀዳሚው ዓመት በ10.73 ቢሊዮን ብር ወይም የ19.95 በመቶ ዕድገት በማሳየት 64.54 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በሌላ በኩል ከወለድ ነፃ አገልግሎት ዘርፍ ባንኩ የሰበሰበው ተቀማጭ ገንዘብ መጠን 3.16 ቢሊዮን ብር ሆኖ ሲመዘገብ ይህም ከቀዳሚው ዓመት የ702.64 ሚሊዮን ብር ወይም 28.64 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ከሪፖርቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ለወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚዎች የተሰጠውን ብድር ጨምሮ በተለያየ ዘርፍ ተሰማርተው ለሚገኙ የባንኩ ደንበኞች የተሰጠው አጠቃላይ ብድር በ14.24 ቢሊዮን ብር ወይም የ31 በመቶ ዕድገት በማሳየት በዓመቱ መጨረሻ ላይ አጠቃላይ የባንኩ የብድር ክምችት 60.18 ቢሊዮን ብር መድረሱም በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡ ባንኩ ከሰጠው ብድር ውስጥ 20.18 በመቶውን ለገቢ ንግድ ያቀረበ ሲሆን፣ ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍና ለአገር ውስጥ ንግድ 17.85 በመቶ፣ ለአገልግሎት ዘርፍ ደግሞ 14.06 በመቶውን እንዳቀረበ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከውጭ ምንዛሪ ግኝት አንጻር ኅብረት ባንክ ከዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት ዘርፍ ያገኘው የ247.80 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ይህ የውጭ ምንዛሪ ግኝት በ2014 የሒሳብ ዓመት ከተገኘው 217.82 ሚሊዮን ዶላር ጋር ሲነፃፀር የ29.38 ሚሊዮን ወይም የ13.45 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

ከተለያዩ ገቢዎች በዓመት ውስጥ 10.32 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ማግኘቱን የገለጸው ኅብረት ባንክ፣ ይህም ገቢ በ2014 የሒሳብ ዓመት ከተገኘው ጋር ሲነፃፀር የ2.22 ቢሊዮን ብር ወይም የ27.45 ዕድገት አሳይቷል፡፡ በዓመቱ ከተመዘገበው ገቢ ውስጥ ከብድር ወለድ የተገኘው ገቢ ትልቁን ድርሻ ይዟል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች