Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትዕውን ይህ ‹የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን› ነው?

ዕውን ይህ ‹የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን› ነው?

ቀን:

በገነት ዓለሙ

በወዲያኛው ሳምንት ዓርብ ኅዳር 7 ቀን 2016 ዓ.ም. ምሽት (ሁለት ሰዓት ላይ) በተላለፈው ዜና ውስጥ አንድ የ‹‹እስራኤል ጋዛ ጦርነት››ን የሚመለከት/የሚጠቅስ ወሬ ወይም ‹ዘገባ› ሰማሁ፡፡ ጦርነቱ መስከረም 26 ቀን (ኦክቶበር ሰባት) 2016 ዓ.ም. ከተጀመረ በኋላ፣ በተለይ በዚህ ጉዳይ ላይ ይህንን ጣቢያ ቻናል ወይም ኢቲቪን የምከታተለው (የማልስተው/ቢያመልጠኝ የማልፈልገው) የዜና፣ የመረጃ ምንጬ አድርጌ ሳይሆን በዚህ በተወሳሰበው፣ ሲበዛና ክፉና በሚያሳስበው ‹‹የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ›› አቋም ውስጥ የእኛ ቤተሰብ፣ ቤተ ዘመድ ‹ጉድ› ምን እንደሚመስል፣ ምን መስሎ እንደሚወከል፣ ወይም አጋጣሚውን አግኝተው ባለቤት ያልተበጀለት ክፍት ቦታ፣ ተጥሎ የተገኘ አደራ፣ ወድቆ አንስተው ተግባሩን የሚከውኑ ሰዎች ምን ብለው እንደሚወክሉን፣ እንዴት አድርገው እንደሚያቀርቡን ለመሰለል፣ ለመታዘብም ነው፡፡ በዝርዝር መብራራት ያለበት ጉዳይ ነውና ሁሉንም ባይሆን አንዳንድ መንደርደሪያዎች ላብራራ፡፡

ሲጀመር መርሁ፣ ሕጉ፣ የጋዜጠኛነት የጥበብ መጀመሪያ የኢቲቪ ዜና፣ የአልጄዚራ ሪፖርት፣ እከሌ ዘገበ የሚባል ነገር አያውቅም፡፡ ኢቲቪ/ኢቢሲዎች ‹‹ዘገባው የይድነቃቸው ሰማሁ ነው›› ሲሉ (ለምሳሌ) የምንታገሳቸው፣ እነሱንም ይህንን ለመሰለ ‹‹ትርፍ›› ነገር የዳረጋቸው፣ ሕግ ምንጭና ኃላፊነት ስጡ፣ ተወጡ፣ መተማመኛም አምጡ ስለሚል ነው፡፡ እንጂማ የአንድ የተዋጣለት፣ ጥሩ፣ ማለፊያ ዘገባ፣ ዜና፣ ሪፖርተር መለኪያ የምንሰማው፣ የሚቀርብልን ዜና ውስጥ፣ ይህ ሪፖርት፣ ይህ ዘጋቢ፣ ይህ ጋዜጠኛ፣ ሪፖርተር፣ ዘጋቢ፣ ጋዜጠኛ መሆኑን ትቶ ዜጋ ሲሆን፣ ለምሳሌ ድምፅ መስጫ ሳጥን ክፍል ውስጥ ገብቶ ምርጫውን ሲጽፍ፣ የፖለቲካ ዝንባሌውን ይፋ ሲያደርግ፣ ይፋ የሚያደርገውን ዜናው ውስጥ መስማት፣ ማወቅ ወይም መጠርጠር የለብኝም፡፡ እናም ዜና፣ ዜና ነው፣ አስተያየት ሌላ ነው ስንል፣ ዜና መሥራት ለእውነት መታመንን፣ የተቋቋመ አሠራር መከተልን ይጠይቃል ብለን ስንናገር፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ጋዜጠኛነት ዕውቀት! ዕውቀት! ዕውቀት! ይጠይቃል ብለን ስንለፈልፍ፣ ስንለፋ አንዱን ጋዜጠኛነት/ወይም ለምሳሌ ኢቲቪን ከዊ ኦን፣ ወይም ቢቢሲን ከአልጄዚራ ወይም እዚህ እኛ አገር፣ አንድ ሠፈርና አንድ ግቢ ውስጥም ኢቲቪን ከዋልታ፣ ከፋና የሚለያቸው ሙሽት፣ ማጠንት፣ ወይም ማዕዘን (አንግል) የለም ማለት አይደለም፡፡ አንድና ያው ዓይነት ካሜራዎች ተመቻችተው የተቀመጡበት ሥፍራ የሚያዩትን ሳይሆን፣ የሚታያቸውን ነገር ይወስናል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ለዚያም ሲባል በጥንቃቄ ደረጃ ‹‹All sides of the story›› ይባላል፡፡ በተራ ሰው ደረጃም ምስክርነት ሲሰጥ ‹‹All the truth›› ሁሉንም እውነት ለመናገር ቃል ያስገቧል፡፡ የእኛም አገር ሚዲያ ግን አናዳጅ፣ ይልቁንም ዕውን ይህ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ነው እስኪያሰኝ ድረስ ዕርጉም የሚያደርጋቸው፣ ከሚያዩበት/ከሚመለከቱበት ማዕዘን (አንግል ይልቅ አንድም ዕውቀታችን አንድም መቀመጫችን፣ አቋማችን) እየተረባረቡ የሚረጩት ችግር ነው፡፡

የፕሬስ ነፃነት ወሳኝ ነው፡፡ ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት አንድ ሌላ መብትና ነፃነት ብቻ አይደለም፡፡ ሰላሳኛው እ.ኤ.አ. የ2023 የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ሲከበር እንደተባለው፣ ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት የሌሎች ሰብዓዊ መብቶች ሁሉ ፊታውራሪ ነው፡፡ ይህን የመሰለ መብትና ነፃነት እንደ ማንኛውም መብትና ነፃነት፣ ነፃነቱን ብቻ ሳይሆን ኃላፊነትም ያስረክባል፣ ያሸክማል፡፡ ይህንን ኃላፊነትና አደራ ለመሸከምና ለመወጣት ጭምር ነፃነቱ ኖረም አልኖረ/ተረጋገጠ አልተረጋገጠ ዕውቀት ለጋዜጠኛ ወሳኝ ነገር ነው፡፡ የጋዜጠኞች የዕውቀት አድማስ አቅማቸውን ከሚወስኑት አንዱና ዋናው ጉዳይ ነው፡፡ ጋዜጠኛ በአጠቃላይ ጥልቅ የታሪክ፣ የባህል፣ የአገር ጥሪቶችና ቅርሶች የዕውቀት ባለቤት እንዲሆን ይጠበቃል፡፡ የሚሠራውን በጥራት ለማዘጋጀት/በሚሠራው ሥራ ላይ በጥረትና በብቃት ለመዘጋጀት የዕውቀት ደርዝና የአስተሳሰብ ችሎታ ያስፈልገዋል፡፡ ጋዜጠኛ ሁሉንም ማወቅ አለበት፣ ወይም ሁሉንም ነገር የሚያውቅ ጋዜጠኛ አይሆንም አላልኩም፡፡ ጋዜጠኛ ማወቅ የሚፈልገውን ነገር ለማወቅ፣ የትና ምን እንደሚፈልግ ማወቅ አለበት ነው የሚባለው፡፡ ጋዜጠኛነት ከዕውቀት ጋርም የሚኖርበትን የፖለቲካ ምኅዳር የሚያውቅና የሚረዳ መሆን አለበት፡፡ ይፋና ፖለቲካዊ መድረኩ ዝርዝር ሐሳቦችን ልዩ ልዩ ተወዳዳሪና ተገዳዳሪ ዝንባሌዎችን ከማፍራትና ከመፈልፈል ጋር መተዋወቅ አለበት፡፡ በፖለቲካም፣ ከፖለቲካ መለስ ባሉ ጉዳዮች ጭምር ከአንዱ ወይም ከሌላው የተለየ ሐሳብን/ዝንባሌን ለመስማት ቻይ መሆንና መልመድ አለበት፡፡ ይህንን ከመሰለ ጥበብ ሲጀመር ጋዜጠኛነት ‹‹ማስተማር! ማሳወቅ! ማዝናናት (ጭምር)›› ቢል የሚያማው የለም፡፡ 

እና ‹‹የቤተ ዘመዱ ይታያል ጉዱ›› የሚል፣ የወግ ሳይሆን ሰቀቀን ያለበት፣ ፍርኃት፣ ሽብር የለቀቀበት ‹‹ሙድ›› ውስጥ እያለሁ (ሙድ ስል በእኛ አገር የአራዳ ቋንቋ ትርጉሙ ሳይሆን፣ እንዲያ ባለ የአዕምሮ ሁኔታ ውስጥ ሳለሁ ማለቴ ነው) ወደ ሰማሁት ዜና ልመለስ፡፡ ኢቲቪ በዕለቱ እነግራችኋለሁ ያለው ዜና ዋና ጭብጥና ሐሳብ በአጭሩና በተቻለ መጠን በተራ ቋንቋ ደቡብ አፍሪካ እስራኤልን በዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ከሰሰች ማለት ነው የኢቲቪ ዜና (እንዳለ የምጠቅሰው የኦንላይን ዜናውን ነው)፡፡ 

‹‹ደቡብ አፍሪካ ከጋዛ ጥቃት ጋር በተያያዘ እስራኤልን ወደ ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት መውሰዷ ተገለጸ፡፡

‹‹ደቡብ አፍሪካ እስራኤል በጋዛ እየወሰደች ባለችው ዕርምጃ አገሪቱን ወደ ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) መውሰዷን ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ አስታወቁ፡፡

‹‹የእስራኤል መንግሥት በጋዛ እየፈጸመ ያለው ተግባር በዓለም አቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት መዳኘት እንዳለበት ከበርካታው አገሮች ጋር መግባባታቸውን ፕሬዚዳንቱ መግለጻቸውን የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል፡፡

‹‹በእስራኤል ጋዛ ጦርነት እስራኤልን አጥብቆ በመተቸትና ለፍልስጤማውያን ግልጽ ድጋፍ እየሰጡ ካሉ ጥቂት አገሮች መካከል ደቡብ አፍሪካ ተጠቃሽ ነች፡፡

‹‹የዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት (አይሲሲ) እንደ ጦር ወንጀልና ዘር ማጥፋት ባሉ ክሶች የተከሰሱ ግለሰቦችን የሚዳኝ ተቋም መሆኑ ይታወቃል፡፡›› 

ይህንን ዜና የሰማሁት በቀጥታ ከተላለፈው የ2፡00 ሰዓት (ምሽት) ዜና ነው፡፡ እዚያ ‹ዜና› ውስጥ ከሁሉም በላይ የገረመኝና ለዚህም ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ አንድ ‹መረጃ› ግን በድፍረቱ በእርግጠኝነቱ፣ የሚደንቅና የሚያስደነግጥም ነው፡፡ ‹‹በእስራኤል ጋዛ ጦርነት እስራኤልን አጥብቆ በመተቸትና ለፍልስጤማውያን ግልጽ ድጋፍ እየሰጡ ካሉ ጥቂት አገሮች መካከል ደቡብ አፍሪካ ተጠቀሽ ነች፤›› ይላል፡፡ ዜናው ውስጥ በአጠቃላይ የሚታየውን ኢንፎርሜሽን ሰጠሁ፣ አሳወቅሁ፣ አስተማርኩ፣ አብራራሁ ባይነቱን ከእነ ጉራውና ከእነ ትዕቢቱ ትተን ዕውን ደቡብ አፍሪካ በተባለው ጉዳይ ‹‹አጥብቆ በመተቸት›› እና ግልጽ ድጋፍ በመስጠት፣ የምትመደብበት ቦታ/ጎራ የ‹‹ጥቂት አገሮች›› ነው ወይ? የቤተ ዘመዱ ይታያል ጉዱ ተቆርቋሪነት ደግሞ በሌላ ወገን፣ ደግሞ በሌላ አቅጣጫ ‹‹እስራኤልን አጥብቆ በመተቸትና ለፍልስጤማውያን ግልጽ ድጋፍ እየሰጡ ካሉ [ጥቂት በማለት ፈንታ] በርካታ አገሮች መካከል ደቡብ አፍሪካ ተጠቃሽ ነች፤›› ቢልም ‹‹አልወድም››፣ አልፈልግም፡፡

እንዲህ እንዲል አልፈልግም/አልወድም የምለው ይህ ራሱ ዜና አይደለም ብዬ አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ፣ ከ‹ፍርድ› ከአስተያየት ጋር የሚምታታ ዜና ግን ሲበዛ ለእውነትና ለሙያ መተማመን ከግል እምነት፣ አቋም የተሻገረ መረጃና ምክንያታዊነትን ተከትሎ ማመዛዘንና ሀቅ ማፈላለግን ይጠይቃል፡፡ የዚህ ምክንያት ይህም ዜና፣ ይህም ኢንፎርሜሽን ነውና፡፡

ባደላቸው አገሮች ‹‹ሕዝብ ምን አለ?›› ለመሰለ፣ እኛ አገር ብዙም ላልተለመደ/ላልታወቀ ጥያቄ መለስ የሚሰጥ አሠራርና ተቋም አለ፡፡ ይህም ፐብሊክ ኦፒኒየን የሚለካ አሠራርና ሥርዓት እንደ ሚዲያው ሥራ ሕዝብ አንጀት ውስጥ መጎዝጎዝ ይችል ዘንድ፣ ሥልጣኔ ያቋቋመውንና የተለመዱትን ሕግና አሠራር መከተል፣ ኃላፊነቱ የሚጠይቀውን ባህርይና ጨዋነት መቀዳጀት ይፈልጋል፡፡ ጉዳዩ በቀረበበት መልክ የእኛም አገር ሆነ የሌላውን አገር ፐብሊክ ፖሊሲም ሆነ ፐብሊክ ኦፒንየን እውነትም ዜና ለማድረግ ከተለፈገ፣ ዕውቀትና ጥረት (እንዲሁም ተጨማሪ ማብራሪያ) ይጠይቃል እንጂ፣ እንዲሁ አሁን ባየነው ምሳሌ እንደሆነው ዝም ብሎ ‹‹ጥንቆላ›› ውስጥ መግባትን፣ ገብቶም ሳይጠየቁ መቅረትን አይመርቅም፡፡ ጥያቄውን ፊት ለፊት እንጋፈጠውና አገላብጠን እንየው፡፡ ዕውን እንደተባለው ደቡብ አፍሪካ ‹‹…እስራኤልን አጥብቆ በመተቸትና ለፍልስጤማውያን ግልጽ ድጋፍ…›› በመስጠት ከ‹‹ጥቂት አገሮች›› መካከል አንዷ/ተጠቃሽ ነች ወይ? ወይም በሌላ አነጋገር ደቡብ አፍሪካ በዓለም ውስጥ ከአገሮች መካከል አንዷ ተጠቃሽ ‹‹ጉዱ ካሳ›› ነች ወይ? ብሎ መጠየቅ ይቻላል (ምንም እንኳን ዜናው ውስጥ ዜናውን የሚተናነቀው ተቀዳሚ የስሜት ፍርድ ደቡብ አፍሪካን ለጉዱ ካሳ የሚሰጠውን ዓይነት ክብርና ማዕረግ መስጠት በጭራሽ አይሻም እንጂ)፡፡

ይህንን መነሻ በማድረግ ዕውን ደቡብ አፍሪካ የምትመደበው ከእነዚህ ‹‹ጥቂት አገሮች›› ጎራ ነው ወይ? ወይም እስራኤልን የሚተች፣ ለፍልስጤማውያን ‹‹ግልጽ ድጋፍ›› የሚሰጡ አገሮች ጥቂት ናቸው ወይስ ብዙ? ኢንተርናሽናል ኮሙዩኒቲው ምን ይላል? ሕዝብስ ምን ይላል? እንዴትስ አድርገን ነው እኛስ ያየነው/የምናየው ዓይነት ተዛነፍ ሳይጫነን፣ የትኛውም ዓይነት የፈላም፣ የደፈረሰም፣ የብልጭታም ውሎ ያደረም ስሜት ሳያውረን ለዚህ ጥያቄ መልስ የምንሰጠው?

ጥያቄው እንግዲህ ሕዝብ ምን ይላል? መንግሥትስ የሚል ነው፡፡ ፐብሊክ ፖሊሲ እና ፐብሊክ ኦፒኒየን በመለኪያቸውም በሚከሰቱበት/በሚገለጹበት መንገድም ይለያያሉ፡፡ ዴሞክራሲ ውስጥ እንደሚባለውና ሕጉም፣ ደንቡም፣ ወጉም እንደሚለው ፐብሊክ ፖሊሲ (ማለትም የመንግሥት አቋም) የሕዝብ አስተያየትን፣ የሕዝብ ሐሳብን መከተል አለበት፣ ነበረበት፡፡ ይህ ሲሆን ግን አናይም፡፡ አሜሪካ ውስጥ ያለው ችግር ይህ ነው፡፡ ከእኛ አገር በተለየ፣ በተሻለ፣ ይልቁንም ከዚያም በላይ በረቀቀና እንዲያውም በአንፃራዊነት በሚያስቀና ሁኔታ የሕዝብ አስተያየትን የሚለካ አሠራር አለ፡፡ በዚህ መሠረት በተለይም አሁን አሁን እየለየለት እንደመጣው፣ በዚህም የፍልስጤሞች ጉዳይ፣ ኩባን በማዕቀብ ጠምዶ ይዞ የሚያሽመደምደውን የቂምና የጥቃት ዕርምጃ ጭምር ጭራሽ የተለያየ ነው፡፡ ፐብሊክ ፖሊሲፐብሊክ ኦፒኒየን የተፈነጋገጡ  ናቸው፡፡ በየጊዜው የሚለካው ፐብሊክ ኦፒኒየንና የፖብሊክ ፖሊሲ ግብዓት፣ የውሳኔው ጥሬ ዕቃ ነዳጅና ቀለብ ቢሆን ኖሮ፣ ማለትም ዴሞክራሲ ቢሠራ ኖሮ ፖሊሲው ዕድሜ ባልኖረው ነበር፡፡

እ.ኤ.አ. በ1958 ጀምሮ እስከ 1962 ድረስ እየተጠናከረ፣ እየጠበቀና እያመረረ የመጣው አሜሪካ በኩባ ላይ የጣለችውና የጫነቸው ዕቀባና ጭቆና ተገቢ እንዳልሆነ ዓለም አቀፋዊው ኅብረተሰብ (ኢንተርናሽናል ኮሙዩኒቲ) ለዘመናት ዕንቢ ሲል ሲቃወም ኖሯል፡፡ ይህንን ከየት አመጣሁት? ኢንተርናሽናል ኮሙዩኒቲው ስንት ነው? ስንትስ ሆኖ ዕንቢ ሲል የት ሰማሁት? የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ እ.ኤ.አ. ከ1992 ጀምሮ በእያንዳንዱ ዓመት ሳያሳልስ አሜሪካ በኩባ ላይ የጣለችው የኢኮኖሚ ማዕቀብ እንዲነሳ ከሰላሳ ጊዜ በላይ በተከታታይ ወስኗል፡፡ ለምሳሌ የዘንድሮ የ2023 የጠቅላላ ጉባዔው ውሳኔ (A/77/L.5) የተላለፈው በ187 ድምፅ ድጋፍ፣ በሁለት ተቃውሞ (አሜሪካና እስራኤል) በአንድ ድምፅ ተዓቅቦ (ዩክሬን) ነው፡፡ የኢትዮጵያን አቋም ለማወቅ ተጨማሪ ማፈላለግ አያስፈልግም፡፡

እና ዝም ብሎ አንዱ ይህ ጉዳይ ተነስቶ፣ ዝም ብሎ ከመሬት ተነስቶ ኢትዮጵያ ከኩባ ጋር ባላት ታሪካዊ ግንኙነት መሠረት አገሪቱን ከሚደግፉት የተጫነባት ማዕቀፍ እንዲነሳ ድምፅ ከሚሰጡት ጥቂት አገሮች መካከል ትጠቀሳለች ቢላችሁ አትናደዱም? አያናድዳችሁም? ዓለም አቀፉ ኮሙዩኒቲ የዓለም ማኅበር ሆኖ፣ ጠቅላላ ጉባዔው ላይ ተሰይሞ፣ አንድ መቶ ሰማንያ ሰባት አገር/መንግሥት ሕዝብ ሆኖ ማዕቀብ ይነሳ ይላል፣ ሁለት አገሮች አይነሳም ይላሉ፡፡ የሁለት አገሮች ድምፅ ገዥ ሲሆን፣ መናደዳችን አንሶ ሌላው መጥቶ በሚዲያ ስም በማስተማር በማሳወቅ ስም አገሮችን ጥቂት/ብዙ ብሎ ሲፈርጅ ከመናደድ ጋር ዕውን ይህ የማን ቴሌቪዥን ነው? የየትኛው ሕዝብ፣ አገርና መንግሥት ድምፅ ነው ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል፡፡

የዓለም ማኅበር፣ ወይም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስተዳደርና ግቢ ውስጥ ከተሠሩ ዋና ዋና ሕጎች መካከል፣ አድልኦንና መድልኦን ወይም በመብት መንጓለል የሚከለክሉና የሚቀጡ ለዚያ መሠረት የሆኑ ሕጎች አሉ፡፡ እነዚህ ሕጎች በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 9 (4) እና 13 (2) መሠረት የኢትዮጵያ ሕግ አካል ናቸው፣ የሌሎች መሠረታዊ መብቶቻችን የአተረጓጎምና የአፈጻጸሙም የውኃ ልኮች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ሕጎች መካከል የዘር መድልኦን የሚመለከቱት ብቻ ሳይሆን፣ የአፓርታይድን ወንጀል የሚከላከሉና የሚቀጡ፣ ስፖርት ውስጥ ሳይቀር እዚያ ውስጥ ጭምር አፓርታይድን የሚከላከሉ የሚታገዱ ሕጎች አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው፣ ለእዚህም የኢትዮጵያ ሕግ አካል የሆኑ ስምምነቶች/ኮንቬንሽኖች ናቸው፡፡ ለእነዚህ ሕጎች መፀነስና መፅደቅ አፈጻጸም ውስጥ ኢትዮጵያ የተጫወተችው ሚና እነ ይድነቃቸው ተሰማ፣ እነ ኔልሰን ማንዴላ፣ እነ ኮልፌ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ታሪክ ውስጥ ብቻ የሚወሳ ጉዳይ አይደለም፡፡ በአንድ ወቅት ኢትዮጵያ ከአዲሲቷ ደቡብ አፍሪካ አገር፣ ከአዲስ አገር ጋር በነፃነትና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነት እስክትፈጥር ድረስ እያንዳንዱ ዜጋ እጅ ውስጥ የገባ የኢትዮጵያ ፓስፖርት የመንግሥት ንብረት በሆነው በዚህ ሰነድ አማካይነት ዜጋውን ሲሸኝና ሲጠብቅ፣ ይህንን ፓስፖርት ለሚመለከቱ ሁሉ ብሎም አደራ ሲል፣ ‹‹ከደቡብ አፍሪካ በስተቀር›› የሚል ክልከላ ነበረው፡፡

ደቡብ አፍሪካ ብዙ በሚታወቀውና በተተረከላት ትግል አማካይነት አፓርታይድን አፍርሳ ነፃ አገር ስትሆን፣ የፍልስጤማውያንን ጉዳይ የገዛ ራሷ ጉዳይ አድርጋ የውጭ ግንኙነቷን ሁሉ በዚያ ልክ የገለባበጠችው የውጭ አገር ነገር፣ የትግል አገርነት ጉዳይ አድርጋ ሳይሆን የመብት፣ የሰብዓዊ መብት ነገር ብላ ነው፡፡ በዚህ የትግል መሰል ደግሞ፣ አባልነቷ፣ ጎራዋ፣ ጥቂቶች ውስጥ አይደለም፡፡ ኢቲቪ የሚያውቀው፣ ኢቲቪ የሚነግረን የጥቂት አገሮች ጫጫታ የትኛው ነው? ለምሳሌ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ የመጨረሻው/ማለትም የቅርብ ጊዜው ውሳኔው የ27 ኦክቶበር ወይም የጥቅምት 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ነበር፡፡ ይህ ስብሰባ ከእነ ስሙ አሥረኛው አስቸኳይ ልዩ ስብሰባ የሚባል መጠሪያ አለው፡፡ ይህ አሥረኛው አስቸኳይ ልዩ ስብሰባ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠራው እ.ኤ.አ. በ1997 አፕሪል ነው፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እየተጠራ፣ በተጠራ ቁጥርም አንደኛው፣ ሁለተኛው፣ ወዘተ. ፕሊነሪ ሚቲንግ እየተባለ እየተጠራ የበቀደም ዕለቱ ‹‹Plenary Meeting›› 39ኛው ነበር፡፡ በዚህ ስብሰባው አስቸኳይ፣ ዘላቂነት ያለው ወደ ተኩስ ማቆም የሚያሸጋግር ትሩስ እንዲኖር ወሰነ፡፡ በተቃራኒው የኦክቶበር ሰባትን ‹‹የሐማስ የአሸባሪነት ጥቃት›› ማውገዝ የሚያስችል ድምፅ ማሰባሰብ ሳይቻል ቀረ፡፡ አንድ መቶ ሃያ አገሮች የደገፉት፣ 14 አገሮች (አሜሪካ፣ እስራኤል፣ ወዘተ) የተቃወሙት፣ እንዲሁም 45 አገሮች (ኢትዮጵያም፣ ካናዳም፣ ጀርመንም፣ ጃፓንም፣ ዩኬም ጭምር) ድምፅ/ተዓቅቦ ያደረጉበት ውሳኔ የጥቂቶች ድምፅ አይደለም፡፡ የተመድ ሪከርድ አያያዝ በዚህ ረገድ በጣም ውብ ነው፡፡ አገር ምን አለ? መንግሥት ምን ብሎ ወሰነ? ተብሎ ቢጠየቅ ድምፅ ሲሰጥና ሲነፍግ ብቻ ሳይሆን፣ በተለያዩ ምክንያቶች ድምፅ ከመስጠት ሲቆጠብ፣ ሲፆም ጭምር ይነግረናል፡፡

የዛሬውን አያደርገውና ወይም ዛሬን ምሥጋና ይግውና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እኮ በውሳኔ ቁጥር 3379 በ1975 ኖቬምበር 10 (ጥቅምት 30 ቀን 1968 ዓ.ም.) ጽዮናዊነት ወይም ዛዮኒዝም ዘረኝነት ነው፣ የዘር አድልኦ ነው ብሎ ወስኖ ነበር፡፡ በ16 ዲሴምበር 1991 (ታኅስስ 9 ቀን 1984 ዓ.ም.) የተነሳው ይህ ውሳኔ ፀንቶ በቆየበት ወቅት የዓለም አቋም፣ ተመድ የወሰነው ፖሊሲ ሆኖ ኖሯል፡፡ ዘረኝነት አፓርታይድና ጽዮናዊነት ስልቻና ቀልቀሎ፣ ቀልቀሎና ስልቻ ናቸው ተብሎ ተኖሯል፡፡ በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ድምፅ 68ም፣ 84 ላይም ድምፀ ተዓቅቦ ነበር፡፡ 

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አላዋቂ ሳሚ ሆኖ የጥቂት አገሮች ጫጫታ፣ የጥቂት አገሮች ጎራ ችግር አድርጎ ያቀረበልን የፍልስጤሞች ጉዳይ ከአገራቸው የተገፉ፣ እ.ኤ.አ. የ1948 ማባረር፣ ማሰደድ የደረሰባቸው ሰዎች እየተበላ፣ እየተቀነሰ፣ እየተወረሰ በመጣ በቁራጭ መሬት ላይ እንደ አገር የመቋቋም ትንሽዬዋን ፍትሕ እንኳን አጥተው ለዕልቂት፣ ለውርደትና ለጥፋት የተዳረጉበት የዓለማችን ትልቁ የመብት ረገጣ ነው፡፡ የአሜሪካና የአውሮፓ አገሮች ተጠያቂነት ያፈነገጡት የመላ ዓለም ሕዝብን ያገባኛል ባይነትና ትግል የሚጠይቅ የሰው ልጅ የሰብዓዊነት ጥሪ ነው፡፡

ክሬግ ሞክሂበር (Craig Mokhiber) ማለት በተመድ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የኒውዮርክ ከፍተኛ ኃላፊ ነበር፡፡ ሥራውን የለቀቀው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ በመልቀቂያ ደብዳቤው በፍልስጤማውያን ላይ የሚደርሰውን ግፍና በደል ገልጿል፡፡  ከጠቃቀሳቸው ብዙ ነገሮች መካከል አንዱን ልድገመው፡፡ የዩኒቨሳል ዲክላሬሽኑን 75ኛ ዓመት ስናከብር፣ ይህ የሰብዓዊ መብቶች ዓለም አቀፋዊ ሰነድ የተወለደው ከተሻገርነው፣ አልፈነው ከመጣነው ግፍ፣ ዕልቂትና አረመኔያዊነት ውስጥ የወጣ ነው የሚለውን ግብዝነታችንንና የነተበ አነጋጋራችንን እርግፍ አድርገን መተው አለብን፡፡ ዩነቨርሳል ዲክላሬሸን ኦፍ ሒዩማን ራይትስ የተወለደው የ20ኛው ምዕተ ዓመት የዘር ማጥፋት ወንጀሎች መካከል አንዱ ከሆነው፣ ከፍልስጤማውያን ጥፋትና ዕልቂት ጋር አብሮ አለ፡፡   

መላው የመንግሥታቱ ድርጅት አጠቃላይ ፍጥርጥር፣ ከፀጥታው ምክር ቤት በስተቀር፣ እያንዳንቸው በየአካሎቻቸውና በየሹማንቶቻቸው አማካይነት ከዋና ጸሐፈው ጀምሮ እስከ ራፖርተሮቻቸው ድረስ፣ ወዘተ ከእውነት፣ ከተጨቆነ፣ ከተበደለ፣ ከተገፋ ጎን ናቸው፡፡ ‹‹መቅደሱን››፣ መቀመጫወን ኢትዮጵያ አዲስ አበባ ያደርገው የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ አስተናጋጁ (ሆስቱ) ሆኖ የሚያገለግለው ትናንት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት፣ ዛሬ የአፍሪካ ኅብረት የፍልስጤሞችን ጉዳይ የገዛ ራሱ ጉዳይ አድርጎ ዲክላሬሽን ሲያወጣ ኖሯል፡፡ ፍልስጤምም ለሌላው የተነፈገ ከእነ ሙሉ ክብሩና ማዕረጉ የታዛቢነት ቦታ ያላት አገር ነች፡፡ እና እንዲህ ማድረግ የ‹‹ጥቂት አገሮች›› ባህርይ ነው ማለት፣ የአፍሪካ ኅብረትን የመሰለ ተቋም አስተናጋጅ የሆነ አገርና ሕዝብ ሚዲያ ወግ ነው?!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...