Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበወረራ የተያዘውን የኢትዮጵያ መሬት በድርድር ለማስመለስ የሱዳንን ሰላም መሆን እየጠበቀ መሆኑን መንግሥት...

በወረራ የተያዘውን የኢትዮጵያ መሬት በድርድር ለማስመለስ የሱዳንን ሰላም መሆን እየጠበቀ መሆኑን መንግሥት አስታወቀ

ቀን:

  • ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብን እንዲቀላቀል በቀረበው ጥሪ ጥናት መጀመሩ ተገልጿል

በወረራ የተያዘውን የኢትዮጵያ መሬት በድርድር ለማስመለስ፣ ሱዳን ከገባችበት አውዳሚ ጦርነት እስክትወጣ እየጠበቀ መሆኑን መንግሥት አስታወቀ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የ2016 ዓ.ም. የሦስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ ዓርብ ኅዳር 14 ቀን 2016 ዓ.ም. ሲያቀርብ ነው ይህ የተገለጸው፡፡

ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በምትዋሰንበት አልፋሽጋ ድንበር ተሻግራ ሰፊ የሚባል የኢትዮጵያን ግዛት መቆጣጠሯ ከተገለጸ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ሁለቱ አገሮ ለይገባኛል ጥያቄው መፍትሔ ለመፈለግ የጋራ ኮሚቴ አቋቁመው መንቀሳቀስ ቢጀምሩም፣ ችግሩ መፍትሔ ሳያገኝ በሱዳን ለወራት በቀጠለው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሳቢያ መስተጓጎሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለቋሚ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በሱዳን በሚያዝያ 2015 ዓ.ም. በሱዳን ጦር ሠራዊትና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል በተጀመረው ጦርነት፣ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ቢሞቱም አሁንም ቀጥሏል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ፍሰሐ ሻውል (አምባሳደር) በጉዳዩ ላይ በሰጡት ማብራሪያ፣ ድንበሩ ከተወረረ ወዲህ ምንም ዓይነት የሁኔታ ለውጥ የለም ብለዋል።

ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ አመራር የተያዘው አቅጣጫ ‹‹እነሱ ያደረጉትን እኛ መድገም አንፈልግም›› የሚል መሆኑን ተናግረዋል። ‹‹ኢትዮጵያ ከድንበር ባሻገር ከሱዳን ጋር ያላት ግንኙነት እጅግ ታሪካዊና በርካታ ጉዳዮችን የሚያካትት በመሆኑ፣ ያንን ግምት ውስጥ በማስገባት ሱዳን ከችግር በምትላቀቅበት ጊዜ በድርድር እንጨርሰዋለን፤›› ብለዋል።

‹‹ኢትዮጵያ ጠንካራ የመከራከሪያ ነጥብ ስላላት እናሸንፋለን፤›› ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ጉዳይ በይደር በመያዙ አሁን ምንም ዓይነት ድርድር እየተካሄደ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ.ር)፣ ከሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን ጋር በቅርቡ በአዲስ አበባ በመከሩበት ወቅት ጉዳዩ ተነስቶ እንደነበር፣ ችግሩን በድርድር ለመፍታት መስማማታቸውን የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የሱዳን ፕሬዚዳንት ሥልጣን እንደያዙ አንዱ የሥልጣን መቆያ አድርገው ሲንቀሳቀሱ የነበረው ከኢትዮጵያ ጋር መናቆርና ወደ ግብፅ መጠጋት የነበረ ቢሆንም፣ መንግሥት ባደረገው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ሱዳኖች ሚዛናቸውን እንዲጠብቁ መደረጉን ፍሰሐ (አምባሳደር) አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ፍላጎት የሱዳንን ብሔራዊ ጥቅም እንጂ የሌላ ማራመድ እንደማይሆን ተነግሯቸው ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ከግብፅ ተላቀው፣ ከኢትዮጵያ ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት መፈራረማቸውን ለቋሚ ኮሚቴው ገልጸዋል።

በመሆኑም በወረራ የተያዘው ድንበር ጉዳይ በቀጣይ በሱዳን መረጋጋት ሲፈጠር በተቋቋመው ኮሚቴ አማካይነት ለመፍታት መንግሥት ወደ ሥራ እንደሚገባ ገልጸው፣ ሱዳን አሁን እየፈረሰችና እየወደመች ባለችበት ሁኔታ ግን የኢትዮጵያን ኃይል ማስገባት ቀላል ቢሆንም ከአንድ ጎረቤት አገር የማይጠበቅ እንደሆነ ገልጸዋል።

ከቋሚ ኮሚቴው ኢትዮጵያ ምንም እንኳ ለጎረቤቶቿ ሰላም የምትጨነቅ ቢሆንም፣ ጎረቤት አገሮች ለኢትዮጵያ ጥቅምና ፍላጎት ምላሽ እየሰጡ አይደለም የሚል ጥያቄ ቀርቦ ነበር።

ይሁን እንጂ ፍሰሐ (አምባሳደር) ምላሽ ሲሰጡ የጎረቤት አገሮች ለኢትዮጵያ ያላቸው አመለካከት እጅግ አዎንታዊና ቀና ነው ብለዋል። ለዚህም በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት ኢትዮጵያ አንድ መንግሥት፣ አንድ ሠራዊት፣ አንድ አገር እንጂ ሌላኛው ኃይል ተገቢ አይደለም ብለው መከራከራቸውን እንደ ማሳያ አቅርበዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በጀኔቫ ጫና በማድረግ በኢትዮጵያ ላይ ችግር ሊያደርስባት በነበረበት ወቅት፣ አሥራ ሦስት የአፍሪካ አገሮች በኢትዮጵያ ላይ የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ መቃወማቸውን አስታውሰዋል።

በተመሳሳይ ከህዳሴው ግድብ ጋር በተገናኘ፣ ‹‹ኢትዮጵያ የግብፅ ምሳ ሆና ከተበላች እኛም አንተርፍም በሚል የእናንተ ጦርነት የእኛ ጦርነት ነው፤›› ብለው ከኢትዮጵያ ጋር መቆማቸውን አክለዋል፡፡

የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተሩ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የኢጋድ አባል አገሮች ሽግግር ውስጥ በመሆናቸው፣ ኢጋድ ምንም እንኳ ጠንካራ የኢኮኖሚ ፕሮግራሞች ያሉት ቢሆንም በአባል አገሮች ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት በፕሮግራሙ መግፋት አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡

በዚህም የተነሳ የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ የመስፋፋት ሁኔታ ማሳየቱንና ብዙ አዳዲስ አባላትም እየተቀላቀሉበት መሆኑን ገልጸው፣ ኢትዮጵያም ለአባልነት ተጠይቃ በጉዳዩ ላይ ጥናት የሚያደርግ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየታየ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በቀጣይ በምን ሁኔታ ኢትዮጵያ ልትቀላቀል ትችላለች የሚለው በጥልቅ ተገምግሞ እንደሚቀርብ ተናግረዋል፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ በተለይ ኬንያ፣ ታንዛኒያና ኡጋንዳ የሚያንቀሳቅሱት መሆኑን፣ በርካታ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በመኖራቸው በአገሮቹ ትልልቅ ሱፐር ማርኬቶችና አገልግሎቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ ብትቀላቀል ሊመጣ የሚችለውን ጥቅምና ጉዳት መንግሥት እያጤነው ነው ብለዋል፡፡

በዚህም የተነሳ ለአባልነቱ ኢትዮጵያ ዝግጁ ናት ወይ የሚለውን በማጤንና የኢትዮጵያን ባለሀብቶች ለሌሎች ኃይሎች አሳልፎ ላለመስጠት፣ አዋጭነቱ ታይቶ የሚገባበት በመሆኑ ጥናቱ ሲጠናቀቅ እንደሚወሰን አስረድተዋል፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓና የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ዘነበ ዘውዴ (አምባሳደር)፣ የአሜሪካ ከቀረጥና ከኮታ ነፃ የንግድ ዕድል (አጎዋ) ጋር በተገናኘ አዲስ ነገር ካለ ተብሎ ከቋሚ ኮሚቴው ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲያብራሩ፣ ሁለቱ አካላት በተገናኙበት አጋጣሚ ሁሉ የአጎዋ ጉዳይ ያልተነሳበት መድረክ አለመኖሩን አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር የሚፈልጉት በየጊዜው ቅድመ ሁኔታ በመቀያየር መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ አንዱ ሲሟላ ሌላ አዲስ ጉዳይ የማምጣት አባዜ እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡ ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ወደ አጎዋ እንድትመለስ ከአሜሪካ መንግሥት የቀረበው ቅድመ ሁኔታ የተሟላ ቢሆንም፣ ‹‹አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይነቃም›› እንደተባለው በመሆኑ ጉዳዩን በዋና መሥሪያ ቤትም ሆነ በኢምባሲ ማሳሰቡንና በተለያዩ መንገዶች ምክክርና ንግግር ቢደረግበትም ምላሽ ማግኘት አለመቻሉን አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...