Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢትዮጵያ በሶማሊያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ለተሰማሩ ወታደሮቿ ካሳና ወርኃዊ ክፍያ በወቅቱ እንዲፈጸም...

ኢትዮጵያ በሶማሊያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ለተሰማሩ ወታደሮቿ ካሳና ወርኃዊ ክፍያ በወቅቱ እንዲፈጸም ጠየቀች

ቀን:

በሶማሊያ በሰላም ማስከበር ግዳጅ ተሰማርተው ለተሰውና ለቆሰሉ የሠራዊት አባላት የጊዜ ገደቡን የጠበቁ ካሳና ወርኃዊ ክፍያዎች እንዲፈጸሙ ኢትዮጵያ ጥያቄ አቀረበች።

ኢትዮጵያ ጥያቄውን ያቀረበችው በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የሰላምና የፀጥታ ዲፓርትመንት ፋይናንስ ኃላፊ በሆኑት ሰሊጂ ባንጊ የተመራ ልዑክ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን የሰላም ማስከበር ማዕከል ዓርብ ኅዳር 14 ቀን 2016 ዓ.ም. በጎበኘበት ወቅት ነው።

የመከላከያ ሠራዊት ሰላም ማስከበር ማዕከል አዛዥ ሜጄር ጄኔራል አዳምነህ መንግሥቴ እ.ኤ.አ ከ2015 ጀምሮ ኢትዮጵያ በሶማሊያ ሠራዊት በማሰማራት ውጤታማ የሰላም ማስከበር ግዳጅ እየተወጣች መሆኗን ገልጸው፣ የአውሮፓ ኅብረትና የአባል አገሮቹ የማያቋርጥ የፋይናንስ ድጋፍ ሠራዊቱ በሶማሊያ የተሰጠውን አስቸጋሪ ግዳጅ መፈጸም አስችሎታል ብለዋል፡፡ 

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሜጄር ጄኔራል አዳምነህ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እ.ኤ.አ. ከ2015 ጀምሮ በሶማሊያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ሳይታክት አልሸባብን ለማጥፋት በርካታ ግዳጆችን ስኬታማ በሆነ መንገድ በመወጣት ምሳሌ መሆኑን ለልዑካን ቡድኑ ማስረዳታቸውን፣ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ግንኙነት መምርያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ይሁን እንጂ በዚህ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ለተሰውና ለቆሰሉ የሠራዊት አባላት ሊከፈል የሚገባ ካሳና ወራኃዊ ክፍያዎችን በወቅቱ የመፈጸም ችግር መኖሩን ጠቅሰው፣ የልዑካን ቡድኑ ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲያፈላልግ ሜጄር ጄኔራል አዳምነህ ማሳሳባቸውን ከመረጃው ለማወቅ ተችሏል።

በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የሰላምና ፀጥታ ዲፓርትመንት ፋይናንስ ኃላፊ ሚስተር ባንጊ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሶማሊያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ለከፈለው መስዋዕትነት ላቅ ያለ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡ ለሰላም ሰላም አስከባሪ አባላቱ አሠራሩንና አስፈላጊውን ዶክመንት በማሟላት ወቅቱን የጠበቀ ክፍያ እንዲፈጸም አቅጣጫ መስጠታቸውን፣ ከመከላከያ ሠራዊቱ የተገኘው መረጃ ለመረዳት ተችሏል። 

ይህንንም ተከትሎ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የሰላምና ፀጥታ ዲፓርትመንትና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሰላም ማስከበር ማዕከል በሶማሊያ በሰላም ማስከበር ግዳጅ ተሰማርተው ለተሰውና ለቆሰሉ የሠራዊት አባላት፣ የተሻለና ጊዜ ገደቡን የጠበቀ ካሳና ወርኃዊ ክፍያዎችን ለመፈጸም የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ላይ ተወያይተው ከስምምነት መደረሳቸው ተገልጿል።

የአፍሪካ ኅብረት ባለፈው መስከረም ወር በአዲስ አበባ ባካሄደው ውይይት በሶማሊያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ከፍተኛ የበጀት ጉድለት ማጋጠሙን፣ ይህም የሰላም ማስከበር ሥራውን ሊያደናቅፍ እንደሚችል ከመግባባት ላይ በመድረስ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን አስቀምጦ ነበር። 

በወቅቱ ካስቀመጣቸው የመፍትሔ አማራጮች መካከልም የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በአፍሪካ ኅብረት የሚመራ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ የገንዘብ ድጋፍ የማድረግ ኃላፊነቱን እንዲወጣ መጠየቅ፣ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን አጋሮች፣ እንዲሁም የግሉ ዘርፍ የፋይናንስ ድጋፍ አማራጮችን በመለየት ሀብት ለማግኘት መጣር የሚሉት ይገኙበታል።

ይሁን እንጂ የአፍሪካ ኅብረት ሊጠናቀቅ አንድ ዓመት ብቻ የቀረውን የሶማሊያ የሰላም ተልዕኮውን ለመወጣት የሚያስፈልገውን የፋይናንስ ድጋፍ እስካሁን እንዳላገኘ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የመከላከያ ሚኒስቴር የሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን ኅዳር 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉዳይና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት፣ ኢትዮጵያ ከምትሳተፍባቸው ዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በሦስት ወራት ውስጥ 12.4 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት አቅዶ 10.4 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን አስታውቆ ነበር፡፡

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሶማሊያ፣ እንዲሁም ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በሚወዛገቡበት የአብዬ ግዛት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ከአፍሪካ ኅብረት የተሰጠውን የሰላም ማስከበር ተልዕኮ እየተወጣ መሆኑ ይታወቃል። 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...