Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበፓርላማ የሚፀድቁ ሕጎች በቂ የሕዝብ ውይይትና ምክክር እንዲደረግባቸው ተጠየቀ

በፓርላማ የሚፀድቁ ሕጎች በቂ የሕዝብ ውይይትና ምክክር እንዲደረግባቸው ተጠየቀ

ቀን:

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአስፈጻሚው አካል የሚላኩለት የሕግ ረቂቆች በቂ የሕዝብ ውይይትና ምክክር ተደርጎባቸው እንዲፀድቁ ጥያቄ ቀረበ፡፡

ጥያቄው የቀረበው በተጠናቀቀው ሳምንት መልካም አስተዳደር ለአፍሪካ የተሰኘው ድርጅት የምሥራቅ አፍሪካ ቢሮው፣ ‹‹ተቋማዊ ልማት አደረጃጀትና መልካም አስተዳደር በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ ባካሄደው ውይይት ነው፡፡

ፓርላማው ተወያይቶ ከሚያፀድቃቸው የአገር ውስጥ ሕጎች በተጨማሪ ከአስፈጻሚው አካል የሚመሩለትን ከውጭ አገሮችና ተቋማት ጋር የሚደረጉ የብድር ስምምነቶችና መሰል ዓለም አቀፍ ሕጎች፣ በቂ ውይይት ሳይደረግባቸው በመጀመሪያ ንባብ እንዲፀድቁ ሲደረጉ ትውልድን ዋጋ ሊያስከፍሉ ስለሚችሉ ጥንቃቄ ሊደረግባቸው እንደሚገባም ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ፈቃደ ተረፈ (ዶ/ር) ‹‹ሕግ አውጭውና ውክልና በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሑፍ፣ በሁለቱ አካላት መካከል ባለው የተጋመደ ግንኙነት ሳቢያ ምክር ቤቱ ከአስፈጻሚ የሚላኩለትን ረቂቅ ሕጎች በቅጡ ሳይገመግም ብለዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በሕግ አወጣጥ ሒደት ዜጎች በቀጥታም ሆነ በወከሏቸው ተመራጮች አማካይነት ተሳትፎ እያደረጉ አይደሉም ብለዋል።

የምክር ቤት አባላት ብቁና በቂ ደጋፊ የሰው ኃይል ስለሌላቸውና ተንቀሳቅሰው ሕዝቡን ለማወያየት የሚያስችል የሀብትና የቴክኖሎጂ አቅም ወስንነት ስላለባቸው ለምክር ቤቱ ማነቆ መሆኑን ያስረዱት ፈቃደ (ዶ/ር)፣ ከዚህ የባሰውና አስከፊው ደግሞ እርስ በርሳቸው በሚዛናዊነት ይጠባበቃሉ ተብለው ከተዋቀሩት ሦስቱ የመንግሥት አካላት መካከል የአንዱ ጫንቃ መጠንከር ትልቁ ሞክንያት መሆኑን አስረድተዋል።

በተጨማሪም ሕግ አውጭው በራሱ ተነሳሽነት ተገቢ በሚባሉ ፖሊሲዎችና ሕጎች ላይ ተመሥቶ ሕግ ማውጣት እንዳለበት፣ እንዲሁም መራጩ ሕዝብ የወከለውን ግለሰብ ለመከታተል እንደሚያመቸው በወካዩ ሕዝብና በተወካዩ መካከል የሚታወቅ ዘላቂነት ያለው የግንኙነት መስመርና ሥርዓት መበጀት ይኖርበታል ሲሉ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ (ኢሶዴፓ) የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ራሔል ባፌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ፓርላማው ሕግ አውጪ ነው ብሎ ለመውሰድ እንደሚከብዳቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹አሁን ባለው አሠራር መሠረት የምክር ቤት አባላት በፓርቲ አለቃቸው በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ የመጣን ሕግ ለመቃወም ሥርዓቱ የማይፈቅድላቸው በመሆኑ፣ አንድ ሕግ ሲወጣ የተለመደውን አሠራር (formality) ለመጠበቅ ብቻ በፓርላማው ያልፋል እንጂ ለምን ብሎ የሚጠይቅ የለም፤›› ብለዋል። ‹‹ነገር ግን የምክር ቤት አባላት አንድ ሕግ ሲወጣ የወከላቸውን ሕዝብ ግምት ውስጥ በማስገባት ጥብቅ ክርክር ሊያደርጉበት ይገባል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ክፍል መምህር ዘካርያስ ቀንዓ (ዶ/ር)፣‹‹እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው›› ዓይነት እንጂ ሕግ አወጣጡ በቂ አስተያየት አይሰጥበትም ብለዋል፡፡ ‹‹ሕዝብ ጠርተን አሳተፍን ከማለት ውጪ በውይይት ወቅት የሚሰጡ አስተያየቶች ሕጉ ሲፀድቅ አይካተቱም፤›› በማለት ተናግረዋል። በመሆኑም የሕዝብ አስተያየት የሚባለው ጉዳይ በራሱ ትርጉም አልባ በመሆኑ አሠራሩ መቀየር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

መልካም አስተዳደር ለአፍሪካ የምሥራቅ አፍሪካ ቢሮ ዳይሬክተር አቶ ዘሪሁን መሐመድ በበኩላቸው፣ በሕግ አውጭውና በአስፈጻሚው መካከል ያለው ግንኙነት የዴሞክራሲ ባህል አለማደግ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

በሁለቱ አካላት ግንኙነት አስፈጻሚው በሕግ አውጭው ላይ የሚያሳድረው ጫና በግልጽ የሚታይ መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ ይህንን ችግር ለማስተካከል ግን ረዥም ጊዜና ትልቅ ሥራ የሚጠይቅ በመሆኑ ድርጅታቸው ተከታታይ ጥናት በማድረግና ውይይቶች በማዘጋጀት የራሱን ሚና ይጫወታል ብለዋል።

ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ ክፍል የተወከሉት ወ/ሮ ሃይማኖት ደበበ፣ የሕግ አወጣጥ ሒደቱ ተገቢውን ሒደት እንዳያልፍ የሚያደርገው ትልቁ ማነቆ የምክር ቤቱ የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ ውስጥ በሠፈረ ድንጋጌ ምክንያት፣ አንድ ሕግ በውይይት ላይ እንዲቆይ የሚፈቀድለት ጊዜ ዝቅተኛ በመሆኑ ነው ብለዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ ሕግ ውስጥ ስለረቂቅ ሕግ የመመርመርያ ጊዜ በሚያብራራው አንቀጽ 57 መሠረት፣ ማንኛውም ረቂቅ ሕግ በምክር ቤቱ አስቸኳይነቱ የሚታመንበት ካልሆነ በስተቀር የተመራለት ቋሚ ኮሚቴ ጉዳዩን አጥንቶ የውሳኔ ሐሳቡን ለምክር ቤቱ ለማቅረብ 20 ቀናት እንደሚሰጠው ተደንግጓል። ይሁን እንጂ የረቂቅ ሕጉን ስፋትና ክብደት ግምት ውስጥ በማስገባት ተጨማሪ ጊዜ በአፈ ጉባዔው ሊሰጥ እንደሚችልም ተካቷል።

ወ/ሮ ሃይማኖት ቋሚ ኮሚቴዎች በአንድ ረቂቅ ሕግ ላይ አስፈላጊውን ጊዜ ተጠቅመው ሕጉ እንዳይበስል የሚገድባቸው አንቀጽ መስተካከል አለበት ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ዓለም አቀፍ ሕጎች ፓርላማው ደርሰው በመጀመሪያ ንባብ እንዲፀድቁ የሚደረግበት መንገድ መስተካከል እንዳለበት የሚናሩት የሕግ ባለሙያዋ፣ ትልልቅ የብድር ሀብት የሚመጣባቸውን አዋጆች ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ያለ ውይይት በአንድ ንባብ መፅደቃቸው ወደፊት ትውልድን ዋጋ ሊያስከፍሉ ይችላሉ ብለዋል።

የወ/ሮ ሃይማኖትን ሐሳብ የደገፉት ፈቃደ (ዶ/ር) ዓለም አቀፍ ሕጎችን ጨምሮ በዓመታዊ የበጀት ድልድል ላይ ምክር ቤቱ፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ ሚዲያውና በርካታ የሚመለከታቸው አካላት ለወራት ውይይትና ፍጥጫ ሳያደርጉበት የሚከናወነው የጥድፊያ የሕግ ማፅደቅ አሠራር ሊስተካከል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...