Monday, February 26, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለገበያ የሚቀርበው ማንጎ በተባይ የተጠቃ መሆኑን ተመራማሪዎች አስታወቁ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአሁኑ ወቅት በመላው ኢትዮጵያ ለገበያ እየቀረበ ያለው ማንጎ በተባይ የተጠቃ መሆኑን ተመራማሪዎች አስታወቁ፡፡

ከህንድ በመጣ ችግኝ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን የተከሰተው የነጭ ማንጎ ተባይ (ዋይት ማንጎ ስኬል) በመላ አገሪቱ መሠራጨቱን፣ የተመረቱ ማንጎዎች ጥቁር ነጠብጣብ ወይም ቡራቡሬ መልክ እንዳላቸው፣ በውስጣቸው ያለው የጁስ መጠን አነስተኛ የሆነ ትንንሽ ማንጎዎች ገበያው ውስጥ በብዛት እንዳሉ ተመራማሪዎች ገልጸዋል፡፡

ለገበያ የሚቀርበው ማንጎ በተባይ የተጠቃ መሆኑን ተመራማሪዎች አስታወቁ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
በተባይ የተጠቁ የማንጎ ፍሬዎች

የነጭ የማንጎ ተባይን በተመለከተ በርካታ የምርምር ጥናታዊ ጽሑፍ ያዘጋጁት የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር ኦፍጋአ ጅራታ (ዶ/ር)፣ ገበያው ውስጥ ያሉ ማንጎዎች በተባይ የተጠቁ መሆናቸውን ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ተጠቃሚዎች ጥቁሩን ክፍል በማውጣት እንደሚመገቡ፣ ለኤክስፖርት የሚቀርበው ማንጎ ሙሉ ለሙሉ መቋረጡን፣ የተሠራጨውን ተባይ በአጭር ጊዜ ለማስወገድ አንዳንድ ሥራዎች ቢጀመሩም፣ የማንጎ ተክሎችን በሙሉ በመንቀል እንደገና መትከል ወይም ‹‹የማንጎ አብዮት ያስፈልጋል›› ሲሉ ኦፍጋአ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

‹‹ተባዩ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲራባ ያደረገው ከህንድ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ ኤርፖርት ውስጥ የግብርና ባለሙያዎች ባለመኖራቸውና የኳራንታይን ሲስተማችን ደካማ ስለሆነ ነው፤›› ሲሉ መነሻቸውን ምክንያት ገልጸዋል፡፡

‹‹በወቅቱ ምሥራቅ ወለጋ ሲገባ ሙሉ ለሙሉ እርሻው እንዲቃጠልና እንዲወድም ቢጠየቅም ተቀባይነት ሳያገኝ በመቅረቱ፣ አሁን በመላው አገሪቱ ተባዩ በስፋት ተሠራጭቶ የጁስ ፋብሪካዎች ሳይቀሩ የምርት ግብዓት እጥረት እያጋጠማቸው ከመሆኑም በላይ የማንጎ ምርት እየቀነሰ ነው፤›› በማለት ኦፍጋኦ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ከአዳማ ዩኒቨርሲቲ ጋር ቡድን በማዋቀር የተጀመረውን ምርምር በጋራ የሚያከናውነው የአርባ ምንጭ የግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ሙሉዓለም መርሻ የኦፍጋአ (ዶ/ር)ን ሐሳብ ሙሉ በሙሉ የሚጋሩ መሆኑን ገልጸው፣ ችግሩን ለመቅረፍ መንግሥት ከአርሶ አደሮች ጋር እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች ከምርምርና ከግብርና ቢሮዎች ጋር ባረጉት ጥናት የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ የመፍትሔ ሐሳቦች መቅረባቸውን አስረድተዋል፡፡

ችግሩ ከአቅም በላይ በመሆኑና የማንጎ ዛፎች እየተቆረጡ ሌሎች ምርቶች እየተተኩ ስለሆነ ባህላዊ አሠራሮችን ማለትም እንደ ውኃ ማጠጣት፣ መግረዝ፣ መጎንደልና ቅርንጫፎችን ማሳጠር ለአጭር ጊዜ መፍትሔ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

አርሶ አደሮች የማንጎ ዛፍ ትልቅ ስለሆነ ለጥላና ለከብት ማሰሪያ እንደሚጠቀሙበት፣ እንዲሁም ማንጎ ሲያፈራ ትልቅ ስለሚሆን በዱላና በድንጋይ በመደብደብ ስለሚያወርዱት ንፅህናውን ያልጠበቀ ምርት ገበያ ውስጥ እንደሚሠራጭ ጠቁመዋል፡፡

ሁለተኛው የአጭር ጊዜ መፍትሔ በቅጠልና በአፈር ላይ የሚደረግ የኬሚካል ርጭት መሆኑን አቶ ሙሉዓለም ገልጸዋል፡፡

ስፓርከስ የሚባለው ኬሚካል ሁለት ግራም ከአንድ ሊትር ውኃ ጋር ተበጥብጦ ከዛፉ ሥር 30 ሴንቲ ሜትር ርቀት ላይ ክብ በመሥራት የሚረጭ መሆኑን፣ ማንኛውም ተክል ውኃን ከአፈር ውስጥ እንደሚመጥ ሁሉ ዛፉ መምጠጥ ሲጀምር ቅጠሉ ላይ ያሉት ተባዮች እንደሚሞቱ ተናግረዋል፡፡

በመካከለኛ ጊዜ የተያዘው ዕቅድ ተባዮችን የሚበሉ የተርብ ዝርያዎች በቅርቡ ከደቡብ አፍሪካ በማስገባት፣ ተርቦቹ በአግባቡ ሥራቸውን እንዲሠሩ በየክልሎቹ የአየር ፀባይ መሠረት ማራባት ነው ብለዋል፡፡

በረዥም ጊዜ የተያዘው ዕቅድ በኢትዮጵያ አሁን ያሉት የማንጎ ዝርያዎች ረዣዥምና የጫካ ይዘት ያላቸው እንጂ ፍሬያቸው ያን ያህል ጠቃሚ ባለመሆኑ፣ በሌላ አዲስ ዝርያ መተካት መሆኑን አቶ ሙሉዓለም ገልጸዋል፡፡

‹‹በመንግሥት ዕቅድ ተይዞ እየተከናወኑ ካሉ ዋና ዋና ተግባራት መካከል ለአርሶ አደሮች ግንዛቤ ለማስጨበጥ፣ በአካባቢ አስተዳደሮች የሚመራ ግብረ ኃይል ተቋቁሟል፤›› ብለዋል፡፡

የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት የባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የምርምር ሥራዎች እንዲከናወኑ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ አዲስ ፕሮጀክት መጀመሩን፣ የኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ ተመራማሪ ብርሃን አዲስ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ኢንስቲትዩቱ ከጀርመን መንግሥት በተገኘ የአምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ፕሮጀክቱ ማስጀመሩን ብርሃን (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

‹‹አርሶ አደሩ የማንጎ ዛፍ እንዲቆረጥበት ስለማይፈልግ ይህን ግንዛቤ ለመፍጠር ከበሽታው የፀዱ ዕፅዋት ተቆርጠው ንፁህ ማንጎ ሲመረት ለማሳየት፣ በየቀበሌውና በየወረዳው ያሉ የገበሬ ማሠልጠኛ ማዕከላት አብረውን እየሠሩ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ለአሥር ዓመታት ያህል በተደጋጋሚ ችግሩ ሲነገር የነበረው በተመራማሪዎች ብቻ እንደነበር በመግለጽ፣ አሁን ግን መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ትኩረት እየሰጡ ነው ሲሉ ብርሃን (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡ 

የዓለም አቀፍ የሥነ ነፍሳት ሳይንስና ሥነ ምኅዳር ማዕከል (ኢሲፔ)፣ በምሥራቅ አፍሪካ ጎጂ የሆኑ የፍራፍሬ ነፍሳትን ለመቆጣጠር የተቀናጀ የተባይ መቆጣጠሪያ ፕሮጀክት መጀመሩን አስታውቋል።

በኬንያ፣ በኢትዮጵያና በታንዛኒያ ደኅንነታቸው የተጠበቀ የፍራፍሬ ምርቶችን ለማምረት በአግሮ ኢኮሎጂ ላይ የተመሠረቱ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዝ ፕሮጀክት መሆኑን፣ የማዕከሉ የማኅበራዊ ሳይንስና ተፅዕኖ ምዘና ክፍል ኃላፊ ምናለ ካሴ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ጎጂ ነፍሳት ምርትና ምርታማነትን እየቀነሱ በመሆናቸው ፕሮጀክቱ የተረጋገጡ የግብርና ሥነ ምኅዳር ተኮር የግብርና ልምዶችን፣ በተለይም የነጭ ማንጎ ተባይን ሥርጭት በመቆጣጠር ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

የዕፅዋት ምርምር ከፍተኛ ሳይንቲስቷ ሰሚራ መሐመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ፕሮጀክቱ ነጭ የማንጎ ተባይን እንደሚከላከልና ችግሮቹን በመፍታት የምግብ ዋስትናን፣ የገቢ ማስገኛን፣ ሥራ አጥነትንና ድህነትን መቀነስና የመሳሰሉትን ተግባራት ያግዛል ብለዋል።

አፍሪካ በነጭ ማንጎ ስኬል ተባዮች በዓመት ሁለት ቢሊዮን ዶላር ታጣለች ተብሎ እንደሚገመት ከተመራማሪዎቹ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች