Sunday, March 3, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትስዊች ከ405 ሚሊዮን ብር በላይ የተጣራ ትርፍ ማግኘቱ ተነገረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ ሁሉም ባንኮች ባለአክሲዮኖች የሆኑበት ኢትስዊች ኩባንያ በ2015 የሒሳብ ዓመት በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ከፍተኛ የሚባለውን የትርፍ ክፍፍል ድርሻ ማስመዝገቡን፣ ዓመታዊ የትርፍ መጠን ጭማሪውን 172 በመቶ በማሳደግ ከታክስ በፊትና በኋላ 405.3 ሚሊዮን ብር ማትረፉ ተገለጸ፡፡  

ኩባንያው የ2015 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸሙን ይፋ ባደረገበት ሪፖርቱ፣ በሒሳብ ዓመቱ ከታክስ በፊት 534.53 ሚሊዮን ብር ማግኘቱን፣ ባለፈው ዓመት ከታክስ በፊት አስመዝግቦት የነበረው ትርፍ 196.8 ሚሊዮን ብር እንደሆነ፣ ከታክስ በኋላ ደግሞ 162.05 ሚሊዮን ብር አትርፎ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

በ2015 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 172 በመቶ ብልጫ ያለው የትርፍ መጠን ዕድገት ማስመዝገቡ በፋይናንስ በኢንዱስትሪው በከፍተኛነቱ የሚጠቀስ እንደሆነም ታውቋል፡፡ እስካሁን ይፋ ከተደረጉት የፋይናንስ ተቋማት ዓመታዊ ሪፖርቶች መገንዘብ እንደተቻለው፣ ዓመታዊ ትርፉን በዚህን ያህል ደረጃ ያሳደገ አለመኖሩን ነው፡፡

ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ በከፍተኛ ሁኔታ ያስመዘገበው የትርፍ ዕድገት፣ 1,000 ብር ዋጋ ያለው አንድ አክሲዮን የትርፍ ድርሻ 719.93 ብር እንዲሆን እንዳስቻለው ታውቋል፡፡ ይህ ትርፍ ድርሻ ባለፈው ዓመት 340 ብር ከመሆኑ አንፃር፣ የትርፍ ክፍፍል መጠኑን ከእጥፍ በላይ ማሳደግ መቻሉን ያመለክታል፡፡ እንዲህ ያለው ውጤት ሊገኝ ከቻለባቸው ምክንያቶች አንዱ የኩባንያው ገቢ እንዲጨምር በመሠራቱና ጥንቃቄ የተሞላበት የወጪ አስተዳደር ተግባራዊ በመደረጉ መሆኑን፣ የኢትስዊች የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበርና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን ደስታ ያቀረቡት ሪፖርት ያስረዳል፡፡

ኩባንያው ያደረጋቸው ማሻሻያዎችና አዳዲስ አገልግሎቶች ለውጤቱ መገኘት ተጠቃሽ ሆነዋል፡፡ ኢትስዊች በሰጠው አገልግሎት የተገኘው ውጤትን በተመለከተ በሪፖርቱ እንደተገለጸው፣ በአጠቃላይ 89.76 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ከ71.4 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ እርስ በእርስ ተናባቢ የኤቲኤም ግብይቶች ማከናወን ችሏል፡፡ እርስ በርስ ተናባቢ በሆኑ የኢቲኤም ግብይቶች የተገኘው ውጤት ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀሩ በ79 መቶ ጭማሪ አሳይተዋል ተብሏል።

በተመሳሳይ የፖስ ተናባቢ አፈጻጸምን በተመለከተ ከ2.64 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው 970,434 የፖስ ግብይቶች የተከናወኑ መሆናቸውን፣ ከቀዳሚው ዓመት የ169 በመቶ ጭማሪ ማሳየታቸው ተጠቅሷል፡፡

በተጨማሪም በሒሳብ ዓመቱ በአጠቃላይ 113.29 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ 14.14 ሚሊዮን ከአንድ ባንክ ወደ ሌላ ባንክ ወይም አነስተኛ የገንዘብ ተቋማት ገንዘብ የማስተላለፍ (P2P Transfer) አገልግሎቶች ማከናወኑን በመቻሉ፣ ዓመታዊ አፈጻጸሙ ከቀዳሚው ዓመት 584 በመቶ ጭማሪ እንዳሳየ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

ከሌሎች ዓመታዊ ክንውኖቹ መካከል በሒሰብ ዓመቱ ኢትስዊች 380,795 የሚሆኑ የካርድና የፒን ፐርሰናላይዜሽን (Personalization) አገልግሎቶችን ለአባል ባንኮች መስጠቱን፣ አገልግሎቶች ካለፈው ዓመት አንፃር የ26 በመቶ ዕድገት ማሳየታቸው ተጠቅሷል፡፡ 

ኩባንያው አሁን ያለውን አገልግሎት የበለጠ ለማሳደግ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ እየተገበረ መሆኑን የገለጹት አቶ ሰለሞን፣ ከዚህ አኳያ ኩባንያው ጉልህ የሆኑ ስኬቶችን ማስመዝገቡን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በጋራ የሞባይል ገንዘብ ፕሮጀክት ላይ በርካታ ማሻሻያዎችን በማድረግ ወደ ሙከራ ለመግባት ዝግጅቱን በማጠናቀቅ እንደሚገኝና ድንበር ተሻጋሪ ገንዘብ መቀበል ለማስቻል የማስተር ካርድ ኤቲኤም አገልግሎት የተተገበረ መሆኑን፣ የፖስ አገልግሎት ሙከራ ከአባል ባንኮች ጋር በማከናወን ይገኛል ተብሏል፡፡

ኢትስዊች አክሲዮን ማኅበር በሁሉም ባንኮችና በበርካታ የማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ባለቤትነት የተያዘ ኩባንያ ነው፡፡

ኩባንያው የተቋቋመበት ዋነኛ ዓላማም ቀላል፣ ተመጣጠኝ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ ቀልጣፋና የኢ-ክፍያ መሠረተ ልማት አገልግሎቶችን ለችርቻሮ ክፍያ ለአገልግሎት ሰጪዎች ለማቅረብ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትስዊች አጠቃላይ የሀብት መጠኑን በ64 በመቶ በማሳደግ 1.78 ቢሊዮን ብር ማድረስ መቻሉ ተገልጿል፡፡ ከአሥር ዓመት በፊት ሲቋቋም 80.5 ሚሊዮን ብር ካፒታል ይዞ የነበረ ሲሆን፣ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት መጨረሻ የተከፈለ ካፒታሉን 941.5 ሚሊዮን ብር አድርሷል ተብሏል፡፡ የተፈረመ ካፒታሉንም 2.2 ቢሊዮን ብር እንዲሆን መወሰኑም አይዘነጋም፡፡

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃ መሠረት አጠቃላይ የባንክ ኢንዱስትሪው በዲጂታል የክፍያ ሥርዓት በ2015 ዓ.ም. ብቻ ከ3.44 ትሪሊዮን ብር በላይ አንቀሳቅሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች