Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ተንከባላይ የሒሳብ ኦዲት ጉድለቶች እንዳሉበት የፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ

ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ተንከባላይ የሒሳብ ኦዲት ጉድለቶች እንዳሉበት የፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ

ቀን:

ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በ2014 በጀት ዓመት ሲንከባለሉ የቆዩ የሒሳብ ጉድለት እንዳሉበት፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተደደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ይህንን ያስታወቀው ኅዳር 12 ቀን 2016 ዓ.ም. ዩኒቪርሲቲው የ2014 በጀት ዓመት የኦዲት ሪፖርት ሕጋዊነትን በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ባደረገበት ወቅት ነው።

የሒሳብ የኦዲት ጉድለቶችን  በተመለከተ የቋሚ ኮሚቴውን ወክለው የተናገሩት ወ/ሮ አያንቱ ጉተታ፣ ለዩኒቨርሲቲው ማስፋፊያ ቦታ ለባለ ይዞታዎች ካሳ ቢከፈልም እስካሁን ከቦታው እንዳልተነሱ ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ለባለ ይዞታዎቹ የካሳ ክፍያ ቢፈጸምላቸውም ምንም ዓይነት ሰነድ (ካርታ) አለማቅረባቸውን፣ ግለሰቦቹ በመሬቱ ላይ ያላቸው ሀብትና ንብረት በሚመለከተው አካል ሳይረጋገጥ ክፍያ መፈጸሙን  የኦዲት ግኝቱ  እንደሚያሳይ ገልጸዋል፡፡

ተነሺዎቹ በገቡት ውል መሠረት የካሳ ክፍያው በተፈጸመ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይዞታቸውን እንዲለቁ ቢጠበቅም፣ አንድም ግለሰብ ቦታውን አለመልቀቁን የኦዲት ግኝት ሪፖርቱ ያመላክታል ተብሏል፡፡

ከተጋባዥ መምህራን ያልተሰበሰበ ቅድመ ግብር፣ ለአካዴሚክ የሕክምና ባለሙያዎች ከደንብና ከመመርያ ውጪ ‹‹ቶፕ አፕ›› ተብሎ በድምሩ ከ41 ሚሊዮን ብር በላይ ማስተካከያ እንዲደረግ ቢጠየቅም እስካሁን አለመስተካከሉ ተገልጿል፡፡

በሥራ ገበታቸው እያሉ ስብሰባ (ኮንፈረንስ) ለሁለት ቀናት ለተሳተፉ ሠራተኞች የ18 ቀናት የውሎ አበል በቀን 171 ብር ተሠልቶ ያላግባብ እንደተከፈላቸው ወ/ሮ አያንቱ አስረድተዋል፡፡

የተሟላ መረጃ ሳይቀርብ በወጪ መመዝገብ፣ ቀኑን በመጨመር ያላግባብ የውሎ አበል መክፈል፣ ከቀረበ ማስረጃ በላይ አስበልጦ መክፈልና የተሽከርካሪ ዕቃዎች  ግዥ ሲፈጸም ያለ ደረሰኝ (በዱቤ) ሽያጭ ደረሰኝ 3,259,439 ብር ክፍያ መፈጸሙን በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡

በግባንታ ላይ ያሉ 12 ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዳልዋሉ፣ ተቋራጮቹ በገቡት ውል መሠረት መሥራታቸውን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ ከግንባታ ክፍል በተገኘው መረጃ መሠረት በርካታ ክፍተቶች መታየታቸው በሪፖርቱ ተብራርቷል፡፡

ከዚህ ውስጥ ሉሲ ኮንስትራክሽን የተሰኘ ኩባንያ 233,432,359.95 ብር ለቴፒ ካምፓስ የመማሪያ ሕንፃ ግንባታና ለመምህራን አዳራሽ ሚያዝያ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ነሐሴ 21 ቀን 2014 ዓ.ም እንዲያጠናቀቅ በውሉ ቢገለጽም፣ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ግንባታው 56 በመቶ ላይ ብቻ ይገኛል ተብሏል፡፡

የኮንስትራክሽን ተቋራጩ በ73,652,906.05 ሳንቲም ለጂምናዚየም ግንባታ ሐምሌ 11 ቀን 2008 ዓ.ም.  ጀምሮ እስከ ታኅሳስ 15 ቀን 2012 ማጠናቀቅ እንደሚገባው፣ ተቋራጩ በተሰጠው ጊዜ ውስጥ ሳይጨርስ ሌላ ፕሮጀክት እንደተሰጠው በሪፖርቱ ተገልጻል፡፡ 

የውኃ አቅርቦት ግንባታ በ300,283,120.83 ብር በጀት ሉሲ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ሰኔ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የካቲት 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ግንባታውን እንዲያጠናቅቅ ፕሮጀክቱ ቢሰጠውም፣ ግንባታው እስካሁን አሥር በመቶ  ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

ለግንባታና ለጥገና ለተደራጁ ማኅበራት ቅድመ ክፍያ ሲሰጥ ካደራጇቸው የመንግሥት ተቋማት የዋስትና ደብዳቤ ሳያቀርቡ 4,918,356.18 ብር መከፈሉ ተነግሯል፡፡  

 ከላይ የተጠቀሱት ክፍተቶች ዩኒቨርሲቲው ለረዥም ጊዜያት ሲንከባበሉ የቆዩ የኦዲት ግኝቶቹን ለማረም የወሰደው ዕርምጃ በቂ አለመሆኑን ማሳያ መሆናቸው በቋሚ ኮሚቴው ተገልጿል።

ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ዓመታት ዕርምጃ ያልወሰደበት ከ46 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን የበጀት ጉደለት መኖሩን፣ ማስተካከያ የተደረገበት የበጀት ጉድለት አንድ በመቶ እንደማይሆን ተጠቁሟል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ  ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ ዩኒቨርሲቲው  የኦዲት ግኝት አስተያየቶችን ለማረም እያደረገ ያለው ጥረት በቂ አለመሆኑን፣  ከዚህ በኋላ ኃላፊነታቸውን በማይወጡ ኃላፊዎች ላይ ተገቢው ዕርምጃ መወሰድ እንዳለበት፣ ሕጎችንና መመርያዎችን ማክበር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ምክትል ሰብሳቢዋ የተማሩ ዜጎች መፍለቂያ የሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች ለራሳቸው ብቁ የሆኑ ሠራተኞችን ሊያፈሩ እንደሚገባ ጠቁመው ትምህርት የሚኒስቴር፣ የመንግሥት ግዥ ኤጀንሲና ሌሎች ባለድርሻዎች የዩኒቨርሲቲዎችን የግዥና የኦዲት ችግሮች በጋራ መቅረፍ እንደሚገባቸው አፅንኦት ተሰጥተው ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የኦዲት  ግኝት መርሐ ግብሩን እስከ ኅዳር ወር መጨረሻ ለቋሚ ኮሚቴው እንዲያቀርብ፣ የፌዴራል ፀረ ሙስና ኮሚሽን የብልሹ አሠራር ምርመራ ለሦስት ወራት እንዲያከናውንና የፍትሕ ሚኒስቴር የተላለፉ ሕጋዊ ወሳኔዎችን እንዲያቀርብ ቋሚ ኮሚቴው አቅጣጫ ሰጥቷል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው፣ በዩኒቨርሲቲው ሕጋዊ ሒደትን ያልተከተለ የግንባታ ፕሮጀክቶች ውል፣ ተገቢ ያለሆነ የአበል ክፍያ፣ ለባለ ይዞታዎች ያለ በቂ መረጃ የተከፈለ የቦታ ካሳ ክፍያና ያለ በቂ የአዋጭነት ጥናት የተጀመሩ የገቢ ማመንጫ ሥራዎች በኦዲት ግኝት ተረጋግጧል ብለዋል፡፡

በተያዘላቸው ጊዜ ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች መኖር፣ በማዕቀፍ መከናወን የነበረባቸው ግዥዎች በግለሰብ መፈጸማቸው፣ ሕጋዊ ደረሰኝ ያልተገኘላቸው ግዥዎች መኖራቸውን ጨምሮ፣ በዩኒቨርሲቲው ዕርምጃ ያልተወሰደበት የኦዲት ግኝት ከ59 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲደርስ አድርገውታል ብለዋል፡፡  

ዋና ኦዲተሯ፣ ዩኒቨርሲቲው የውስጥ ቁጥጥርና የኦዲት ሥርዓት ደካማ በመሆኑ፣ ከ200 ሺሕ ብር በላይ ወደ ግለሰብ ኪስ እንደገባና ሕጋዊ ሒደቱን ባልተከተለ ግዥ መንግሥት ከ1.9 ሚሊዮን ብር በላይ ማጣቱን አስረድተዋል፡፡ 

የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አህመድ ሙስጠፋ (ዶ/ር) የኦዲት ግኝቶችን ለማረም ጥረቶች በመደረግ ላይ መሆናቸውን ተናግረው፣ በዩኒቨርሲቲው የሚገነቡ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ የበጀት እጥረት፣ የፀጥታ ችግርና የግንባታ ግብዓቶች ዋጋ መናር ምክንያቶችች እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲውን የበጀትና የንብረት አጠቃቀም ለማስተካከል የዕውቀት ክፍተት  እንዳለ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመሆን የሰው ኃይል የማብቃት ሥራ  በማከናወን ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

የካሳ ክፍያ የተከፈለባቸው ከ60 በላይ ይዞታዎች ውስጥ 46 ያህሉን ዩኒቨርሲቲው መረከቡን፣ ሕግና ሥርዓትን በጣሱ ግለሰቦች ላይ የዕርምት ዕርምጃ እየተወሰደባቸው እንደሆነ ፕሬዚዳንቱ ለቋሚ ኮሚቴው አስረድተዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...