Friday, March 1, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አርብቶና አርሶ አደሮችን ከሕገወጥ ደላሎች ይታደጋል የተባለ የዲጂታል ሥርዓት ዝርጋታ ስምምነት ተደረገ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያን ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት፣ ፊድ ዘፊውቸር ኢትዮጵያና ሜርሲ ኮር ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቅ አርሶና አርብቶ አደሮችን ከሸማቾች ጋር በቀጥታ ያገናኛል የተባለለትን የዲጂታል መረጃ ሥርዓት ለመዘርጋት ኅዳር 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ስምምነት አደረጉ።

የመግባቢያ ሰነዱ የእንስሳት ገበያ መረጃን በብሔራዊ ገበያ የመረጃ ሥርዓት ቋት (NMIS) ውስጥ በማስገባት ወቅታዊ፣ ትክክለኛና አስተማማኝ መረጃዎችን ለአርብቶ አደርና ለከፊል አርብቶ አደር ማኅበረሰቦችና ለሌሎች የዘርፉ ተዋናያን ለማሠራጨት እንደሚያተኩር ተገልጿል፡፡

በስምምነቱ መሠረት ሶማሌና አፋርን ከብሔራዊ መረጃ ማዕካል ጋር በማገናኘት የእንስሳት ጤና፣ እንዲሁም የዕርባታና የገበያ ሁኔታን በተመለከተ የሚያገናኝ መሆኑን፣ ከተለዩ 157 የገበያ ማዕከላት በየወረዳው ባሉ ባለሙያዎች አማካይነት መረጃውን በመሰብሰብ ወደ ብሔራዊ ቋት እንዲገባ ይደረጋል ተብሏል።

የሦስቱ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች የመግባቢያ ስምምነቱን ሲፈራረሙ እንደተገለጸው፣ ለአርሶና ለአርብቶ አደሩ በየሳምንቱ ከየአካባቢው የሚሰበሰበውን መረጃ በማድረስ ለሚያመርተው ምርትና ለሚያረባው እንስሳ የገበያ መረጃ ወቅቱን ጠብቆ የሚቀርብለት መሆኑን፣ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማንደፍሮ ንጉሤ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ይተገበራል የተባለው ይህ ስምምነት በአርሶና በአርብቶ አደሩና በሸማቾች መካካል እየተገባ ያልተገባ ዋጋ ጭማሪ ወይም ቅናሽ የሚያደርግ አሠራርን፣ ምርት እያለ እንደሌለ በማድረግ የገበያ ጤና የሚነሳውን ሕገወጥ ደላላ እንደሚያስቀር አስረድተዋል።

ሕገወጥ ደላላ አገር እያፈረሰ መሆኑንና በግብርና ልማት ላይ የተደቀነ አደጋ በመሆኑ፣ የግብይት ሥርዓቱ በዘመናዊ መንገድ መመራት አለበት ያሉት በኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ ተመራማሪ ጭምዶ አንጫለ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

በተመሳሳይ ኢንስቲትዩቱ ክፍያ ፋይናንሺያል ቴክኖሎጂ ከተሰኘ ኩባንያ ጋር የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረመ ሲሆን፣ ስምምነቱ ማዳበሪያን ጨምሮ እስካሁን ሲፈጸም የነበረውን የወረቀት (manual) የግብርና ግብዓት ግዥ ክፍያና ሥርጭት ሥርዓትን (input voucher system) በዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ለመቀየር ያለመ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡

በትብብሩ የሚጎለብተው የዲጅታል ክፍያ ሥርዓት የግብዓት አቅርቦትንና ሥርጭትን ኤሌክትሮኒክ ከማድረጉም ባሻገር፣ አነስተኛ አርሶ አደሮችን ከአነስተኛ የፋይናንስ ተቋማትና የኅብረት ሥራ ዩኒየኖች ጋር በማስተሳሰር ለግብርና ግብዓቶች ግዥና ሥርጭት የብድር አቅርቦት ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች