Sunday, March 3, 2024

የከሸፈው የመንግሥትና የኦነግ ሸኔ የታንዛኒያ ንግግር

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ኩምሳ ድሪባ (ጃል መሮ)፣ ‹‹ፖለቲካ አያውቁም፣ ዓላማ የላቸውም ተብለን ብንናቅም ከመንግሥት ጋር ለድርድር ተቀመጥን፤›› ብሎ ሲናገር መደመጡን የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ዘግበውታል፡፡ እሱ የሚመራው ላለፉት አምስት ዓመታት በኦሮሚያ ጫካዎችና ከተሞች ከመንግሥት ኃይል ጋር በጠብመንጃ ሲገዳደር የቆየው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነግ ሸኔ) የሚባለው የትጥቅ ቡድን የፖለቲካ ግብ፣ ከመንግሥት ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ እስከ መወያየት ድረስ ብቻ ነው ወይ የሚለው ጉዳይ ግን ጥያቄ ይነሳበታል፡፡

ባለፈው ቅዳሜ ከቡድኑ ደጋፊዎች ጋር ጃል መሮ ተነጋገረ ተብሎ በተሠራጨው የዙም ስብሰባ ላይ፣ ‹‹ፖለቲካ አያውቁም፣ ልጆች ናቸው፣ ዓላማ የላቸውም፣ እርስ በርስ አይስማሙም ተብለን ስንናቅ የነበረው ዛሬ ኃያላን ባሉበት እየተደራደርን ነው፤›› ብሎ ስለመናገሩም ተዘግቧል፡፡ ይሁን እንጂ ኦነግ ሸኔ ከዚህ ድርድር ከተደራዳሪነት ባለፈ የሚፈልገው የፖለቲካ ውጤት ምንድነው የሚለው፣ የኦሮሚያ ክልልን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን የሰላም ሁኔታ የሚወስን እንደሆነ ይገመታል፡፡

ጃል መሮ ሲቀጥል፣ ‹‹አሁን እየተካሄደ ስላለው ድርድር ይህ ነው ያ ነው ማለት አልፈልግም፡፡ ነገር ግን ትልቅ ፈተና እንዳለብን ማወቅ አለባችሁ፡፡ በሥራችን ገምግሙን እንጂ በወሬ ብቻ አትመሥረቱ፡፡ እኛ ሥራ ላይ ነን፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ መወዳደር ያለበት በወሬ ሳይሆን በተግባር ነው፡፡ አንገታችሁን ደፍታችሁ በርትታችሁ ሥሩ፡፡ ታይታ ጥቅም የለውም፡፡ በገንዘብ ለምታደርጉት ድጋፍ እናመሠግናችኋለን፡፡ እኔ በበኩሌ ገንዘቡም ይቅር እያልኩ ነው፡፡ ሁሉም ሰው ባለው ሙያና ችሎታ እንዲደራጅ እፈልጋለሁ፡፡ በሁሉም ነገር ባንስማማ እንዳልተስማማን አምነን በሰላም መኖር ራሱ እንደ አንድ ትግል ነው የማየው፤›› በማለት መናገሩ ተወስቷል፡፡

ይህ የጃል መሮ አነጋገር በታንዛንያው ንግግር ከአንድ ስምምነት ላይ መድረስ ባይቻል እንኳን ያለ ስምምነትም ቢሆን በሰላም መኖር እንደሚቻል አመላካች ሆኖ ነው የታየው፡፡ በኢትዮጵያም ሆነ በኦሮሚያ ክልል ያለው የፖለቲካ ልምድ ይህን የሚደግፍ ባይሆንም፣ ጃል መሮ ግን ከእነ ልዩነታችን ባንስማማም ተግባብተን መኖር አያቅተንም ሲል ተደምጧል፡፡

ጃል መሮ ንግግሩን ሲቀጥልም፣ ‹‹እኛ መገንባት የምንፈልገው ሥርዓት ነው፡፡ ለሚመጣው ትውልድ ምን ዓይነት ሥርዓትና አገር እናስረክባለን የሚለው ነው የሚያሳስበን፡፡ እኛ እናልፋለን፡፡ ነገር ግን ለመጪው ትውልድ ምን ዓይነት አሻራ ጥለን ነው የምናልፈው የሚለው ነው የሚያሳስበኝ፡፡ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ብቻም አይደለም ሌላ ፓርቲ መሥርቱ፡፡ ለዚህ ሰፊ ሕዝብ ብዙ ፓርቲዎች ቢኖሩት እኔ ተቃውሞ የለኝም፡፡ ነገር ግን በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ስም መነገድ ይቁም፤›› በማለት መናገሩ ተዘግቧል፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ)፣ አሜሪካ፣ ኖርዌይና ኬንያ የሚያሸማግሉት የታንዛኒያው ድርድር ከአሥር ቀናት በላይ አስቆጥሯል፡፡ መንግሥት ድርድሩን በሚመለከት ዝርዝር መረጃ ሳይሰጥ ቢቆይም ከፍተኛ ወታደራዊና የመንግሥት ባለሥልጣናትን ወደ ድርድሩ ቦታ መላኩ ቀደም ሲል መላኩ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን ከረጅም ጊዜ ዝምታ በኋላ ትናንት ምሽት ንግግሩ ያለ ውጤት መበተኑን አስታውቋል፡፡ ከሁለት ዓመት ቀደም ብሎ ከሕወሓት ጋር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው ኦነግ ሸኔ በዚህ ድርድር ያቀረባቸው ጥያቄዎችም ሆነ ከድርድሩ ያገኛቸው ውጤቶች ምን እንደሆኑ የታወቀ ነገር የለም፡፡ የቡድኑ የጦር መሪ ጃል መሮ ለሕዝባችን በዚህ ድርድር ድል እናጎናፅፋለን ማለቱ ቢሰማም፣ ምን ዓይነት የድርድር ድል እንደሆነ ግን ማብራሪያ አልሰጠም፡፡

ይህ የድርድር ግልጽነት ጥያቄ የከበበው የመንግሥትና የኦነግ ሸኔ ሁለተኛ ዙር የታንዛኒያ ድርድር ምን ውጤት ያመጣል የሚለው ጥያቄ ከግምት ውጪ ተጨባጭ ነገር ሳያገኝ ነበር የቆየው፡፡ የኦሮሚያን ብሎም የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖች፣ ድርድሩ ባለፉት አምስት ዓመታት ከግጭትና ጦርነት ተላቆ የማያውቀውን የኦሮሚያ ክልል ወደ ሰላም ካመጣ በራሱ እጅግ ውጤታማ ተብሎ መገለጽ የሚችል እንደሆነ እየተናገሩ ነበር፡፡

ለወትሮው ቡና፣ ማንጎና ፍራፍሬ ይለቀምባቸው የነበሩ የወለጋ ጫካዎች የሰዎች አስከሬን መልቀሚያ ከሆኑ ከራርመዋል፡፡ በደህናው ጊዜ ማዕድን ማውጫ የነበሩ የጉጂ ጫካዎች የጥይት ባሩድ ሽታ ያወዳቸው ከሆኑም ሰነባብቷል፡፡ ጤፍ የሚታፈስባቸው የሸዋ መሬቶች መታኮሻ ዓውደ ውጊያዎች ከሆኑ ቆይተዋል፡፡ የብርቱ አርሶ አደር መኖሪያ ቀዬዎች ሰላም አጥተው ውለው ማደራቸው የተለመደ ከሆነም እንዲሁ፡፡ በኦሮሚያ ክልል ባለፉት አምስት ዓመታት ከኦነግ ሸኔ ጋር በሚደረገው ጦርነት የሚዘጉ ኢንዱስትሪዎች፣ የሚቃጠሉ የአበባ እርሻዎች፣ የሚወድሙ የሆርቲካልቸር ልማቶች፣ የንግድ ተቋማትና የሕዝብ መገልገያ መሠረተ ልማቶች በርካታ ናቸው፡፡

መንግሥት በበርካታ የኦሮሚያ አካባቢዎች ከኦነግ ሸኔ ጋር የሚያደርገው ጦርነት  ለንፁኃን ሕልፈት ዋና ምክንያት ሆኖም ነው የዘለቀው፡፡ ይህ ለበርካታ ንፁኃን መቀጠፍ ምክንያት የሆነና ብዙ ውድመት ያስከተለ ግጭት፣ በታንዛኒያ በሚካሄደው ድርድር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ዕልባት እንዲያገኝ የሚፈልጉ ዜጎች በርካታ የነበሩ ቢሆንም አሁንም ሊሳካ አልቻለም፡፡

ይሁን እንጂ ይህ ድርድር እየተካሄደ ነው እየተባለ በነበረበት ወቅት የኦሮሚያ ክልል ቀውስ ጋብ የሚል አዝማሚያን አለማሳየቱ፣ በዚህ ላይ ያለ ውጤት ተጠናቀቀ መባ ቀቢፀ ተስፋ የሚያሳድር ነበር፡፡ ከሰሞኑ የመከላከያ ሚኒስቴር ይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች፣ ‘ኦነግ ሸኔን ደመሰስን፣ ማረክን ወይም አፀዳን’ በሚሉ ዜናዎች የተሞሉ ሆነው መታየታቸው ይህን የሚደግፍ መሆኑ ይገመታል፡፡

በሌላ በኩል በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች የንፁኃን መገደል በወለጋ እንደቀጠለ መሆኑን የሚጠቁሙ መረጃዎች እየተሠራጩ ነው፡፡ በሸዋ አንዳንድ ቦታዎች የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ዕገታ፣ ግድያና ጥቃት ስለመቀጠሉም ይሰማል፡፡ ‘ሰፋሪ’ እንዲሁም ‘መጤ’ ናቸው በሚል ፍረጃ በወለጋ አንዳንድ አካባቢዎች የአማራ ተወላጆች ግድያ እየተፈጸመባቸው እንደሚገኝ የቅርብ ሰሞን መረጃዎች አረጋግጠዋል፡፡

በዚህ ሁሉ ምስቅልቅልና ውጥረት በበዛት የፖለቲካ ከባቢ አየር ውስጥ ሆነው፣ መንግሥትና ኦነግ ሸኔ በታንዛኒያ ሲያደርጉት በነበረው ድርድር በመጨረሻ በሰላም ስምምነት ይቋጫል የሚለውን ግምት ብዙዎች ጥርጣሬ ውስጥ እየከተቱት ነበር፡፡ መንግሥትና ኦነግ ሸኔ ከአንድ ስምምነት ላይ ደርሰው በኦሮሚያ የሚፈሰው የንፁኃን ደም እንዲቆም ብዙዎች ምኞታቸውንና ተስፋቸውን ቢገልጹም፣ ይሁን እንጂ ሁለቱ ኃይሎች መግባባት ላይ ደርሰው በኦሮሚያ የዘለቀውንና አገር አቀፍ ችግር የሆነውን የሰላም ዕጦት የሚያስቆም መፍትሔ ማስገኘት አልቻሉም፡፡

የድርድሩን ስኬት የሚጠራጠሩ ወገኖችም ኦነግ ሸኔ በድርድሩ በሚያነሳቸው ጥያቄዎች ተቀባይነት ያግኙ/አያግኙ በሚለው ብቻ ሳይሆን፣ በኦሮሚያ ፖለቲካ ላይ ደጋግሞ ጥላ እያጠላ በሚገኘው የንግግር/ድርድር ግልጽነት በማውሳት አለመግባባቱ እንደሚያይል እንደሚገምቱ ይናገራሉ፡፡

ከዚህ ቀደም በተለይም በለውጡ ማግሥት ለብሔራዊ ዕርቅና መግባባት ይበጃል ተብሎ የተካሄደው የአስመራ ንግግር፣ የኦሮሚያ ክልልንም ሆነ ኢትዮጵያን ወደ ባሰ ቀውስ እንደከተተ እነዚህ ወገኖች ያስታውሳሉ፡፡

ከለውጡ መሪዎች አንዱ ሲባሉ የነበሩት አቶ ለማ መገርሳ የመሩት የመንግሥት ባለሥልጣናት የልዑካን ቡድን አስመራ አቅንቶ ከኦነግ ጋር ስምምነት አደረገ የሚለው ጉዳይ በጊዜው ትልቅ ዜና ሆኖ ነበር፡፡ በጊዜው ኤርትራ መሽጎ በትጥቅ ትግል መንግሥትን ሲቃወም የኖረው ኦነግ መሣሪያ ጥሎ አገር ቤት በመግባት፣ በሰላማዊ ትግል ሊሳተፍ ነው የሚለው ግምትም ሚዛን የደፋ ሆኖ ነበር፡፡

ኦነግ ወደ አገር ቤት ሲገባም ታላቅ አቀባበል ጠበቀው፡፡ ይሁን እንጂ በሒደት ቡድኑ ትጥቅ አልፈታም ብሎ ተመልሶ በኦሮሚያ ጫካዎች መሸገ የሚል መረጃ መሠራጨት፣ እንዲሁም በመንግሥትና በኦነግ መካከል ግንኙነቱ መልሶ ሻከረ መባልም ጀመረ፡፡ ቀስ በቀስ ደግሞ የኦነግ ወታደራዊ ክንፍ ነው የሚባለው ኦነግ ሸኔ (የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት) ደግሞ ወደ ትጥቅ ትግል ገባ የሚለው ጉዳይ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ተቆጣጠረው፡፡

ኦሮሚያ ክልልን በሰቆቃ የተሞላ የግጭት ቀጣና አድርጎታል የሚባለው የመንግሥትና የኦነግ ሸኔ ግጭት ልክ እንደ ሰሜኑ ጦርነት ሁሉ በአገሪቱ ላይ ከባድ ቀውስ ማስከተሉ ይታወቃል፡፡ ከኦነግ ሸኔ ጋር የሚካሄደው ግጭት ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በቀጥታ ቁርኝት የፈጠረ ተብሎም ሲነገር ቆይቷል፡፡ የኦነግ ሸኔ ችግር አገሪቱ ዛሬ ለገጠማት አዳዲስ ቀውሶች ጭምር መነሻ እንደሆነ በተደጋጋሚ ይወሳል፡፡

በአማራ ክልል በአሁኑ ጊዜ ያጋጠመው ጦርነት በኦሮሚያ ክልል የቀጠለውና በኦነግ ሸኔ እየተፈጸመ ነው የሚባለው የአማራ ተወላጆችን ዒላማ ያደረገው ብሔር ተኮር ጥቃት አንዱ መነሻው መሆኑ ይነገራል፡፡ ከኦነግ ሸኔ ጋር የተያያዘውን ችግር መፍታት ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት ትልቅ ዕገዛ አለው የሚሉ ወገኖች፣ በኦሮሚያ የቀጠለው ብሔር ተኮር ጥቃት በአማራ ክልል ለተቀጣጠለው ግጭት የብሶትና ቁጣ ምንጭ በመሆን ማገልገሉን አያይዘው ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ በመነሳትም ከኦነግ ሸኔ ጋር መንግሥት በታንዛኒያው ከስምምነት መድረስ ከቻለ ይህ ውጤት ሌሎች አገራዊ ቀውሶችንም ለመፍታት እንደሚረዳ ብዙዎች ቢገምቱም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው በኢትዮጵያ የሚፈጸሙ ዘር ተኮር ጥቃቶችን በመመዝገብና ሪፖርት በማድረግ የሚታወቀው ‹‹ጄኖሳይድ ፕሪቬንሽን ኢን ኢትዮጵያ›› ተቋምን ወክለው የሚናገሩት ሰናይት ሰናይ (ዶ/ር)፣ የታንዛኒያው ድርድር  ‘ውስብስብ’ መሆኑን ተናግረው ነበር፡፡

‹‹የሰሜኑን ጦርነት አስቆመ የሚባለው ከሕወሓት ጋር የተደረገው ድርድር ራሱ የጦርነቱ ዋና ሰለባ የሆኑ የአማራና የአፋር ክልሎች ኃይሎች ያልተወከሉበት ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ እየተደረገ ነው የሚባለው ድርድር የአማራ ተወላጆች በወለጋና በመተከል እንደ ኦነግ ሸኔ ባሉ ኃይሎች እየተጨፈጨፉ ባለበት የሚደረግ ነው፡፡ የታንዛኒያው ድርድር በፕሪቶሪያ ስምምነት ማግሥት በአማራ ክልል ደም አፋሳሽ ግጭት ተከስቶ ባለበት ወቅት የሚደረግ ነው፡፡ በድርድሩ ምን እየተካሄደ እንደሆነ ብቻ ሳይሆን ይዞት የሚመጣው ውጤትም በማይታወቅበት ሁኔታ ላይ ነው አገሪቱ ያለችው፤›› በማለት በወቅቱ ስለድርድር ጉዳይ እየሆነ ነው ያሉትን ሁኔታ በሰፊው አብራርተዋል፡፡

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ምክትል ሰብሳቢ አቶ ሙላቱ ገመቹ በሕወሓትና በብልፅግና መካከል በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ላይ መደረስ የተቻለው፣ ‹‹የሁለቱ ፀብ የሥልጣን ሽኩቻ ብቻ ስለነበር፤›› ነው በማለት ይናገራሉ፡፡ ከኦነግ ሸኔ ጋር የተደረገው ድርድር ግን ሌላ ዓይነት ይዘት ያለው መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

‹‹የኦነግ ሸኔ ጥያቄ ሁላችንም ስናነሳው የቆየነው የኦሮሞ ሕዝብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱ ይከበር የሚል መሠረታዊ ጥያቄን ያነገበ ነው፡፡ ኦሮሞ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ራሱ በመረጠው አካል ይተዳደር ከሚል ነው ጥያቄው የሚነሳው፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ በራሱ ቋንቋ የመተዳደርና የመዳኘት መብቱን ጨምሮ ማንነቱ ይከበር የሚል ነው ጥያቄው›› ይላሉ፡፡ አቶ ሙላቱ ከዚህ በተጨማሪ ኦነግ ሸኔ የጊዜያዊ ሽግግር መንግሥት ይመሥረት የሚል ጥያቄን ጨምሮ፣ መንግሥትን የሚፈትኑ ሌሎች ጠንካራ የመደራደሪያ ሐሳቦች ሊያነሳ እንደሚችል ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡

ድርድሩ በኦሮሚያ ክልል ሰላም ይፈጥራል ወይ ለሚለው ጥያቄ በድርድሩ ሒደት ጥያቄዎቹ ምላሽ በሚያገኙበት ሁኔታ እንደሚወሰን ነው አቶ ሙላቱ ምላሽ የሰጡት፡፡ በሌላ በኩል ድርድሩ እናንተን ጨምሮ በኦሮሚያ የሚንቀሳቀሱ ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎችን ባለማቀፉ የተሟላ ውጤት ላይኖረው ይችላል ተብለው ተጠይቀው ነበር፡፡

አቶ ሙላቱ ይህን በተመለከተ፣ ‹‹የኦሮሞን ጥያቄ እስከመለሰ ድረስ ማንም ቢሆን ቢደራደር ችግር የለውም፡፡ እኔ ያልተገኘሁበት ስለሆነ አይጥመኝም ልንል አንችልም፡፡ ድርድሩ የኦሮሞን ጥያቄ ይመልሳል ወይስ አይመልስም በሚለው ነው መታየት ያለበት፤›› ብለዋል፡፡

በኦሮሞ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ትንተና በመስጠት የሚታወቁት ፀጋዬ አራርሳ (ዶ/ር)፣ ‹‹ለድርድሩ ቅርብ ከሆኑ ምንጮች ሰማሁት›› ብለው ከሰሞኑ በሰጡት ማብራሪያ ድርድሩ ስምምነት ይዞ አይመጣም ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡ ‹‹በድርድር ስም የኦነግ ሸኔ ኃይልን ለመዋጥና ለማዳከም የተደረገ ጥረት ነው፤›› ሲሉ ሒደቱን የጠቀሱት ተንታኙ፣ ብልፅግና ለራሱ ሥልጣን ማቆያ የጀመረው ጥረት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹‹ብልፅግና በአማራ ክልል ውስጥ ጦርነት ላይ ይገኛል፡፡ ከእንግዲህ የአማራን ሕዝብ ልብም ሆነ ድጋፍ አገኛለሁ ብሎ አያስብም፡፡ ከትልልቆቹ ከአማራም፣ ከኦሮሚያም የድጋፍ መሠረት አጥቶ ተንሳፎ መኖር ከባድ እንደሆነ የተረዳው የብልፅግና መንግሥት፣ በድርድር ስም በኦሮሚያ ክልል ድጋፍ ለማግኘት በሚል ነው ድርድሩን የጀመረው፡፡ ዕርቅ፣ ሰላም፣ የሕዝቡን ሰቆቃ ለማቆም እየተባለ በብልፅግናና በደጋፊዎቹ ድርድሩ አጀንዳ ቢሆንም፣ ዋና ዓላማና ግቡ ግን የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትን መዋጥ ነው፡፡ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትን በመዋጥና የኦሮሚያ ክልል ሕዝብን ከጎን በማሠለፍ የአማራ ፋኖን፣ እንዲሁም ኤርትራን ወግተን የባህር በር እናስመልሳለን በሚል ቅዠት የተጀመረ ግብታዊ ጥረት ነው፤›› በማለት የድርድር ጥረቱን ተችተውታል፡፡

ከሰሞኑ ድርድሩን በሚመለከት ኦነግ ሸኔ ባወጣው አጭር መግለጫ፣ ‹‹የሕዝባችንን ፍላጎትና ጥያቄ በሚመልስ ሁኔታ በሰላማዊ መንግድ የፖለቲካ መፍትሔ ለማምጣት በቁርጠኝነት እየሠራን እንገኛለን፤›› የሚል ሐሳብ የሚንፀባረቅበት መልዕክት ማስተላለፉ አይዘነጋም፡፡ ድርድር በመጀመሩ ብዙ አዎንታዊ አስተያየቶች ከግራም ከቀኝም የሚደመጡ ቢሆንም እንኳን፣ ድርድሩ የአካታችነትና የግልጽነት ጥያቄ ተነስቶበት ነበር፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ መንግሥት ስለድርድሩ ከመግለጽ ተቆጥቦ ቆይቶ፣ በመጨረሻ የተጀመረው ሁለተኛ ዙር ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ማስታወቁ በብዙዎች ዘንድ አግራሞት ፈጥሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -