Sunday, March 3, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አቢሲኒያ ባንክ ካፒታሉን ለሁለተኛ ጊዜ በ2.5 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ወሰነ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ባንኩ ለመጠባበቂያ የያዘው የገንዘብ መጠን 3.3 ቢሊዮን ብር ደርሷል

ባለፈው ዓመት ካፒታሉን በ2.5 ቢሊዮን ብር ውሳኔ አሳልፎ የነበረው አቢሲኒያ ባንክ ዘንድሮም ተጨማሪ 2.5 ቢሊዮን ብር አዲስ ካፒታል በመጨመር የተከፈለ ካፒታሉን ወደ አሥራ አምስት ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያቀረበው የውሳኔ ሐሳብ በባለአክሲዮኖች ተቀባይነት አግኝቶ መጽደቁ ተገለጸ፡፡

ባንኩ በ2014 የሒሳብ ዓመት ካፒታሉን በ2.5 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ በማድረግ ውሳኔ ማሳለፉ የሚታወስ ሲሆን፣ ሰሞኑን ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔም የባንኩን ካፒታል በተመሳሳይ 2.5 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ወስኗል፡፡

ባንኩ በ2014 ሒሳብ ዓመት ካፒታሉን በ2.5 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያሳለፈው ውሳኔ በአንድ ዓመት ውስጥ እንደሚፈጸም ተገልጾ የነበረ ሲሆን፣ በዚሁ መሠረት እስከ 2015 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ድረስ የባንኩ የተከፈለ ካፒታሉ ከአሥር ቢሊዮን ብር ወደ 11.9 ቢሊዮን ብር ማደግ ችሏል፡፡

ባለፈው ቅዳሜ በተካሄደው የባለአክሲዮኖች ጉባዔ ውሳኔ መሠረትም ተጨማሪው 2.5 ቢሊዮን ብር አዲስ ካፒታልም በተመሳሳይ መንገድ በሚደለደለው የአክሲዮን መጠን እንደሚፈጸም ተገልጿል፡፡

የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ መኮንን ማንያዘዋል፣ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት የባንኩ የተከፈለ ካፒታል በቀደመው ዓመት ከነበረበት 8.32 ቢሊዮን ብር በ2015 መጨረሻ ላይ 11.9 ቢሊዮን ብር መድረሱን፣ ይህም የ43.02 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል ግን የባንኩ መጠባበቂያ ገንዘብ በ985 ሚሊዮን ብር ወይም በ41.83 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 3.34 ቢሊዮን ብር መድረሱን አመልክተዋል፡፡

የባንኩን የ2015 የሒሳብ ዓመት አጠቃላይ አፈጻጸም በተመለከተ በቀረበው ሪፖርት ከ36.4 ቢሊዮን ብር በላይ አዲስ ተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰብ አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን 158.5 ቢሊዮን ማድረስ ችሏል፡፡ ይህ ተቀማጭ ገንዘብ በ29.9 በመቶ ዕድገት ማሳየቱንም ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ ባንኩ በ2014 የሒሳብ ዓመት የነበረው አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 122.05 ቢሊዮን ብር እንደነበር ያስታወሱት አቶ መኮንን፣ ተቀማጭ ገንዘቡ በ36.5 ቢሊዮን ብር ማደግ ችሏል ብለዋል፡፡

በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ ባንኩ ከደረሰበት አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ ከወለድ ነፃ የባንኩ አገልግሎቱ የተሰበሰበው አሠራድ በመቶ ድርሻ መያዙንም ከባንኩ ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል፡፡

ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ያሰባሰበው አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ ከ18.07 ቢሊዮን ብር በላይ ሆኗል፡፡ በዚህ ዘርፍ የተሰበሰበው ተቀማጭ ገንዘብ ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲትይ በ50.1 በመቶ ማደጉንና በአንድ ዓመት ብቻ ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ከወለድ ነፃ አዲስ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ መቻሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ባንኩ ከወለድ ነፃ የሚያሰባስበው ተቀማጭ ገንዘብ እያደገ ሲሆን በ2013 የሒሳብ ዓመት 8.3 ቢሊዮን ብር በ2014 ደግሞ 12.06 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡

ከቀተማጭ ገንዘብ አሰባሰብ ባሻገር ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ከ33.18 ቢሊዮን ብር በላይ አዲስ ብድር በመስጠት አጠቃላይ የብድር ክምችቱ ከ145.5 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱ ተገልጿል፡፡ የቦርድ ሊቀመንበሩ በሪፖርታቸው እንደጠቀሱትም ባንኩ ከወለድ ነፃ ያደገውን ፋይናንስ ጨምሮ አጠቃላይ የሰጠው ብድር በ29.27 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ከተለቀቁት ብድሮች ውስጥ ለወጪ ንግድ፣ ለኢንዱስትሪና ለአገር ውስጥ የተሰጡት ብድሮች 64.1 በመቶ ድርሻ እንዳላቸው ተጠቅሷል፡፡

ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ተነጥሎ ሲታይ ደግሞ በሒሳብ ዓመቱ የቀረበው የብድር መጠን ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ ከባንኩ ዓመታዊ የሒሳብ ሪፖርት መገንዘብ እንደሚቻለውም በዓመቱ ውስጥ ፋይናንስ ያደረገው 4.22 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህ የብድር መጠን ከቀዳሚው ዓመት በ187 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

አቢሲኒያ ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ከቀደሙት ዓመታት ብልጫ ያሳየበት ሌላው አፈጻጸሙ አጠቃላይ ከወለድ ነፃ አስቀማጮችን ቁጥር በቀደመው ዓመት ከነበረበት በ55 በመቶ በማሳደግ 1.55 ሚሊዮን አሰቀማጮች ማግኘት መቻሉ ነው፡፡ ይህም ባንኩ ካሉት ጠቅላላ አስቀማጮች ውስጥ ከወለድ ነፃ አስቀማጮች ቁጥር 15 በመቶ እንዲይዝ አስችሎታል፡፡

ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ አጠቃላይ ገቢውን በ35.94 በመቶ በማሳደግ 22.73 ቢሊዮን ብር ማግኘቱንም ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡ ጠቅላላ ወጪው ደግሞ በ45.1 በመቶ ጨምሮ 17.5 ቢሊዮን ብር መድረሱም በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡  

ከባንኩ ጠቅላላ ገቢ ውስጥ ከብድር ወለድ የተገኘው ገቢ 20.96 ቢሊዮን ብር ድርሻ ሲይዝ፣ ከዚህ ውስጥ የወለድ ወጪው ሲቀነስ ከብድር ወለድ የተጣራ 14.82 ቢሊዮን ብር ማሰባሰብ መቻሉንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ሌላው ከፍተኛ ገቢ ሲገኝበት የነበረው የአገልግሎትና የኮሚሽን ገቢ ማለትም፣ ከወጪ አገር ምንዛሪ ተመን ለውጥ የተገኘ ትርፍ፣ ከአገልግሎት ገቢና ከኮሚሽን ያገኘው የተጣራ ገቢ በሒሳብ ዓመቱ እንደቀነሰ ከሪፖርቱ መረዳት ተችሏል፡፡ ከገልግሎትና ኮሚሽን በ2015 የሒሳብ ዓመት የተገኘው ገቢ 1.19 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ነገር ግን ከሌሎች ዓመታት በተለየ በ2015 የሒሳብ ዓመት የአገልግሎት ገቢው ከቀዳሚው ዓመት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ ባንኩ ከዚህ ዘርፍ በ2014 የሒሳብ ዓመት አግኝቶት የነበረው ገቢ 2.14 ቢሊዮን ብር እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከዚህ ዘርፍ የተገኘው ገቢ ለመቀነሱ በባንኩ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ መነጋገሪያ ሆኖም ነበር፡፡ ከዘርፉ ለተገኘው ገቢም ቅናሽ ሊመዘገብ የቻለበት ዋነኛ ምክንያት በሒሳብ ዓመቱ ባንኩ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ ከመቀነሱ ጋር የተያያዘ ነው፡፡

የቦርድ ሊቀመንበሩ ሪፖርት ላይም ባንኩ ከሌሎች አፈጻጸሞቹ በተለየ ከዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ቅናሽ አሳይቷል ብለዋል፡፡

ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ከዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት ያገኘው የውጭ ምንዛሪ መጠን 457.87 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ይህ ገቢ በምን ያህል ቅናሽ እንዳሳየ የቦርድ ሊቀመንበሩ በሪፖርታቸው ባይጠቅሱም፣ የባንኩ የ2014 የሒሳብ ዓመት ያገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ 674.64 ሚሊዮን ዶላር በመሆኑ የ2015 ያገኘው ገቢ ከ217 ሚሊዮን ዶላር በላይ ቅናሽ ያሳየ ስለመሆኑ መገንዘብ ይቻላል፡፡

ሆኖም ባንኩ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን ለማሳደግ ከዓለም አቀፍ የንግድ አጋሮቹ ጋር ግንኙነትን በማጠናከር፣ የዓለም አቀፍ ካርዶች ተጠቃሚ ደንበኞቹን ቁጥር በመጨመርና የአገልግሎቱ ጥራቱን በማሻሻል የሚያደርገውን ጥረት በሙሉ አቅሙ አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፤›› በማለት የቦርድ ሊቀመንበሩ አስታውቀዋል፡፡

በርካታ ተግዳሮቶች በነበሩበት የ2015 የሒሳብ ዓመት ውስብስብ ተግዳሮቶችን በመቋቋም በአጠቃላይ ሀብት፣ በተቀማጭ ገንዘብና በአጠቃላይ ገቢ፣ ቅርንጫፍ በማስፋፋትና በደንበኞች ቁጥር ጭማሪ አበረታች የሆኑ ውጤቶች ስለመሰብሰባቸው የቦርድ ሊቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡

ትርፋማ ሆኖ ለመቀጠልም የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ማድረጋቸውን የገለጹት አቶ መኮንን፣ በሒሳብ ዓመቱ ከታክስ በኋላ ያስመዘገበው ትርፍ 3.87 ቢሊዮን ብር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በ2014 ከታክስ በኋላ ያገኘው ትርፍ 3.23 ቢሊዮን ብር እንደነበር ይታወሳል፡፡

ይህ የትርፍ ምጣኔ ለባንኩ ባለአክሲዮኖች በአንድ አክሲዮን 39 በመቶ የትርፍ ድርሻ አስገኝቷል፡፡ በቀዳሚው ዓመት አንድ አክሲዮን አስገኝቶ የነበረው ትርፍ ድርሻ 57 በመቶ ነበር፡፡

ባንኩ እያካሄዳቸው ያሉ የሕንፃ ግንባታዎችን በተመለከተ በአዲስ አበባ ከተማ ሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ የሚገኘው የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ በዋናነት ተጠቅሷል፡፡ ግንባታ ደረጃውን በተመለከተ የቦርድ ሊቀመንበሩ እንደገለጹት፣ የዋናው ታወር (ብሎክ A) የአፈር ቁፋሮ ሥራ ተከናውኖ 40 በመቶ የአፈር ድጋፍ ግንብ ፓይል ሥራና የተቋራጩ ቢሮ ሥራ ተሠርቶ ተጠናቋል፡፡

ይህ የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ 60 ወለሎች ያሉትና በ9,763 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚገነባ ነው፡፡ የዚህ ሕንፃ ግንባታ አጠቃላይ ወጪ ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚሆን የግንባታ ሥራውን ለማከናወን ከተቋራጩ ጋር ስምምነት በተደረሰበት ወቅት መገለጹ አይዘነጋም፡፡

አቢሲኒያ ባንክ ከ11,508 በላይ ሠራተኞች ያሉት ነው፡፡ በመላ አገሪቱ ከ864 በላይ ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን፣ በ2015 ብቻ 123 ቅርንጫፎችን ከፍቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች