Friday, March 1, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኅብረት ባንክ አጠቃላይ ሀብቱን 83 ቢሊዮን ብር አደረሰ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከ25 ዓመታት በፊት በ20 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመው ኅብረት ባንክ፣ በ25ኛ ዓመቱ ላይ የባንኩን አጠቃላይ የሀብት መጠን ከ83 ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ መቻሉ ተገለጸ፡፡

የባንኩን 25 ዓመት ኢዮቤልዩ ክብረ በዓል ትናንት ኅዳር 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ ባደረገበት ፕሮግራም ላይ እንደተገለጸው፣ በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ የሀብት መጠኑን 83 ቢሊዮን ብር በማድረስ በሀብት ምጣኔያቸው ቀዳሚ ከሚባሉ የግል ባንኮች መካከል አንዱ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

የኅብረት ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ከበደ፣ የባንኩን 25ኛ ዓመት ክብረ በዓል አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፣ በ20 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተመሠረተው ኅብረት ባንክ፣ በአሁኑ ወቅት የተከፈለ ካፒታሉን አምስት ቢሊዮን ብር ማድረሱንና የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ መጠንም ከ64 ቢሊዮን ብር በላይ መሻገሩን አመልክተዋል፡፡

ከሃያ አምስት ዓመት በፊት ባንኩ ሥራ በጀመረበት ዓመት የነበረው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 40 ሚሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ አሁን ላይ 64.54 ቢሊዮን ብር መድረሱ ባንኩ ያሳያውን ዕድገት እንደሚያመላክት ጠቁመዋል፡፡   

አጠቃላይ የብድር ክምችቱም ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ የደረሰ ሲሆን፣ ባንኩ በ25 ዓመታት ጉዞው በየዓመቱ ከ25 እስከ 30 በመቶ እያደገ ዛሬ ላይ የደረሰ መሆኑንም ዋና ሥራ አስፈጻሚ አስረድተዋል፡፡ አመራር በተለዋወጠ ቁጥር ባንኩ ዕድገቱን ይዞ መቀጠል መቻሉንም አመልክተዋል፡፡

ባለፉት 25 ዓመታት የባንክ አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ በየወቅቱ ዘመኑ የደረሰባችውን የባንክ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ፣ የቁጠባ ባህልን ለማሳደግና ለተለያዩ ተቋማት ፋይናንስ በማቅረብ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደነበረው የገለጹት አቶ መላኩ፣ ለኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪም የራሱ የሆኑ አበርክቶዎች እንደነበሩት ተናግረዋል፡፡  

ለአብነት ከጠቀሷቸው መካከል ለመጀመርያ ጊዜ የኢንተርኔትና የሞባይል ባንክ አገልግሎት በመጀመር ቀዳሚው ባንክ መሆኑን ነው፡፡ አሁን ሞባይል ባንክ የሚባለውን አገልግሎት ‹‹ኤስኤምኤስ›› ባንክ በሚል መጠሪያ በቀዳሚነት ማስጀመሩም በ25 ዓመቱ ታሪኩ ሊጠቀስ የሚችል ተግባሩ ነው ብለዋል፡፡

አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ከማስፋፋት ባሻገር በውስጥ አቅም በማልማት፣ እንዲሁም የኮር ባንኪንግና የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎቶችን በማዘመን በዘርፉ ዓይነተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት እንደቻለ የገለጹት ሥራ አስፈጻሚው፣ ይህም ከራሱ አልፎ በቴክኖሎጂ የዕውቀት ሽግግር ለሌሎች ባንኮች ልምድ ማከካፈል ጭምር እንዳስቻለው ተናግረዋል፡፡ በራስ ኃይል የሠራቸውና ያበለፀጋቸውን የተለያዩ ባንክ ቴክኖሎጂ ሲስተሞችን ለመጠቀም፣ ከሦስት ባንኮች ጋር ስምምነት በመፈጸም የጀመረው ሥራ ባንኩ በቴክኖሎጂ ረገድ የደረሰበትን ደረጃ ያሳያልም ተብሏል፡፡

ከውጭ ባንኮች ጋር ሊኖረው ከሚችለው ውድድር አንፃርም ባንኩ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ እንደሆነ የገለጹት የባንኩ ኃላፊዎች፣ በተለይ ከቴክኖሎጂ ጋር የተገናኙ የባንክ አገልግሎቶች ላይ ብቁ ተወዳዳሪ ሊሆን የሚችልበትን መሠረት ስለመጣሉ አመልክተዋል፡፡   

የባንኩ 25ኛ ዓመት አስመልክቶ የመክፈቻ ፕሮግሙን ያስጀመሩት የኅብት ባንክ ዳይሬከተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ሳምራዊት ጌታመሳይ (ኢንጂነር)፣ በበኩላቸው ባንኩ በተመሠረተበት ወቅት አንግቦ የተነሳበትን ዓላማ መሥራት ላይ በመዋል፣ የሁሉንም የአገሪቱ ክፍል ማኅበረሰብ የሚያገለገልበትና የሚሠራበት፣ እንዲሁም ያለ ምንም ልዩነት ሁሉንም በእኩልነት የሚያስተናግድ ባንክ ሆኖ፣ ዛሬ ላይ ሊደርስ መቻሉን ገልጸዋል፡፡ ለዚህም የ25 ዓመታት ያልተቋረጠ ዕድገት የባንኩ መሥራቾች ሊመሠገኑ ይገባል ብለዋል፡፡

ኅብረት ባንክ በኢትዮጵያ የግል ባንኮች ምሥረታ ታሪክ ግንባር ቀደም ከሆኑት የግል ባንኮች መካከል አንዱ ሲሆን በ1991 ዓ.ም. የተመሠረተ ነው፡፡

ባንኩ ከ25 ዓመት በፊት ሲመሠረት ስድስት አደራጆችን በመያዝ ሲሆን፣ በዋናነት የሚጠቀሱት ደግሞ ታዋቂው የኢንሹራንስ ባለሙያ አቶ እየሱስ ወርቅ ዛፉና ታዋቂው ነጋዴና የአማልጋሜድ ሊሚትድ ባለቤት አቶ ገብረየስ ቤኛ ናቸው፡፡ ከተቋማት ደግሞ ኅብረት ኢንሹራንስ ይህንን ባንክ በመፍጠርና ዋነኛ ባለድርሻ በመሆን ተጠቃሽ ነው፡፡

በአንድ ቅርንጫፍና በጥቂት ሠራተኞች ሥራ የጀመረው ኅብረት ባንክ፣ በአሁኑ ወቅት 8,840 ሠራተኞችና ከ475 በላይ ቅርንጫፎች አሉት፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች