Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየባህር በር ጉዳይ እንደ ማዕዘን ድንጋይ

የባህር በር ጉዳይ እንደ ማዕዘን ድንጋይ

ቀን:

በደምሰው በንቲ

ወደብ አልባ የሆነች ወይም የባህር በር የሌላት አገር ማለት ከውቅያኖስ ጋር የተገናኘ ክልል የሌላት ወይም የባህር ዳርቻ የሌላት አገር ናት፡፡ በአሁኑ ወቅት 44 ወደብ የሌላቸው አገሮችና በከፊል ተለይተው የሚታወቁ የመሬት አቀማመጥ ያላቸው ግዛቶች አሉ፡፡ ካዛኪስታን በዓለም ትልቋ ወደብ አልባ አገር ናት፡፡ በዓለም በትልቅነቷ ዘጠነኛ የሆነችው ይህች አገር የሕዝቦቿ ቁጥር ግን 19 ሚሊዮን ነው፡፡ ኢትዮጵያ የ106 ሚሊዮን ሕዝብ  ቁጥር ብልጫ እንዳላት በህሊናችን ይዘን ንባባችንን እንቀጥል፡፡

በአፍሪካ ሩዋንዳ፣ ዛምቢያ፣ ዚምባብዌ፣ ማላዊ፣ ቦትስዋና፣ ኡጋንዳ፣ ኒጀር፣ ማሊ፣ ኢትዮጵያና ቡሩንዲ የባህር በር ከሌላቸው አገሮች ተርታ የሚመደቡ ናቸው፡፡ ታድያ የእነዚህ አገሮች የሕዝብ ቁጥር ከኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር አንፃር ሲታይ፣ የኢትዮጵያ የስድስት አገሮችን ሕዝብ ቁጥር የሚተካከል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እ.ኤ.አ. በ1990 በዓለም ውስጥ 30 ወደብ የሌላቸው አገሮች ብቻ ነበሩ፡፡ የዩጎዝላቪያ መበታተን፣ የሶቪየት ኅብረትና የቼኮዝሎቫኪያ ብተናዎች፣ የደቡብ ኦሴቲያ ምሥረታ፣ የኤርትራ መገንጠል፣ የሞንቴኔግሮ፣ የደቡብ ሱዳንና የሉሃንስክ ሕዝብ የነፃነት ምርጫዎች፣ የኮሶቮና የዶኔትስክ ሕዝብ ሪፐብሊክ አገር ነን መግለጫዎች 15 አዳዲስ የመሬት አቀማመጥ ያላቸውን አገሮችና በከፊል ዕውቅና ያገኙ አገሮችን እ.ኤ.አ. በ1993 ፈጥረዋል፡፡

በአውሮፓ ውስጥ አንዳንድ ወደብ አልባ አገሮች እንደ አንዶራ፣ ኦስትሪያ፣ ሊቼንስተንቲን፣ ሉክሰምበርግ፣ ሳን ማሪኖ፣ ስዊዘርላንድና ቫቲካን ሲቲ ያሉ ሲሆን በአፍሪካ፣ በእስያና በደቡብ አሜሪካ ውስጥ ያሉ መሬቶችን በሙሉ ጨምሮ ከ44 ወደብ አልባ አገሮች ውስጥ 32 ያህል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደ ወደብ አልባ ታዳጊ አገሮች ተመድበዋል፡፡

ወደብ አልባ አገር መሆን ለአንድ አገር ልማትና ዕድገት እንቅፋት ነው፡፡ ለዓሳ ዕርባታ፣ የባህር ላይ ንግድ ለማከናወን፣ ፀጥታን በአስተማማኝ መሠረት ላይ ለመትከል፣ ከማዕድን ምርቶች ለመቋደስና የሥራ ዕድልን በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡

በአንፃራዊነት ሲታይም የባህር ዳርቻዎች ያሏቸው ወይም የዓለም ውቅያኖስ መዳረሻ ያላቸው የውቅያኖስ ክልሎች፣ የዓለም ውቅያኖስ መዳረሻ ከሌላቸው ከባቢዎች እጅግ በጣም የተሻለ ሀብት አላቸው፡፡ ወደብ አልባ ታዳጊ አገሮች የባህር ዳርቻ ካላቸው ታዳጊ አገሮች ጋር ሲነፃፀሩ በዓለም አቀፍ የጭነት መጓጓዣ ወጪዎች ከፍተኛ ወጪ አለባቸው፡፡  

አገሮች ወደ ባህር የሚደርስ መሬት ለማግኘትና ጥቅማቸውን ማስከበር እንደቻሉ ማሳያዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ እ.ኤ.አ. በ1885 በበርሊን ኮንፈረንስ ከባህር ጋር ለማገናኘት በአንጎላ በኩል ጠባብ የሆነ የመሬት ቁራጭ አግኝታለች፡፡

ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በቨርሳይለስ ስምምነት ውስጥ “የፖላንድ ኮሪደር” ተብሎ የተሰየመ የባህር ወሽመጥ፣ በባልቲክ ባህር ወደ ጀርመን ለመድረስ ለፖላንድ ሪፐብሊክ  ተሰጥቷል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2005 ከዩክሬን ጋር በተደረገው የመሬት ልውውጥ ምክንያት ሞልዶቫ የዳኑብ 600 ሜትር (650 ያርድ) ዓለም አቀፍ የውኃ መንገድ እንድታገኝና የጊርጊሊቲ ወደብ እዚያው እንድትገነባ ሆኗል፡፡

ዳኑብ ዓለም አቀፍ የውኃ መንገድ ነው፡፡ እናም ኦስትሪያ፣ ሃንጋሪ፣ ሞልዶቫ፣ ሰርቢያ፣ ስሎቫኪያ የጥቁር ባህር ደኅንነቱ የተጠበቀ መዳረሻ አላቸው (ምንም እንኳን ጀርመንና ክሮሺያ መሬት ላይ ባይያዙም) ተመሳሳይ መዳረሻ ለጀርመንና ለክሮሺያ የውስጥ ክፍሎች ተሰጥቷል፡፡  

ወደ አገራችን ነባራዊ ሀቅ ስንመለስ የፖለቲካ ሴራዎች በፈጠሯቸው ሽንቁሮች ሳቢያ የ30 ዓመቱ የኤርትራ የነፃነት ጦርነት ኤርትራ እንድትገነጠል አድርጓል፡፡ የኤርትራ ነፃነት እ.ኤ.አ. በ1991 ሲረጋገጥ ኢትዮጵያ የተቆለፈባት አገር ሆናለች፡፡

ለምፅዋና ለአሰብ ወደቦች ብቻ ሳይሆን ለከተማዎቹም ግርማና ሞገስ የነበሩት የኢትዮጵያ መርከቦች፣ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገሮች የራሳቸውን አገር ባንዲራ እያውለበለቡ በቀጣናው በብቸኝነትና በኩራት የሚያገለግሉ ቢሆንም ቤታቸው ተቆልፎ በጎረቤት አገሮችና በውጭ አገር የወደብ መዳረሻዎች ይንከራተታሉ፡፡

የመርከቦቻችን መጠጊያ ማጣት፣ የወደብ አገልግሎት ወጪ፣ ለዘላቂና ለአስተማማኝ ሰላም መረጋገጥ ለወደብ አገልግሎት ለምናወጣው ከፍተኛ ነዋይ ብቻ ሳይሆን ትውልዱ ከባህርና ከወደብ አገልግሎቶች ጋር ተያይዞ ሊፈጠሩ የሚችሉ የሥራ ዕድሎችን እንዳያይ በር ተዘግቶበት ራዕይ እንዳይኖረው ሆኗል፡፡

ለምሳሌ በዓለም አቀፍ የንግድ መርከቦች የሚያገለግሉ መርከበኞች ብዛት አንድ ሚሊዮን 892 ሺሕ 720  ሲገመት ከእነዚህም 857 ሺሕ 540 ያህሉ ኦፊሰሮችና አንድ ሚሊዮን 35 ሺሕ 180 ባለ ደረጃዎች ናቸው። የዓለም አቀፍ የመኮንኖች አቅርቦት በየጊዜው እየጨመረ እንደሚሄድ ሲተነብይ ይህ አዝማሚያ ፍላጎትን በመጨመር ይበልጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በአገር ደረጃ ለይተን የተመለከትን እንደሆነ የፊሊፒንስ እ.ኤ.አ. የ2023 የሕዝብ ብዛት በዓመቱ አጋማሽ ላይ 117 ሚሊዮን 337 ሺሕ 368 ሆኖ ይገመታል። የፊሊፒንስ ሕዝብ ከጠቅላላው የዓለም ሕዝብ 1.46 በመቶ ጋር እኩል ሲሆን ባለፉት ዓመታት ፊሊፒንስ ባህረኞችን ለዓለም አቀፍ ገበያ በማቅረብ ረገድ ከዋና አቅራቢዎች መካከል አንዱ ሆና ቆይታለች። አገሪተዋ ከ2017 ጀምሮ በየዓመቱ ከ400,000 በላይ መርከበኞችን በማሠማራት ላይ ትገኛለች፡፡ ይህ ቁጥር እ.ኤ.አ. በ2019 እስከ 507,730 ደርሶ ነበር።

በብዝኃኑ የባህር ትራንስፖርት አገልግሎት መርከብ ላይ ከሚሠሩ ባህረኞች መካከል ከአራትና አምስት ሠራተኞች መካከል አንድ ፊሊፒናዊ ባህረኛ እንዳለ ይገመታል። በውጭ አገር ተቀጥረው ከሚሠሩት ባህረኞች ወደ አገር ውስጥ የሚላከው ገንዘብ (ሬሚታንስ) ቢያንስ 22 በመቶ የሚሆነውን የዶላር OFW መላኪያ ይይዛል።

ሁለተኛዋ ምሳሌያችን ከፊሊፒንስ ቀጥላ በርካታ ቁጥር ያላቸው ባህረኞችን ለዓለም በማበርከት የምትታወቀው ህንድ ናት፡፡ የወቅቱ የህንድ ሕዝብ ቁጥር 1,428,627,663 ሆኖ ይገመታል። የህንድ ሕዝብ ከጠቅላላው የዓለም ሕዝብ 17.76 በመቶ ጋር እኩል ነው።

እ.ኤ.አ. በ2022 ከ250 ሺሕ በላይ የህንድ ባህረኞች በአገር ውስጥ ወይም በውጭ መርከቦች ላይ ተቀጥረዋል፡፡ ታዲያ ይህ ከፍተኛ ቁጥር ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪን ከማስገኘት አኳያ ያለው ድርሻ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡

የዓለም ሕዝብ ቁጥር 8.1 ቢሊዮን ሲሆን የኢትዮጵያ የ2023 ዓ.ም. የሕዝብ ብዛት 126 ሚሊዮን 527 ሺሕ 060 ሆኖ ይገመታል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጠቅላላው የዓለም ሕዝብ 1.57 በመቶ ጋር እኩል ነው። ይሁንና ኢትዮጵያ ካላት የሕዝብ ቁጥር አኳያ በዓለም የባህር አገልግሎት ላይ ተሠማርቶ የሚገኘው የባህረኛ ቁጥር ከሕዝብ ቁጥር ድርሻ ጋር ሲመዘን 0.000375 ወይም በቁጥር 7‚500 ብቻ ሲሆን ሊሳተፍ ይገባ ከነበረውና ለአገሪቱ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ሊፈጥር ይገባው የነበረው በአማካይ ሲታይ ቢያንስ  እስከ 100 ሺሕ ሊደርስ በተገባው ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ትውልዱ በባህር ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ዙሪያ ገባው የተከረቸመበት በመሆኑ ዕይታው ተጋርዶበት ራዕዩ ተነጥቋል፡፡ በአገሪቱ ውስጥ የገዘፈ ሚና ሊጫወቱ ይችሉ የነበሩ ሁለት የማሪታይም አካዳሚዎች ቢኖሩም አካዴሚዎቹ ሊያሠለጥኑት ከሚያቅዱት አንፃር ሲታይ ማሠልጠኛ ማዕከል ስለመኖሩና ዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ዕድል ስለመኖሩ እንኳ ግንዛቤ ያለው ዜጋ ቁጥር ውስን ነው ብቻ ሳይሆን ከአገሪቱ ሕዝብ ቁጥር አንፃር ከዜሮ በታች ነው፡፡

ኢትዮጵያ ዕምቅ አቅም አላቸው ስትል በብሉ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ንዑስ ዘርፎችና በብሔራዊ ብሉ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ላይ አፅንኦት የሰጠችባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ እነዚህም ዓሳና አኳካልቸር፣ ቱሪዝም፣ ኢነርጂ፣ ማዕድን (ጨው፣ አሸዋ፣ ሶዳ፣ ኖራ)፣ የአገር ውስጥ ውኃ ትራንስፖርት ለማስፋትና የባህር ማጓጓዣና ተዛማጅ አገልግሎቶች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ የባህር ዘርፍ ማደግ፣ እናም አቅም መጨመር ለዕድገቷ ወሳኝ ነው ሲል የብሉ ኢኮኖሚው ስትራቴጂ ይዳስሳል። የዕቃ ማጓጓዣ መርከቦችን ቁጥር ለማሳደግ፣ የመርከብ ዕቃዎችን በማምረትና የመርከብ ጥገናን፣ እንዲሁም እንደ አዲስ የንግድ መስመሮችን የመጠገንና የማሳደግ አቅምንም እንደሚጨምር ስትራቴጂው ይዳስሳል።

በምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኘው ባሮ ወንዝ የደቡብ ሱዳንን ሕዝብ በውኃ ትራንስፖርት አማካይነት ከኢትዮጵያ ጋር የሚያገናኝ ሲሆን፣ ኬንያውያን የቱርካና ሐይቅን በመጠቀም በውኃ ትራንስፖርት ሸቀጦችን በመለዋወጥ ከኢትዮጵያ የሚመረተውን ዓሳ እየወሰዱ ነው። የብሉ ኢኮኖሚ ስትራቴጂው ከባህር በር (ከቀይ ባህር) ጋር በተያያዘ በሰነዱ ላይ ያስቀመጠው ባይኖርም፣ ዕድሉ እስከ ተገኘ ጊዜ ድረስ ግን በተዳባይነት እንዳይሠራ አይከለክልምና ሌላውንም ዕድል እንመልከት፡፡

ከላይ እንደተጠቀሰው በባሮ ወንዝና በቱርካና ሐይቅ አማካይነት ከደቡብ ሱዳንና ከኬንያ ጋር እያደረግናቸው ያሉ የንግድ ግንኙነቶች ቀይ ባህር በአፍሪቃና በእስያ መካከል የሚገኝ ረጅም ባህረ ሰላጤ እንደመሆኑ ኢትዮጵያ ቀይ ባህርን ከሚቋደሱ የምሥራቅ አፍሪካ፣ የሰሜን አፍሪካና የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች በመዘርጋት ንግድን፣ ባህልንና በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ማኅበራዊ መስተጋብሮቿን ልታሰፋ የምትችልበት ዕድል ዝግ አይደለም፡፡

ሲጠቃለል የባህር በር ጉዳይ የወጭ ገቢ ንግዱን በውጤታማነትና በአስተማማኝነት ለመምራት፣ የማዕድን ሀብቶችን ለመጠቀም፣ በርካታ ቁጥር ላላቸው ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ በቀጣናው አስተማማኝ ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ፣ የዓሳ ምርቶችን ለመጠቀም፣ አገሪቱ ለወደብ የምታወጣቸውን ክፍያዎች ለማዳን፣ በባህር አገልግሎት አሰጣጥ የጎለበተ ዕውቀት፣ ፍላጎትና ራዕይ ያለው ትውልድ በመፍጠር ራሱንና አገሪቱን የሚጠቅም ዜጋ ለማፍራት፣ የመርከብ ጥገናና ግንባታ መሠረተ ልማቶችን ዘርግቶ የገቢ ምንጭ ለመፍጠር፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችንና ማኅበራዊ መስተጋብሮችን ለማስፋት፣ ብሎም የታላቂቱን ኢትዮጵያ ቅድመ ታሪክ መልሶ ለመገንባት የባህር በር እንደ ማዕዘን ድንጋይ አስፈላጊና ዋልታ ጉዳይ  ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው kerawud2016@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...