Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየአማራ ክልል አርሶ አደሮች ለምርታቸው ገበያ ማጣታቸው የፌዴራል አዋጅ እንዲጣስ ማስገደዱ በጥናት...

የአማራ ክልል አርሶ አደሮች ለምርታቸው ገበያ ማጣታቸው የፌዴራል አዋጅ እንዲጣስ ማስገደዱ በጥናት ተገለጸ

ቀን:

በናርዶስ ዮሴፍ 

የአማራ ክልል አርሶ አደሮች የሁለት ሚሊዮን ኩንታል አኩሪ አተር የገበያ ዕጦት ችግር፣ የፌዴራል የጥሬ ዕቃ ንግድ አዋጅን የሚጥስ ክልላዊ መመርያ ተግባራዊ እንዲደረግ ማስገደዱ በጥናት ቀረበ።

ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት በ340 ሺሕ ሔክታር መሬት ካመረተችው 7.9 ሚሊዮን ኩንታል አኩሪ አተር ውስጥ በ240 ሺሕ ሔክታር መሬት ስድስት ሚሊዮን ኩንታል የተመረተው በአማራ ክልል መሆኑን፣ የኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት አዲስ ጥናት አመላክቷል። 

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከስድስት ሚሊዮን ኩንታል አኩሪ አተር ውስጥ ሦስት ሚሊዮን ያህሉ ለውጭ ገበያ የቀረበ መሆኑን፣ የተቀረው ሦስት ሚሊዮን ኩንታል ግን ገበያ ጠፍቶ የአርሶ አደሩና የክልሉ ራስ ምታት ወደ መሆን መሸጋገሩ በጥናቱ ተገልጿል። 

የመተማ ኅብረት ሥራ ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አርሶ አደር ሀብታሙ ዘውዴ፣ ‹‹ትልቁ ችግራችን የዋጋ ማሽቆልቆል ነው። ምርቱን በ2013 እና በ2014 ዓ.ም. ስንሸጥ ከነበረበት በኩንታል አምስት ሺሕ ብር ባለፈው ዓመት እስከ ሁለት ሺሕ ብር ወርዶ ነበር፤›› ብለዋል። 

በአማራ ክልል አዊ ዞንና መተማ ብቻ በ2015 ዓ.ም. 135 ሺሕ ሔክታር ታርሶ 2.1 ሚሊዮን ኩንታል አኩሪ አተር ቢሰበሰብም፣ ከ70 በመቶ በላይ ምርት የገበያ ዕጦት እንደገጠመው ገልጸዋል። 

ከአርማጭሆ የመጡ አርሶ አደር አላምረው ሁሴን ደግሞ፣ ‹‹ለማምረት 2,500 ብር አውጥተንበት 1,400 ብር እየሸጥን ነው፤›› ብለዋል።

የምግብ ዘይት አቀነባባሪዎች ኢንዱስትሪ ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አዲሴ ጋርኬቦ የገበያ ዕጦት ችግር እንዲፈጠር ያደረገው፣ የኢትዮጵያ የምርት ገበያ ከሐምሌ 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ በተደረገው የጥሬ ዕቃ አዋጅ 337/2013 የአኩሪ አተር ምርትን ራሱ ብቻ ከአርሶ አደሩ መግዛት እንዲችል በመደረጉ ነው ብለዋል። 

‹‹ለምሳሌ ምርት ገበያው በቀን 100 ኩንታል የሚያቀርብበት ጊዜ አለ። ይህ ደግሞ 30 የዘይት አቀነባባሪዎች ይቃመሱት ካልተባለ በቀር ለምርት በቂ አይደለም፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

የአማራ አርሶ አደሮች የገጠማቸውን ከሁለት ሚሊዮን ኩንታል በላይ የገበያ ዕጦት ችግር የመፍታት ግዴታ ጀርባው ላይ የወደቀው የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ በ2015 ዓ.ም. የፌዴራል አዋጅን የሚቃረን አሠራር ሥራ ላይ አውሏል ተብሏል። 

ይህም ክልሉ የአኩሪ አተር አቀነባባሪዎች ቀጥታ ምርቱን ከአርሶ አደሮች እንዲገዙ ማስቻሉን፣ በሌላ በኩል በድጎማ ግዥ ገበያውን ለማንሳት ሁለት ቢሊዮን ብር በጀት መለቀቁን የክልሉ ንግድ ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ ኢብራሂም መሐመድ (ዶ/ር) ተናግረዋል። 

‹‹የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በተመረተው ምርት መጠን የመንቀሳቀስ አቅም ሊያዳብር ይገባዋል፤›› ያሉት ኢብራሂም (ዶ/ር)፣ ‹‹ምርት ገበያው በ2015 ዓ.ም. መሸጥ የቻለው 121 ሺሕ ኩንታል ሲሆን፣ ክልሉ ግን በወሰዳቸው ዕርምጃዎች ምክንያት አንድ ሚሊዮን ኩንታል መሸጥ ተችሏል፤›› ብለዋል። 

አርሶ አደር ሀብታሙ በበኩላቸው፣ በክልሉ የተመደበው ሁለት ቢሊዮን ብር ድጎማ አርሶ አደሩ ምርቱን በርካሽ ዋጋ ከሸጠ በኋላ ነበር የደረሰው ሲሉ ተናግረዋል። የገበያ ማሽቆሉቆሉን በተመለከተም በዓመቱ መጀመሪያ ላይ ‹‹ኩንታሉን 3,500 ብር ተለምኖ ነበር የሚገዛው፤›› በማለት፣ አሁን ዋጋው በኩንታል 3,000 ብር ላይ መቆሙን አስረድተዋል፡፡

በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የተሠራው የአኩሪ አተር ገበያ ትስስር ጥናት፣ አሁን ባለው ሁኔታ አኩሪ አተር ተመርቶና በአቀነባባሪ ኢንዱስትሪው በኩል አልፎ ተጠቃሚዎች ዘንድ እስኪቀርብ ድረስ ባለው ሒደት ውስጥ ካሉ አካላት ሁሉ ትልቁን ወጪ የሚያወጣው አርሶ አደሩ መሆኑን ድምዳሜ ላይ ደርሷል። 

ጥናቱ አርሶ አደሩ በስድስት ዋና ዋና ጉዳዮች ምክንያት የሚደርስበት ጉዳት ዘርዝሯል። ተቀዳሚው ምክንያት ምርቱን የሚያከማችበት ሥፍራ ወይም ጎተራ ከሚፈለገው የጥራት ደረጃ ያነሰ መሆኑ፣ አርሶ አደሩ በቀጥታ ለአቀነባባሪ ኢንዱስትሪው እንዳይሸጥ የሚከለክሉ መመርያዎች፣ ለአርሶ አደሩ በተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት የሚፈቀድ ወይም ማግኘት የሚችለው የመሥሪያ ገንዘብ (Working Capital) የማግኘት ዕድሉ እጅግ በጣም ውስን መሆንም ተጠቅሰዋል፡፡

በተለይ በኅብረት ሥራ ማኅበር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ አርሶ አደሮች ምርቱን ካቀረቡበት ክፍያ እስከሚቀበሉበት ድረስ ባለው የተራዘመና የተለጠጠ የጊዜ ርዝመት ያለው የገንዘብ አከፋፈል ሒደት፣ በአርሶ አደሩ ምርቱ ሙሉ ለሙሉ የታወቀና ሥራ ላይ ያለ የሽያጭ የደረጃ ቁጥጥር ወይም አሠራር አለመኖር፣ እንዲሁም ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ገበያ የሚያቀርበው ገዥ ለአርሶ አደሩ ምርት የሚያቀርበው ዋጋ መዋዠቅ ችግሮች የአርሶ አደሩን ጉዳት እንዲባባስ ያደርጋሉ ተብለው በጥናቱ ከተጠቀሱት ዋና ዋናዎቹ ናቸው። 

የመተማ ኅብረት ሥራ ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሀብታሙ፣ ‹‹ማኅበራት ምርቱን ከአርሶ አደሮች የመግዛት ፍላጎት ቢኖረንም ከፍተኛ የፋይናንስ እጥረት አለብን፤›› ብለዋል። 

የክልሉ ንግድ ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ በበኩላቸው፣ ባንኮች ብድር ሲሰጡ የኅብረት ሥራ ማኅበራትን በዓመቱ መጨረሻ ላይ እንደሚያስተናግዱ ግልጽ ምላሽ ሊሰጡ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የአቅርቦት ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ማሞ፣ የግብርናው ዘርፍ ለፋይናንስ ትንበያ የማይመችና አብዛኛውን ጊዜም የተበላሹ ብድሮችን አብዛኛውን ክፍል የሚይዝ በመሆኑ ምክንያት ብድር በሚገባ ማቅረብ እንዳይቻል አድርጓል ብለዋል።

ከአራት ዓመታት በፊት ባንኩ የመዘጋት ዕጣ ፈንታ ተጋርጦበት የነበረው ለግብርናው ዘርፍ አቅርቧቸው በተበላሹ ብድሮች ምክንያት መሆኑን ገልጸው፣ አሁንም ባንኩ ካለው አጠቃላይ የተበላሸ 11 ቢሊዮን ብር ብድር ውስጥ 84 በመቶ የግብርናው ዘርፍ መሆኑን አስረድተዋል። 

በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጥናት መሠረት በአርሶ አደሩ ዘንድ እንደ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ያሉ ግብዓቶች እጥረት ሲኖር፣ ደረጃውን የጠበቀ የአኩሪ አተር ምርት ክምችትና አያያዝን በተመለከተ የዕውቀት ማነስ አለ። 

የምርት ጥራት ለማሳደግ ቁልፍ የሆኑ የእርሻ ማሽኖች፣ ግብዓቶችና በሰብል ስብሰባ ወቅት ብክነትን በከፍተኛ ደረጃ ዝቅ ለማድረግ አስፈላጊ መሣሪያዎች አለመኖር በጥናቱ የቀረበ ሲሆን፣ እነዚህ ችግሮች በከፍተኛ ደረጃ ምርቱ ለቤት ውስጥ ጥቅም እንዲውል ማስገደዳቸው ተገልጿል። 

ጥናቱ እንደሚያሳየው በ2015 ዓ.ም. በአማራ ክልል በመኸር ወቅት ብቻ 23 በመቶ የሚሆነው ምርት ጥራቱ ወርዶ ለገበያ መቅረብ አልቻለም፡፡ ከዚህ ውስጥ 18.4 በመቶ የሚሆነው በሰብል ስብሰባ ወቅት የሚከሰት ብክነት ሲሆን፣ በዓለም ቀዳሚ የአኩሪ አተር ምርት አቅራቢ የሆነችው ህንድ የመኸር ብክነቷ 13 በመቶ ብቻ ነው ተብሏል።

አርሶ አደሩ በቀጥታ ለማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች እንዲሸጥ ባለመፈቀዱና ገበያ በማጣቱ፣ በቤት ውስጥ እንዲጠቀም በመገደዱና የምርቱ ተፈላጊነት ባለመኖሩ ምክንያት ከአጠቃላይ ምርቱ ለገበያ ያልቀረበው በ2011 ዓ.ም. 32 በመቶ የነበረ መሆኑን፣ በየዓመቱ መዋዠቆችን እያሳየ በ2014 ዓ.ም. ዝቅተኛ ሆኖ የተመዘገበው 21.9 በመቶ ደርሶ፣ በ2015 ዓ.ም. እንደገና ከፍ ብሎ 29.49 በመቶ ስለመሆኑ በጥናቱ ተመላክቷል፡፡ 

የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጥናት ችግሮቹን ለመፍታት ሦስት ዋና ዋና የመፍትሔ ሐሳቦችን አስቀምጧል። እነዚህም አንደኛ የኮንትራት እርሻ (Contract Farming)፣ ሁለተኛ ተዘዋዋሪ ፈንድ፣ ሦስተኛ ደግሞ የመጋዘን ደረሰኝ አሠራር (Warehouse Receipt System) ተግባራዊነት ናቸው። ከሁሉም መካከል ቁልፍ መፍትሔ ተደርጎ የተቀመጠው የኮንትራት እርሻ (contract farming) ነው። 

የኮንትራት እርሻ አሠራር አርሶ አደሮች ምርታቸውን ከሚፈልጉ አቀነባባሪዎች ጋር አስቀድመው ውል ሲፈጽሙ፣ ምርቱን የሚገዙ አቀነባባሪዎች ለአርሶ አደሮቹ አስፈላጊ የሆኑትን እንደ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ያሉ ግብዓቶችን ለማቅረብ የሚስማሙበት ሲሆን፣ በሚገዙት መጠንም ለአርሶ አደሮቹ ግብዓቶቹን በማቅረብ የሚያግዙበት፣ በቅድሚያ በተስማሙበት ዋጋ መሠረት የገበያ ትስስርን ያስቀደመ የእርሻ አሠራር ሒደት ነው። 

በጥናቱ እንደተገለጸው በማምረት ሒደት የሚባክነውን በማስቀረትም ሆነ ቤት ውስጥ ጥቅም ላይ ውሎ የሚቀረውን መሸጥ የሚቻል የምርት መጠን ጥራት በማሳደግ፣ የአርሶ አደሩን የገበያ ዕጦት በመቅረፍና ችግሮችን በመፍታት ረገድ ዋነኛ መፍትሔ ነው ተብሏል። 

የኮንትራት እርሻ በተሳካ ሁኔታ ተግባራዊ ለመሆን የሚቻለው ግን ከእርሻ ወቅት ቀደም ብሎ ተፈጻሚ መሆን ከቻለ እንደሆነ፣ ይህንን አስመልክቶ መንግሥት መመርያዎችን በማውጣትና በማፅደቅ ለአርሶ አደሩም በማሳወቅ መሥራት ከተቻለ ብቻ እንደሆነ ጥናቱ ያመለክታል፡፡ 

የኮንትራት እርሻ ሊያልፍባቸው የሚገባ ሦስት ዋና ዋና ደረጃዎች አሉት ተብሏል። የመጀመርያው በሚመለከተው የመንግሥት አካል የስምምነት ሰነዱ እውነተኛነት መረጋገጥና መመዝገብ፣ አርሶ አደርና ገዥ በቅድሚያ ውሉን መፈራረምና በግብርና ሚኒስቴር ስምምነታቸውን ማስመዝገብ አለባቸው። ሁለተኛው ገዥው ውሉን ለሚፈጽመው አርሶ አደር የእርሻ ግብዓቶችንና አስፈላጊ የቴክኒክ ድጋፎችን ለማቅረብ መስማማት አለበት። ሦስተኛው ደግሞ ለገዥው የሚቀርበው ምርት ጥራት ተመርምሮ መረጋገጥ አለበት። ምርቱ ሲቀርብ ክፍያዎች ለሁሉም አካል ተፈጻሚ መደረግ ያለባቸው ሲሆን፣ ምርቱ ለገዥው መድረሱም መረጋገጥ አለበት የሚለውንም ያካትታል። 

በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጥናት መሠረት የአርሶ አደሩን ችግር ለመፍታት በመፍትሔነት የቀረበው ሌላው ሐሳብ ገንዘብ በብድር የሚቀርብበትና ተመልሶ የሚከፈልበት፣ የተከፈለው ገንዘብ በድጋሚ ለብድር የሚቀርብበት የተዘዋዋሪ ፈንድ ፋይናንስ አሠራርን ተግባራዊ ማድረግ ነው። 

በዚህም በገጠር የሚገኙ ትንሽ መሬትና የገንዘብ አቅም ያላቸውን አርሶ አደሮች በብድር የፋይናንስ አቅማቸውን በማሳደግ የማያቋርጥና ቀጣይነት ያለው የፋይናንስ ምንጭ እንዲኖራቸው በማድረግ፣ አርሶ አደሮቹ መልሰው በከፈሉት ገንዘብ መጠን ምርታቸውን ለማሳደግ ኢንቨስት ማድረግ እንደሚያስችላቸው ተጠቅሷል። ይህ ለአቅም ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ቢገለጽም የምርት ጥራት ደረጃን በማረጋገጥ በኩል ግን አናሳ ውጤት አለው ተብሏል። 

በመጨረሻ ደረጃ የቀረበው የመፍትሔ ሐሳብ የመጋዘን ደረሰኝ አሠራር (Warehouse Receipt System) አምራቾች ምርታቸውን ደረጃውን በጠበቀ መጋዘን በማስቀመጥ፣ ለአገልግሎት ተጠቃሚነታቸው ማረጋገጫ ሰነድ መቀበል የሚያስችል የመጋዘን አቅርቦት አገልግሎት አሠራር ነው። 

ይህም አርሶ አደሮች በምርት ክምችት አያያዝ ምክንያት የሚደርስባቸውን የምርት ብክነት እንደሚያስቀር፣ እንዲሁም አገልግሎቱን ከሽያጭ በኋላ መክፈል የሚያስችላቸውና ብድር የማግኘት አቅማቸውንም ከፍ ያደርጋል ተብሏል። በተጨማሪም በመኸር ወቅትና በኋላ የሚከሰቱ ብክነቶችንና የጥራት ችግሮችንም ያስቀራል ተብሎለታል። 

ዓላማውን ተፈጻሚ ለማድረግ ግን ይህንን አሠራር ፋይናንስ የማድረግ ፍላጎት ያላቸው ባንኮች ቁጥር እጅግ አናሳ መሆኑ ሲገለጽ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ መጋዘኖች እጥረትና አርሶ አደሮች መጋዘኖቹን ማግኘት የሚችሉበት ሥፍራ በአቅራቢያቸው አለመገኘት ተግዳሮት መሆናቸው በጥናቱ ተመላክቷል። 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...