Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሕግ የማያግዛቸው የቤት ውስጥ ሠራተኞችና አሠሪዎች

ሕግ የማያግዛቸው የቤት ውስጥ ሠራተኞችና አሠሪዎች

ቀን:

በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሕፃናትን ጨምሮ በርካታ ወጣቶች ለሥራ ከቦታ ቦታ ይዘዋወራሉ። በዚህ መካከል አንዳንዶች ዕድል ገጥሟቸው ካሰቡት ደርሰው የልባቸው መሻት ሲሳካላቸው፣ ሌሎች ደግሞ መንገዳቸው ጠሞባቸው ህልማቸው ሳይሳካ የኑሮ ቀንበር ጠቧቸው ወጣትነታቸውን በከንቱ ሲያሳልፉ ይስተዋላሉ፡፡

ከዚህም ሲከፋ ሕይወታቸውን እስከማጣት የሚደርሱ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። ለዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ደግሞ ከወንዶች ይልቅ ሴቶች ተጋላጭ ናቸው።

ድህነትና ሥራ አጥነት ሲበራከት ሴቶች ሥራ ሠርተው የራሳቸውንም ሆነ የቤተሰባቸውን ኑሮ ለማቃናት ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎች ያማትራሉ። የበርካቶች ትኩረት የሚሆነው ደግሞ ወደ ዓረብ አገሮች በባህርም ሆነ በየብስ፣ ከተሳካ በአየር ተጉዘው በቤት ሠራተኝነት ተቀጥረው ሠርተው መመለስ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ በአገራቸው ሠርተው ያሰቡትን ለማሳካት ይሞክራሉ።

በተለይ በሕገወጥ መንገድ ወደ ውጭ አገር በሚሄዱ ሴቶች ላይ የሚደርሰው ጭካኔ የተሞላበት ግፍና በደል በየጊዜው እንደሚታየውና እንደሚሰማው ሆኖ ሳለ፣ በአገራቸው ሆነው በቤት ሠራተኝነት ተቀጥረው የሚሠሩ ሴቶችም የሚደርስባቸው ኢሰብዓዊ ድርጊትም እንዲሁ ችላ ተብሎ ሊታለፍ የሚችል እንዳልሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በቤት ሠራተኝነት ተቀጥረው ለመሥራት ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ወደ አዲስ አበባ ከሚገቡት አብዛኞቹ በቤተሰብና በጓደኞቻቸው ተገፋፍተው ነው።

አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ የመጀመሪያ ችግራቸው በቤት ውስጥ ቀጥሮ የሚያሠራ ሰው ማጣታቸው ሲሆን፣ ይህም በሕገወጥ ደላላ እጅ እንዲወድቁ ያደርጋቸዋል። ደላሎችም ብዙ ገንዘብ ከመጠየቅ ጀምሮ ወደማይፈልጉት ሥራ ውስጥ እስከ ማስገባት ያደርሷቸዋል።

በቤት ውስጥ የሚቀጠሩትም መደፈር፣ ከአቅማቸው በላይ መሥራት፣ በሚሠሩት ልክ ደመወዝ አለማግኘት፣ ለረዥም ሰዓት መሥራትና የመሳሰሉት እንግልቶች ይደርስባቸዋል።

በሌላ በኩል አሠሪዎችም በቤት ሠራተኞቻቸው የሚደርስባቸው ኪሳራ በቀላል የሚታይና የሚታለፍ አይደለም።

የቤት ሠራተኞችና አሠሪዎች እንደ ማንኛውም ሥራ ተስማምተው፣ አሠሪም የሚከፍለውን ዋጋ፣ ሠራተኛም የሠራችበትን የላቧን ልክ የማታገኝበት የችግሩ ሥረ መሠረት ምን ይሆን? ለሚለው በዚህ ዙሪያ አዋጅ አለመውጣቱና የሕግ ማዕቀፍ አለመዘጋጀቱ መሆኑን በአዲስ አበባ ፍትሕ ቢሮ በሰዎች መነገድና ሰዎችን በሕገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል መከላከል ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ዓቃቤ ሕግ ወ/ሮ መሊያ ዲኖ ይገልጻሉ፡፡፡

የቤት ውስጥ ሠራተኞች ለአስገድዶ መደፈር፣ ከሚገባቸው በላይ እንዲሠሩ ለማድረግ፣ በደላሎች እንዲንገላቱና በርካታ ችግሮች እንዲደርስባቸው ምክንያቱ ሕግ አለመውጣቱ እንደሆነ የተናገሩት ወ/ሮ መኪያ፣ ይህም የቤት ሠራተኞች ለችግር ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች እንዲሆኑ አድርገዋል ብለዋል፡፡

መብታቸውን አክብሮ ለማስከበር የሥራ ላይ ደኅንነታቸውንና ሰብዓዊ ክብራቸውን ለማስጠበቅ ሕጉ ስለማያግዝ ለከፋ ቀውስ ተጋላጭ እየሆኑ ነው ብለዋል።

ስለአሠሪና ሠራተኞች አዋጅ ሲወጣ የቤት ሠራተኞችን ያላካተተ እንደሆነ አንስተው፣ አጠቃላይ ስለአሠሪና ሠራተኞች ግንኙነት የሚያወራው አዋጅ ቁጥር 11/56 በግል ድርጅቶች፣ በሆቴሎችና በመሳሰሉት መሥሪያ ቤቶች ስለሚሠሩ ሰዎች ካብራራ በኋላ፣ በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ 3 ‹‹የቤት ውስጥ ፅዳት ለሚሠሩ ለቤተሰብ የሚሆን ምግብ የሚያዘጋጅና በአጠቃላይ ከቤት ሠራተኞች ጋር በተያያዘ ለሚሠሩ ሠራተኞች ወደ ፊት መመርያ ይወጣል›› በማለት እንደሚዘለው ዓቃቤ ሕጓ አስረድተዋል፡፡

በቤት ሠራተኞችና አሠሪዎች መካከል የሚታየውን ውስብስብ ችግር በቀላሉ ለመፍታት አዋጅ መፅደቅና በሥራ ላይ መዋል ይኖርበታል ያሉት ወ/ሮ መኪያ፣ ለተግባራዊነቱም ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረጉ እንደሆነ ተናግረዋል።

የሕግ ማዕቀፍ ከወጣለት፣ ሠራተኞችም የሚጠበቅባቸውን ሥራ ሠርተው በሠሩት ልክ እንዲከፈላቸውና ሰብዓዊ መብታቸው ተከብሮ ሥራቸውም እንደ ማንኛውም ሥራ ዕውቅና እንዲያገኝ የሚረዳ ሲሆን፣ አሠሪዎችም በከፈሉት ልክ ሥራቸው እንዲሠራላቸውና በአጠቃላይ ሰላማዊ ግንኙነት እንዲፈጠር ያደርጋል ብለዋል።

‹‹ዕድሜያቸው ለአቅመ ሥራ ያልደረሱ 15 ዓመት ያልሞላቸው ሕፃናትን ከባድ ሥራ የሚያሠሩ አሠሪዎች የጉልበት ብዝበዛ እያደረሱ እንደሆነ ሊያውቁ ይገባል፤›› ያሉት ወ/ሮ መኪያ፣ ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በላይ የሆኑ ታዳጊዎች ግን አቅማቸው የፈቀደውን መሥራት እንደሚችሉ አክለዋል።

እነዚህንና በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ሕጉ ፀድቆ በሥራ ላይ እስከሚውል፣ ‹‹ሴት የቤት ሠራተኞች ተደራጅተው መብታቸውን እንዲያስከብሩ ማድረግ ይኖርባቸዋል፤›› ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በአሠሪዎቻቸው በደል የሚፈጸምባቸው ሴት የቤት ሠራተኞች፣ ተገቢውን ፍትሕ እያገኙ አይደለም ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሌንሳ ቢያና ናቸው ።

ዳይሬክተሯ ይህንን ያሉት ረቡዕ ኅዳር 5 ቀን 2016 ዓ.ም ለሴት የቤት ሠራተኞች ምቹ የሥራ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ያለመ የፓናል ውይይት በተካሄደበት ወቅት ነው።

ውይይቱ በራስ አገዝ ቡድን አሠራር ድርጅቶች ኅብረት በኢትዮጵያ፣ ከኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበርና ከፓካርድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነበር።

የውይይት መድረኩ ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት የተዘጋጀው ብሔራዊ ረቂቅ ፖሊሲ ፀድቆ ወደ ሥራ ይገባ ዘንድ ጫና ለመፍጠርና ግፊት ለማድረግ ያለመ እንደነበር የተናገሩት ወ/ሮ ሌንሳ፣ የሕግ ማዕቀፉ ፀድቆ በሥራ ላይ ሲውል ለአሠራር አስቸጋሪ የሆኑ ጉዳዮችን ለመፍታት ይረዳል ብለዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...