Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ‹‹የሙዚቃ ትምህርት ቤት ለመክፈት የገጠመኝ ፈተና ተስፋ አያስቆርጠኝም›› ሙዚቀኛ ሳሙኤል ይርጋ

‹‹የሙዚቃ ትምህርት ቤት ለመክፈት የገጠመኝ ፈተና ተስፋ አያስቆርጠኝም›› ሙዚቀኛ ሳሙኤል ይርጋ

ቀን:

ሙዚቀኛ ሳሙኤል ይርጋ ተወልዶ ያደገው፣ የመጀመርያና የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀው አዲስ አበባ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቅዱስ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት በፒያኖ ሜጀር የመጀመርያ ዲግሪውን ሠርቷል፡፡ በተለያዩ የአውሮፓና የአፍሪካ አገሮች እየተዘዋወረ የኢትዮጵያን የሙዚቃ ቅኝቶች በጃዝ መልክ በዓለም አቀፍ መድረኮች አስተዋውቋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2012 ‹‹ጉዞ›› በሚል ርዕስ ያዘጋጀው ሙዚቃ በቢዩኤስ እና በባዩኬ አይቲዊንስ ተለቅቆና ለተወሰነ ሳምንት በሽያጭ ላይ ከዋለ በኋላ አንደኛ ሆኗል፡፡ እንዲሁም በዚሁ ዓመት ሀፊንግቶን ፖስትና አርት ዴስክ በተባሉ ጋዜጦች ላይ ከወጡት አሥር አልበሞች የሙዚቀኛ ሳሙኤል አልበም አንደኛ ሆኗል፡፡ መቀመጫውን ፓሪስ ያደገው ‹አፍሪካን ሪፖርት› የተባለውና በዓለም አቀፍ ደጃ ታዋቂ የሆነው መጽሔት እ.ኤ.አ. በ2014 ከመረጣቸው 50 ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ውስጥ ሙዚቀኛ ሳሙኤል ተካቶበታል፡፡ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ የብላቴን ጌታህሩይ ወልደሥላሴ የሥነ ጥበባት ማዕከል አዘጋጅነትና በዛጎል የመጻሕፍት ባንክ አስተባባሪነት በተካሄደው ሙያዊ የውይይት መድረክ የባለሙያው የሙዚቃ ሕይወት፣ ‹‹ጉዞ›› ሙዚቃና ፍልስፍናው በስፋት ተነስቷል፡፡ ከዚህም ሌላ ለኢትዮጵያ የሙዚቃ ዕድገት ያበረከተው አስተዋጽኦ፣ በዚህም ያጋጠሙት ተግዳሮቶችና ሌሎችም ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሮታል፡፡

ሪፖርተር፡– የኢትዮጵያ ሙዚቃ አሁን ያለበትን ሁኔታ እንዴት ትገመግመዋለህ?

ሙዚቀኛ ሳሙኤል፡- በኢትዮጵያ ሦስት የሙዚቃ ትምህርት ቤቶች አሉ፡፡ እነርሱም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የያሬድ እንዲሁም የጃዝ አምባና ሴሚናሪ ሙዚቃ ትምህርት ቤቶች ናቸው፡፡ የተጠቀሱት ትምህርት ቤቶች የሚሰጡት ሥልጠና (ትምህርት) በልዩ ልዩ የሙዚቃ መሣሪያዎች አጠቃቀም ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ደግሞ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ባለበት አገር ሦስት የሙዚቃ ትምህርት ቤቶች ብቻ መኖራቸው አንገት ያስደፋል፡፡ ሌላው ችግር ደግሞ የሙዚቃ ኮንሰርት ማሳያ አዳራሾችና አምፊ ቴአትር የሚታይበት ቦታ አለመኖር ሲሆን፣ ይህም ችግሩን ድርብርብ አድርጎታል፡፡ ይህም በመሆኑ የሙዚቃ ኮንሰርት እየተካሄደ ያለው በቴአትር አዳራሾች፣ ማለትም በብሔራዊና በአገር ፍቅር የቴአትር አዳራሾች ነው፡፡ አዳራሾቹ ግን ትኩረታቸው በዋነኛነት ለቴአትር ነው፡፡ ሚሌኒየም አዳራሽም የሙዚቃ ኮንሰርት ሲከናወንበት ይስተዋላል፡፡ በመሠረቱ ሚሌኒየም አዳራሽ የተሠራው ለስብሰባ እንጂ ለሙዚቃ ኮንሰርት ማስተናገጃ ተብሎ አይደለም፡፡ በዚህም የተነሳ አቀማመጡም ሆነ የሳውንድ ሲስተሙ ሁሉ ለሙዚቃ ኮንሰርት ተብሎ አለመዘጋጀቱ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ የአምፊ ቴአትርም ቦታ እንዳለ አይቆጠርም፡፡ በወዳጅነትና በእንጦጦ ፓርኮች ያሉት ቦታዎችን እንደ አምፊ ቴአትር ለመቁጠር በጣም ያስቸግራል፡፡ ለዚህም ቦታዎቹ ትናንሽ ከመሆናቸውም በላይ እንደ ልብ ገብቶ ለመሥራት አመቺ አይደለም፡፡ በእርግጥ አፍሪካ አንድነት ድርጅት ቅጥር ግቢ ወደ አንድ ሺሕ ሰው መያዝ የሚችል አምፊ ቴአትር አለ፡፡ እዚህ ግቢ ውስጥ ለመግባት ደግሞ አስቸጋሪ ነው፡፡ እንደ ልብ ገብቶ ለመጠቀም አይቻልም፡፡ የአምፊ ቴአትር ቦታ መሆን ያለበት ልክ እንደ መስቀል አደባባይ ዓይነት ሆኖ ብዙ ሰው ማስተናገድ የሚችልና ሰፋ ያለ ክፍት ቦታ ሲሆን ነው፡፡ እነዚህ ችግሮች ተጠቃሎ ሲታይ በሙዚቃ ላይ ብዙ መሥራትን ያመለክታል፡፡

ሪፖርተር፡– ይህ ዓየነቱ ችግር ሊከሰት የቻለው ለምን ይመስልሃል? ወይም የችግሩ መንስዔ ምንድነው ትላለህ?

ሙዚቀኛ ሳሙኤል፡- መንስዔው መንግሥት ለሙዚቃ ዕድገት የሰጠው ትኩረት ኢምንት፣ ወይም በጣም ዝቅ ያለ በመሆኑ ነው፡፡ ሙዚቀኞቹም ቢሆኑ ለሙዚቃ የሚሰጡት ዋጋና ቦታ በጣም የወረደ ነው፡፡ ሙዚቀኞች ይህን ያህል ዋጋ ካልሰጡት መንግሥት ደግሞ በሁለተኛ ደረጃ ቢያየው አያስገርምም፡፡

ሪፖርተር፡– አንተ ከፍተኛ የሙዚቃ ባለሙያ ነህ፡፡ በተለያዩ አገሮች ተዘዋውረህ የኢትዮጵያን ሙዚቃ በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውተሃል፡፡ በዚያው ልክ አንተን ከመሰሉ የውጭ ባለሙያዎች ጋር የመገናኘት የመተዋወቅ ዕድል አግኝተሃል፡፡ ስለሆነም ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ዕድገት በራስህ ያደረከውን ጥረትና በዚህም የተነሳ መንግሥት ላይ ያሳደርከውን ተፅዕኖ ልታብራራልን ትችላለህ?

ሙዚቀኛ ሳሙኤል፡- ብዙ ጥረቶችን አድርጌያለሁ፡፡ ካደረጉትም ጥረቶች መካከል የሙዚቃ ትምህርት ቤት ለማቋቋም የሚያስችል ፈቃድ ለማግኘት ለአዲስ አበባ ቱሪዝምና ባህል ቢሮ ከሁለት ዓመት በፊት፣ እንዲሁም ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከአምስት ዓመት በፊት ፕሮፖዛል አቅርቤ እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት መልስም ሆነ ፈቃድ አላገኘሁም፡፡

ሪፖርተር፡– ፕሮፖዛሉን በተመለከተ ብታብራራልን?

ሙዚቀኛ ሳሙኤል፡- ፕሮፖዛሉ ሁለት ዕቅዶችን የያዘ ሲሆን፣ ሁሉም ዕቅዶች የሚተገበሩት አዲስ አበባ ውስጥ ነው፡፡ የመጀመርያው ዕቅድ አዲስ የሙዚቃ ትምህርት ቤት መገንባትን የሚያመላክት ሲሆን፣ ሌላው ዕቅድ ደግሞ ከፒያሳ በመነሳት ካዛንቺስ እንደተደረሰ ከመስቀለኛ መንገድ መታጠፊያና ቤንዚን ማደያ ፊት ለፊት ቆሞ የነበረው ዕድሜ ጠገቡን ሕንፃ ታሪካዊነቱንና ቅርስነቱን በጠበቀ መልኩ አድሶና አሻሽሎ ለሙዚቃ ትምህርት ቤት እንዲውል የሚያደርግ ነው፡፡

ሪፖርተር፡– ይህ ዓይነቱን ሥራ ዳር ለማድረስ በግልህ አቅም ነው የምታከናውነው ወይስ የሚያግዙህና የሚተባበሩህ አካላት አሉ?

ሙዚቀኛ ሳሙኤል፡- አዲሱን የትምህርት ቤት ሕንፃ ለመገንባት ጀርመን የሚገኘው ቫይመር ዩኒቨርሲት ቃል የገባልኝ ሲሆን፣ ዕድሜ ጠገቡን ሕንፃ አሻሽሎና አድሶ ለሙዚቃ ትምህርት ቤት እንዲውል የማድረጉን ሥራ ለማከናወን ፈቃደኝነቷን ያሳየችኝ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ለዚሁ ዓይነቱ ትብብር እጇን ልትዘረጋ የቻለችው ሕንፃው በኢጣሊያ ፋሺስት ወረራ ዘመን የተሠራ፣ በዚህም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሆኖ በማገልገሉና የቤተ ክርስቲያኗ አሻራ ስላረፈበት ነው፡፡

ሪፖርተር፡– ዕድሜ ጠገቡን ሕንፃ እንደገና አሻሽሎ የመሥራትና አዲስ ሕንፃ የመገንባቱ ጉዳይ ከምን ደረሰ?

ሙዚቀኛ ሳሙኤል፡- ዘመን ተሻጋሪ የነበረው ይህ ሕንፃ የአዲስ አበባ ከተማ ግብርና ጽሕፈት ቤት ሆና አገልግሏል፡፡ ግብርና ሚኒስቴርም አልፎ አልፎ አዳራሹን ለስብሰባ ይጠቀምበት ነበር፡፡ ይህ ዓይነቱ ሕንፃ ታሪካዊነቱንና ቅርስነቱን በጠበቀ መልኩ ታድሶና ተሻሽሎ ለታሰበው ዓላማ ቢውል ኖሮ በዙሪያው ከተገነቡትና ወደፊትም ከሚገነቡት ሕንፃዎች ጋር ተደምሮ ለአካባቢው እጅግ የጎላ ውበትና ድምቀት ይሰጠው ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ግን ህልም ሆኖ ቀርቷል፡፡ ሕንፃውም ፈርሶ በምትኩ ለሌላ አገልግሎት የሚውል አዲስ ሕንፃ በመገንባት ላይ መሆኑ ይስተዋላል፡፡ ለትምህርት ቤቱ የሚውል አዲስ ሕንፃ የመገንባቱ ጉዳይን በተመለከተ ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ዲን ኢትዮጵያ ድረስ መጥተው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤትን ጎብኝተዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ እንዲህ ያሉ አነስተኛ ትምህርት ቤት መኖሩ ተገርመዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ብቸኛ መፍትሔው ሌላ አዲስ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ማቋቋም መሆኑን አምነውበታል፡፡ ለተግባራዊነቱም ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ ነግረውኛል፡፡

ሪፖርተር፡– ትምህርት ቤት ከተሠራ የሙዚቃ መሣሪያዎችን ጉዳይ እንዴት ታየዋለህ?

ሙዚቀኛ ሳሙኤል፡- የሙዚቅ መሣሪያዎችን በተመለከተ ቤልጂየም የሚገኙ የሙዚቃ ተቋማት ኃላፊዎች ሊረዱኝ ቃል ገብተዋል፡፡ ቃል የገቡት ዘመናዊ የሙዚቃ መሣሪያዎችን ከሰበሰቡ በኋላ በሁለት ኮንትይነሮች አሽገውና በመርከብ አስጭነው እስከ ወደብ ድረስ ለማጓጓዝ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሚከናወነው ግን ከኢትዮጵያ መንግሥት ተገቢ የሆነ ፈቃድ ሲገኝ ብቻ መሆኑን አጫውተውኛል፡፡

ሪፖርተር፡– ይህን ጉዳይ ለማን አመለከትክ?

ሙዚቀኛ ሳሙኤል፡- ጉዳዩን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመለከትኩ፡፡ ሚኒስቴሩም ጉዳዩ በይበልጥ ወደሚመለከተው መንግሥታዊ አካል መራው፡፡ የተመራለትም መንግሥታዊ አካል የሙዚቃ መሣሪያዎችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት በመጀመርያ አስመጪው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት (መያድ) ማቋቋም አለበት፡፡ የሙዚቃ መሣያዎቹ የሚገቡትም የሚፈለገው መያድ እንደተቋቋመ ወዲያውኑ ሳይሆን፣ ቢያንስ ለሦስት ዓመት መቆየት አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ መሣሪያዎቹን ለማስገባት እንደማይቻል ነው የተገለጸልኝ፡፡

ሪፖርተር፡– የተባልከውን ለመፈጸም ወይም መያድ የማቋቋሙን ሁኔታ ምን አደረግከው? መሣሪያውን ለመላክ ቃል የገቡልህን ኃላፊዎች እንዴትና በምን መልኩ ነው ያገኘኃቸውና ከእነርሱም ጋር ግንኙነት የፈጠርከው?

ሙዚቀኛ ሳሙኤል፡- መያድ የማቋቋሙን ጉዳይ ለማሳካት አልቻልኩም፡፡ ምክንያቱም ሙዚቃን በተመለከተ ከዩኒቨርሲቲው ጋር የጀመርኩት ፕሮግራም ስለነበር የትኩረት አቅጣጫዬን ሁሉ ወደዚሁ አደረኩ፡፡ ለሌላው ሥራ ጊዜና ፋት አጣሁ፡፡ የሙዚቃ መሣሪያዎችን ለመረዳት ፍላጎት ያሳዩ የተቋማት ኃላፊዎች ያገኘኋቸው በተለያዩ ሁለት ፕሮግራሞች ላይ በተሳተፍኩባቸው ጊዜ ነው፡፡ አንደኛው ፕሮግራም ‹‹ቤልጂየም የኢትዮጵያ አሶሴሽን›› ብራሰልስ ውስጥ እ.ኤ.አ. በ2014 ባካሄደው ስብሰባ ላይ የሙዚቃ ኮንሰርት እንዳቀርብ በመጋበዜ ነው፡፡ በነገራችን ላይ በዚህ ዓይነቱ ስብሰባ ላይ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ተገኝተዋል፡፡ ሁለተኛውና ሌላው ፕሮግራም ደግሞ የአውሮፓ ኅብረት እ.ኤ.አ. በ2019 ‹‹የአውሮፓ ዴቨሎፕመንት ዴይን››ን ምክንያት በማድረግ ባካሄደው ስብሰባ ሲሆን፣ በዚህም ስብሰባ የተገኘሁት በፓናሊስትነት ከኅብረቱ በቀረበልኝ ግብዣ መሠረት ነው፡፡ በተለያዩ ዓመታት በተከናወኑት በእነዚሁ ስብሰባዎች ላይ ንግግር አደረኩ፡፡ በንግግሬም ውስጥ ኢትዮጵያ ውስጥ የሙዚቃ ችሎታ ያላቸው ብዙ ወጣቶች አሉ፡፡ ነገር ግን ችሎታቸውን ማርካት የሚያስችላቸው የሙዚቃ ትምህርት ቤቶች የተፈለገውን ያህል የለም ብዬ ነበር፡፡ በሁለቱም ስብሰባዎች ያደረኩትን ንግግር እንዳበቃሁ ከታዳሚዎች መካከል የሙዚቃ ተቋማት ኃላፊዎች ወደ እኔ እየመጡ እኛ በሙዚቃ መሣሪያና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ እንረዳችኋለን የሚል ቃል በየተራ ገቡልኝ፡፡ ይህም ቢሆን ግን ከፍ ብሎ በተጠቀሱት ምክንያቶች ነገሮች ተወሳስበውብኛል፡፡

ሪፖርተር፡– ተስፋ እንድትቆርጥ አድርጎህ ይሆን?

ሙዚቀኛ ሳሙኤል፡- ተስፋ አልቆርጥም፡፡ የጀመርኩትን ዳር ለማድረስ ከመታገልና ከመፍጨርፈር ወደኋላ አልልም፡፡ ገና ስጀምርም ልዩ ልዩ ተግዳሮቶች እንደሚያጋጥሙኝ አውቅ ነበር፡፡ ችግሮችን እየተጋፈጡ መንቀሳቀሱ የኋላ ኋላ ፍሬያማ የሆነ ውጤት ያስገኛል የሚል እምነት አለኝ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...