በዓለም በተለይ ሴቶችን በዘላቂነት ከድህነት ለማውጣት ጥቅም ላይ ከሚውሉ ሥልቶች መካከል የ‹‹ሴቶች ራስ አገዝ›› አሠራር ሥርዓት አንዱ ነው፡፡ አሠራሩም ትኩረት የሚያደርገው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሴቶችን በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ እንዲሁም በአመለካከታቸው ዙሪያ ለውጥ በማምጣት ራሳቸውን፣ ቤተሰቦቻቸውንና ማኅበረሰቡን የዘላቂ ልማት ባለቤት እንዲሆን ማስቻል ነው፡፡
ይህንኑ መሠረት አድርጎ የተቋቋመው የራስ አገዝ ቡድን አሠራር፣ ድርጅቶች ኅብረት በኢትዮጵያ፣ (ኮሳፕ) ከተመሠረተ ጀምሮ 300 ሺሕ ሴቶች፣ በ18 ሺሕ ቡድኖች እንዲደራጁ በማድረግና ሥልጠና በመስጠት ወደ ሥራ ገብተው ሕይወታቸውን መለወጥ መቻሉን ይገልጻል፡፡
ተቋሙ ሃምሳኛ ዓመት ክብረ በዓሉን አስመልክቶ ከኅዳር 4 እስከ 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ባካሄደው ዝግጅት፣ የኅብረቱ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሙሉጌታ ገብሩ እንደገለጹት፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ የሚገኙ ሴቶች በራስ አገዝ ቡድን ውስጥ በመደራጀት ራሳቸውን፣ ቤተሰቦቻቸውን ብሎም አካባቢያቸውን እየቀየሩ ነው፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ በራስ አገዝ የተደራጁ ሴቶች ቁጠባቸውን በማሽከርከር ከ320 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል እያንቀሳቀሱ መሆኑን የተናገሩት የቦርድ ሰብሳቢው፣ በዚህም 600 ሺሕ የሚሆኑ እናቶች ልጆቻቸው የምግብ፣ የትምህርትና የጤና እንክብካቤ በተገቢው መንገድ እንዲያገኙ ማስቻላቸውን አስረድተዋል፡፡
የራስ አገዝ ቡድን ፕሮግራም በኢትዮጵያ ደረጃ በ20 ሴቶች ደብረ ብርሃን ከተማ ላይ በእየሩሳሌም ሕፃናትና ማኅበረሰብ ድርጅት አማካይነት ተጀምሮ አሁን መስፋፋቱንና በአሁኑ ወቅት በአገር አቀፍ ደረጃ 33 ድርጅቶች ይህንን አሠራር ተግባራዊ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በጣም ብዙ ሀብት ያላት አገር እንደመሆኗ መጠን፣ ሴቶች ያላቸውን አቅም በመጠቀም በተለያዩ ሥራዎች በመሳተፍ ኢኮኖሚያቸውን ማሳደግ ይኖርባቸዋልም ብለዋል፡፡
በዘርፉ የተሰማሩ አባላትን በማብዛት እንዲሁም ተደራሽ ባልሆኑ ክልሎች በመግባት ተቋሙ ሰፊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ዕቅድ መያዙንም አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል በዚህ ሥራ የተሰማሩ ሴቶች በሰላም ማስከበር፣ የወጣቶችን ባህሪ በመቀየር፣ የተሻለ ዜጋ በመፍጠርና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች በመሳተፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የራስ አገዝ ቡድን አሠራር ሃይማኖት፣ ቋንቋንና የመሳሰሉ ልዩነቶችን በሥራ ላይ እንዲኖር የማያደርግ መሆኑን ጠቅሰው፣ በርካታ አካል ጉዳተኞችንም በማካተት እየሠራ መሆኑን የቦርድ ሰብሳቢው ተናግረዋል፡፡
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በአዋጅ ቁጥር 1113/2011 የተሰጠውን ሥልጣን ለማስፈጸም የሲቪል ማኅበራት በትምህርት፣ በጤና፣ በምግብ ዋስትና፣ በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የሚያስችሉ አዳዲስ አሠራሮችን ቀርፆ ተግባራዊ እያደረገ ነው ያሉት የተቋሙ ተወካይ አቶ አብድሬ አህመድ ናቸው፡፡
በዚህ መሠረት አዲሱ አዋጅ ከወጣ ጊዜ ጀምሮ ከ4,000 በላይ የሲቪል ማኅበራትን መዝግቦ እያስተዳደረ ሲሆን፣ የሲቪል ማኅረበሰብ ድርጅቶች ለአገሪቱ ልማትና ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱና ዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር አቅምን በማሳደግ ረገድ ተገቢውን ሚና እንዲጫወቱ ለማድረግ የሚጠበቅበትን እየተወጣ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የራስ አገዝ ቡድኖች ድርጅቶች ኅብረት በባለሥልጣኑ ተመዝግበው ከሚንቀሳቀሱ ከ50 በላይ ኅብረቶች አንዱ ሲሆን፣ በተለይ አባል ድርጅቶቹን በማስተባባር ሴቶችን በራስ አገዝ ቡድን ማኅበራት በማደራጀት የፆታ እኩልነት፣ ሰብዓዊ መብት፣ እንዲሁም ሴቶች በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ ብሎም በፖለቲካዊ ሁነቶች ተካታችና ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሥልት ዘርግቶ እየሠራ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
ራስን በራስ ለመርዳት በራስ አገዝ ቡድን ተደራጅተው ሴቶች ዕርዳታ ጠባቂ ሳይሆኑ ቆጥበውና በገቢ ማስገኛ ሥራ ተሰማርተው የለውጥ አርዓያ ለመሆን የሚሄዱበትን አካሄድ ባለሥልጣኑ የሚደግፈው መሆኑን ተወካዩ ገልጸዋል፡፡
በዚህ መሠረት ኮሳፕና አባል ድርጅቶቹ ሥራቸውን በማስፋፋት ተጨማሪ ሴቶችን በራስ አገዝ ቡድን በማደራጀት ድህነትን ለመቅረፍ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ላይ ባለሥልጣኑ የሚፈለገውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት የሰላም ዕጦት ላይ በራስ አገዝ ቡድን የተደራጁ ሴቶች በተለያዩ መንግሥት ባስቀመጣቸው አደረጃጀት ውስጥ በመግባት ተሳታፊ እንዲሆኑ የተለያዩ የአቅም ዕገዛዎችን ማድረግ እንደሚገባም አክለዋል፡፡
የአዳማ ከተማ የጥምረት ለውጥ ራስ አገዝ ቡድን ሰብሰቢ ወ/ሮ ትዕግሥት እጅጉ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በራስ አገዝ ቡድን ውስጥ ከገቡ ጊዜ ጀምሮ ጥሩ ሕይወት እየኖሩ ነው፡፡
ከዚህ በፊት በኪራይ ቤት ይኖሩ እንደነበር ያስታወሱት ሰብሳቢዋ፣ በራስ አጋዝ ቡድን ውስጥ ገብተው ቁጠባን በመለማመድ የራሳቸውን ቤት መግዛት መቻላቸውን ይናገራሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ፣ ባለቤታቸውም የስኳር በሽተኛ በመሆናቸው ቁጭ ብለው እሳቸው በሚያመጡት ገቢ አንድም ሕመማቸውን እንዲያስታምሙ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ረፍት አድርገው የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ እያደረጉ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
ከዚህ በፊት ባለቤታቸው በግንበኝነት ተሰማርተው ይሠሩ እንደነበር ያስታወሱት እኚሁ እናት፣ በቆጠቡት ገንዘብ ከራሳቸው የመኖሪያ ቤት አልፈው ሦስት የሚከራዩ ቤቶችን ሠርተው በማከራየት ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ ይገልጻሉ፡፡
በተለይ ጓደኞቻቸውም ሆኑ እሳቸው በራስ አገዝ ቡድን ውስጥ ከገቡ ጊዜ ጀምሮ በሕይወታቸው ለውጥ ማምጣታቸውን፣ አሁን ከብት አደልበው በመሸጥ ንግድ መሠማራታቸውን ለሪፖርተር ያስረዳሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት 2,010 የሚሆኑ እናቶች በዚህ ቡድን ውስጥ እንደሚገኙ ገልጸው፣ እያንዳንዱ እናቶችም በባልትና ውጤቶች፣ በከብት ዕርባታ፣ በምግብ ሽያጭ፣ በዶሮ ዕርባታና በሌሎች ሥራዎች ተሰማርተው እየሠሩ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡
እያንዳንዱ ቡድን ከ300 ሺሕ ብር በላይ እንዳለው ጠቅሰው፣ አጠቃላይ ቡድኑም ከስምንት ሚሊዮን ብር በላይ በመቆጠብ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ብለዋል፡፡
የጥምረት ለውጥ ራስ አገዝ ቡድን አሁን ላይ ሕጋዊ ፈቃድ አግኝቶ እየተንቀሳቀሰ ነው ያሉት እኚህ እናት፣ በቀጣይ የአዳማ ከተማ አስተዳደርን የቦታ ይዞታ በመጠየቅ ትልቅ የኢንቨስትመንት ሥራ ላይ ለመግባት ዕቅድ መያዛቸውን አስታውሰዋል፡፡
ከዚህ በፊት ቡድኑ የቢሮና ሕጋዊ ዕውቅና የማግኘት ችግር አጋጥሞት እንደነበር፣ አሁን ላይ ችግሩ ተፈትቶ ለመንግሥት የቦታ ይሰጠን ጥያቄ ለማንሳት ቀጠሮ መያዛቸውን ሰብሳቢዋ ያስረዳሉ፡፡
በኢትዮጵያ ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ የራስ አገዝ ቡድን የሚያስተባብሩ ድርጅቶች ሥራቸውን በአገር አቀፍ ደረጃ ለማስፋፋትና ለማቀናጀት ኅብረት ፈጥረዋል፡፡
የራስ አገዝ ቡድን አሠራር ድርጅቶች ኅብረት በኢትዮጵያ የሴቶችን አቅም በማጎልበት ላይ በሚሠሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የተመሠረተ ሲሆን፣ በኢፌዴሪ የሲቪል ማኅበረሰብ ኤጀንሲ በቁጥር 1591 ተመዝግቦ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑም በወቅቱ ተገልጿል፡፡