Monday, December 11, 2023

የገጠር መሬት የመጠቀም መብትን አስይዞ የመበደር ሕግ ምን አዲስ ነገር ይዟል?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የመሬት ጥያቄ በኢትዮጵያ ፖለቲካ መንግሥታትን ሲፈትን የኖረና ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ የፖለቲካ ጥያቄ መሆኑ ይነገራል፡፡ ‹‹መሬት ለአራሹ›› ተብሎ መፈክር ከተማሪዎች የለውጥ ንቅናቄ ጋር አብሮ የተነሳው የመሬት ጉዳይ፣ በደርግ ዘመነ መንግሥትም ዋና የፖለቲካ አጀንዳ ሆኖ ነው የኖረው፡፡ ደርግ ሥልጣን በያዘ መንፈቅ እንኳ ሳይሞላው የካቲት 25 ቀን 1967 ዓ.ም. የገጠር መሬት አዋጅ በማውጣት የመሬት ለአራሹ ጥያቄን ፈጥኖ ለመመለስ እንደሞከረ ታሪክ ያወሳል፡፡ አዋጁ በጊዜው ለረጅም ዘመናት በኢትዮጵያ ሰፍኖ የቆየውን የመሬት ሥሪት የቀየረ ተብሎም ነበር፡፡

መሬትን ከባለርስቱ ወደ አራሹ የሚያዛውር የተባለው የደርግ መንግሥት አዋጅ ሥር ነቀል ለውጥ በአገር ደረጃ ያመጣ ስለመሆኑ ይነገርለታል፡፡ የመሬት አጠቃቀም ላይ ጉልህ ለውጥ እንዳመጣ የታመነበት ይህ አዋጅ፣ ግብርናን የተመረኮዘችውን አገር በልማት በእጅጉ እንደሚያራምድ ብዙ ሲባልለት እንደነበርም ያወሳል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ያጠኑ በርካታ ተቺዎች እንደሚናገሩት ከሆነ ግን ሥር ነቀል ለውጥ ያመጣል የሚባል አዋጅ ያወጀው ደርግ በስተኋላ አከታትሎ ባወጣቸው አርሶ አደሩን የምርቱ ባለቤት እንዳይሆን በሚያደርጉ ሕጎቹና አሠራሮቹ፣ ወደ ሥልጣን ሲመጣ የሰጠውን መብት መልሶ ነቅሎ ወስዶታል ይላሉ፡፡

ይህ ሁኔታ ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ሲመጣ በሚወስዳቸው ዕርምጃዎች ይሻሻላል ተብሎ ተገምቶ ነበር፡፡ በኢሕአዴግ ዘመን በፀደቀው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 40 ላይ የመሬት ጉዳይ ድንጋጌ አገኘ፡፡ በአንቀጽ 40/3 ላይ የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግሥትና የሕዝብ ብቻ ነው ተባለ፡፡ መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ንብረት ነው ተብሎ ታወጀ፡፡ በንዑስ አንቀጽ አራት ላይ ደግሞ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች መሬት በነፃ የማግኘትና ከመሬታቸው ያለ መነቀል መብታቸው የተከበረ ነው ተብሎ ተደንግጓል፡፡

የመሬት ጥያቄ እስከ ሕገ መንግሥት ድረስ ድንጋጌ ቢያገኝም ነገር ግን የመሬት ባለቤትነትም ሆነ የመሬት መጠቀም ነፃነት ጉዳይ፣ በአገሪቱ ጉልህ ለውጥ አልታየበትም የሚለው ብዙ ሲያከራክር ነው የዘለቀው፡፡

የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የራስወርቅ አድማሴ (ዶ/ር)፣ በመሬት ጉዳይ ላይ ለውጥ እንዲደረግ ብዙ ምሁራን ግፊት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ይናገራሉ፡፡ እሳቸውም ሆኑ ሌሎች በርካታ ምሁራን የመሬት ሥሪቱ የገበሬውን የይዞታ ባለቤትነት መብት ካላረጋገጠ ገበሬው የዕለት የዕለቱን ብቻ እያረሰ መሬቱ ጥበቃ ያጣል፣ እንዲሁም የተለየ ጠቀሜታም ሳይሰጥ ይቀራል የሚል ግፊት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ያስታውሳሉ፡፡

‹‹ስለመሬት አጥንተን የምናቀርበውን የጥናት ውጤትም ሆነ ምክረ ሐሳብ የመቀበል ዝንባሌ መንግሥት አልነበረውም፤›› የሚሉት ምሁሩ፣ ‹‹መሬቱ ላይ ለሚኖረው ሰው ትንሽ እንኳ የባለቤትነት ስሜት የሚፈጥር ሕግ አውጡ ብንል የሚሰማ አልነበረም፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በብዙ ጫናና ውትወታ በስተኋላ ‹‹የመሬት ባለቤትነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት የመስጠትን ሐሳብ ተቀበሉ፤›› የሚሉት የራስወርቅ (ዶ/ር)፣ አሁን ደግሞ ከዚህ ከፍ በማድረግ መሬትን አስይዞ መበደር የሚፈቅድ አዋጅ እንዲዘጋጅ መደረጉን ይናገራሉ፡፡

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ‹‹የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ›› አይነኬ ሆኖ የቆየውን የመሬት ጉዳይ የበለጠ ነፃ የሚያደርግ ድንጋጌ መያዙ እየተነገረ ይገኛል፡፡ አንዳንዶች የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሊያመጣ ከሚችል የዘርፉ ለውጥ በመለስ፣ ከፍተኛ ነፃነት በመሬት አጠቃቀም ላይ የሚሰጥ ስለመሆኑ እየተናገሩለት ነው፡፡

ሕገ መንግሥቱን የማሻሻሉና የመሬት ሥሪቱን ሙሉ ለሙሉ የመቀየሩ ጥረት ዛሬ በቀላሉ የሚሳካ ባይሆን እንኳን፣ የመሬት አጠቃቀምን ይህ አዋጅ እንደሚለውጥ ብዙ ወገኖች እምነታቸውን ከወዲሁ እየገለጹ ነው፡፡ አዲሱ ረቂቅ አዋጅ በተጨባጭ ምን ውጤት ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል በሚለው ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ ምን አዲስ ነገሮችም ይዞ መጥቷል የሚለውን ጉዳይ በተመለከተ በረቂቁ ሒደት የተሳተፉት አቶ አበባው አበበ ሐሳብ ይሰጣሉ፡፡ በግብርና ሚኒስቴር ውስጥ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ሥራ አስፈጻሚ የሥራ ክፍል ውስጥ የሕግ ባለሙያ የሆኑት አቶ አበባው፣ ሕጉ ሲረቀቅ በአርቃቂ ቡድኑ ውስጥ በሰብሳቢነትና በጸሐፊነት መሳተፋቸውን ይናገራሉ፡፡ ከዚህ በመነሳት በመሬት አጠቃቀምም ሆነ በዜጎች ሕይወት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ የሚያመጣ አዋጅ መዘጋጀቱን ያስረዳሉ፡፡

‹‹ሕጉ የገጠር መሬትን ሳይሆን የገጠር መሬት የመጠቀም መብትን አስይዞ የመበደር መብትን ነው የሰጠው፡፡ የገጠር መሬትን ማስያና መበደር ቢፈቀድ ብድሩ ባይመለስ መሬቱን ወደ መሸጥ ሊገባ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ በሕገ መንግሥቱ የተፈቀደ አይደለም፡፡ ያን ማድረግ የሚያስችል ሥልጣንም ሆነ የሕግ መሠረት ስለሌለ የገጠር መሬት የመጠቀም መብትን ማስያዝ የሚፈቅድ አዋጅ ነው ለጊዜው ያዘጋጀነው፤›› ሲሉ ሕጉ የተዘጋጀበትን ዓውድ ተናግረዋል፡፡

በላንድ ፎር ላይፍ ተቋም ውስጥ የፖሊሲ አድቮኬሲ ባለሙያ የሆኑትና በፕላንና ልማት ሚኒስቴር የፕላን ልማት ፕሮጀክት አስተባባሪ የሆኑት አቶ ቡልቻ በሪቻ፣ በመሬት አጠቃቀምም ሆነ በዜጎች ሕይወት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ የሚያመጣ አዋጅ መዘጋጀቱን ይናገራሉ፡፡

‹‹የአርሶ አደሩን፣ የከፊል አርብቶ አደሩንና የአርብቶ አደሩን የሕይወት ደረጃ ለመቀየር የሚያስችል ነው፡፡ ምርትና ምርታማነትን ይጨምራል፡፡ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥም ወሳኝ ነው፤›› በማለት አዲሱን ረቂቅ የመሬት አጠቃቀም አዋጅ ገልጸውታል፡፡

ሌላኛው አስተያየተ ሰጪ በግብርና ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ጌታቸው ድሪባ (ዶ/ር)፣ መንግሥት በመሬት አሠራሩ ላይ ማነቆ የሆኑ ችግሮችን በየጊዜው እያጠና መፍትሔ ሲሰጥ መቆየቱን ይናገራሉ፡፡ ለአገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሪፎርሙ ግብዓት ይሆናል ያሉትን ‹‹The Evolving Question of Land in Ethiopia›› የሚል ጥናት ቀደም ብለው ያቀረቡት ጌታቸው (ዶ/ር)፣ የመሬት አጠቃቀምን በተመለከተ የሕግ ማሻሻያ እንደሚያስፈልግ ቀደም ብለው ሲሠሩ የቆዩ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ስድስት መሠረታዊ ለውጦች የማድረግን አስፈላጊነት ባሠፈሩበት የጥናታቸው ግርጌ፣ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ሕጉን ማሻሻል አንዱ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የአሁኑ አዲሱ የሕግ ረቂቅ ለዚህ መልስ ይሰጥ እንደሆነ የተጠየቁት ጌታቸው (ዶ/ር)፣ ‹‹ከነበርንበት በጣም ብዙ ወደፊት የሚያስኬድ ሕግ ነው፤›› ሲሉ መልሰዋል፡፡ ሕጉ መዘጋጀቱ በመሬት ጉዳይ ብዙ ለውጦች እንዲመጣ የሚያደርግ መሆኑንም ይናገራሉ፡፡ ‹‹የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ ለማዘጋጀት፣ የመሬት ዘርፉን በባለቤትነት የሚመራ ተቋም ለመፍጠርና የመሬት አጠቃቀሙን ውጤታማ ለማድረግ ከፍተኛ ዕገዛ ያለው ነው፤›› በማለት ይገልጹታል፡፡

የከተሞች ዕድገት በፈጣን ሁኔታ እየሄደ መሆኑን የተናገሩት ጌታቸው (ዶ/ር)፣ ይህን ከገጠር ልማት ጋር አስታርቆ መሄድ እንደሚያስፈልግ በመጠቆም ሕጉም ለዚህ በእጅጉ አጋዥ ነው ብለዋል፡፡

አዲሱ ረቂቅ አዋጅ በመሠረታዊነት የአርሶ አደሩን፣ የከፊል አርብቶ አደሩንና የአርብቶ አደሩን ሕይወት የመቀየር ዓላማ እንዳለው በረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ ላይ ተመላክቷል፡፡ የአርብቶ አደሩን የመሬት አጠቃቀም ባህልም ያማከለ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ይህ አዋጅ የገጠር መሬት ምዝገባ መረጃን ጥራት የሚያስጠብቅ፣ እንዲሁም የተለያየ አካባቢ ሥነ ምኅዳርን ያማከለ የመሬት አጠቃቀም እንዲኖር የሚያግዝ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

አዋጁ ሲረቀቅ ጀምሮ በቅርበት የሚያውቁት የመሬት አስተዳደር ባለሙያው አቶ አበባው፣ የአርሶና የአርብቶ አደሩ የመሬት የመጠቀም መብት ብዙ ዓይነት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ሕጉ እስከ አሥር ዓመት የሚደርስ የመሬት መጠቀም መብታቸውን የመሬት ባለይዞታዎች ለፋይናንስ ተቋማት አስይዘው እንዲበደሩ ይፈቅዳል፤›› ይላሉ፡፡ ዝርዝሩ ነባር ለክልሎች የተተወ ቢሆንም ከአሥር ዓመት ያልበለጠ የመሬት መጠቀም መብትን አስይዞ መበደር መፈቀዱን ጠቁመዋል፡፡

ብድር ሰጪዎቹ የፋይናንስ ተቋማት የመሬቱን ጥቅም በማጥናት የብድር ግምት እንደሚያወጡም አቶ አበባው ይገልጻሉ፡፡ ባለይዞታው ለብድር ከጠየቀው የመሬት የመጠቀም መብት ጊዜ ገደብ መሬቱ ይሰጣል ተብሎ ከተገመተው ጥቅም ጋር ተደምሮ ብድሩ እንደሚሰጥም አስረድተዋል፡፡

‹‹በሚሰጠው ብድር የመሬት ባለይዞታው ማሽነሪዎችን ሊገዛ ይችላል፣ የመስኖ መሠረተ ልማት ሊያለማ ይችላል፣ ከእርሻ ሥራ በተጨማሪ ግብርና ማቀነባበር ሊሠራ ይችላል፣ የአዋጭነት ጥናት አዘጋጅቶ ሌላ ሥራም ይችላል፤›› በማለት ባለሙያው ያስረዳሉ፡፡ የመሬት ባለይዞታው ብድሩን ካልከፈለ የፋይናንስ ተቋሙ በጊዜ ገደቡ መሠረት የመሬት መጠቀም መብቱን ወስዶ ሊያከራየውና ወደ ጥቅም ሊቀይረው እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ ‹‹ባለመሬቱ የሁለት ዓመት የመጠቀም መብቱን አስይዞ ከተበደረ ባንኩም ለሁለት ዓመታት መሬቱን ለዕዳ መክፈያ ጥቅም ላይ በማዋል ለባለይዞታው መሬቱን ያስረክባል፡፡ ይህ መሬት አይሸጥም አይለወጥም የሚለውን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ሳይጣስ የመሬትን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በእጅጉ የሚጨምር ነው፤›› ብለውታል፡፡

ይህ አሠራር በአዋጅ ተዘጋጅቶ ቀረበ እንጂ ከተጀመረ መቆየቱን አቶ አበባው ያክላሉ፡፡ በሙከራ ደረጃ ከሰባትና ከስምንት ዓመታት በፊት እንደጀመረ ይናገራሉ፡፡ በደቡብ፣ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ተሞክሮ ውጤታማ ሆኗል የሚሉት አቶ አበባው ይህን መሠረት አድርጎ አዋጁ መቅረቡን ያስረዳሉ፡፡ ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጀው አዋጅ ቁጥር 1117/2019 ላይ የማይንቀሳቀስ ንብረትን አስይዞ ስለመበደር የተቀመጠውን ሕግ መሠረት በማድረግ ሲሠራበት መቆየቱን ያክላሉ፡፡ ‹‹ወደ 2.6 ቢሊዮን ብር ብድር በዚህ መንገድ ተሰጥቷል፡፡ በጠለፋ ዋስትና ሲሰጥ ከነበረው ብድር በተሻለ ይህ ተደራሽና የመመለስ ዕድሉም የተሻለ መሆኑ ተረጋግጧል፤›› ሲሉም ነው አቶ አበባው የገለጹት፡፡

አቶ ቡልቻ በበኩላቸው አዲሱ አዋጅ የመሬት ዘርፍን በባለቤትነት ማን ይምራው የሚለውን ጉዳይ አሁንም ዕልባት አልሰጠም ይላሉ፡፡ አዋጁ ላይ ክልሎች የራሳቸውን የመሬት አስተዳዳሪ አካል ማቋቋም እንደሚችሉ መፈቀዱን በመጠቆም፣ ‹‹እኛ ግን ዘርፉን ሰብሰብ አድርጎ ወጥ በሆነ መንገድ የሚመራ አንድ አካል ያስፈልጋል ነው የምንለው፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በፌዴራል ደረጃ እስካሁንም እየተሠራበት ያለው፣ ‹‹በግብርና ሚኒስቴር ሥር ባለ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ዳይሬክቶሬት በተባለ የሥራ ክፍል ይህን ሰፊ ዘርፍ የመምራት አካሄድ ነው፤›› ይላሉ፡፡ በተበጣጠሰ ሁኔታ የግብርና ሚኒስቴር፣ የከተማ ልማት፣ የኢንዱስትሪና ሌሎችም ዘርፎች በየፊናቸው የመሬት ጉዳይ እንዲያገባቸው ተደርጎ መቀመጡ ዘርፉን ሲጎዳው እንደቆየም አመልክተዋል፡፡

አቶ ቡልቻ፣ ‹‹እንደ አገር የመሬት ዘርፍ ሚኒስቴር ቢመጣ ይፈለጋል፤›› ይላሉ፡፡ አሁን የገጠር መሬትን አስይዞ መበደር የሚያስችል ሕግ መቅረቡ በራሱ ትልቅ አመርታ እንደሆነ ያሰመሩበት አቶ ቡልቻ፣ መንግሥት የገጠሩን ብቻ ሳይሆን የከተማ መሬት አጠቃቀምን ባቀናጀ መንገድ ዘርፉን ለማሻሻል ዕቅድ አውጥቶ መንቀሳቀስ መጀመሩን ትልቅ እመርታ እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡

በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና አለመረጋገጡ ብዙ ጊዜ የመሬት ፖሊሲውና የመሬት አጠቃቀም ሕጉ በተጠያቂነት ይጠቀሳል፡፡ የመሬት አጠቃቀም ሕጉ ለባለይዞታው የሚሰጠው ነፃነት ውስን መሆኑ የመሬት ምርታማነትን ጎድቶታል ይባላል፡፡ ከመሬት ምርታማነት በዘለለ የመሬት ጥበቃ ለማድረግም ባለይዞታው እንደማይበረታታ ነው የሚነገረው፡፡ አዲሱን ሕግ በሚመለከት አስተያየት የሰጡ የመሬት ጉዳይ ባለሙያዎች፣ ሕጉ የተሻለ ነፃነት የሚሰጥ በመሆኑ በዚህ ዘርፍ ያለውን ክፍተት እንደሚሞላ ነው ተስፋቸውን የገለጹት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -