Friday, June 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ባለፉት 25 ዓመታት ባለን አቅም ሁሉ የተለያዩ አጀንዳዎችን ለመዳሰስ ሞክረናል›› የራስወርቅ አድማሴ (ዶ/ር)፣ የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

‹‹ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ›› በመባል የሚታወቀውን በኢትዮጵያ ታሪክ ከመንግሥትም ሆነ ከሌላ አካል ገለልተኛ ሆኖ የተቋቋመ ሐሳብ አመንጪ የጥናት ተቋም (ቲንክ ታንክ) ከመሠረቱት አንዱ መሆናቸውን በኩራት ይናገራሉ፡፡ የዛሬ አምስት ዓመታት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማስተማር ሙያቸው በጡረታ ሲገለሉ በተቋሙ በቋሚነትና በኃላፊነት ወደማገልገሉ እንደመጡም ያስረዳሉ፡፡ በድርጅቱ ውስጥ የቦርድ አባል፣ የአስተዳደር ኮሚቴ አባል፣ አጥኚና ተወያይም እየሆኑ ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለረዥም ዓመታት በሶሺዮሎጂ (ሥነ ማኅበረሰብ) ትምህርት ክፍል በመምህርነትና በትምህርት ክፍል ኃላፊነት ያገለገሉት የራስወርቅ አድማሴ (ዶ/ር)፣ ከጥናትና ከምርምር ሥራዎች ተነጥለው እንደማያውቁ ነው የሚገልጹት፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሚመሩትና 25ኛ ዓመት ምሥረታውን እያከበረ ያለው ‹‹ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ›› ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ያለፈባቸውን ዓመታት የሥራ ሒደት በተመለከተ ከሪፖርተር ጋር ሰፊ ቆይታ አድርገዋል፡፡ የተቋሙን የ25 ዓመታት ጉዞ መነሻ በማድረግ በኢትዮጵያ ያለውን የጥናት ተቋማት እንቅስቃሴ፣ እንዲሁም ለሚሠሩ ጥናቶች የሚሰጠውን አቀባበል በተመለከተ ዝርዝር ሐሳቦችን ያነሱበት ዮናስ አማረ ከእሳቸው ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ተቋማችሁ 25 ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ በእነዚህ ዓመታት ምን ዓይነት የጥናትና የኅትመት ሥራዎችን ስትሠሩ ቆያችሁ? ያለፉት 25 ዓመታት እንቅስቃሴያችሁ ስኬታማ ነበር ብላችሁ ታስባላችሁ?

የራስወርቅ (ዶ/ር)፡- ተቋማችንን ስናቋቁም ብዙ መነሻ ነበረን፡፡ ብዙ ጊዜ ጥናቶች የሚያካሂዱት በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ነበር፡፡ የዛሬ 25 ዓመታት ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከሞላ ጎደል ብቸኛው ትልቁ ዩኒቨርሲቲ ነበር፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ብዙ ስንሠራ የቆየን ሰዎች ተሰባስበን ለምን የጥናት ተቋም አንፈጥርም በሚል ነበር ምሥረታውን የጀመርነው፡፡ ብዙዎቻችን በዩኒቨርሲቲ ስናስተምርና ስናጠና ብንቆይም፣ ነገር ግን ጥናቶቻችን የመጻሕፍት መደርደሪያ ከማሞቅ አላለፉም የሚል ቁጭት ነበረን፡፡ ‹ጥናቶቻችን ሳይታዩ ይታለፋሉ› የሚል ስሜት ነበር ውስጣችን፡፡ ብዙ ጊዜ ደግሞ በዩኒቨርሲቲዎች ያለው የአሠራር ጥልፍልፎሽና ቢሮክራሲም የጥናት ሥራዎችን ለመሥራት ችግር ነበር፡፡ ፋይናንስ ማግኘት ችግር ብቻ ሳይሆን፣ ለጥናት ወደ መስክ ስንሠማራ ፈቃድ ያለማግኘት ችግሮችም ያጋጥሙን ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ ወጣ ብለን እስኪ በነፃነት እንሥራ የሚለው ስሜት በውስጣችን አደገ፡፡ ወጣ ብሎ ከቢሮክራሲ ነፃ ሆኖ በነፃነት ከመሥራት በተጨማሪ፣ አገር የሚጠቅም ተፅዕኖ የሚፈጥር ጥናት ለማበርከት ዕድል እንደሚፈጥርልን በማመን ነው ተቋሙን ወደ መመሥረቱ የገባነው፡፡ ጥናት ከማድረግ በተጨማሪ አባላት ፈጥረንና ሰዎችን አሰባስበን ጥናታዊ ውይይት ማድረግም እንችላለን በሚል ምኞት ነው ወደ እዚያ የተገባው፡፡

የተቋማችን ዓላማ ዛሬም ድረስ ጥናት ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ በጥናት ላይ የተመሠረተ ውይይት ማድረግ ነው፡፡ አጥኚውንም ተጠኚውንም በአንድ አዳራሽ አሰባስበን ሚዲያዎችና የሚመለከታቸው አካላትን ጋብዘን ውይይት እናደርጋለን፡፡ በዚህ ውይይትም ጥናቱን እናዳብረዋለን፡፡ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ውይይት በማካሄድ ጥናቱ ተደራሽ እንዲሆን ከማድረግ በዘለለ፣ የሠለጠነ የውይይት ባህል እንዲገነባ ጎን ለጎን እንሠራለን፡፡ ሰዎች ተቃራኒ ሐሳብ ቢኖራቸውም፣ አንድ ላይ ሆነው በሠለጠነ ውይይት ልዩነቶቻቸው ለማጥበብ እንዲችሉ ጥረት እናደርጋለን፡፡ የሚነሱ ሐሳቦች በዚህ መንገድ ከግራም ከቀኝም በሚቀርቡ አስተያየቶች በደንብ ይፈተሻሉ፡፡ በዚያም ጠቃሚ ውጤት ይመጣል ብለን ነው ይህንን የጀመርነው፡፡

ሪፖርተር፡- ጥናቶች ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲያመጡ የምትሠሩት ሥራ ምን ይመስላል?

የራስወርቅ (ዶ/ር)፡- በእንግሊዝኛው ‹‹ሀይበሪ ታወር›› እንደሚሉት እኛ መደላድል ላይ ተነጥለን ቆመን ሂስ ብቻ በማዝነብ መወሰን የለብንም ብለን ነው የተነሳነው፡፡ ከመንግሥት ጋር መገናኘት አለብን፡፡ ከተቃዋሚዎች ጋር መገናኘት አለብን፡፡ ከሕዝብ ጋር መገናኘት አለብን ብለን ነው የተነሳነው፡፡ ከመጀመሪያው ጀምሮ ጥናቶቻችን በሚቀርቡባቸው መድረኮች ሁሉ በተቻለ መጠን ሁሉንም ወገን አካታች ሆነን ነው ለማሳተፍ ስንሞክር የቆየነው፡፡ የመጀመሪያውን የጥናት መድረካችንን በመሬት ጉዳይ ላይ ስናካሂድ ከመንግሥት በኩል የተገኙት አቶ ማንያዘዋል የሚባሉ ምክትል ሚኒስትር ነበሩ፡፡ ከዚያ በኋላ በነበሩ የጥናት መድረኮቻችንም ቢሆን ብዙ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጭምር ሲካፈሉ ቆይተዋል፡፡ ይህንን ሥራ የጀመርነው የደርግ መንግሥት ከሥልጣን ከወረደ ገና ብዙም ሳይርቅ ነበር፡፡ የመናገርና የመጻፍ መብቶች በተወሰነ ደረጃ ለቀቅ ያሉበት ጊዜ ነበር፡፡ የመንግሥት ሰዎች በእኛ መድረኮች እየመጡ የውይይት መነሻ ጽሑፎችን በማቅረብ ጭምር ይሳተፉም ነበር፡፡ እኛ የመገናኛ ድልድይ ሆነን ነው ሥራውን የጀመርነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሐሳብ አመንጪ (ቲንክ ታንክ) ተቋም መመሥረት በሌላው አገር አዲስ ባይሆንም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተለመደ መሆኑ ይታመናል፡፡ ከዚህ አንፃር ሥራው ሲጀመር የገጠማችሁ ችግር የለም?

የራስወርቅ (ዶ/ር)፡- በመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ከባድ ችግር ነበረብን፡፡ የገንዘብና የቁሳቁስ ችግር ነበረብን፡፡ በግለሰቦች ፈቃድ፣ ከሰዎች ቤት በሚመጣ ቁሳቁስ ነበር ስንገለገል የቆየነው፡፡ ሁለት ሰዎች በተለይ ወ/ሮ ዘነበወርቅ ታደሰና አቶ ደሳለኝ ራህመቶ በነፃ አገልግለዋል፡፡ ለስታፎች የሚከፈል ገንዘብ ሁሉ ችግር ነበር፡፡ አንድ ላይብረሪያን ጸሐፊ፣ አንድ ደጋፊ ስታፍ ካልሆነ በስተቀር መደበኛ ሠራተኛ አልነበረንም፡፡ ከራስ ዓምባ ሆቴል በታች ሁለት ክፍሎች ባላት በአነስተኛ የኪራይ ቤት ነበር ሥራው የተጀመረው፡፡ ዩኒቨርሲቲ የምናስተምረው በትርፍ ሰዓታችን የአስተዳደር ሥራዎችን ተከፋፍለን በመሥራት ነው የተጀመረው፡፡ 

የመጀመሪያው ዕርዳታ ሰጪያችን ‹‹ፍሬድሪክ ኤበርት ስቲፍተንግ›› የተባለው የጀርመን ፋውንዴሽን ነበር፡፡ አንዳንድ የጥናት ውይይቶችን ለማድረግ ትልቅ ዕገዛ አደረገልን፡፡ የምንሠራቸውን ጥናቶችና ዓውደ ጥናቶች ወደ ሕዝብ የምናደርሰውም በራሳችን ኅትመቶችን በማተም ነው፡፡ በሬዲዮም ሥራዎቻችንን እናስተዋውቃለን፡፡ በሒደት የራሳችን ላይብራሪ አበጀን፡፡ በአገር ጉዳይና በሌላውም እናግዛችሁ የሚሉ ምሁራን መጡ፡፡ በተለይ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን በሰፊው አብረውን ይሠሩ ጀመር፡፡ በቀጣይ ደግሞ ዌብሳይት ገነባን፡፡ በዚህ አሁንም ለተጠቃሚዎች ምቹ ሆኖ በተገነባ ዌብሳይትም የሠራናቸው የጥናት ውጤቶች እንዲጫኑ በማድረግ ለሕዝብ ተደራሽ እንዲሆኑ አስችለናል፡፡ የጥናት ውጤቶቻችንን ማንም ሰው ከዌብሳይታችን ማግኘትና መጠቀም ይችላል፡፡

አንዳንድ የጥናት ሥራዎቻችን ሰፊና ዳጎስ ያሉ ሊሆኑ ይችላል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ጥናቶች ለፖሊሲ አውጪዎች እንዲደርሱ የሚፈለጉ ይሆናል፡፡ በዚህ ጊዜ ግን ሙሉውን ሰፊ ጥናት ለማንበብና ለመረዳት ጊዜም ሆነ ጉልበቱ ላይኖራቸው ይችላል፡፡ ስለዚህ የጥናቱ ዋና ፍሬ ነገር እንዲደርሳቸው በማሰብ ባለአራት ገጽ ምጥን የፖሊሲ ፍሬ ሐሳብ (የፖሊሲ ብሪፍ) ኅትመቶችን እያተምን ማቅረብ ጀምረናል፡፡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እነዚህን የፖሊሲ ፍሬ ሐሳብ ኅትመቶች በማድረስ ላይ እንገኛለን፡፡ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር የመግባቢያ ስምምነትም በተጨማሪ ተፈራርመናል፡፡

እኛ ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ጥናቶቻችን ለፖሊሲ አውጪዎች እንዲደርሱ በሩን ስናንኳኳ ቆይተናል፡፡ በኢትዮጵያ እንደሚታወቀው የመንግሥትና የመንግሥት የአካሄድ ለውጦች ተከስተዋል፡፡ እኛ እንግዲህ ሐሳብ አመንጪ (ቲንክ ታንክ) ብንሆንም የሲቪክ ማኅበረሰቡ አካል ተደርገን ነው የምንታየው፡፡ ሲቪክ ማኅበረሰቡን በሚመለከት መንግሥት የተከተላቸው አቋሞች በየጊዜው ተለዋዋጭ ነበሩ፡፡ በተለይ በ2001 ዓ.ም. አካባቢ አፋኝ የሚባል የሲቪክ ማኅበረሰቡን የሚመለከት አዋጅ ታውጆ ነበር፡፡ መንግሥት በሲቪክ ማኅበራት ላይ የተለየ ትኩረት ያደርግም ነበር፡፡ በየጊዜው ሲቪክ ማኅበራት ሲዘጉና ሲተኩ የእኛ ድርጅት ግን ውጤቱ የሚታይ ስለነበር ምንም ሳይሆን ያን ፈታኝ ጊዜ ማለፍ ችሏል፡፡ 

ከመጀመሪያው መናገር የነበረብኝ የእኛ ድርጅት ከማንም ወገንተኝነት ነፃ የሆነ ድርጅት ነው፡፡ የመንግሥት አካል አይደለም፣ የማንም የፖለቲካ ድርጅት አካል አይደለም፣ የማንም የሃይማኖት ተቋም ወይ ሌላ ቡድን አካል አይደለም፡፡ ድርጅቱ ለትርፍ አይደለም የተቋቋመው፡፡ ድርጅቱ የተመሠረተው አባላትን አሰባስቦ ነው፡፡ ብዙዎቹ ከትምህርት ተቋማት የመጡ ወደ 40 አባላት አሉት፡፡ እነሱ የሚሳተፉበት ዓመታዊ ጉባዔ ነው ሁሉንም ነገር ወሳኙ፡፡ እነሱ የሚመርጡት ሰባት አባላት ያሉት ቦርድ በጠቅላላ ጉባዔው በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት ድርጅቱን ያስተዳድራል፡፡ ይህችን ቦታ ሠርቶ የራሱን ዋና ጽሕፈት ቤት የገነባው ሁሌም በረጂዎችና በገንዘብ ሰጪዎች ላይ ጥገኛ ላለመሆንና ነፃነቱን ለማረጋገጥ ሲል ነው፡፡ ተቋሙ ሥራውን በተመለከተም ሆነ ንብረቱን ከማንም ጥገኝነት ተላቆ በራሱ እንዲችል ለማድረግ ብዙ ጥረት አድርጓል፡፡ ወደፊትም ቢሆን ድርጅቱ ሥራውን ቢያቆም ንብረቱ ዕዳ ካለበት ተከፍሎ ሌላው በሙሉ መሰል ሥራዎች ለሚሠራ ድርጅት እንዲሰጥ የሚያደርግ መተዳደሪያ ደንብ ነው ያለው፡፡ ሥራውን ቢያቆምም ሆነ ቢዘጋ ለአባላቱ የሚያወርሰው አንዳችም ንብረት የሌለው የሕዝብና የአገር ንብረት ሆኖ እንዲሠራ የተደረገ ድርጅት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከፖሊሲ ተቋማት ጋር ተባብሮ የመሥራት ጥረታችሁ ምን ይመስላል?

የራስወርቅ (ዶ/ር)፡- ከተወካዮች ምክር ቤት ጋር ሞክረናል፡፡ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ጋር ታስቦ ነበር፣ ብዙም አልሄዱበትም፡፡ ሆኖም ጥናትም ሆነ የምንሠራው ሥራ ሲፈለግ ከማንም ጋር ተባብሮ ለመሥራት ዝግጁ ነን፡፡ ሌላው አንድ ጥናት ለማጥናት ስንነሳ የፌደራልም ሆነ የክልል መንግሥታት ፈቃድ ያስፈልጋል፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ረገድ ብዙም ችግር አልገጠመንም፡፡ አብረውን የሠሩ በዩኒቨርሲቲዎች ያስተማርናቸው ተማሪዎችና በተለያዩ አጋጣሚዎች የምናውቃቸው ሰዎች በብዙ የመንግሥት ሥራ ኃላፊነቶች ላይ ስላሉ ይተባበሩናል፡፡ ድርጅታችን ጥሩ ስም ስለገነባ በተለያዩ የአገር ቤት ቋንቋዎች መሥራቱና በሬዲዮ ዝግጅቶች ሥራዎቹን ማቅረቡ ሁሉ በጎ ገጽታ ለማግኘትና ቀና ትብብር እንዲያገኝ ረድቶታል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን ጉዳይ አታጥኑት፣ ተውት፣ እሱ ቀይ መስመር ነው የሚል ነገር አልገጠማችሁም? ለምሳሌ የኤርትራን ሪፈረንደም፣ የኢትዮ-ኤርትራን ጦርነት፣ የባህር በር የታጣበትን አጋጣሚ፣ የፌዴራላዊ ሥርዓቱን፣ ሕገ መንግሥቱና የብሔር ፖለቲካውን የመሳሰሉ አወዛጋቢ ጉዳዮችን አትነካኩ የሚል ግፊት አልገጠማችሁም?

የራስወርቅ (ዶ/ር)፡- አርዕስቱን ሳይሆን ለምሳሌ የወደብ ነገር አታንሱ የሚል አስተሳሰብ በኢሕአዴግ የመጀመሪያ ዓመታት ይታይ ነበር፡፡ እነ አቶ ስብሃት ይህንን በተለያዩ ቃለ መጠይቆች በግልጽ ሲናገሩት ነበር፡፡ አንዳንድ ጉዳዮች ላይ ጥናት እንዲካሄድ ያለመፈለግ ዝንባሌ በመንግሥት ወገን ነበር፡፡ ለምሳሌ ስለወደብ ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግሥት ግድ የለኝም ማለት ብቻ ሳይሆን፣ መሄዱ ጥሩ ነው የሚል ዓይነት አቋም ሁሉ ያንፀባርቅ ነበር፡፡ ስለዚህ ከዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብም ሆነ ከአካዴሚው ማኅበረሰብ ጋር ግጭት ነበር፡፡ በዚህ ረገድ ሆድና ጀርባ ሆነው ነበር፡፡ ነገር ግን እኛም ብንሆን አንዳንድ ስሜት ቀስቃሽ የነበሩ ነገሮችን እናጥና ብለን አንጠይቅም ነበር፡፡ ለምሳሌ ስለአሰብ እናጥና ብለን የማይሆን ጥያቄ አንጠይቅም ነበር፡፡ እናጥና ቢባልስ ምንድነው የምናጠናው? ነገር ግን በአገራዊ ጉዳዮች አጠቃላይ ፖለቲካዊ ትንታኔ የሚሰጡ ጥናቶችን ስናደርግ ቆይተናል፡፡

ለምሳሌ በቅርቡ በመጣው የፖለቲካ ሪፎርም ማግሥት በሦስት አገራዊ ጉዳዮች ላይ ጥናታዊ ውይይቶች አድርገን በኅትመት አቅርበናል፡፡ በጋዜጣና በተለያዩ ሚዲያዎችም እንዲዘገቡ አድርገናል፡፡ አንዱ ሕግና ደንብን የተመለከቱ ተቋማዊ ጉዳዮች የቀረቡበት ነበር፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ኢኮኖሚውን በሚመለከት የቀረቡ ናቸው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ የውጭ ግንኙነትን የተመለከቱ ነበሩ፡፡ በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ምሁራንን እያመጣን ጥናታዊ ጽሑፎችን አቅርበው እንዲከራከሩ አድርገናል፡፡ በመድረክ ላይ ያቀረቧቸው ጥናታዊ ውይይቶችም ታትመው እንዲሠራጩ አድርገናል፡፡ በሕግ ዘርፍ ሕገ መንግሥቱን በተመለከተ ክርክር የተደረገ ሲሆን፣ ‹‹ሕገ መንግሥቱ ይቀየር›› ወይም ‹‹ሕገ መንግሥቱ አይቀየር›› በሚለው ላይ ሰዎች እንዲከራከሩ አድርገናል፡፡ የፓርቲ ፖለቲካን በሚመለከትም እንዲሁ ሁለት ሰዎች የተከራከሩ ሲሆን ውይይቱ ታትሟል፡፡ በኢኮኖሚው ዘርፍም ቢሆን ዓለማየሁ ገዳ (ፕሮፌሰር) እና ቴዎድሮስ መኮንን (ዶ/ር)ን ጋብዘን አከራክረናል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ችግር መዋቅራዊ ነው? የፋይናንስ ችግር ነው? ዕዳና ብድር ነው?›› የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተው ምሁራዊ ክርክር ተደርጓል፡፡

በሌላ በኩል ከኢኮኖሚ ጋር በተያያዘ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች መሸጥ አለባቸው? የለባቸውም? በሚለው ጉዳይ ላይም ምሁራዊ ውይይት አድርገናል፡፡ በጊዜው ይህ ጉዳይ ጎልቶ የተነሳበት ወቅት ሲሆን፣ በኢኮኖሚ ሪፎርሙ ውስጥም ይሸጡ የሚለው ሐሳብ ሚዛን ደፍቶ ነበር፡፡ በገንዘብ ሚኒስቴር የተጠቆሙትን ከፍተኛ የኢኮኖሚ አማካሪውን ብሩክ ታዬን (ዶ/ር)፣ እንዲሁም ከግል ዘርፉ አቶ ክቡር ገናን ጋብዘን በቴሌኮም ተቋም መሸጥ/አለመሸጥ ጉዳይ ላይ እንዲከራከሩ አድርገናል፡፡ በዚያ ጥናታዊ መድረክ ላይ አሁን በሕይወት የሌሉት አቶ ተረፈ የራስወርቅ የተባሉ ኢትዮ ቴሌኮምን ከመሠረቱ አንዱ የነበሩና በዓለም አቀፉ የቴሌኮም ድርጅት ውስጥ ሆነው ከ90 ያላነሱ አገሮችን ልምድ የተመለከቱ ሰው ገንቢ ሐሳብ አበርክተዋል፡፡ እናንተ ኢትዮጵያውያን ለማንም አናስነካም ብላችሁ በራሳችሁ አቅም የራሳችሁን ትርፋማ የቴሌኮም ተቋም ገነባችሁ ብለው ሌሎች አገሮች በኢትዮጵያውያን እንደሚደነቁ ልምዳቸውን አካፍለዋል፡፡

በአንድ ወገን ከብሔራዊ ጥቅምም ሆነ ከብሔራዊ ደኅንነት አንፃር ኢትዮ ቴሌኮም ለውጭ መሸጥ የለበትም በሚል፣ በተቃራኒው ደግሞ ሊሸጥ ይገባል በሚል የተካሄደው ክርክር እጅግ ገንቢ ውጤት የተገኘበት ነበር፡፡ በአንድ ወቅት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማሪያም ደሳለኝ ጭምር ኢትዮ ቴሌኮም ትርፋማ መሆኑንና ከእሱ በተገኘ ገቢ የባቡር ሐዲድ እንደሚገነባ ተናግረው ነበር፡፡ ‹‹ትርፋማ ከሆነ ድርጅቱ ለምን ይሸጣል?›› የሚለው ጥያቄ በክርክሩ ወቅት ጎልቶ ተነስቷል፡፡ ሌሎች ተመሳሳይ የውጭ ድርጅቶች ይግቡ/አይግቡ የሚለው ጉዳይም ጎን ለጎን በደንብ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ ይህ ሁሉ ምሁራዊ ክርክር በሰላም፣ በመተቃቀፍና በወዳጅነት መንፈስ ነበር የተካሄደው፡፡ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎች ላይም ተመሳሳይ ውጤታማ ውይይት ተደርጓል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም በዓባይ ጂኦ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ጥናታዊ መድረክ ተካሂዷል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮ ሱዳን ድንበር ውዝግብን የመሳሰሉ አከራካሪ አጀንዳዎችን ያጠናችሁበት አጋጣሚ አለ?

የራስወርቅ (ዶ/ር)፡- እንግዲህ ሁሉንም ዓይነት ጉዳይ መሸፈን የምንችልበት አቅም የለም፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት ባለን አቅም ሁሉ የተለያዩ አጀንዳዎችን ለመዳሰስ ሞክረናል፡፡ የኢትዮ ሱዳን ድንበር ያኔ ጎልቶ የወጣበት ሁኔታም አልነበረም፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የጥናት ተቋማት (ቲንክ ታንኮች) ሚና ውስንነት ይታይበታል ይባላል፡፡ ቁጥራቸው ካለመብዛቱ ጀምሮ የሚሠሩት የጥናት ውጤትም በቂ አለመሆኑ ይነገራል፡፡

የራስወርቅ (ዶ/ር)፡- ሚናቸው ውስን ነው የሚባለው እኮ መጀመሪያ እነሱ ራሳቸው ሲኖሩ ነው፡፡ ገለልተኛ የጥናት ተቋማት መቼ ነው እዚህ አገር የመጡት? በእኛ አስተያየት እኛ የመጀመሪያዎቹ ነፃ የጥናት ተቋም ነን፡፡ የዛሬ 25 ዓመት ነው ነፃ ቲንክ ታንክ የተፈጠረው፡፡

ሪፖርተር፡- ቁጥራቸው ለምን አልበዛም?

የራስወርቅ (ዶ/ር)፡- ደሃ አገር እኮ ነን፡፡ እልም ያልን ደሃ እኮ ነን፡፡ የዛሬ 25 ዓመት ደግሞ የባሰብን ደሃ ነበርን፡፡ የዛሬ 50 ዓመታት ደግሞ የከፋ ድህነት ውስጥ ነበርን፡፡ የዛሬ 100 ዓመት ደግሞ የሚለበስ ልብስ የሚቸግረን የታረዝን ሕዝቦች ነበርን፡፡ የተማሩ ሰዎች ቁጥር ያኔ 20 ወይም 30 የሚባል ነበር፡፡ ከየት ነው የተነሳነው የሚለውን ሁል ጊዜ ማስታወስ አለብን፡፡ እኔ በተማሪዎች ንቅናቄ ወቅት ተሳታፊ ስለነበርኩ የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ይወቀስባቸው የነበሩ ነገሮችን አስታውሳለሁ፡፡ ያን ጊዜ ይህንን ለምን አላደረገም እያልን መንግሥትን እንወቅስ ነበር፡፡ ነገር ግን ወራሪው ፋሺስት ጣሊያን ከኢትዮጵያ የወጣው በ1933 ዓ.ም. ነው፡፡ ከ1933 ዓ.ም. ጀምሮ በእነ መንግሥቱ ንዋይ እስከተሞከረው የ1953 ዓ.ም. መፈንቅለ መንግሥት ወቅት ድረስ 20 ዓመታት ነው ያለፈው፡፡ በእነዚህ 20 ዓመታት ውስጥ ግን ስንት መንገድ እንደተሠራ አንመለከትም ነበር፡፡ አንደኛ ደረጃ (ኤለመንተሪ) ትምህርት ቤት ብቻ የነበራት አገር ኮሌጅና ዩኒቨርሲቲ ድረስ መድረሷን አናስተውልም ነበር፡፡ በሁለተኛ ደረጃ (ሃይስኩል) ትምህርት እንኳ ዕፍኝ የማይሞሉ የመሣፍንት ልጆች ግብፅ እስክንድሪያ እየተላኩ ነበር የሚማሩት እኮ፡፡

ከጣሊያን ወረራ ማክተም እስከ 1953 ዓ.ም. በነበሩ ዓመታት በተደረገ ፈጣን የልማት ጉዞ በርካታ ሃይስኩሎች፣ ተግባረ ዕድ፣ ሚሊታሪ አካዴሚ፣ አየር ኃይል አካዴሚ፣ አውራ ጎዳና፣ ቴሌኮሙዩኒኬሽን፣ ባንክና ሌላም ብዙ ነገሮች ተሠርተዋል፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴ ልጅ ሳሉ እሳቸውና 13 የሚሆኑ ልጆች የቤተ መንግሥት ምንጣፍ ላይ ተቀምጠው ነበር ዘመናዊ ትምህርት መሰጠት የተጀመረው፡፡ እሳቸው ከሥልጣን ሲወገዱ ግን ሁለት ሚሊዮን የኢትዮጵያ ልጆች በየተማሪ ቤቱ በመላ አገሪቱ ትምህርት ይከታተሉ ነበር፡፡

ይህ ሁሉ ለውጥ በአገሪቱ መጥቶም ግን ዕድገቱ በፍጥነት አልሄደም በሚል የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለውጥ እንጠይቅ ነበር፡፡ ያኔ በወጣትነት ‹‹ልማት የለም! የንጉሡ መንግሥት ይውደም!›› ብንልም አሁን ላይ ሆኜ ተመልሼ ሳየው ግን ሁኔታው ሌላ ነገር ሆኖ ነው የሚታየኝ፡፡ ለዚህ ማነው ተጠያቂው ለሚለው እኛ አይደለንም፡፡ የቀደመው ትውልድ የተሠራውን ነገር አልነገረንም፣ አልጻፈልንም ወይም በቅጡ አላሳወቀንም፡፡ የእኛ የመረጃ ምንጭ ታላላቆቻችን ሳይሆኑ ፈረንጅ ጸሐፊያን ነበሩ፡፡ ተቺ የሆኑ እንደ ‹‹ሪቻርድ ግሪንፊልድ›› ያሉ የውጭ ጸሐፍት እንዲህ ነው ብለው የሚጽፉትን እያነበብን ነበር አብዮታዊ ለውጥ ካልመጣ ስንል የነበረው፡፡ በጊዜው የኢትዮጵያ መንግሥት ተጨባጩን መረጃ ከማቅረብ ይልቅ፣ አታንብቡ እያለ የውጭ ጽሑፎችን ያቃጥልና ይቆልፍባቸው ስለነበር ለእኛ የበለጠ ጉጉት የሚጨምር ሆነ፡፡ የውጭ ጸሐፊያንን ሂስ ከማንበብ በዘለለ ለትምህርት ወደ ውጭ አገሮች በመሄድ ሌሎች አገሮች የደረሱበትን ቦታ ስናይ፣ ‹‹ኢትዮጵያ አብዮታዊ ለውጥ ያስፈልጋታል›› የሚል ስሜትን የሚያሳድር ነበር፡፡ የነበረውን ማሻሻል ይቻላል ከሚለው ይልቅ፣ ያለውን አፍርሶ መገንባት ነው የሚሻለው የሚለው ስሜት በወጣቶች ዘንድ የሰረፀው በዚህ መንገድ ነበር፡፡

አሁን ላይ ሆኜ እኔ 20 ዓመታት ምን ያህል አጭር ጊዜ እንደሆኑ በደንብ አውቃለሁ፡፡ ዕድሜዬ ስለገፋ ያለፉት 20 እና 30 ዓመታት እንዴት ሽው ብለው እንዳለፉ በደንብ እገነዘባለሁ፡፡ ያኔ ወጣት ሆኜ ግን ስለ20 ዓመት የማስበው ዛሬ ላይ ስለ2,000 ዓመት እንደማስበው የረዘመ ነበር የሚሆንብኝ፡፡ ዘጠነኛ ክፍል ሆነህ የኮሌጅ ተማሪዎችን ስታይ የሚፈጠርብህ ስሜትን ማስተያየት ትችላለህ፡፡ ከ25 ዓመታት በፊት ወይም የዛሬ 32 ዓመት ደርግ ነበር፡፡ በደርግ መንግሥት ወቅት ሁሉም ነገር በመንግሥት ሥር እንዲወድቅ ተደርጓል፡፡ ሁሉን ነገር የሚመራው ካድሬው ነው፡፡ ቢሆንም ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የተወሰነ ነፃነት ነበረ፡፡ ጥናት በደንብ ይጠና ነበር፡፡ ስለመሬት መከላት፣ ስለደን መጨፍጨፍ፣ ስለጤና ሁኔታና ሌላም ጉዳይ እናጠና ነበር፡፡ የደርግ ካድሬዎች መጥተው ይህን ነገር አታጥና ብለውኛል የሚል ካለ እሱ እውነተኛ አይደለም፡፡ እኔም አጠና ነበር፣ ነገር ግን ይህንን አታጥና ተብዬ አላውቅም፡፡ በክፍል ውስጥ ስታስተምር ይህንን ዓይነት ነገር አትናገር ብለውኝም አያውቁም፡፡ እኔ በራሴ ራሴን ሳንሱር ላደርግ እችላለሁ፡፡ ዝም ብዬ እያጠናሁ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማሪያምን አልሳደብም፡፡ ነገር ግን በዚያ ወቅትም ቢሆን ስናስተምርና ስናጠና ጣልቃ እየገቡ እንዲህ አድርጉ ይሉናል ማለት አይደለም፡፡

ከደርግ በኋላ የመጣው ኢሕአዴግ ዩኒቨርሲቲውን የበለጠ ለመቆጣጠር ሞክሯል፡፡ እነ አቶ መለስ ዩኒቨርሲቲውን ጥለው ጫካ የገቡ ቢሆንም፣ ነገር ግን ወደ ሥልጣን ሲመጡ ሁሉንም ነገር ለመቆጣጠር ሞክረዋል፡፡ በተለይ በባህር በር፣ በብሔር ፌዴራሊዝሙና በማይፈልጉት ርዕሰ ጉዳይ ላይ እንዳይጠና ለማፈን ፈለጉ፡፡ የበለጠ ነፃ ሆኖ ለማጥናት በማሰብ ከዩኒቨርሲቲ ውጪ ‹‹ኤፍኤስኤስ››ን መሠረትን፡፡ በሒደት እንዳየነው ከሆነ ግን ስለብሔር ፌዴራሊዝሙም ሆነ ስለሌሎች አወዛጋቢ ጉዳዮች ማጥናት የሚቻልበት ዕድል ነበረ፡፡ የብሔር ፌዴራል ሥርዓት ጠቀመ፣ ጎዳ የሚለው መጠናት የሚችል ጉዳይ ነበር፡፡

በቅርቡ ለምሳሌ ሮጦ ስላመለጠውና በሰፊው መነሳት ስለጀመረው የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጥያቄ ላይ ጥናት አድርገናል፡፡ እስካሁንም እየተነሳ የቀጠለው የወረዳ፣ የዞን፣ የክልልነትና ከዚያ ጋር የተያያዘውን ጥያቄ በተመለከተ ምን ቢደረግ ይሻላል ለሚለው በአራት ሰዎች ጥናታዊ ውይይቶችን አቅርበናል፡፡ ሕገ መንግሥቱ በዚህ ጉዳይ ላይ የጠየቀ ይሰጠዋል ነው የሚለው፡፡ አንድ ማኅበረሰብ 200 ሺሕ ሆነም ከሚሊዮን በላይ ቢበዛ ልሁን ብሎ የጠየቀው የማንነትና የአስተዳደር ወሰን እንደሚሰጠው ያስቀምጣል፡፡ የጠየቁ ሁሉ በወረዳ፣ በዞን፣ በክልል እንዲደራጁ የሚፈቅድ ሕገ መንግሥታዊ መብት አለ፡፡ በሌሎች አገሮች ሕገ መንግሥቶች ይህ ጉዳይ እንዴት ይወሰናል የሚለውን አጥኚዎቹ በደንብ ፈትሸውታል፡፡ አስናቀ ከፋለ (ዶ/ር)፣ አቶ አንዳርጋቸው አሰግድ፣ ገብሬ ኢንቲሶ (ፕሮፌሰር)፣ እንዲሁም ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥናት ተቋም አንድ ሰው በመጋበዝ በዚህ ጉዳይ ላይ የሌሎች አገሮች ልምዶችን የቀሰመ ጠቃሚ ጥናቶቻቸውን አቅርበዋል፡፡

በኢኮኖሚ ሪፎርሙ ታስቦ የነበረውን በፋይናንስ ተቋማት ለውጭ ገበያ ክፍት መደረግ ጉዳይ ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ መድረኮችንም አዘጋጅተናል፡፡ የፋይናንስ ተቋሞቻችንን የግልና የመንግሥት፣ እንዲሁም ባንኮችንና ኢንሹራንሶችን ባካተተ ሁኔታ የውይይት መድረክ አዘጋጀን፡፡ የዘርፉን ገበያ ለውጭ ኢንቨስትመንት መክፈቻው ጊዜ አሁን ነው ወይ በሚለው ጉዳይ ላይ ጠቃሚ ነጥቦች የተነሱበት መድረክ ነበር፡፡ የራሳችንን የቤት ሥራ ሳንሠራ ዘርፉ ቢከፈት ሊፈጠር የሚችለውን ምስቅልቅል በደንብ የፈተሸ ነበር፡፡ ዘርፉ ክፍት ቢሆን ምን ሊመጣ ይችላል በሚለው ጉዳይ ላይ ጠንካራ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

ሪፖርተር፡- የጥናት ተቋማት (ቲንክ ታንኮች) በአገራችን መኖራቸው ምን ለውጥ አመጣ?

የራስወርቅ (ዶ/ር)፡- በዚህ በ25ኛ ዓመት በዓላችን ላይ ካዘጋጀናቸው ጥናታዊ የውይይት አጀንዳዎች አንዱ የጥናት ተቋማት (ቲንክ ታንኮች) የልማት አስተዋጽኦ በኢትዮጵያ የሚለው ይገኝበታል፡፡ በዚህ ለሁለት ሰዓታት በሚካሄድ የፓናል ውይይት ላይ አራት ‹‹ቲንክ ታንክ›› ወይም ‹‹ቲንክ ታንክ›› መሰል ተቋማት ናቸው የሚሳተፉት፡፡ ‹‹ቲንክ ታንክ›› መሰሎች ያልኩት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ከተሳታፊዎቹ አንዱ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማኅበር ይገኝበታል፡፡ ይህ ተቋም የሙያ ማኅበር ቢሆንም፣ የ‹‹ቲንክ ታንክ›› ሥራ ስለሚሠራ ነው በዚህ ዘርፍ ስሙ የሚጠራው፡፡ ሁለተኛው ተሳታፊ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ ነው፡፡ እሱም የሙያ ማኅበር ቢሆንም የ‹‹ቲንክ ታንክ›› ሥራ ስለሚሠራ ነው በዚህ ውስጥ የተካተተው፡፡ ሦስተኛው በመንግሥት የሚደገፈው በበየነ ጴጥሮስ (ፕሮፌሰር) የሚመራው የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ነው፡፡ አራተኛው ግን በእኛ እምነት ብቸኛው፣ ነፃ ሆኖ የተመሠረተው የእኛው ‹‹ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ›› ነው፡፡ ከመንግሥት ነፃ የሆነ ብቻ ሳይሆን የሙያ ማኅበር ያልሆነ፣ ሐኪሙን፣ የሕግ ምሁሩን፣ ሶሺዮሎጂስቱን፣ ኢኮኖሚስቱንና ሁሉንም ዓይነት የሙያ ባለቤት በአባልነት ያቀፈው ‹‹ቲንክ ታንክ›› ‹‹ኤፍኤስኤስ›› ነው፡፡ በዚህ መድረክ የሚቀርበው የአራቱ ተቋማት ጥናታዊ ውይይት የ‹‹ቲንክ ታንኮች››ን ሚና በኢትዮጵያ መልስ የሚሰጥ ነው ብለን እንገምታለን፡፡

ሪፖርተር፡- ከአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር በጋራ የምትሠሩበት ሁኔታ አለ?

የራስወርቅ (ዶ/ር)፡- እኛ ግብዓት ነው የምንሰጠው፡፡ እኛ የጥናት ተቋም ነን፡፡ ጥናቶቻችንን ደግሞ ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽንም ሆነ ለሚፈልግ ለማንኛውም ወገን ማቅረብ ነው ሥራችን፡፡ ጥናቶቻችን ደግሞ በግልጽ በዌብሳይታችንና በኅትመቶቻችን የሚቀርቡ ናቸው፡፡ ለመንግሥትም ይሁን በውጭ አገር ላለ፣ ለሚዲያም ሆነ ለሌላ ጥናታችንን ለሚፈልግ ወገን ጥናቶቻችን ክፍት ናቸው፡፡ በቅርቡ ለምሳሌ ‹‹ኢትዮጵያ ወዴት›› በሚል የ‹‹ሴናሪዮ›› ትንተና የያዘ ጥናታዊ መድረክ አዘጋጅተን ነበር፡፡ በዚያ ላይ እንዲካፈሉ የኮሚሽኑን አመራሮች ጋብዘን ነበር፡፡ አልተመቻቸውም መሰለኝ አልተገኙልንም፡፡ አሁንም ቢሆን በ25ኛ ዓመት በዓላችን ጥናታዊ መድረክ ላይ እንዲካፈሉ ጋብዘናቸዋል፣ ይገኛሉም ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ከዚህ ውጪ ግን አዲስ ጥናት እናዘጋጅላችሁ፣ ገንዘብ ስጡን ወይም ደግፉን አንልም፡፡ ስናጠና ኖረናል፡፡ ካቀረብናቸው ጥናቶች የሚፈልጉትን ግብዓት ወስደው መጠቀም ይችላሉ፡፡ ‹‹የሚነጋገረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው›› ብለዋል፡፡ ይህን እናሳካበታለን ያሉትን ዕቅድም ይፋ አድርገዋል፡፡ እኛ ማድረግ የምንችለው ለእነሱ ጠቃሚ ነው የምንለውን መረጃ ማቅረብ ብቻ ነው፡፡ በሚፈልጉት ጉዳይ ላይ መረጃ አምጡ ካሉን በጠየቁን ጊዜ ሁሉ ያለንን እንጨምራለን፡፡ በመሬት ጉዳይ አጥንተናል፣ በሥነ ፆታ ጉዳይ አጥንተናል፣ በትምህርት፣ በከፍተኛ ትምህርትና በሌሎችም ጉዳዮች አጥንተናል፡፡ ይህን ሁሉ ደግሞ ለሚፈልግ ማቅረብ ነው ሥራችን፡፡

ሪፖርተር፡- ሐሳብ አመንጪ የሆኑ ምሁራንንም ሆነ የጥናት ተቋማትን (ቲንክ ታንክ) የጥናት ውጤት ወይም ምክረ ሐሳብ የመስማትና የመቀበል ዝንባሌ በኢትዮጵያ ምን ይመስላል?

የራስወርቅ (ዶ/ር)፡- አንድ ምሳሌ ለዚህ መጥቀስ እችላለሁ፡፡ ሁለት ጥናቶችን በተለያዩ ጊዜያት አቅርቤ አውቃለሁ፡፡ አንዱ የሐበሻ አረቄ አወጣጥን የተመለከተ ሲሆን፣ ግብይቱና አጠቃቀሙን ሁሉ የፈተሸ ነበር፡፡ ሌላው ጥናት ደግሞ በጫት ላይ የተደረገ ሲሆን፣ አጠቃቀሙና ግብይቱን የተመለከተ ነበር፡፡ ከፍትሕ ሚኒስቴር ተደውሎ ጥናቶቹን ይዤ እንድቀርብ ጠየቁኝ፡፡ የፍትሕ ሚኒስትር ሰዎችን ሳገኝ እንደነገሩኝ በአልኮል፣ በትምባሆና በጫት ላይ አዋጅ አዘጋጁ ተብለው ነበር፡፡ የቀረቡት ጥናቶች ሥራቸውን እንደሚያግዝ ገልጸውልኝ በጥሩ ውይይት ነበር በጊዜው የተለያየነው፡፡ በሌላ ጊዜ ደግሞ ‹‹ፐብሊክ ሔልዝ ኢንስቲትዩት›› የሚባለው ተቋማት በዚሁ ጥናት ጉዳይ ደብረ ዘይት ጠርቶ ባዘጋጀው ዓውደ ጥናት ላይ እንዳቀርብ ጋብዞኝ ያውቃል፡፡

በጫትም በአረቄም ሊወሰዱ ስለሚገባቸው የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦች ጥናቱን መሠረት በማድረግ በተለያዩ መድረኮች አቅርቤያለሁ፡፡ የመንግሥት ተቋማቱ በተለያዩ ጊዜ ጥናቶቹን ሕግ ለማውጣት በግብዓትነት እንደሚጠቀሙ ቃል የገቡ ቢሆንም፣ መልሰው ግን ይጠፋሉ፡፡ የጫቱ ጥናት ጫት ላይ ሕግ ቢወጣ ነገሩ በሕገወጦች እጅ እንደሚገባ በግልጽ አስቀምጧል፡፡ ጫት በባለሥልጣናት ጭምር የሚዘወተርና ጫትን ልከልክል ማለቱ በቀላሉ እንደማይቻል ያሳያል፡፡ የውጭ ንግድ ገቢን ጨምሮ ብዙ ጉዳዮችን የሚነካ መሆኑን በመጥቀስ ጫት ላይ ሕግ ማውጣቱ እንደሚከብድ በደንብ አመላክቷል፡፡ አንድ ወቅት ብቻ ‹‹ሕግ ልናወጣ ነው›› እየተባለ ብልጭ የሚል ሐሳብ ቢታይም፣ እስካሁን በዚህ ላይ ዕርምጃ መውሰድ አለመቻሉን በተግባር ታይቷል፡፡      

ሪፖርተር፡- የሚሰማ ከሌለ ወይም የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦችን የሚቀበል ከጠፋ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ማጥናት፣ መመራመሩም ሆነ ገንዘብ፣ ጊዜና ጉልበትን ማባከኑ ጥቅሙ ምንድነው?

የራስወርቅ (ዶ/ር)፡- የጥናትና የፖሊሲ ተቋማት ጥናትን በግብዓትነት የመጠቀም ዝምድና ልክ እንደ መስታወት ነፀብራቅ ነው፡፡ አንዱ ሌላውን ቢነካም ከየትኛው የተነሳው የትኛውን እንደነካ ግን በውል አይለይም፡፡ ብዙ ጊዜ ጥናት የፖሊሲ አውጪዎች ላይ እንዴት ተፅዕኖ እንዳሳደረ አይታወቅም፡፡ አንዳንዴ ጭራሽ ማን በማን ላይ ተፅዕኖ እንዳሳረፈ አይለይም፡፡ ለምሳሌ በመሬት ጉዳይ ላይ የእኛ ተቋማት ፈር ቀዳጅ በመሆን ጥናቶችን በተለያዩ ጊዜያት አቅርቧል፡፡ የእኛ ባልደረባ የሆኑት አቶ ደሳለኝ ራህመቶ በመሬት ጉዳይ ላይ ሲያጠኑ 60 ዓመታትን አሳልፈዋል፡፡ በጃንሆይ ዘመን የነበረውን የመሬት ሥሪት አጥንተዋል፡፡ ከዚያ በደርግ ጊዜ አዋጁ መጣ፡፡ አዋጁ የፈጠረውን ውጣ ውረድ በተመለከተ አጥንተውታል፡፡ በኢሕአዴግ ዘመንም ቢሆን የነበረውን የመሬት ሥሪት በሚመለከት እያጠኑ ፖሊሲ አውጪዎችን ሞግተዋል፡፡

በመሬት ጉዳይ ላይ እሳቸውም ሆነ ብዙ ተመራማሪዎች የመሬት ሥሪቱ የገበሬውን የይዞታ ባለቤትነት መብት ካላረጋገጠ፣ ገበሬው የዕለት የዕለቱን ብቻ እያረሰ መሬቱ ጥበቃም ሆነ የተለየ ጠቀሜታ ያጣል የሚል ሙግት ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡ ለአርሶ አደሮች የመሬት መጠቀም ዋስትና ይሰጥ ብለው ሞግተዋል፡፡ በመሬቱ ዙሪያ ዛፍ በመትከሉ እኮ የታሰረ ገበሬ ጭምር በዚህ አገር ነበር፡፡ ስለመሬት አጥንተን ስናቀርብ እንደ ካሱ ኢላላ (ዶ/ር) ያሉ የፖለቲካ አመራሮች በቀይ ስክሪፕቶ ነበር አታንሱ ብለው ሐሳቡን ሰርዘውና ደልዘው የሚመልሱት፡፡ ‹‹መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ ነው ብትሉም መሬቱ ላይ ለሚኖረው ሰው ትንሽ እንኳ የባለቤትነት ስሜት የሚፈጥር ሕግ አውጡ›› ብንል የሚሰማ አልነበረም፡፡ ካርታ ወይም ይዞታ ማረጋገጫ ነገር ይሰጠው ቢባሉም ሆነ የማከራየት መብት ይሰጠው ቢባሉ ሲቃወሙ ነበር፡፡ በሒደት ግን የተቃወሙትን ወደ መቀበሉ ገብተው የመሬት ባለቤትነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት የመስጠትን ሐሳብ ተቀበሉ፡፡ አሁን ደግሞ ይህንን ከፍ አድርገው ‹‹መሬትን አስይዞ መበደር ይቻላል›› የሚል አዋጅ ማዘጋጀታቸውን ሰምተናል፡፡

ይህ ቀስ በቀስ የመጣ የሁላችንም የተከማቸ የትግል ውጤት ነው፡፡ ይህ የእኔ ነው፣ ይህ የአቶ ደሳለኝ ነው፣ ወይም ይህ የእከሌ ነው ማለት አልችልም፡፡ ነገርየው በአጭር ጊዜ የመጣ ሳይሆን ረዥም ጊዜ የወሰደ ነው፡፡ ደግሞም አካሄዱ ገባ ወጣና ጠመዝማዛ ያለው ነው፡፡ የጥናት ተፅዕኖና ፋይዳ በቀጥታ የሚታይ ወይም በቀላሉ የሚለካ ሳይሆን፣ ወደፊትም ወደኋላም የሚጓዝና በሒደት የሚመጣ እንደሆነ ከዚህ መማር ይቻላል፡፡

ብዙ ጊዜ የእናንተ ምሁራን ፋይዳ ምንድነው በሚል እጠየቃለሁ፡፡ ይህ ሁሉ የምታጠኑት ነገር ምን ያመጣል? ይባላል፡፡ እኛ የምናጠናውን ወትዋች ድርጅቶች (አድቮኬቶች) ይወስዱና ይወተውታሉ፡፡ ለምሳሌ በጫት ላይ የተጠናውን ጥናት መቋሚያ የተባለው ጫትን የሚቃወም ሲቪክ ማኅበር ተጠቅሞ አንድ ነገር ይደረግ ሊል ይችላል፡፡ ጥናቶችን የሚጠቀሙ በተለያዩ መንገዶች የሚመጡ ተቋማት ይኖራሉ፡፡ በእምነት ተቋማት፣ በማኅበራት፣ በዕድር፣ በትምህርት ቤት፣ በሌላም መንገድ የሚመጡ ጥናቱን ተመርኩዘው የራሳቸውን ዓላማ ለማሳካት ይጥራሉ፡፡ ጥናት ልክ እንደ እዚህ በተለያዩ መንገዶች ነው ጥቅም ላይ የሚውለው፡፡

የተለያዩ አካላት ድምር ጥረት ነው ጥናትን ወደ ውጤት የሚቀይረው እንጂ፣ ምሁራን ተቀምጠው ጽፈው ብቻ በቀጥታ የጻፉት ነገር በተግባር የሚቀየርበት ሁኔታ ብዙ ጊዜ የለም፡፡ እነ ፕሌቶ እና አርስቶትል ያኔ ጥናት ሲያጠኑ በቀጥታ በተግባር የሚተረጎም ይመስላቸው ነበር፡፡ አርስቶትል ለምሳሌ የታላቁ እስክንድር አስተማሪም ነበር፡፡ ነገር ግን አርስቶትል ሐሳብ እየሰጠው ያን በሥራ ላይ እያዋለ አይደለም የኖረው፡፡ እንዲያውም ተማሪው እስክንድር ነበር፡፡ በወረራ ከሚይዛቸው አካባቢዎች ለጥናትና ለምርምር የሚሆነውን የአትክልትና የአውሬ ዘሮች የሚልክለት፡፡ ጥናትና ተግባር የአንድ ለአንድ ቀጥታ ግንኙነት የላቸውም፡፡ ከጥናት ወደ ተግባር የሚል የግንኙነት መስመር የለውም፡፡ መያዣው እስኪጠፋ ድረስ ከተለያየ አቅጣጫ የሚፈስ ሐሳብ ነው ተጠራቅሞና በተግባር ላይ ውሎ ለውጥ የሚያመጣው፡፡        

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...

‹‹በሁለት ጦር መካከል ተቀስፎ ያለ ተቋም ቢኖር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው›› አቶ ዘገየ አስፋው፣ የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተነሳው ግጭት በተጋጋለበት ወቅት በ2014 ዓ.ም. በአገሪቱ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ...

‹‹ዘላቂ ጥቅም ያመጣል ብዬ ያሰብኩትን ሥራ ለመተግበር እንደ መሪ መጀመሪያ ቃሌን ማመን አለብኝ›› እመቤት መለሰ (ዶ/ር)፣ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ለመቀላቀል የሚያስችለውን ፈቃድ ካገኘ 25ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ ለበርካታ ዓመታት ጉዞው በውጤታማነት ሲራመድ የነበረ ባንክ ቢሆንም፣ ከጥቂት ዓመታት...