Sunday, July 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሕይወት መድንን ዘንግቶ በተሽከርካሪ ሽፋን ላይ የተንጠለጠለው የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ዘርፍ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ዝቅተኛ የአገልግሎት ተደራሽነቱ ባሻገር ከሌሎች የዓለም አገሮች የኢንሹራንስ ዘርፎች የሚለይባቸው ባህሪያት እንዳሉት ኢንዱስትሪውን የተመለከቱ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ 

የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ዘርፍ ከሌሎች የዓለም አገሮች አቻዎቹ በእጅጉ ለየት የሚያደርገው አንዱና ዋነኛ መገለጫው የመድን ሽፋን ይዘቱ ሕይወት ነክ ባልሆነው ወይም በንብረት ላይ በተለይም በተሽከርካሪ የመድን ሽፋን ላይ ተንጠለጠ መሆኑ ነው፡፡ በአገሪቱ ውስጥ በዘርፉ የሚንቀሳቀሱ 18 ኩባንያዎች በየዓመቱ ከ90 እስከ 95 በመቶ የሚሆነው የዓረቦን ገቢ የሚሰበስቡት ሕይወት ነክ ካልሆነው የኢንሹራንስ ዘርፍ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ደግሞ የሞተር ወይም የተሽከርካሪዎች መድን ሽፋን 75 በመቶ በላይ የሚሆነው ድርሻ ይይዛል፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎችና ዓለም አቀፍ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ በኢንሹራንስ አገልግሎት ብልጫ መያዝ ካልሆነም ሚዛኑን የጠበቀ ድርሻ የሕይወት ኢንሹራንስ ሊኖረው የሚገባ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ግን በተቃራኒው ሆኖ መዝለቁ ይገለጻል። በዚህም ሳቢያ ኢትዮጵያ ዝቅተኛ የሕይወት ኢንሹራንስ ሽፋን ያላት አገር አድርጓታል፡፡  

የሕይወት መድንን ዘንግቶ በተሽከርካሪ ሽፋን ላይ የተንጠለጠለው የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ዘርፍ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በ2015 የሒሳብ ዓመት ብቻ ካሰባሰቡት አጠቃላይ የዓረቦን ገቢ ውስጥ ሕይወት ነክ ያልሆነው የኢንሹራንስ ዘርፍ 93.1 በመቶውን ድርሻ የያዘ ሲሆን፣ ከሕይወት ኢንሹራንስ አገልግሎት የዓረቦን ድርሻ ደግሞ 6.3 በመቶ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃ ያሳያል፡፡ በዚሁ መረጃ መሠረት፣ ከወለድ ነፃ የኢንሹራንስ አገልግሎት (ታካፉል) የተሰበሰበው ዓረቦን የ0.6 በመቶ ድርሻ ይዟል።

ሁሉም የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከሕይወት መድን ሽፋን ለመጀመሪያ ጊዜ ከሁለት ዓመት በፊት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የዓረቦን ገቢ መሰብሰብ የቻሉ ሲሆን፣ ይህንኑ በማጠናከር በ2014 የሒሳብ ዓመት 1.35 ቢሊዮን ብር በ2015 የሒሳብ ዓመት ደግሞ 1.46 ቢሊዮን ብር ዓረቦን ገቢ አግኝተዋል፡፡ ይህም የሕይወት ኢንሹራንስ ዓመታዊ ዕድገት እጀግ አዝጋሚ መሆኑን አመላካች ነው።

በአንፃሩ በ2015 የሒሳብ ዓመት ሁሉም የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ሕይወት ነክ ካልሆነ የመድን ሽፋን 21.5 ቢሊዮን ብር ዓረቦን ገቢ ያገኙ ሲሆን፣ ይህም ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ40.1 በመቶ ዕድገት የታየበት ነው። ከዚህ ሕይወት ነክ ካልሆነው የመድን ሽፋን የዓረቦን ገቢ ውስጥ ደግሞ 75 በመቶ የሚሆነው ከሞተር ኢንሹራስ ሽፋን የተሰባሰበ ነው፡፡ ሁሉም የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በ2015 የሒሳብ ዓመት ከሰጡት አጠቃላይ የመድን ሽፋን ካገኙት 23 ቢሊዮን ብር የዓረቦን ገቢ ውስጥ የሕይወት ኢንሹራንስ ድርሻ 8.2 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ይህ አኃዛዊ መረጃ የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ አገልግሎት በተሽከርካሪዎች ላይ የተመሠረተ መሆኑ ከሌሎች አገሮች የተለየ ገጽታ እንዲይዝ አድርጎታል። ከዚህም ባሻገር በኢንዱስትሪው ብልጫ መያዝ የነበረበት የሕይወት ኢንሹራንስ አገሪቱን በዘርፉ ዝቀተኛ ደረጃ ላይ እንደሚያስቀምጣት ያነጋገርናቸው የኢንሹራንስ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ 

የኢንሹራንስ ባለሙያው አቶ ኢብሳ መሐመድ እንደሚገልጹትም፣ የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ በአመዛኙ በተሽከርካሪ መድን ላይ የተንጠለጠለ መሆኑ አግባብነት እንደሌለው ያመለክታሉ፡፡ ከተሽከርካሪ የኢንሹራንስ ሽፋን በላይ ዘርፉ በዋናነት ሊሠራበት ይገባ የነበረው የሕይወት ኢንሹራንስ ሽፋን ላይ እንደሆነ፣ ነገር ግን ይህንን የሕይወት መድን ሽፋን ለማሳደግ ታስቦበት እየተሠራበት አለመሆኑንም ያስረዳሉ፡፡ በሌላው ዓለም በአብዛኛው የሕይወት መድን ሽፋን ከ50 እስከ 65 በመቶ ድርሻ እንዳለው፣ በኢትዮጵያ ግን ይህ የተገላቢጦሽ ሆኖ፣ የኩባንያዎች ዋነኛ የዓረቦን ገቢ በተሽከርካሪ መድን ሽፋን ላይ መንጠልጠሉን ያብራራሉ።

የኢትዮጵያ መድን ሰጪዎች ማኅበር በቅርቡ ባስጠናው ጥናት፣ ኢትዮጵያ በሕይወት መድን ዘርፍ ኋላቀር ከሚባሉ አገሮች አንዷ መሆኗን ነው፡፡ በማኅበሩ መረጃ መሠረት እ.ኤ.አ. በ2022 በዓለም አቀፍ የኢንሹራንስ ገበያ ውስጥ የሕይወት መድን ሽፋን 44 በመቶ ገበያ ድርሻ አለው። ይህም በገንዘብ ሲተመን 1.2 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ነው፡፡ 

በአውሮፓና በእስያ ደግሞ የሕይወት ኢንሹራንስ ገበያ ከ60 እስከ 65 በመቶ መሆኑንም የማኅበሩ መረጃ ያመለክታል፡፡ በአፍሪካ የሕይወት መድን ዘርፍ 69 በመቶ ድርሻ ቢኖረውም፣ በኢትዮጵያ ግን የገበያ ድርሻው ስምንት በመቶ መሆኑን መረጃው ይጠቁማል። የኢትዮጵያ የገበያ ድርሻ ከዓለም አቀፉ የሕይወት ኢንሹራንስ የገበያ ድርሻ አንፃር ሲታይ 0.0087 በመቶ ብቻ እንደሆነም ይኼው መረጃ ያስረዳል። ከአፍሪካ ደግሞ የኢትዮጵያ የሕይወት መድን ሽፋን የያዘው ድርሻ 0.5 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ ላይ እጅግ ዝቅተኛ እንቅስቃሴ ማድረጓን ፍንትው አድርጎ የሚያሳየው የደቡብ አፍሪካ የኢንሹራንስ ኢንደስትሪ የመድን ሽፋን ስብጥር ነው። መረጃው እንደሚያመለክተው፣ በደቡብ አፍሪካ የሕይወት ኢንሹራንስ ሽፋን የገበያ ድርሻ 78.7 በመቶ ነው፡፡  

በኬንያም ቢሆን ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነው የገበያ ድርሻ በሕይወት ኢንሹራንስ የተያዘ ነው፡፡ በተለይ ኬንያ ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት ከ46 በላይ ከሚሆኑ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውስጥ በሕይወት ኢንሹራንስ ላይ ብቻ የሚሠሩ ከ12 በላይ ኩባንያዎች እንዳሏት መረጃው ያመለክታል።

እነዚህ አኃዞች ከኢትዮጵያ አንፃር ሲታዩ ልዩነቱ የጎላ መሆኑን መገለጫ ናቸው። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች የሕይወት ኢንሹራንስ እጅግ አስፈላጊ የመሆኑን ያህል በአግባቡ ሊሠራበት ያለመቻሉ ብዙ ነገሮችን እንዳሳጣም የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

በኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ በተለይም በሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ ለረዥም ዓመታት የሠሩትና አሁንም በኅብረት ኢንሹራንስ የሕይወት ኢንሹራንስ ዲፓርትመንትን እየመሩ ያሉት ወ/ሮ አዛለች ይርጉ፣ በሥራ ዘመናቸው በእጅጉ ከሚቆጫቸው ነገሮች አንዱ የኢትዮጵያ የሕይወት ኢንሹራንስ ሽፋን እንዲህ ወደኋላ መቅረቱ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ካላት ሰፊ የቆዳ ስፋትና የሕዝብ ቁጥር አንፃር የሕይወት ኢንሹራንስ አለመስፋፋቱ በቁጭት ይናገራሉ፡፡ ዘርፉ ማኅበረሰቡን ከመጥቀም አልፎ አገራዊ ጠቀሜታውም እጅግ የበዛ መሆኑ ግልጽ ቢሆንም፣ ዕድገቱ በዚህ ደረጃ መገለጹ እንደሚያሳዝናቸውም ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ዋነኛው ምክንያት የአገልግሎቱን ጠቀሜታ በሚገባ አስረድተው ኅብረተሰቡ እንዲጠቀም አለመደረጉ ነው፡፡ በዚህ የዘርፉ አንሳቃሶች ተወቃሾች ነን ይላሉ፡፡ 

የሕይወት ኢንሹራንስ በሥሩ በርካታ የሽፋን ዓይነቶች ያሉ ቢሆንም፣ ሽፋኑ የሚገባበት መንገድ ግን በዋናነት በሁለት ተከፍሎ ሊታይ የሚችል ነው፡፡ አንደኛው ለተሰነ የጊዜ ገደብ ደንበኛው ገንዘቡን የሚያገኝበት ዕድል የሚፈጥር ነው፡፡ ሰውየው የመጀመርያውን ዓረቦን ከፍሎ በሞት የኢንሹራንሱ ገንዘብ ለቤተሰቡ መክፈል ያስችላሉ ያሉት ወ/ሮ አዛለች፣ ሌላው ደግሞ የኢንሹራሱ ሽፋኑን የገዛው ለአምስት ዓመት፣ ለአሥር ዓመት ብሎ ሲገዛ  ያ ገንዘብ የተጠቀሰው ቀነ ገደብ ሲደርስ ይሰጠዋል፡፡ ወይም ጡረታ ሲወጣ የሚከፈል ነው፡፡ ብዙ ጊዜ በማንኛውም መንገድ በሚከሰት ሞት፣ የአካል ጉድለት ሲደርስና በመሳሰሉ ወቅቶች ለሕይወት ኢንሹራንስ ለተገባ ዋስትና ለቤተሰብ መክፈል ዕድል የሚሰጠው ይህ የኢንሹራንስ ዘርፍ ነው፡፡ 

ስለዚህ ሁሉም ሰው ሊያገኘው የቻለውን ያህል የሕይወት ኢንሹራንስ ቢገዛ ብዙ ነገር ሊያቃልል ይችላል፣ ቤተሰቡን ይታደጋልም ይላሉ፡፡ ‹‹እኔ በጣም ከሚያሳስቡኝ ነገሮች አንዱ የሕይወት ኢንሹራንስ በመግዛት ሊከሰቱ የሚችሉ ቀውሶችን ለመቀነስ አለመቻሉም ነውም ይላሉ፡፡ እንደምሳሌ የሚጠቅሱትም ቤት ሠሪዎች ኢንሹራንስ ሳይኖራቸው ባንክ ተበድረው ቤቱን ከገዙ በኋላ ቢሞቱ ባንኩ ቤቱን በሐራጅ ይሸጣል፡፡ ቤተሰብ ይበተናል፡፡ ነገር ግን ቤተሰቦች ለሕይወት ኢንሹራንስ ቅድሚያ ሰጥተው ቢሆን ኖሮ የሚፈጠረውን ቀውስ ማስቀረት ይቻል እንደነበር ያስረዳሉ፡፡

‹‹ብዙ የአፍሪካ አገሮች አንድ ባንክ ለአንድ ቤት ሠሪ ወይም ገዥ ሲያበድር የሞርጌጅ ኢንሹራንስ አብሮ ይገዛላቸዋል፡፡ በዚህም በየወሩ ከሚከፍሉት ብድር ጋር ትንሽ መጠን የመድን ዓረቦን ጨምረው እየከፈሉ ይጨርሳሉ፣ ተበዳሪው በአጋጣሚ ቢሞት እንኳ ቤቱን ባንክ አይወስድባቸውም፡፡ የሟች ቤተሰቦች በዚያው ቤት ሕይወታቸውን ይቀጥላሉ፡፡ እንዲህ ያለው የሕይወት መድን ሽፋን እዚህ አለመኖሩ በአገራችን የሕይወት ኢንሹራንስ እንደ አንድ ክፍተት የሚታይ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ግን በኢትዮጵያ የሞርጌጅ ኢንሹራንስ ይገባ ነበር፣ ሲሞቱ ይከፈላል፤›› ሲሉ ወ/ሮ አዛለች ያስረዳሉ፡፡

ሌላው የኢንሹራንስ ባለሙያ አቶ ኢብሳ መሐመድም፣ ሕይወት ኢንሹራንስ በአንድ ኅብረተሰብ ውስጥ ወሳኝ ጉዳይ ሆኖ ሳለ፣ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ተገቢውን ሥራ ባለመሥራታቸው የተፈጠረ ክፍተት መሆኑን ያምናሉ፡፡

እንደ አገርም ቢሆን መሥራት ያለበት የሕይወት ወይም የረዥም ጊዜ የኢንሹራንስ ሽፋን ላይ ኩባንያዎቹ በርትተው እንዲሠሩ በመንግሥቱ በኩል ምንም ሊደረግ ባለመቻሉ ዘርፉን አቀጭጮታል ይላሉ፡፡ ለምሳሌ በሞተር ኢንሹራንስ ሦስተኛ ወገንን አስገዳጅ እንዳደረገው ሁሉ ኩባንያዎቹ ለሠራተኞቸው የሕይወት ኢንሹራንስ እንዲገዙ ቢያስገድድ በሥራ ቦታዎች ላይም የሕይወት ኢንሹራንስ መግዛት አስገዳጅ ቢሆን አሁን በሞተር ኢንሹራንስ ላይ ጥገኛ የሆነው ኢንዱስትሪ በተወሰነ ደረጃ መቀየር ይችል ነበር የሚል ምልከታ አላቸው፡፡ 

አቶ ኢብሳ በበኩላቸው፣ ‹‹የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ዘርፍ ዘገምተኛ ለውጥ ላይ ነው። እንደ ባንክ ዕድገት እየበረረ አይደለም፡፡ ለዚህ አንዱ ምክንያት ዘላቂ ጠቀሜታ ያለው የሕይወት ኢንሹራንስ ላይ በበቂ ሁኔታ አለመሥራቱ ነው፤›› ሲሉ ያሰምሩበታል፡፡ 

ከዚህ ባሻገር ለሕይወት ኢንሹራንስ ሽፋን ደካማ መሆን ኩባንያዎቹ ራሳቸው የዘርፉን ጠቀሜታ በማስረዳት ኅብረተሰቡን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆን አለመሥራታቸው ሊሸሸግ አይገባም ይላሉ፡፡ ‹‹ይህ ጉዳይ እንዲያውም በቀዳሚነት መነሳት ያለበት ችግር ነው፤›› የሚሉት አቶ ኢብሳ፣ ኩባንያዎች የሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ እንዲያድግ መንግሥትን በማሳመን ሊሠሩ የሚገባቸውን ሥራዎች አለመሥራታቸው እንጂ፣ ኅብረተሰቡ ሽፋኑን የመግዛት ፍላጎት ማጣት ብቻ ተደርጎ መውሰድ እንደሌለበትም ገልጸዋል፡፡ የአገራችን የሕይወት ኢንሹራንስ በዚህን ያህል ደረጃ ዝቅተኛ ለመሆኑ ዋናው ጉዳይ የሕይወት ኢንሹራንስ በዋናነት ተጠቃሚ ሊሆን ለሚገባው ዝቅተኛ የኅብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ሊሆን የሚያስችለው በሕግ የተደገፈ አሠራር እንዲዘረጋ ባለመደረጉ ነው የሚሉት ደግሞ ሌላው የኢንሹራንስ ባለሙያው አቶ አሰግድ ገብረ መድህን ናቸው፡፡

ለምሳሌ ድርጅቶች የቀጠሯቸው ሠራተኞች ሥራውን በሚሠሩበት ጊዜ ከሥራው በሚመነጭ ማንኛውም የሥጋት ሽፋን ይሰጣቸዋል ተብሎ በአሠሪና ሠራተኞች ሕግ እንደተደነገገው ለሕይወት ወይም ለጤና ኢንሹራንስ አስገዳጅ ነገር ቢኖር ዘርፉ ሊያድግ እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላት በመሆኑ፣ ቀጣሪ ድርጅቶች የሕይወት መድን እንዲገዙ ቢያስገድድ ጠቀሜታው ኢንሹራንሱን ለተገዛለት ሠራተኛ ብቻ አይደለም፡፡ ለኢንቨስትመንት የሚሆን ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ መሰባሰብ የሚያስችል ሲሆን፣ መንግሥትም ተጠቃሚ ይሆንበታል ብለዋል፡፡ እንደ ሌሎቹ የኢንሹራንስ ሽፋኖች ለአንድ ዓመት ሽፋን የሚገባለት ያለመሆኑና የረዥም ጊዜ ስለሆነ ገንዘቡን ብዙ ኢንቨስትመንቶች ላይ ማዋል እንደሚያስችልም አቶ አሰግድ ጠቅሰዋል፡፡   

ኩባንያዎች ተግባብተው ዘርፉን ያለማስተዋወቃቸው የሕይወት ኢንሹራንስን በሚፈለገው ደረጃ ማራመድ አለመቻሉን ያነጋገርናቸው የኢንሹራንስ ባለሙያዎች የሚስማሙበት ሐሳብ ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ሥራ አጥብቆ ባልተሠራበት ሁኔታ የሕይወት ኢንሹራንስ ዕድገትን መጠበቅ እንደሚያስቸግር አቶ ኢብሳ በበኩላቸው፣ የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ ሁሉም እየተረባረቡበት ያሉት ተሽከርካሪ ላይ ሆኖ ለመቅረቱ፣ አንዱ ምክንያት ዋነኛ ሥራቸው ሊሆን ይገባ የነበረው የሕይወት ኢንሹራንስ ላይ ባለመሥራታቸው፣ ዘርፉ ለአገራዊ ኢኮኖሚው ያለውን አስተዋጽኦ አሳንሶታል፡፡ መረጃዎች የሚጠቀሙትም ከጠቅላላ አገራዊ ኢኮኖሚው ኢንሹራንስ ዘርፉ ከአንድ በመቶ ያልበለጠ አስተዋጽኦ ብቻ ያለው መሆኑም ያለውን ክፍተት ያሳያል ተብሏል፡፡ 

ኢትዮጵያን የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ለየት የሚያደርገው ሌላው መገለጫው አገሪቱ በየዓመቱ ለተሽከርካሪ የመድን ሽፋን ዋስትና የምትከፍለው ካሳ በእጅጉ እየጨመረ መሆኑ ነው፡፡ የበለጠ አስገራሚ የሚያደርገው ኢትዮጵያ ያሏት ተሽከርካሪዎች ቁጥር አነስተኛ ሆኖ ሳለ፣ ከኢትዮጵያ ሦስትና አራት እጥፍ የተሽከርካዎችን ያላቸው አገሮች ለተሽከርካሪዎች አደጋ የሚከፍሉት ካሳ ከኢትዮጵያ ያነሰ መሆን ነው፡፡ 

በኢትዮጵያ በ2015 በሒሳብ ዓመት ብቻ 18ቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ለካሳ ክፍያ ያዋሉትን ገንዘብ ከ3.54 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱንና ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነጻጸርም ከ2.4 ቢሊዮን ብር በላይ ወይም በ47.1 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

የ2015 የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ አጠቃላይ የዓረቦን ገቢ ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት በሁለት አኃዝ እያደገ የመጣ ሲሆን፣ በ2015 የተመዘገበው የዓረቦን ዕድገት ከፍተኛው በመሆን የተመዘገበበት ነው፡፡ 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዓመታዊ ሪፖርት ይህንን የሚያመለክት ሲሆን፣ በ2014 የሒሳብ ዓመት 16.8 ቢሊዮን ብር የነበረው የዓረቦን ገቢ በ2015 መጨረሻ ላይ ከ23 ቢሊዮን ብር በላይ ሆኗል፡፡ ይህም 38 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ እንዲህ ያለው መረጃዎች የሚያሳዩት ኢንዱስትሪው በሕይወት መድን ላይ ባለመሥራቱ ሲሆን፣ ኢኮኖሚው ላይ ጫና በሚፈጥረው በሞተር ኢንሹራንስ ላይ አብዝቶ መሥራት አንድ ቦታ ላይ መቆም የሚገባው መሆኑን ነው፡፡ 

በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በየዓመቱ ለካሳ ክፍያ ከሚያውሉት ገንዘብ ውስጥ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነውን ደግሞ የሚከፍለው ከተሽከርካሪ አደጋዎች ጋር ለተያያዙ አደጋዎች የመሆኑ ጉዳዩ ዘርፉን በተሽከርካሪ ላይ የተንጠለጠለ ነው ተብሎ ብቻ የሚታለፍ እንዳልሆነም አቶ ኢብሳ ይገልጻሉ፡፡ ከአገራዊ ኢኮኖሚ አንፃር ሲታይ ያልተነገረለትና የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ እየበላ ያለም ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ 

በየዓመቱ ለጉዳት ካሳ ከሚከፈለው ውስጥ ከ70 በመቶ በላይ ለተሽከርካሪ የጉዳት ካሳ የሚከፈል ከሆነ ይህ ክፍያ በኢትዮጵያ በብር ተሠልቶ ይነገር እንጂ፣ የተከፈለውን ካሳ ያህል አገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እንዳባከነች የሚቆጠር ነውም ይላሉ፡፡ ምክንያቱም ለተሽከርካሪዎች አደጋ የሚከፈው የጉዳት ካሳ ሁሉ ከውጭ ምንዛሪ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገቡ ተሽከርካሪዎችና የተሽከርካሪ መለዋወጫዎችን መልሶ ለመተካት የሚሰጠው ካሳ የውጭ ምንዛሪውን በመሆኑም በሕይወት ኢንሹራንስ ላይ አተኩሮ መሥራት በተሽከርካሪ የጉዳት ካሳ የሚታጣውን የውጭ ምንዛሪ በመቀነስ አገርንም መታደግ ይሆናል ብለው ያምናሉ፡፡  

የሞተር ኢንሹራንስ ኢኮኖሚው ላይ ጫና ማሳረፉ እርግጥ ስለመሆኑ ጠቅሰው፣ በተለይ በአሁኑ ጊዜ ያለው የዋጋ ንረት ከሞተር ኢንሹራንስ ሽፋን ጋር የተያያዙ የካሳ ክፍያዎችን እንዳናሩት አቶ አሰግድ ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ በመቶ ሚሊዮን ብሮች የሚገመተው ቅንጡ ተሽከርካሪዎች ገበያ ላይ እየታዩ በመሆኑ አንድ አካላቸው ቢጎዳ በተጎዳውን አካል የሚተካው በውጭ ምንዛሪ ገዥ ተፈጽሞ በመሆኑ፣ የሞተር ኢንሹራንስ ኢኮኖሚያው ጉዳት ቀላል አለመሆኑንም አስረድተዋል፡፡ 

ከኢኮኖሚ አንፃር ያለውን ጉዳት በተመለከተ አቶ ኢብሳም በአቶ አሰግድ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ አገሪቱ ማውጣት የማይገባትን የውጭ ምንዛሪ በተሽከርካሪ አደጋዎች ብዛት እያጣችም ነው ይላሉ፡፡ የተሽከርካሪ አደጋ መብዛት ለኢኮኖሚው ጠንቅ ከመሆኑም በላይ፣ ሌሎች ንብረቶች መውደምም መንስዔ መሆኑን የጠቀሱት ባለሙያው እየቀጠፈ ያለውን የሰው ሕይወት ካሰብን ጉዳቱ ማኅበራዊ ቀውስ የሚፈጥር ጭምር መሆኑን ያሳያል፡፡ ስለዚህ ተሽከርካሪ አደጋ የሚከፈለው ዋጋ እንዲህ እየገዘፈ የመጣው የማሽከርከር ልምዶች ላይ ባለ ችግር ጭምር በመሆኑ ከተሽከርካሪ መድን ሽፋን የገነነበት ኢንዱስትሪ ለመቀየር የሕይወት ኢንሹራንስ ላይ መሥራት ቁልፍ ጉዳይ ሆኖ ሳይሆን አሽከርካሪዎች በዚህን ያህል ደረጃ ጉዳት የሚደርሱት ለምንድነው? ብሎ መፍትሔ ማፈላለግ ጭምር ይጠይቃል፡፡  

አሁን ተሽከርካሪ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ያለው አንዱ ምክንያትም የአደጋ መብዛት በመሆኑ ይህንን መለወጥ ካልተቻለ ለአገር የሚጠቅመው የሕይወት ኢንሹራንስ ላይ ኩባንያዎች ጨክነው እንዳይገቡ እንቅፋት ይሆንባቸዋል የሚል ሥጋታቸውንም ገልጸዋል፡፡ 

ስለዚህ የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ በተሽከርካሪ ኢንሹራንስ ላይ ሊንጠለጠልበት የቻለበት አንዱ ምክንያት የተሽከርካሪዎች አደጋ ከመብዛት ጋር የተያያዘ በመሆኑ አደጋን መቀነስ የኢንዱስትሪውም ሆነ የአገርን ኢኮኖሚ መታደግ የባለሙያዎች ማብራሪያ አመላክቷል፡፡   

የሕይወት መድን ሽፋን በሥሩ በርካታ የአገልግሎች ዓይነቶች ያሉት ሲሆን፣ ኅብረተሰቡ ከዚህ አገልግሎት ይልቅ ለንብረት ከ90 በመቶ በላይ ለተሽከርካሪ ቅድሚያ የመስጠቱ ጉዳይ የኢንዱስትሪው ውስጥ ሌላው አስደማሚ ትዕይንት ነው፡፡ 

ሌላው ቀርቶ ለተሽከርካሪው የኢንሹራንስ ሽፋን የገዛ አሽከርካሪ እኔ ብጎዳ ብሎ ለራሱ መድን ሽፋን ያለመግዛቱ ብዙ ሊያነጋግር የሚችል ጉዳይ ሆኗል፡፡ 

በተሽከርካሪው የመድን ሽፋን የገዛ አንድ ተሽከርካሪ ለሕይወቱ የመድን ሽፋን ለመግዛት የማይበረታታበት ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል? ለሚለው ጥያቄ አቶ ኢብሳ አሁንም ግንዛቤውን ማስጨበጥ ባለመቻላችን የተፈጠረ ችግር ነው ይላሉ፡፡ 

ለምሳሌ ብዙ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ማስታወቂያ ሲያስነግሩ በተለይ በካሳ ክፍያ ጠንካራ ስለመሆናቸው ለመግለጽ ሲፈልጉ በንብረት ላይ ለደረሱ አደጋዎች ብቻ ነው የሚናገሩት፡፡ ካሳ የተከፈለውም ሰው እከሌ ኢንሹራንስ ደረሰኝ ይላል፡፡ ንብረቴ ወይም መኪናዬ ተቀጥሎ እከሌ የሚባል ኢንሹራንስ ካሰኝ ይላሉ፡፡ የሕይወት ኢንሹራንስ ሽፋን አንድ አደጋ የገጠመው የቤተሰብ አካል እሱ በድንገት በማለፉ ለቤተሰቡ በተገባ የመድን ሽፋን የቤተሰብ ያገኘው ጥቅምና ቤተሰቡ እንዳይበተን ማስቻሉን የሚገልጽ ማስታወቂያ የላቸውም፡፡ ስለዚህ የሕይወት ኢንሹራንስ ደረጃ ለማሳደግ እንዲህ ያሉ ነገሮች ሁሉ ሊታሰቡበት እንደሚገባ ያመለክታል፡፡  

ከራስ ሕይወት ይበልጥ ለተሽከርካሪው ቅድሚያ መስጠቱ ትክክል ባይሆንም በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የሚያሳየው ይህ ነው፡ በአሁኑ ወቅት አንድ የቤት አውቶሞቢል ሙሉ የኢንሹራንስ ሽፋን በገዛበት በዓመት በአማካይ የሚከፈልበት ዓረቦን ከ10 ሺሕ ብር በላይ ነው፡፡ አንድ ሰው ለሕይወት ኢንሹራንስ በዓመት ሊከፍለው የሚችለው የዓረቦን መጠን ግን በወር ከአሥርና ከሃያ ብር ጀምሮ ዓረቦን የሚገዛ የሕይወት ኢንሹራንስ ቢኖርም ኅብረተሰቡ ይህንን አውቆ እየተጠቀመ አይደለም፡፡ 

ዛሬ ሕይወቴ ቢያልፍ ለቤተሰቦቼ ሕይወት ቀጣይነት ይሆናል ብሎ በዓመት የአንድና የሁለት ሺሕ ብር የሕይወት መድን ሽፋን ባለመግዛት ብቻ የስንቶች ቤት እንደፈረሰ መገመት አያቅትም የሚሉት ወ/ሮ አዛለች በሥራ ዘመናቸው ሕይወት ኢንሹራንስ ባለመግባታቸው ብዙ ጉዳት የገጠማቸው ቤተሰቦች ማየታቸውን አመልክተዋል፡፡ በአንፃሩ የሕይወት ኢንሹራንስ ገዝተው ሲያልፉ ቤተሰባቸውን ከመበተን ያዳኑ ሰዎች ስሜት የማየት ዕድል ስለገጠማቸው የሕይወት ኢንሹራንስ ለኢትዮጵያ እጅግ አስፈላጊ ነው ይላሉ፡፡ የሕይወት ኢንሹራንስ ኢትዮጵያ ውስጥ የገበያ ድርሻው በስምንት በመቶ ላይ መገደቡ አሳዛኝ የሚያደርገው ሌላው ጉዳይ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የነበረውን ልምድ ማስቀጠል ባለመቻሉ እንደሆነ ከባለሙያዎች ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ 

በኢትዮጵያ የሕይወት ኢንሹራንስ ሽፋን መሰጠት የጀመረው እ.ኤ.አ. በ1958 ነው፡፡ ይህም በወቅቱ ኢምፔሪያል ኢንሹራንስ በሚል ይጠራ በነበረ ተቋም ውስጥ ነው፡፡ የአልግሎቱ አስፈላጊነት ታምኖበት ራሱን የቻለ የሕይወት ኢንሹራንስ ኩባንያ የተቋቋመው እ.ኤ.አ. በ1967 ዓ.ም. ይህም ላይፍ ኤንድ ፔንሽን ሶሳይቲ ኦፍ ኢትዮጵያን ሊሚትድ በሚል ተቋቁሞ ይሠራ ነበር፡፡ እንደገና እ.ኤ.አ. በ1973 የሕይወት ኢንሹራንስ ብቻ የሚሰጡ ሦስት ኩባንያዎች ተቋቁመው ሲሠሩ ነበሩ፡፡ እነዚህ ሦስት ኩባንያዎች የአሜሪካ ኢንሹራንስ ኩባንያ፣ የኢትዮጵያ ሕይወት ኢንሹራንስ ኩባንያና ላይም ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ 

እነዚህ ኩባንያዎች ራሳቸውን ችለው በሚንቀሳቀሱበት ወቅት የሕይወት ኢንሹራንስ ከ15 በመቶ በላይ ገበያ እንደነበረው ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከአሥር ዓመት በፊት ደግሞ የሕይወት ኢንሹራንስ ብቻ ነጥሎ ለመሥራት የነበረው አንድ የኢንሹራንስ ኩባንያ የመድን ሽፋኑን ለመግዛት እያቀረቡ ያሉት ሰዎች ዝቅተኛ መሆን የሕይወት የመድን ዘርፍን ብቻ ማስቀጠል አክሳሪ በመሆኑ የግድ ሕይወት ነክ ያልሆነ የኢንሹራንስ አገልግሎትን ደርቦ ለመሥራት መገደዱ ሲታይ ደግሞ ወደኋላ መሄዳችንን እንደሚያሳይ ከባለሙያዎቹ ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡  

ኢትዮጵያ በተለየ የሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ ለምን ዝቅተኛ ሆነ? ኩባንያዎቹ በዚህ ዘርፍ ላለመሥራታቸው ምክንያት ምንድነው? ለሚለው ጥያቄ እንደባለሙያ ምክንያቱ የተለያየ ነው፡፡ አንዱ ኩባንያዎች ይህንን ዘርፍ ለማሳደግ በሚገባ አለመሥራታቸው ሲሆን፣ ኅብረተሰቡም ጠቀሜታውን አውቆ ወደ ኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ እንዲመጡ አለመደረጉ ነው ይላሉ፡፡

የሞተር ኢንሹራንስ ኢኮኖሚያዊ ጉዳትን ለማስቀረትና የሕይወት ኢንሹራንስ ለማሳደግ ምን ይደረግ በሚለው መፍትሔ ላይ አቶ አሰግድና አቶ ኢብሳ አስገዳጅነት እስከሌለ ድረስ ሕይወት ኢንሹራንስን ማሳደግ አይቻልም ይላሉ፡፡ ስለዚህ አገልግሎቱን ማስተዋወቅ አስገዳጅ መሆን ያለባቸውን ዘርፎች ለይቶ አስገዳጅ ማድረግ ከተቻለ ብዙ ነገር መለወጥ ይቻላል ይላሉ፡፡ ሌላው ቢቀር በግለሰብ ደረጃ የሕይወት ኢንሹራንስ መግዛት ባይቻል እንኳን ኩባንያዎች ለሠራተኞቻቸው ይህንን ሽፋን እንዲገዙ ማድረግ፣ ግለሰብም ሊገባው የሚችል አነስተኛ የዓረቦን መጠን የሚከፈልበት በመሆኑ ማበረታታት ያለበት ግለሰቦች እንዲገዙት ለማድረግ ኩባንያዎች በጋራ ማስተዋወቅ እንደሚኖርባቸው ይመክራሉ፡፡ 

ወ/ሮ አዛለች ይህንን ዘርፍ ለማሳደግ መፍትሔ ተብሎ በአቶ ኢብሳና አቶ አሰግድ የተጠቀሰውን ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ ባስጨበጥ የሚለውን ሐሳብ የሚጋሩ ቢሆኑም ዘርፉን ለመታደግ የሕይወት ኢንሹራንስ አስገዳጅ ይሁን በሚለው ሐሳብ አይስማሙም፡፡ በአስገዳጅነት አይሆንም፡፡ ይህንን ከማድረግ ሰው እንዲያውቅ ማድረግ ነው፡፡ ስለጥቅሙ ደጋግመህ ከነገርከው ዕውቀት ኖሮት አገልግሎቱን ለመግዛት ይነሳሳል፤›› ያሉት ወ/ሮ አዛለች፣ የሕይወት ኢንሹራንስ ማስገደድ የማይቻለው የግሰቦች ጉዳይ ሳይሆን አንተ ስታምን ይህንን ገንዘብ ማግኘት አለብህ ብለህ ሊታዘዝ አይችልም፡፡ ነገር ግን ይህንን ብታደርግ ይህንን መሰለ ጥቅም ታገኛለህ ቢባል የተሻለ ይሆናል፡፡ ባይሆን በሌላው ዓለም እንደሚደረገው ለሕይወት ኢንሹራንስ መቶ ብር ዓረቦን ስትከፍል 100 ብሩ ከታክስ ነፃ ይደረጋል፡፡ መንግሥት ታክስ አይጠይቅም፡፡ ስለዚህ ለሕይወት ዋስትና ሲገዛ ታክስ አለመጠየቅ በራሱ ማበረታቻ (ኢንሰንቲቭ) ነው፡፡ ብዙዎቹ አገሮች የሕይወት ኢንሹራንስን ያለማመዱት እንዲህ ባለው መልኩ በመሆኑ፣ እዚህም መደረግ ያለበት እንዲህ ያለው ነገር ነው፡፡ የሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ መጠናከር ለአገር ኢንቨስትመንት ዕድገት ጠቃሚ ነው ያሉት ባለሙያዋ የሚሰበሰበው ዓረቦን ኢንቨስተመንት ላይ የሚውል በመሆኑ ኢኮኖሚ ጠሜታው ከፍተኛ በመሆኑ ሥራው በጋራ መሥራትን የሚጠይቅ ነው፡፡ ትልቁ ነገር ግን የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ተስማሚ የሆኑ አዳዲስ የሕይወት ኢንሹራንስ አገልግሎቶች ማውጣት የግድ መሆኑንም ወ/ሮ አዛለች ገልጸዋል፡፡ በዚህ ዘመን አገልግሎቱን ለማስፋት ቴክኖሎጂ ወሳኝ በመሆኑ በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት መስጠት ዘርፉን የሚያሳድገው ይሆናል ይላሉ፡፡ በአፍሪካ ደረጃ የሕይወት ኢንሹራንስ የሚሸጠውና የሚገዛው በሞባይል በመሆኑ እንዲህ ያሉ ቴክኖሎጂዎትን ከአዳዲስ አልግሎቶች ጋር አጣምሮ መሥራት እስካሁን የምንቆጭበትን ነገር ሊቀይር ይችላል ብለዋል፡፡ የሞተር የመድን ሽፋን በሕይወት ኢንሺራንስ መቀየር የሚችለውም ከዚህ በኋላ በቁጭት ከሠራነው ይላሉ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች