Wednesday, November 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉብሔር ተኮር ፌዴራሊዝሙ ረዥም ርቀት ይወስደናል?

ብሔር ተኮር ፌዴራሊዝሙ ረዥም ርቀት ይወስደናል?

ቀን:

በገለታ ገብረ ወልድ

“የሰላምና የዕርቅ ትርጉምና መንገዶች” መጽሐፍ ደራሲ እስቅያስ አሰፋ (ፕሮፌሰር)፣ ‹የግጭቶች ታላቅ መንስዔ ‹እኔነት› (Ego) ነው፡፡ ይህ እኔነት በግል ደረጃ (Personal Ego) ወይም በቡድን ደረጃ (Collective Ego) ተብሎ ሊገለጽ ይችላል፡፡ ይህን የራስ ወዳድነትና ለሌሎች ያለማሰብ የክፋት ዕሳቤ ቀይሮ ወደ ‹እኛነት› ማሳደግ የቻሉ ሁሉ በማኅበረሰባቸውና በአገራቸው ውስጥ ሰላምና መረጋጋትን ፈጥረዋል፡፡ ይህ ደግሞ የሚፈጠረው ሥርዓታዊ በሆነ መተማመን፣ መተሳሰብና የመንፈስ ዕድገት ነው ይላሉ (2014፣ 158)፡፡

በተለይ ደግሞ አገራችን እንደምትከተለው ዓይነት ፌዴራላዊ ሥርዓት ውስጥ በማንነትም፣ ሆነ በእምነት፣ ወይም በፖለቲካ፣ አመለካከትና ሌላ ልዩነት መገፋፋትና የተገኘን አጋጣሚ ሁሉ ወደ “ራስ” እና “የቅርብ ወገን“ መሰብሰብ አብሮ ሊኖር አይችልም፡፡ የጋራ ደኅንነትና ዋስትና አለመፍጠር፣ ኢፍትሐዊነትና የሥርዓት ብልሽት እስካለ ድረስም አመፃ፣ ግጭትና አለመግባባት መባባሱ አይቀሬ ነው የሚሉት ምሁራን፣ ቅድሚያ ለብሔራዊ ዕርቅና መተማመን ብሎም መፃኢ ዕድልን በጋራ ስለመወሰን ረጅሙን መንገድ መተለም መስጠት ይገባል ነው የሚሉት፡፡ ግን የእኛ አገር ችግር ይህ ብቻ ነው ወይስ ከራሱ ከብሔር ተኮሩ ፌዴራሊዝም የሚመነጨው ተቃርኖ ብሎ መፈተሽ ነው በዚህ ጽሑፍ የተፈለገው፡፡

በመሠረቱ ፌዴራሊዝም ራስን በራስ ለማስተዳደር፣ ለመዳኘትና ለመጠበቅ የሚያስችል፣ ትውልድን በራስ ቋንቋ ለማስተማር የሚያግዝ፣ የአናሳውንም ሆነ የብዝኃኑን ባህል፣ ታሪክ፣ ማንነት ለማጎልበትና ለማሳደግ የሚረዳ ሥርዓት መሆኑ ላይ ልዩነት የለም፡፡ እምነትና የሃይማኖት፣ የባህልና የማኅበረሰብ ልማዶችን ለይቶ ለማጉላትና ለማሳደግ የሚያመች፣ የታሪክና የቅርፅ ፀጋዎችን ለላቀ ጥቅም ለማብቃት የሚያግዝ ሥልትም ነው፡፡ ሥርዓቱ ዋስትና ባለው ዴሞክራሲና በጠንካራ ሰላማዊነት ከታጀበ ደግሞ የዕድገትና የብልፅግና መሠረት መሆኑም ተደጋግሞ የተባለ ነው፡፡

ከዚህ በተቃራኒው በስመ ፌዴራሊዝም ሥርዓቱን ለከራር ዘውጌያዊነትና የብሔር ንትርክ ለማዋል ከተሞከረ፣ በጥገኛ መንገድ የብሔረሰቦችና የክልሎችን ሀብትና ንብረት ለመበዝበዝ የፖለቲካ ሥልጣንን መንጠልጠያ ማድረጉ ከቀጠለ፣ አገር ውድ ዋጋ የምትከፍልበት መሆኑ አይቀርም፡፡ በውስብስብና አወዛጋቢ የታሪክ ትርክት፣ እንዲሁም በእምነት፣ በብሔር፣ በታሪክና በቋንቋ ለዘመናት የተሰባጠረ ብዝኃነትን ለአደጋ በሚያጋልጥ ጥላቻ ከተሄደ አብሮነትን የሚያዳክም አገር አጥፊ መሆኑም አይቀርም (በምነገኝበት ሁኔታ እኮ ተማምኖ የጋራ ምክክር ኮሚሽን መፍጠርና መነጋገር አለመቻሉን ልብ ይሏል)፡፡

አሁን በኢትዮጵያ እየታየ ባለው አክራሪ ብሔርተኛው ኃይል አካሄድ፣ አገረ መንግሥትና የሕዝብንም ደኅንነት ለአደጋ የሚያጋልጥ እየሆነ የሚገኘው ከዚሁ አንፃር ነው ብሎ መደምደም ይቻላል፡፡ በተጨባጭ እየታየ እንዳለው አብዛኛውን ማኅበረሰብ የሚወክለው ፖለቲከኛ (በተለይ የኦሮሞ፣ የአማራና የትግራይ ልሂቅ) በጋራ የተስማማበትን አገረ መንግሥት መመሥረት እንኳን አልቻለም፡፡ እናም በተናጠል መንግሥትና የፌዴራል ተቋማቱን (የፀጥታ፣ ደኅንነትና መከላከያውን ኃይል) መገዳደር ቀጥሏል፡፡ መፈራረጁና  መወነጃጀሉም ተባብሷል፡፡ ሕዝብ ግን እየተጎዳ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ለዘመናት ከዘለቀው ከአሀዳዊ ፀረ ዴሞክራሲ አገዛዞች በፊትም ሆነ በኋላ የየራሳቸው አስተዳደር፣ ሕዝብና ወሰን ያላቸው ነገሥታትና መሪዎች ያሏቸው ቦታዎች አገር ነበረች፡፡ ሌላው ቀርቶ የዘመነ መሣፍንትን የመበላላት ክስተት ብንመረምር አንዱ ሌላውን ለማስገበርና ለመጠቅለል ከፍተኛ ፍልሚያ ተካሂዷል፡፡ አሀዳዊ ሥርዓት ከ125 ዓመታት ወዲህ ተጠናክሮ የአሁኗን ኢትዮጵያ ቅርፅ አካቶ በአዲስ መልክ ሲዋቀርም በኃይልና በጦር አቅም በመጨፍለቅ ብቻ ሳይሆን፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ማንነትንም በማስቀየር ጭምር መሆኑ የቅርብ ጊዜ የታሪክ ትውስታ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ የዓለም እውነትም ነበር፡፡

የአፄ ኃይለ ሥላሴ የዘውድ አገዛዝ ዕድሜ ከበቃም በኋላ ኢትዮጵያውያን ያጋጠማቸው ፀረ ዴሞክራሲያዊና ጠበቅ ያለ ማዕከላዊ አስተዳደር ስለነበር፣ ስለፌዴራሊዝም የሚያውቁት ነገር አልነበረም፡፡ በዚሁ መዘዝ ብቻ ሳይሆን ለዘመናት በተፈጠረው የብሔርና የመደብ ጭቆና ላይ ተመሥርተው በትጥቅ ትግል ሥርዓቱን የተፋለሙ የፖለቲካ ኃይሎች፣ በደርግ ዘመን መጨረሻ አካባቢ 17 ያህል ደርሰው እንደነበር ይነገራል፡፡

እነዚህ ሁሉ ኃይሎች ታዲያ ሁሉን አሳታፊና አቃፊ አገረ መንግሥት ለመመሥረትና በአገሪቱ የተሻለ ፌዴራላዊ ሥርዓት ለመዘርጋት በሙሉነት ተሳትፈው ሕዝቡን የታደገ የፖለቲካ መስተጋብር ተፈጠሯል ለማለት አይቻልም፡፡ በተለይ ሰፊ ቁጥርና የተሰባጠረ ማንነት ያላቸው የአማራ ማኅበረሰብን የመሰሉ ሕዝቦች ካለበቂ ውክልና የታለፉበት የሕገ መንግሥት መሠረታዊ ሒደት መደረጉን አሁን ድረስ የሚተቹ ቁጥራቸው ትንሸ አይደለም (ይህንን እንዴትና ለምን ብሎ መፈተሽ ለምን ያቅታል)?

እንዲያውም በአብዛኛው በኢሕአዴግ ግንባር ቀደም ተዋናይነት የተጠናቀቀው የደርግ ሥርዓት መገርሰስም ሆነ የሽግግር መንግሥቱ የፌዴራላዊ ሥርዓትን የመመሥረት ሒደት፣ የአሸናፊዎች አስተሳሰብ ሆኖ ነበር የወጣው የሚሉ ብዙ ናቸው፡፡ በዚህም መዘዝ ቀደም ያሉት አገዛዞች መሪዎች የወጡበትን ማኅበረሰብ እንደ ጠላት የሚፈርጅ፣ በታሪክ አጋጣሚ የተጋባና የተዋለደውን ስብጥር (ኢትዮጵያዊ ማንነት ያለውን) ሕዝብ የሚያገልግል የዘውግ ፌዴራሊዝም እንዲያቆጠቁጥ ሆኗል፡፡

በዚህ ምክንያት አሁን ለውጥ መጣ እየተባለ እንኳን ሕዝቡ ወደኋላ ተመልሶ፣ እርስ በርስ በሚያጠራጥርና ደም በሚያቃባ መንገድ ብሔር ከብሔር ተለያይቶ የሚጠዛጠዘው አፍራሽ በሆነው የፖለቲከኛው መውገርገር ምክንያት ነው፡፡ አነሰም በዛም በሠለጠነ የምርጫ ሒደት አገር እየመራ ያለው ኃይል ሄዶ ሄዶ የአንድ ብሔር ጠበቃ የመሰለውም ሆነ እንዲመስል እየተደረገ ያለውም በከረመው ብልሽት መነሻ ነው፡፡ እነሆ መቋጫ ያጡ ጦርነቶችና የሰላም ዕጦቶችስ ማን ፈጠራቸውና?

በተለይ ‹‹ለዘመናት ተረስተን ኖርን›› የሚለው የአገራችን የኅብረተሰብ ክፍልና ‹‹የብሔር ጭቆናን›› የፖለቲካዊ ትግሉ ዋነኛ መሣሪያ አድርጎ የዘለቀው (የኦነግና የሕወሓት አተያይ አቀንቃኝ) ልሂቅ፣ በየፊናው ሲጻፍለት የነበረውን የተዛባ ትርክት ሲያመነዥክ መኖሩ አንሶ አሁንም መቀጠሉ የሥርዓቱ ክስረት ማሳያ ነው፡፡ አካሄዱ ጠንካራ አገረ መንግሥትና ኅብረ ብሔራዊት አገር ለመገንባት ያስችላል ብሎ ማሰብም አጉል የዋህነት ነው፡፡ እናም የቆምንበትን መሠረት መፈተሽ ብልህነት ነው፡፡

ፌዴራሊዝሙ በአፍራሽና ኢሚዛናዊነት የተቃኘ ብሎም በቂም በቀልና መጨካከን የተለበጠ በመሆኑ ነው ጠንካራ አገራዊ ኅብረት ለመፍጠር ያላስቻለው የሚሉ ተቺዎች አሉ፡፡ ለዚህም ባለፉት 30 ዓመታት የተከሰቱ የቁርሾና መበላላት ዓውዶችን ያወሳሉ፡፡ ይህ ሥርዓት ዕውን ከሆነ በምሥራቅ ሐረርጌ፣ በአርሲና በባሌ፣ በወለጋ፣ በቤኒሻንጉልና በጋምቤላ፣ እንዲሁም በሶማሌ ክልልና በአንዳንድ የደቡብ አካባቢዎች (ጉራፈርዳ፣ ጌዴኦ)፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህም በወለጋ ልዩ ልዩ አካባቢዎች፣ በማይካድራና በወልቃይት  በአብዛኛው በአንድ ማኅበረሰብ ላይ ያተኮረ ጥቃት መፈጸሙ የበቀል አዙሪቱ እንዳይበጠስ አድርጓል ባይ ናቸው፡፡

ሌላው ቀርቶ ከአምስት ዓመታት ወዲህ በአንዳንድ ክልሎች ንፁኃንን በማንነታቸው ብቻ መግደል፣ ማቁሰልና ንብረት ማውደም ብቻ ሳይሆን፣ በመቼውም ጊዜ በዚች አገር ያልታየ የሰው ልጅን መስቀልና ማረድ መታየቱ የደረስንበትን የዘረኝነትና የጭካኔ አዘቅት ቁልጭ አድርጎ አሳይቷል የሚሉ ወቃሾች ተደጋግመው ተደምጠዋል፡፡ የዘውግ ፌዴራሊዝሙ መካረርና ውድቀት ዋነኛ ማሳያም ተደርጎ የሚታየው ራሰን ማስተዳደር ማለት፣ ክልሎችን ሌላ ማንነት ካላቸው ሰዎች ማፅዳት እየመሰለ በመምጣቱ ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ሁኔታ እንዴት መቀጠል ይቻላል?

በእርግጥ የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት በተናጠል እየወረደበት ያለው ሂስና ትችት፣ አንድ ጊዜ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ እያለ እዚህ መድረሱ ይታወቃል፡፡ ሥርዓቱ በተለይ ቋንቋና ብሔር ተኮር መሆኑ፣ ‹‹በአስተዳደር የየራሳቸው ሉዓላዊ ሥልጣንና መዋቅር ያላቸው ክልሎች በጋራ የሰየሙት አንድ ፌዴራላዊ መንግሥት ይኖራቸዋል›› ከሚለው ወደ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የመምጣት ዕሳቤ ይልቅ፣ መለያየትና ራሱን የቻለ መንግሥት ለመሆን የሚቋምጥ ‹‹አካል›› እንዲበረክት በማድረጉ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከአጉል ጥገኝነትና በሕዝብ ስም ሥልጣን ላይ ተፈናጥጦ ለመበዝበዝ ከመመኘት የሚመነጭ ሲሆን፣ ለአገር ብልፅግናም ሆነ ለሕዝቡ ከችግር መውጣት ፋይዳ የለውም፡፡

በዓለም ላይ ከሦስትና ከአራት ያልበለጡ አገሮች ብቻ የሚከተሉትና አብሮነትን የሚሸረሽር ለመሆኑ ያለፉትን አምስት ዓመታት ምስቅልቅል ብቻ ማየት በቂ ነው፡፡ በእነዚህ አጭር ወቅቶች እጅግ ደም አፋሳሽ የሚባሉ የእርስ በርስ ጦርነቶችና ግጭቶች በተለይ በዋና ዋናዎቹ ሦስት ክልሎች ተከስተው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ፣ የአካልና የሥነ ልቦና ጉዳቱም ከፍተኛ ሆኖ ይታያል፡፡ እንደ ደሃ አገር ሀብትም ሰፊ ቁጥርና መጠን ያለው ገንዘብ በጦርነቱ እየተበላ ነው፡፡

አሁንም ባልቆመ ፍልሚያ አገርም ለከፋ ችግር ስትዳረግ ታይቷል፡፡ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 39 የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብት ደንግጓል፡፡ ይህ መብት ተፈጻሚ የሚሆንበት የራሱ ቅድመ ሁኔታዎችና ሕዝበ ውሳኔዎች ያሉት ቢሆንም፣ ብዙዎች ‹‹አገሪቱን ለብተና የሚጋብዝና አፍራሽ ነው›› ሲሉ የሚተቹት ሁሉም የብሔር ክልሎች የራሳቸውን ብቻ በማቀፍ ሌሎች ሕዝቦችን በመግፋትና የጋራነታቸውን በመዘንጋት የዕውር ድንብር ጉዞ ውስጥ እየገቡ በመሆናቸው ነው፡፡ ክልሎች በወሰንና በማንነት ጥያቄ የተነሳ ወደ ጦርነት የሚያስገባቸው ገፊ ምክንያትም የሚመነጨው ከዚሁ የእኔ የእኔ ባይነት (Ego) የተነሳ ነው፡፡ ሥርዓቱን ወደ አልሆነ አዘቅት እየከተተው የሚሄደው ወረርሽኝም ይኼ ነው፡፡

አሁን ማን ይሙት ከዚህ በኋላ የትኛው ኢትዮጵያዊ ነው ባልተወለደበትና በማንነቱ የእኔ በማይለው አካባቢ/ክልል ውስጥ ዋስትና ተሰምቶት ሀብት የሚያፈሰው፣ የሥራ ዕድልስ ልፍጠር ብሎ የሚሠራው? በታሪክ አጋጣሚ እዚያው ተወልደው ቋንቋ፣ ባህልና እምነቱን ብቻ ሳይሆን በደም የተቀላቀሉ ወገኖችን ጭምር የለበለበና መድረሻ ያሳጣ የውንብድናና የተዳፈነ እሳትስ እንዴት የፌዴራሊዝም ውጤት ሊባል ይቻላል? በየአካባቢው እየታየ ያለው የእርስ በርስ ጦርነትም ቢሆን ማንነት ተኮር እየሆነ መሄዱ እንዴት ሊሸፈን ይችላል? አካሄዳችን ይፈተሽ፣ አገር ትትረፍ፡፡

ይልቁንም መግደርደሩንም ሆነ ማለባበሱን ትቶ ይህ አፍራሽና አብሮነትን የማይሰብክ ሥርዓት ገና ከአፈጣጠሩ ጀምሮ አብሮነታዊ አገረ መንግሥትን መገንባት የማይችል፣ የአገራችንን ብዝኃነት የማይመጥን ነው ይሉ የነበሩ ሂሶችን አዳምጦ መጠገንና ማሻሻል ነው የሚበጀው የሚሉ ሰዎችን ማዳመጥ ያስፈልጋል፡፡ በጦርነትም ሆነ በግጭት በመተላለቅ የሚፈታ ችግር እንደሌለ ተገንዝቦ ሁሉም ይመለከተኛል የሚል ፖለቲከኛና ምሁር ወደ ምክክርና ድርድር እንዲመጣ፣ በቀዳሚነት አገረ መንግሥቱ የተመሠረተበትን ሥርዓት ለመፈተሽ መነሳቱ ነው የሚጠቅመው፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ለቋንቋና ለማንነት በሰጠው የተንቦረቀቀ የክልልና የሥልጣን መለያ ምክንያት መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ የአስተዳደር አመቺነትና የመሠረተ ልማት ሁኔታ እንኳን ታሳቢ ሳይደረግ ሁሉም እንደ ጉንዳን ‹‹ብሔሩን›› እየፈለገ የሚቧደን መሆኑን ሲተቹ የኖሩ ሰዎች አሁን ባስከተለው ጣጣ ምክንያት ሊደመጡ የሚገባቸው ናቸው፡፡ እነሆ ከ33 ዓመታት ሥርዓቱ የማንነት ወይም የወሰን ይባል የአስተዳፈር ችግሮችን ፈትቶ አይደለም አዳርሶስ መቼ ጨረሰ? የእርስ በርስ መተማመንና አብሮነትስ መቼ አመጣ? እንዲያም ወደ ዘመነ መሣፍንት የእርስ በርስ ትርምስና መገዳደል ሲመልሰን የት አየሁ የሚሉ ወገኖች ሊደመጡ ይገባቸዋል፡፡

ይኼ የፌዴራሊዝም መሳከርና የብሔር ፍጥጫ ሌላም መገለጫ አለው፡፡ ለዘመናት ተቃቅፎ የኖረውና በወያኔ ከፋፍለህ ግዛው አስተዳደር እንኳን በአንድ ክልል ውስጥ የቆየው ደቡብ ክልል አብሬ አልኖርም በሚሉ ካድሬዎች ጭንቅላቱ እየዞረ ነው፡፡ በዚሁ ግዛት ከ50 የማያንሱ ብሔረሰቦች እንዳሉ ቢነገርም፣ ጥምርና ኅብረ ብሔራዊ ማንነት ያላቸው ወገኖች ግን ትንሽ አይደሉም፡፡ ጉራጌ፣ ወላይታና ጋሞን የመሳሰሉት  ደግሞ አዲስ አበባን ጨምሮ ሁሉ አገርሽ ሆነው የኖሩ ሕዝቦች ነበሩ፡፡ ግን አቅጣጫው መደጋገፍና ተቀናጅቶ መኖር ሳይሆን እየተከፋፈለ፣ ሥልጣን በመቀራመት ውስጥ ወድቋል፡፡

በተጨማሪም አብዛኞቹ እነዚህ ሕዝቦች ተቀራራቢና በአንድ የቋንቋ ቤተሰብ ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውና በተመሳሳይ የጭቆና ታሪከ ማለፋቸው እንኳን እንዲያሰባስባቸው አይፈልግም፡፡ በባህል፣ በወግና በታሪክም የሚቀራረቡ መሆናቸውን ፖለቲከኛው እንደ ፀጋ አይወስድም፡፡ እናም ካለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ወዲህ ብቻ  ከ18 የማያንሱ የማንነት ጥያቄዎች ተነስተውባቸው አጋጭተዋል፣ አከራክረዋቸዋል፡፡ ቢያንስ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀርበው ውድቅ የተደረጉትም በርካታ ነበሩ፡፡ ከለውጡ ወዲህ ደግሞ የብሔር ክልል እንሁን የሚለው ጩኸት እንደ አዲስ አገርሽቶ ሕዝብ እያፋጠጠና እያጋጨ (የሲዳማና የወላይታ፣ የጉራጌና የከምባታን ልብ ይሏል) መንግሥትን እያስጨነቀ ቢቆይም ደቡብ ወደ አራት ክልልነት ከመበተን አልዳነም፡፡ እንደ ጉራጌ ያሉ የክልል ጥያቄዎችና የክልል ማዕከል ጥያቄዎችም ገና የተመለሱ አልሆነም፡፡ የትግራይና የአማራ ክልሎች ሥር የሰደደ ንትርክና ፀብ በአብዛኛው ከወሰንና ከማንነት ጋር የተቆላለፈ ነው፡፡

የዘውግ ፌዴራሊዝሙ የፍጥጫ ዳራ በዚህ ብቻ የሚያቆም አይደለም፡፡ አንዳንዴ ጋብ ያለ ቢመስልም፣ በጋምቤላ ዓመታትን እየተሻገረ ያለው የኑዌርና የአኙዋ ፍጥጫ በመጠፋፋት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአንፃራዊነት ‹‹ብዙኃን›› የሚባለው በርታ ተጭኖናል የሚሉ የጉሙዝ፣ የማኦና የኮሞ ልሂቃን ጥያቄ አለ፡፡ የጉሙዝና በክልሉ ሰፊ ቁጥር ያለው የአማራ ማኅበረሰቦች እስካሁንም ድረስ በማንነትና በወሰን ጥያቄ ሰበብ በተደጋጋሚ ሲዳሙ ታይቷል፡፡ ተስማምተው አብረው መኖር ቢችሉ ግን አይደለም ለእነሱ ለሌላም የሚተርፍ የፀጋ ባለቤት ነበር ክልሉ፡፡ ግን ቅኝቱ አንዴ ተበላሽቷልና ነገም ሰላም ውሎ ማደር ቀላል አይሆንም፡፡

በአፋርና በሶማሌ፣ በሶማሌና በኦሮሚያ (የቅርቡ የባቢሌ ግጭትን ያስታውሷል) ሲጋጩ እንደነበሩ ሊካድ አይችልም፡፡ ይህ ሁሉ እንግዲህ ‹‹ዶሮ ብታልም ጥሬዋን›› እንዲሉ ዓለም ወደ አንድ ትልቅ የጋራ ማኅበረሰብ ለመሰባሰብ ሲባትልና ሲተባበር፣ በእኛ አገር ሁሉም በጎሳ ቆጡ ሥር ተጠልሎ የበለጠ እንዲናቆር እያደረገው ያለው ተንጋዶ በበቀለው የዘውግ ፌዴራሊዝም ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ መንግሥት የወልቃይትና የራያን የማንነት ጥያቄዎች ለመፍታት እንዴት ያለ ቅርቃር ውስጥ እንደገባ ማን ሊስተው ይችላል? ችግሩ አሁን በተያዘው መንገድ ይፈታስ ይሆን? እንጃ፡፡

ይህ በአፍራሽ አስተሳሰብ የታጀበው ግን በስም ብቻ ትልቁ ፌዴራሊዝምን የያዘው አካሄዳችን ነው ግጭትና ጥፋት እየጋበዘ ያለው ቢባል ስህተት የለውም፡፡ የተጀመረውን የአገር ልማትና የግል ባለሀብቱን ሰፊ እንቅስቃሴም እየገደበ የሚገኘው፡፡ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን የትም ዓለም ሠርተው፣ ተበድረውና አሰባስበው ሀብት ያመጡ ባለሀብቶች ጭምር በዋና ከተማዋና በአንዳንድ ክልሎች እንደፈለጉ  እንዳያለሙና አገር እንዳይቀይሩ፣  ‹‹አይዟችሁ›› ባይ ወገን ሕዝብ እያጡ የሚገኙት፡፡ መንግሥትም በብሔርተኝነት የሚወቀስ ተቋም ወደ መሆን እየወረደ የሚገኘው፡፡

በመሠረቱ በአገራችን የዘውግ ፌዴራሊዝሙ የተዘራበት መንገድ የተንሸዋረረና ሆን ተብሎ ጥቂቶችን በኢፍትሐዊነት ለመጥቀም ተብሎ ስለሆነ፣ ቢታሰብም ኅብረ ብሔራዊና ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለመፍጠር አላስቻለም፡፡ አገራዊ አንድነትና የሕዝቦችን አብሮነት ዕውን ለማድረግ  የተሠራው ሥራም እዚህ ግባ የሚባል ውጤት አለማምጣቱ የታወቀ ነው፡፡ ሚዲያው፣ መንግሥትና አንዳንዱ ፖለቲከኛ ‹‹ለአፍ ያህል›› አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ እየተፈጠረ ነው ቢሉም፣ ውጤቱ የተገላቢጦሽ እየመሰለ መምጣቱ ነው የዛሬው እውነታ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየው፡፡ ጭራሸ እርስ በርሱ የሚተጋተግ የጋራ ዕሴት አልባ ትውልድ በግላጭ መምጣቱ ነው የሚታየው፡፡

ትናንትም ሆነ ዛሬ እውነቱ እየተድበሰበሰ እንጂ በዚች አገር ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ተገንብቷል ከተባለ የኖረውን ቁስል ያውም በተዛባ ፍረጃ እያከከ ከክልሌ ውጣ፣ ወይም እዚህ እንዳትደርስ የሚለው እንዴት ሊበዛ ቻለ? የጥቂት አክራሪ የብሔር ፖለቲከኞችን ውዥንብርና ጥሪ እየሰማ እንዴት በአገርና ሕዝብ ሀብት ላይ የሚዘምት፣ ወገኑን ቀጥቅጦ የሚገል ግሪሳ ተበራከተ ብሎ መመርመር ያስፈልጋል፡፡ በማንነት እየተሰባሰበ የጋራ መንግሥትን ወይም ሌላውን ክልል ለመውጋትስ ምን አነሳሳው? አለመተማመኑና መጠራጠሩስ አንዴት ተባባሰ? አንዳንዱ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያለውን ጥገኛ ጨምሮ፣ በሕዝብ ደም ለመበልፀግና ሥልጣን ለመቆናጠጥ የሚዳዳውስ ፖለቲከኛ በምን ሒሳብ የፌዴራሊዝም ጠበቃ ሊባል ይችላል ብሎ መፈተሽ ይገባል፡፡

በመሠረቱ ፌዴራሊዝም ማለት በፌዴራል መንግሥቱ ውስጥ የጋራ ድምፅና እኩልነት የሰፈነበት አወቃቀር ማስፈን ነው፡፡ ይኼም ነገ ኢትዮጵያዊያን ፍትሐዊነትና እኩልነትን አስፍኖ አብሮ ከመኖር ውጪ የተሻለ አማራጭ እንደሌላቸውም ዕሙን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን በአውዳሚ አስተሳሰብና በተዛባ ትርክት የተመራ በመሆኑ ከእውነታው ውጪ እየነጎደ ነው፡፡ ትናንት ብቻ ሳይሆን ዛሬም ቢሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በማንነታቸው ብቻ፣ በሌላ ክልል ስለሚኖሩ የመምረጥና የመመረጥ መብት ይነፈጋሉ፡፡ እንደ ዜጋ ሥራ የማግኘትም ሆነ ቤት ሠርቶ የመኖር ዕድላቸውም ውስን ነው፡፡ ይኼ ከእኛ አገር ውጭ የት ይኖር ይሆን ብሎ መመርመር ያሻል፡፡ በአካሄዱስ የትኛውን ፍትሕ ለማረጋገጥ ይቻላል?

በዚህች አገር የተጀመረው ፌዴራላዊ ሥርዓት በሽታው ዘውግ ተኮር ከመሆኑ የሚመነጭ ነው ብቻ እንዳይባልም፣ የመንግሥት አባል ክልሎችን ሲያደራጅ ግልጽና የማያሻማ መሥፈርትን አለመከተሉ እያደር ራስ ምታት እየሆነ ነው፡፡ የክልልነት መሥፈርቱ በጎሳ ወይም በብሔረሰብ ነው እንዳይባል ሁሉንም ብሔረሰቦች በክልል ደረጃ ዕውቅና አለመስጠቱ የሚታይ ነው፡፡ በሕዝብ ብዛት፣ በቆዳ ስፋትና በመልክዓ ምድር እዳይባልም ዝብርቅርቅ ነገር ነው የሚታየው፡፡ ለምን ያስብላል፡፡ በዚህ አካሄድስ የት መድረስ ይቻላል?

ከተገባበትና ትውልዱ ሊቀይረው ከሚገባው ሥርዓታዊ ክፍተት ለመላቀቅ 

እንደ ፖለቲካ ንፍቀ ክበብ የሥርዓቱን እንከኖችን እየነቀሱ ከፍጥጫና ቀስ በቀስ ከሚደፈርስ አገራዊ የሥጋት ስሜት የሚያወጣ የፖለቲካ ምክክርና ድርድር መጀመር ግድ ይላል፣ ይገባልም፡፡ በቀዳሚነት ፌዴራሊዝም ያለ አብሮነትና መከባበር፣ ያለ እውነተኛ ዴሞክራሲ አይረጋምና ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት ለድርድር ሳያቀርቡ በፅናትና በጥልቅ ለመተሳሰብና ለስምምነት መትጋት ግድ ይላል፡፡

በሌላ በኩል ብሔር ተኮርና ማንነት አቀንቃኝ ፌዴራሊዝም ያለገደብ ሲለጠጥ፣ በሌላው ዓለም ያመጣውን ቀውስ መርምሮ እኛ የቆምንበትን መሠረት መፈተሽና ወደ ገደል የተዘረጋውን ሀዲድ መነቃቀል አስፈላጊ ነው፣ ዋጋ ተከፍሎም ቢሆን፡፡ ለዚህ ደግሞ ከሁሉ በፊት ጦርነትና ግጭት ቆሞ ምሁራን፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የእምነት አባቶችና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ወደ መድረኩ ይምጡ፡፡ መንግሥት የዕርቅና የሰላም ተዋናይ ብቻ ሳይሆን ጠንካራ አመቻች ይሁን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...