Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

ከጠዋት እስከ ማታ እየባዘንኩ የሳምንቱ ቀናት እንዴት እንደተገባደዱ አላስተዋልኩም። የዓርብ ምሽት ላይ ቤቴ ሶፋ ላይ ቁጭ ብዬ  የቴሌቪዥኔን  ጣቢያ  ስቀያይር  ነበር  መብራቱ  ድርግም  ብሎ የጠፋው፡፡ “ወይ መብራት ኃይል ምን ይሻላችሁ ይሆን…” እያልኩ ሻማ ፍለጋ መሳቢያ ስጎረጉር ከመብራት ኃይል ሳይሆን ችግሩ ከእኔ መሆኑን ልጄ አረዳኝ፡፡ “ሳይ ካርድ ነው ካርዱ አልቆ እኮ ነው…” ብሎኝ እርፍ፡፡ ያለኝ  አማራጭ  በካርዱ  መበደርና  ለነገ  መዘጋጀት  ነበርና  ካርዴን  ቆጣሪው ላይ  ሰክቼ  ምሽቷን  ያለ  ስቶቭ  ለማሳለፍ  ተገደድኩ።

ጥሎብኝ  የካርድ  ሒሳቡን  ከቆጣሪ  ላይ  ማንበብና ስንት እንደቀረው የማስተዋል ልማድ የለኝም። ታድያ  ቅዳሜ  ቢሮ  ከመግባቴ  በፊት  አንድ  አፍታ  ደረስ  ብዬ  ካርድ  ለመሙላት  እያሰብኩ  ወደ  መኝታዬ አዘገምኩ፡፡ ጧት  የመንግሥት  ሥራ  መጀመሪያ  ላይ  መድኃኔዓለም  አካባቢ የሚገኘው  የመብራት ኃይል ክፍያ ጣቢያ ስደርስ በሁለት ረድፍ የተሠለፈው ሕዝብ  ከግቢው ወጥቶ እስከ ውጪ ፈሷል። የማይሆን መሆኑን ስረዳ ቀጥ  ብዬ ወደ  መሥሪያ ቤቴ አመራሁ፡፡ ይሁንና  እስከ  ስድስት  ሰዓት  ካርዴን  ካልሞላሁ  ሦስት  ቀናት  በጭለማ  ልዋጥ ነው፡፡

ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ችግር ገጥሞኝ መሳለሚያ አካባቢ ወደ የሚገኘው የመብራት ክፍያ ጣቢያ አምስት ሰዓት አካባቢ ደርሼ መብራት የለም በሚል ሳልሞላ ቀርቼ ሁለት ቀን በጭለማ ማሳለፌ ትዝ ይለኛል መብራት ኃይል መብራት አጥቶ ልብ ይሏል፡፡ አለቃዬን  አስፈቅጄ  አምስት  ከምናምን  አካባቢ  ከቢሮ  ወጥቼ  ወደ  ጊዮርጊስ  ውቤ  በረሃ  ተብሎ  የሚጠራው  ሥፍራ  የሚገኘው  መብራት  ክፍያ  ጣቢያ  ሳመራ መጠነኛ ወረፋ ነበር፡፡ ወጣቶች፣  አረጋዊያን፣  ታዳጊዎችና ከሁሉም ዓይነት  በአግዳሚው  ወንበር  ላይ  ተቀምጠው  ሠልፍ  ይዘዋል። እኔም  እንዳመጣጤ  ከአንዲት  ባልቴት ጎን ቁጭ  አልኩ። ክፍያው  ለፍጥነት  ተብሎ  በአዲስ  መልክ  በቴሌ  ብር  የተጀመረ  ቢሆንም  የአንድ  ሰው  ክፍያ ለመፈጸም ጊዜ እየወሰደ ይገኛል። እንደ ምንም ከእኔ ፊት ያሉት ባልቴት ተራቸው ደረሰ። ገንዘብ  ሰብሳቢዋ   “እማማ  ክፍያ  በቴሌ  ብር  ነው…”  አለቻቸው፡፡ እማማ  መለሱ፣  “ቴሌ  አይደለም  መብራት  ነው…”   ተቀባይዋም  እኔም  ፈገግ አልን። “አያይ እንደሱ ማለቴ አይደለም ለማለት የፈለኩት” ብላ ማብራራት ጀመረች። እማማ ሊረዷት  ስላልቻሉ የሚከፈለው  በቴሌ  ብር  ነው  ጥሬ  ብር አንቀበልም!!” አለች ፍርጥም አድርጋ።

“እንዲያው ምን ይሻላል?” አለች ገንዘብ ተቀባይዋ።  “አሁን ምን ማድረግ ይሻላል!” ደገመችው። “የተሰጠን መመርያ በቴሌ ብር ካልሆነ አትቀበሉ” ነው የሚለው፡፡ ግራ የገባው ትዕዛዝ መሆኑን እያሰብኩ ሳለ እማማ አሁንም ጥያቄ አቀረቡ፡፡ “በሕይወቴ ሙባይል የሚባል ነገር ይዤ አላውቅ ታድያ ምን ላድርገው?” ብለው የሁለት የመቶ ብር ኖቶች እያሳዩ ጠየቋት። ገንዘብ ተቀባይዋ ወደ እኔ እያየች “ቴሌ ብር ትጠቀማለህ?” አለችኝ፡፡ አዎን አልኳት ። “ከቻልክ የሳቸውንም ብር ተቀበልና ሙላላቸው…” አለችኝ ። በቂ ገንዘብ እንዳለኝ ካረጋገጥኩ በኋላ ይቻላል አልኳት፡፡ የሁለታችንንም አስገብቼ ክፍያዬን ከጨረስኩ በኋላ እኔና እማማ ተያይዘን ወጣን፡፡

ወቸ ጉድ ! የሚል የመገረም ቃል ካፋቸው አውጥተው ያወጉኝ ጀመር አንድም ትልቅ ሰው እያወራህ ጥሎ መሄድ ባህልም ስላልሆነ እንዲሁም የአዛውንቶች ንግግር ስለሚመስጠኝ አንዳንዽ ቃል ጣል እያረግሁ አዳምጣቸው ጀመር፡፡ “ድሮ ድሮ መብራት፣ ውኃና ስልክ፣ ቤታችን ድረስ መጥተው ነበር ጥሪታቸውን የሚሰበስቡት፡፡” በር ሲንኳኳ “ማነው?” ሲባል መብራት ፣ ውኃ ወይም ስልክ ነው። ተብሎ ከአሥር ብር ያልዘለለ ክፍያ እንጠየቅ ነበር፡፡ ከሌለን  “የሉም!” እናስብልና ቀይ ማስጠንቀቂያ የያዘ ወረቀት እናስለጥፍ ነበር አሉ፡፡ “ይኸው ዛሬ ቤታቸው  ድረስ  መጥተን  ተሠልፈን ተንገላተን  የምንከፍለውን የትየለሌ ብር ተጠየፉት መሰል አንቀበልም ይሉ ጀመር!!” ከዚህ በላይ ምንጉድ አለ፡፡ የሚገርም ምልከታ አወሱኝ፡፡ “ልክ ኖት እማማ ጥሩ ታዝበዋል፡፡ አሁንም ግን አገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ እየጣሩ ይመስለኛል ስል ግምታዊ አስተያየቴን ሰጠሁ። “ወይ ቅልጥፍና… ቅልጥፍና ነው ቅርፍፍና!!”  አሉኝ። “ገንዘብ አንቀበልም ብሎ ሰው ማሰቃየት ነው ቅልጥፍና ብለው ሳቅ እያሉ መሻገሪያቸው መድረሳቸውን ነገሩኝ። የእኔ መንገድ ሌላ ስለሆነ መንገዱን አሻግሪያቸው ተሰናበትኩዋቸው እሳቸው ቆመውም እየሄዱም ይመርቁኝ ጀመር እኔም አሜንታዬን እየተቀበልኩ ጉዞዬን ቀጠልኩ፡፡

ግን ግን ይህ የቴሌ ዲጂታል አከፋፈል ልክ እንደ እማማ ምክንያቱ በደንብ አልገባ አለኝ፡፡ ለቀልጣፋ  አገልግሎት  አሰጣጥ  እንዳንለው  ብራችንን  ይዘን  እንደምንመጣው  ሞባይላችንንም ይዘን ነው የመጣነው፡፡ ብሩን በቴሌ ብር በኩል ከመስጠት ባሻገር ምንም ቀልጣፋ አገልግሎት አልታይህ አለኝ፡፡ እንደውም  የቴክኖሎጂውን  አዲስነት  ያልተረዱ  ሰዎችን  በማስረዳትና  አጠቃቀሙን  በማሳየት  የሚወስደው  ጊዜ  ቀላል  ባለመሆኑ  ይባስ ጊዜ የሚበላ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ በዚያ ላይ የሞባይል አጠቃቀም የማያውቁ በርካታ ዜጎቻችን ለእንግልት የሚዳረጉበት ሁኔታም ፈጥሯልና፡፡ ቴሌም ይሁን የኢትዮጵያ መብራት ኃይል መፍትሔ ሊያበጅለት የሚገባ ይመስለኛል። በዘላቂነትም ይህ አገልግሎትን ባለንበት ሆነን ክፍያ የምናስገባበት ሲስተሙ ካልተዘረጋ በስተቀር ለተቋማቱ ካልሆነ በቀር ለኅብረተሰቡ የሚሰጠው ፋይዳ ያለ አይመስለኝም። በመሆኑም ባለንበት የመክፈል ሲስተሙ በቶሎ ተግባራዊ ቢደረግ በርካታ ዜጎቻችን  ቀልጣፋ  አገልግሎት  እንዲያገኙ የሚያስችል ነውና ሊታሰብበትና ጥረት ሊደረግበት ይገባል፡፡

                                                                      (ሚስባህ አወል፣ ከአዲስ አበባ)

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...