Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትበጥሩነሽ ዲባባ አትሌቲክስ ማዕከል የሚገኙ አትሌቶች በምግብ አቅርቦት ምክንያት ተቃውሟቸውን አሰሙ

በጥሩነሽ ዲባባ አትሌቲክስ ማዕከል የሚገኙ አትሌቶች በምግብ አቅርቦት ምክንያት ተቃውሟቸውን አሰሙ

ቀን:

በኦሮሚያ ክልል በአሰላ ከተማ በሚገኘው በጥሩነሽ ዲባባ አትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከል የሚገኙ አትሌቶች ከምግብ አቅርቦት ችግር ጋር በተያያዘ ቅሬታቸውን በሰላማዊ ሠልፍ ማሰማታቸው ተገለጸ፡፡

በማዕከሉ ትምህርትና ሥልጠና እየተከታተሉ የሚገኙ የተለያዩ አትሌቶች፣ ‹‹የሚቀርበው የምግብ ጥራትና መጠን ከተማሪው ሥልጠና ጋር የሚመጣጠን አይደለም፤›› የሚል ቅሬታ ማቅረባቸው ተጠቅሷል፡፡፡

አትሌቶቹ በትራክና ሜዳ ተግባር፣ እንዲሁም እግር ኳስ ተጫዋቾችን ጨምሮ በማዕከሉ መደበኛ ሥልጠናና ትምህርት ለመውሰድ የዘንድሮውን ዓመት ለመጀመር ከመስከረም 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ማዕከሉ መግባታቸው የተጠቀሰ ሲሆን፣ ከምግብ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ችግሮች እየገጠሟቸው እንደሆነ፣ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ለሪፖርተር ምንጮች አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

ለአትሌቶች የሚቀርበው የምግብ መጠን ከሥልጠናው ጋር የሚመጣጠን እንዳልሆነ፣ አትሌቶቹን በሚፈለገው መጠንና አቅም ማሠልጠን አለመቻሉንም  አስረድተዋል፡፡

በማዕከሉ ከምግብ ጋር በተያያዘ የጥራት፣ እንዲሁም የመጠን ችግሮች መስተዋል የጀመሩት ከ2015 መጨረሻ ወራት ጀምሮ እንደሆነ የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ ዘንድሮ ይሻሻላል የሚል እምነት የነበረ ቢሆንም እንዳልተሻሻለ አስታውቀዋል፡፡

ሪፖርተር በማዕከሉ ከሚሠለጥኑ አትሌቶች ባገኘው መረጃ መሠረት በርካታ አትሌቶች በታይፎይድ ሕመም እየተጠቁ እንደሚገኙ፣ ለዚህም በማዕከሉ ከሚገኙ ክሊኒኮች ወደ ሆስፒታሎች ተጨማሪ ሕክምና እንዲደረግላቸው እየተላኩ መሆኑን አንስተዋል፡፡

እንደ አትሌቶቹ አስተያየት ከሆነ ስምንት ሴቶች አትሌቶችና አራት ወንድ አትሌቶች ወደ ማዕከሉ ከገቡበት መስከረም 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በሕመም ላይ እንደሚገኙ ተጠቁሟል፡፡

‹‹በማዕከሉ የሚገኘው ክሊኒክ ውስጥ በርካታ ታማሚዎች ይስተዋላሉ፡፡ አብዛኛዎቹም ወደ ሆስፒታሎች ይወሰዳሉ፡፡ የአብዛኛዎቹ ምክንያት ከምግብ ጋር የተያያዘ ነው፤›› በማለት ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ አትሌት ለሪፖርተር አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

ችግሩን ለመፍታት ከአሠልጣኞችና ከአትሌቶች የተወጣጡ ኮሚቴዎች ተዋቅርው ጉዳዩን ሲከታተሉ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፣ በመሀል የኮሚቴ አባሎቹ ራሳቸውን ከኃላፊነት ማንሳታቸው ተጠቁሟል፡፡

እንደ አትሌቶቹ አስተያየት ከሆነ፣ ከጥቅምት 20 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ የሚቀርብላቸው እንጀራ ላይ የጥራት ችግር መኖሩን ማስተዋላቸውንና ጉዳዩንም ለሚመለከተው አካል ማሳወቃቸውን አንስተዋል፡፡

የጥሩነሽ ዲባባ አትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከል ዲን አቶ ጎሳ ሞላ አስተያየት ከሆነ፣ ከተፈጠረው ችግር ጋር ተያይዞ ከአትሌቶች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ጠቅሰው፣ ችግሩን ለመፍታት ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

በ2002 ዓ.ም. የተቋቋመው የጥሩነሽ ዲባባ አትሌቲክስ ማዕከል ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ስፖርተኞችን በመመልመል በአትሌቲክስ ሥልጠና ዘርፍ በ100፣ 110፣ 400 ሜትር መሰናክል ርቀቶች፣ እንዲሁም በ100፣ 200፣ 400 እና 800 ሜትር ርቀቶች ሥልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡

ከዚህም ባሻገር ማዕከሉ በሜዳ ተግባር ማለት ርዝመት ዝላይ፣ ዲስከስ ውርወራ፣ ጦር ውርወራ፣ አሎሎ ውርወራ፣ ምርኩዝ ዝላይ፣ ከፍታ ዝላይና ሱልስ ዝላይ ሥልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

አካዴሚው ላይ በተለይ በኦሊምፒክ ዓመታት አትሌቶችን አፍርቶ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ክለቦች፣ ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ እንዲሁም ተቋማት ብቁ ተወዳዳሪ ያደርጋል፡፡ ከማዕከሉ የወጡ በርካታ አትሌቶች በተለያዩ ርቀቶች ኢትዮጵያን በመወከል በተለያዩ ዓለም አቀፍ መደረኮች ወክለው መሳተፍ ችለዋል፡፡

 ማዕከሉ በተለይ ተተኪ አትሌቶች ከማፍራት አንፃር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚጠበቅበት ይታመናል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...