Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየመከላከያ ሠራዊትን ስም የሚያጠለሹ በሕግ የሚጠየቁበት ድንጋጌ እንዲወጣ ጥያቄ ቀረበ

የመከላከያ ሠራዊትን ስም የሚያጠለሹ በሕግ የሚጠየቁበት ድንጋጌ እንዲወጣ ጥያቄ ቀረበ

ቀን:

  • የሰላም ማስከበር አባላት ሲመለመሉ መሥፈርቱ ግልጽ ንዲሆን ተጠይቋል

የአገር መከላከያ ሠራዊትን ስም የሚያጠለሹና የሠራዊቱን ቁመና የሚረብሹ አካላት በሠራዊቱ ሕግና ሥርዓት ተጠያቂ እንዲሆን የሚያደርግ ድንጋጌ እንዲዘጋጅ፣ የመከላከያ ሚኒስቴር ለፓርላማ ጥያቄ አቀረበ፡፡

የመከላከያ ሚኒስትሩ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) የተቋማቸውን የሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ሐሙስ ኅዳር 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የውጭ ጉዳይና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሲያቀርቡ፣ ባለፈው ዓመት እንደገና ተሻሽሎ በወጣው የአገር መከላከያ ሠራዊት አዋጅ ውስጥ ስም ማጠልሽት ተጠያቂ እንዲያደርግ ተካቶ የነበረው ድንጋጌ ግልጽ ባልሆነ ምክንያት እንዲወጣ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ፣ የመከላከያ ሠራዊት አዋጅ ለሦስተኛ ጊዜ ተሻሽሎ የወጣው በ2015 ዓ.ም. ነበር፡፡

ሚኒስትሩ የሠራዊቱን ህልውና ለማናጋትና በሰላም ማስከበር ሚና እንዳይሳተፍ ቅስቀሳ የሚያደርጉ አካላት መኖራቸውን ገልጸው፣ በማጠልሸት ድርጊት የሚሳተፉ አካላትን የሚገራና ለመዳኘት የሚያስችል ሕግ እንደ አዲስ በአዋጁ ተካቶ እንዲወጣ ቋሚ ኮሚቴውን ጠይቀዋል፡፡ 

በየትኛውም አገር ‹‹የመከላከያ ሠራዊትን የሚደፍርና ክብር የሚነካ ሰው የለም›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ አስተማሪ የሕግ ሥርዓት እንዲኖርና ሰዎች የመከላከያን ስም ለማጠልሽት እንዳያስቡ ለማድረግና ካሰቡም ተጠያቂ እንዲሆኑ ካልተደረገ፣ ‹‹ማንም ወሮበላ፣ ሌባና አክቲቪስት እየተነሳ ሠራዊቱን በውሸት ስም የሚያጠፋበት ዕድል ከሰፋ፣ ችግሩ ከባድ በመሆኑ ዕገዛ ይደረግልን፤›› ብለዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት የተፈጠረ ክፍተት ካለ አዋጁን ተከትለው በሚያወጡት ደንብና ሥርዓት ሊታይ እንደሚችል፣ ካልሆነ ደግሞ አዋጁ ማሻሻያ የሚደረግበት መንገድ እንደሚኖር ገልጸዋል፡፡

በአገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች የፀጥታ ችግሮች መስፋፋት በሥርዓቱ ላይ ዘላቂና ቀጣይነት ያለው አቅም ለመገንባት እንቅፋት መፍጠሩን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ አመራሮች ሕዝባቸውን በማስተባበር አካባቢያቸውን ከሽፍቶች ማፅዳት ባለመቻላቸው፣ የሠራዊቱ ግዳጅ አፈጻጸም እንዲሰፋና የክልል መንግሥታት መዋቅር ሥራን ሸፍኖ እንዲሠራ መገደዱን ተናግረዋል፡፡

‹‹የመከላከያ ሠራዊት ተልዕኮ ሌባ፣ ሽፍታና ወንበዴ ማፅዳት አይደለም፡፡ ሚሊሻ ምን ይሠራል? ከዚያ ካለፈ ፌዴራል ፖሊስ የት ይሄዳል? ይህንን አስተሳሰብ ካላስተካከልነው፣ በየመንደሩ ያለውን የሌባ እንቅስቃሴ መከላከያ መጥቶ ያፅዳ የሚል ፍላጎት እየሰፋ ከሄደ፣ ሠራዊቱ ሥራውን ማከናወን አይችልም፤›› ብለዋል።

የመከላከያ ሠራዊት ተልዕኮ የአገር ሉዓላዊነት ማስጠበቅና ወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን መመከትና ማስቀረት የሚያስችል በመሆኑ፣ ጠንካራ የመከላከያ ሠራዊት መገንባት አለብን እንጂ፣ የሠራዊቱ ተግባር በየመንደሩ ያለን ሌባ ማሳደድ ባለመሆኑ ይህ መሠረታዊ ችግር መስተካከል አለበት ሲሉ ለቋሚ ኮሚቴው ማሳሰቢያ አቅርበዋል፡፡

በድንበር አካባቢ በተለይም በጋምቤላና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል፣ የመከላከያ ሠራዊት አደረጃጀትና ሥምሪት መሰጠቱን ጠቅሰው፣ ሠራዊቱ ከዚህ ቀደም በሰሜን ጦርነት ምክንያት አቀማመጡ፣ ሥራውና ሥምሪቱ ሌላ ስለነበር ጦርነቱ ሲቀንስ ወደ ዋናው ተግባሩ ድንበርና ሉዓላዊነትን መጠበቅና መቆጣጣር የሚችልበት ሥምሪት ተሰጥቶ ውጤት እየመጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በጦር ሜዳ በግዳጅ የተሰው የመከላከያ ሠራዊት አባላት በተመለከተ የተደራጀ መረጃ፣ የድጎማና የጥቅማ ጥቅም አፈጻጸም ክፍተቶች ተነስተዋል፡፡ ለአብነትም ከደሴ ከተማ አስተዳደር ለህልውና ዘመቻ ሄደው የነበሩ 87 ሰዎች ያሉበት ባለመታወቁ ቤተሰቦቻቸው ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑን፣ በተጨማሪም በደሴ ከተማ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት የሆኑ ባለቤቶቻቸው መረጃ በተገቢው መንገድ ሳይታወቅ በየወሩ የሚሰጣቸው ተቆራጭ በመቋረጡ ችግር ውስጥ መሆናቸውና ጡረታ አለመከፈሉና የመሳሰሉ ጥያቄዎች ከቋሚ ኮሚቴ አባላት ተነስተዋል፡፡

የመከላከያ ሚኒስትር ደኤታዋ ወ/ሮ ማርታ ሉጂ በሰጡት ምላሽ፣ በጦር ሜዳ የተሰው የሠራዊት አባላትን መረጃ ለሕዝቡና ለቤተሰቦቻቸው መርዶ መንገር፣ መረጃና ጥቅማ ጥቅም የሚያደርሱ የተደራጁ ቢሮዎች በየክልሉና በዞኖች መኖራቸውን፣ ነገር ግን የቤተሰብ አድራሻና ወራሽ በትክክል ያልሞሉ የሠራዊቱ አባላት በመኖራቸው፣ አንድ አባል መሰዋቱ ሲነገር ወራሽ ነን ብለው የሚመጡት፣ አባሉ ከሞላው መረጃ ጋር የማይመሳሰል በሚሆንበት ወቅት፣ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ሄዶ በመጓተቱ ምክንያት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም ችግር የሚያጋጥመው በጦርነቱ ገና ጉዳያቸው ያልታወቀ፣ መረጃቸው ያልተጣራና በፀጥታ ችግር ምክንያት ያልተደረሰባቸው አካባቢዎች በመኖራቸው ነው ብለዋል። በዓለም አቀፍ ሰለም ማስከበር ሥምሪት በሦስት ወራት ውስጥ 12.4 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 10.4 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የውጭ ጉዳይና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ከ1950ዎቹ ጀምሮ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ከፍተኛ ሚና  ያላትና ሠራዊቱ ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ፣ ተወዳጅነትንና ተቀባይነት ያገኘ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ የሠራዊት አባላት የምልመላ መሥፈርት ግልጽ እንዲሆንና ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል፡፡

በተጨማሪም አገር ጠንካራና የተደራጀ የባህር ኃይል ግንባታ እንዲኖራት አስፈላጊ ግብዓቶች፣ የሙያ ብቃትና ክህሎት ያለው የሰው ኃይል ማሟላት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ደረጃውን ያሟላ ጠንካራ አደረጃጀት እንዲኖርና መሠረታዊ የሥልጠና ማዕከል የመገንባት ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...