Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየጠቅላይ ሚኒስትር የሥልጣን ዘመን እንዲገደብ በርካታ ኢትዮጵያውያን እንደሚፈልጉ አንድ ጥናት አመላከተ

የጠቅላይ ሚኒስትር የሥልጣን ዘመን እንዲገደብ በርካታ ኢትዮጵያውያን እንደሚፈልጉ አንድ ጥናት አመላከተ

ቀን:

  • አዲስ አበባ ክልል ሆኖ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል መሆን አለባት ተብሏል

ብዙኃኑ ኢትዮጵያውያን የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የሥልጣን ዘመን እንዲገደብና አዲስ አበባ የፌዴሬሽን ክልልና አባል እንድትሆን እንደሚፈልጉ ‹‹አፍሮ ባሮሜትር›› በተባለው ታዋቂ የምርምር ተቋም የተካሄደ ጥናት አመለከተ፡፡ ጥናቱ ሐሙስ ኅዳር 6 ቀን 2016 ዓ.ም. በኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል ይፋ ተደርጓል፡፡

በአፍሮ ባሮሜትር ጥናት መሠረት፣ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የሥልጣን ዘመን መገደብ አለበት የሚሉ 66 በመቶ እንደሚሆኑ፣ አዲስ አበባ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል እንድትሆን የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ደግሞ 53 በመቶ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ጥናቱ በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች በ2,400 ቃለ መጠይቆች መካሄዱን፣ ዕድሜያቸው ከ18 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን ያሳተፈ እንደነበር ተገልጿል፡፡

- Advertisement -

በኢትዮጵያ የአፍሮ ባሮሜትር ብሔራዊ አጋር አቶ ሙሉ ተካ ከግንቦት 17 ቀን 2015 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 15 ቀን 2015 ዓ.ም. በተለያዩ አካባቢዎች ጥናቱ ሲከናወን መቆየቱን፣ የናሙናው መጠን በአገር አቀፍ ደረጃ የተሠራና ወካይነት እንዳለው ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ሙሉ ገለጻ የጥናቱ የስህተት ህዳግ ከሁለት በመቶ ያነሰ ሲሆን፣ የአስተማማኝነት ወይም የትክክለኛነት ደረጃው 95 በመቶ ነው ተብሏል፡፡  

በጥናቱ መሠረት የፖለቲካ ልሂቃን በሚከራከሩበት የጠቅላይ ሚኒስትር የሥልጣን ዘመን እንዲገደብ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን 66 በመቶ እንደሆኑ፣ የተቀሩት 27 በመቶ ያህሉ ደግሞ የሥልጣን ዘመን መራዘሙን እንደሚደግፉ ተመልክቷል፡፡

የቀሩት ሰባት በመቶ የሚሆኑት ስለጉዳዩ ምንም ግንዛቤ የሌላቸውና ሐሳብ መስጠት የማይፈልጉ መሆናቸውን ከጥናቱ ማወቅ መቻሉን አቶ ሙሉ ገልጸዋል፡፡  

አዲስ አበባ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል እንድትሆን 54 በመቶ የጥናቱ ተሳታፊዎች እንደሚግፉ አቶ ሙሉ ገልጸው፣ 34 በመቶ የሚሆኑት ከዚህ በተቃራኒ የሆነውን መምረጣቸውን አስረድተዋል፡፡

በዚህ ጥናት የተሳተፉ 12 በመቶ የሚሆኑት ምንም ዓይነት ድምፅ ከመስጠት የተቆጠቡና ስለጉዳዩ ምንም ዓይነት ዕውቀትና ግንዛቤ የሌላቸው መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

አፍሮ ባሮሜትር በ2012 ዓ.ም. አዲስ አበባ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል እንድትሆን የሚደግፉና የማይደግፉ ተብሎ በተደረገው ጥናት፣ ከ2016 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀር የ2012 ዓ.ም. 35 በመቶ፣ አሁን ደግም 53 በመቶ ወይም 18 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን ጥናቱ ያመለክታል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ብዙዎች ከተማከለ የመንግሥት ሥርዓት (አሀዳዊ) ይልቅ ፌዴራላዊ መንግሥት እንደሚመርጡ የአፍሮ ባሮሜትር ሌላው ጥናት ማመላከቱ ተገልጿል፡፡

አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን አሁንም ነፃ የክልል መንግሥት ያለው ፌዴራሊዝም ለአገሪቱ የተሻለ የመንግሥት መዋቅር አድርገው እንደሚመለከቱ ጥናቱን ዋቢ በማድረግ የገለጹት አቶ ሙሉ፣ በዚህም መሠረት 54 በመቶ ኢትዮጵያውያን የባህልና የቋንቋ ብዝኃነት ለማስተናገድ፣ ከአሀዳዊነት ይልቅ ፌዴራላዊ የመንግሥት ሥርዓትን እንደሚመርጡ ታይቷል ብለዋል፡፡

ከዚያ ውጪ ያሉት ወይም 42 በመቶ የሚሆኑት ፌዴራላዊ የመንግሥት ሥርዓት ወደ ግጭት የሚመራ አድርገው የሚመለከቱ በመሆናቸው፣ ከፌዴራላዊ ይልቅ አሀዳዊ የመንግሥት ሥርዓትን የሚደግፉ ናቸው ብለዋል፡፡

በዚህ ላይ ተቋሙ በ2012 ዓ.ም. ካደረገው ጥናት ጋር ሲነፃፀር፣ ፌዴራላዊ ሥርዓተ መንግሥት የሚደግፉ ሰዎች ቁጥር በሰባት በመቶ መቀነሱን፣ ይህ ማለት ከ61 ወደ 54 በመቶ መውረዱ ተገልጿል፡፡

ይሁን እንጂ አሀዳዊ ወይም የተማከለ የመንግሥት ሥርዓትን የሚደግፉ ደግሞ የአምስት በመቶ ብልጫ ማሳየታቸውን ጥናቱ ያመለክታል፡፡

ነገር ግን ‹‹የፌዴራላዊ ሥርዓት ከቀጠለ ምን መምሰል አለበት?›› ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የሰጡ የጥናቱ ተሳታፊዎች ለሁለት መከፈላቸውን አቶ ሙሉ ጠቁመዋል፡፡

ግማሽ ያህሉ ወይም 49 በመቶ ፌዴራሊዝም በብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነት መሠረት ክልሎች መዋቀር እንዳለባቸው ሲናገሩ፣ 48 በመቶ ያህሉ በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ መከለል እንደሚገባቸው ሐሳባቸውን መግለጻቸውን አስረድተዋል፡፡

የአፍሮ ባሮሜትር ዓላማ በዋናነት ተከታታይ ጥናቶችን በማቅረብና የፍሪካውያንን ድምፅ በጥናት በማስደገፍ ለፖሊሲና ለውሳኔ አሰጣጥ ምክረ ሐሳብ ማቅረብ እንደሆነ አቶ ሙሉ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የተደረጉ የጥናት ግኝቶች ለፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ ለሕዝብ ተወካዮችና ለሚመለከታቸው አካላት እንደቀረቡላቸውና በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ከመስጠታቸው በፊት የማኅበረሰቡን ውሳኔ ከግምት ውስጥ እንዲያስገቡ ጥናቱ እንደሚጠቁም ገልጸዋል፡፡

አፍሮ ባሮሜትር አፍሪካ ላይ ትኩረት ያደረገ ገለልተኛ የጥናትና ምርምር ሥራዎች የሚሠራ ተቋም መሆኑን፣ በዴሞክራሲ አስተዳደርና በኑሮ ጥራት ላይ መረጃዎችን በማሰባሰብ የካበተ ልምድ እንዳለው ተገልጿል፡፡

ተቋሙ እ.ኤ.አ. ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ በዘጠኝ ዙር ጥናቶች የሠራ መሆኑን፣ የዘጠነኛው ዙር ጥናት 2022/2023 የተካሄደ እንደሆነና በዚህም 39 አገሮች መሳተፋቸውን ከአቶ ሙሉ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በተለይ ከላይ የተጠቀሱት ሁለቱ ጥናቶች ለተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በአምስት ቋንቋዎች የተዘጋጁ መሆናቸውን፣ የጥናቱ ተሳታፊዎችም በመረጡት አካባቢያዊ ቋንቋ ተጠቅመው ተሳትፈዋል ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...