Wednesday, November 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊዩኒቨርሲቲ መግባት ያልቻሉ ከ33 ሺሕ በላይ ተማሪዎች ቴክኒክና ሙያ እንዲማሩ ሊደረግ ነው

ዩኒቨርሲቲ መግባት ያልቻሉ ከ33 ሺሕ በላይ ተማሪዎች ቴክኒክና ሙያ እንዲማሩ ሊደረግ ነው

ቀን:

የዘንድሮውን የቴክኒክና ሙያ ትምህርት የመግቢያ ነጥብ ያስመዘገቡ 33 ሺሕ 766 ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማሠልጠን ነገ ሰኞ ኅዳር 10 ቀን 2016 ዓ.ም. የበይነ መረብ ምዝገባ እንደሚጀምር፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮ ኃላፊዋ ወ/ሮ ሐቢባ ሲራጅ ዓርብ ኅዳር 7 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በአዲስ አበባ ከተማ 15 የመንግሥትና 114 የግል በድምሩ 129 የቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ኮሌጆች እንደሚገኙ ተናግረው፣ በእነዚህ ኮሌጆች የተመደቡ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማሠልጠን በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ዘርፍን መሠረት ያደረጉ በ22 የሥልጠና ዘርፎችና በ123 ሙያዎች በመደበኛ ደረጃ ሥልጠናው እንደሚሰጥ ኃላፊዋ ጠቁመው፣ በሌላ በኩል በ85 የሙያ ዓይነቶች ከአንድ መቶ ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ሠልጣኞች አጫጭር ሥልጠናዎች ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡

አዲስ ስለሚገቡ ሠልጣኞች አቀባበል ማብራሪያ የሰጡት ወ/ሮ ሐቢባ፣ ተማሪዎችን ከዚህ በፊት ከተለመደው ምደባ ውጪ እንደሚቀበሉ ገልጸዋል፡፡ ሠልጣኞቹ ዩኒቨርሲቲ ከገቡ ተማሪዎች የሚለያቸው በምግብና በመኝታ ካልሆነ በስተቀር አመዳደባቸው ተመሳሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በምደባው ወቅትም ሦስት ነገሮችን ታሳቢ መደረጋቸውን ያስረዱት ኃላፊዋ፣ የመጀመሪያው ኮሌጁ 12ኛ ክፍል ከተማሩበት ትምህርት ቤት ጋር ያለውን ርቀት ያገናዘበ መሆኑን፣ ሁለተኛው የትራንስፖርት አቅርቦትን እንዳማከለ፣ ሦስተኛው አካል ጉዳተኞችን መሠረት ያደረገ ምደባ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

ምዝገባው ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ ዕድሉን ሳያገኙ የቆዩ ተማሪዎችን ማካተቱንና በወቅቱ በነበረው የመግቢያ ነጥብ እንደሚገቡ፣ በበይነ መረብ መመዝገብ ስለማይችሉ በየኮሌጁ እየሄዱ እንዲመዘገቡ የቢሮ ኃላፊዋ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ ያሉ ተመዝጋቢዎች ደግሞ ቢሮው ባዘጋጀው የበይነ መረብ መመዝገቢያ ቅጽ www.aatuetb-edu.et በሚሉ ድረ ገጽ መመዝገብ እንደሚችሉ አብራርተዋል፡፡

አዲሱ የትምህርት ሥልጠና ፖሊሲ ከ2015 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል ያሉት ወ/ሮ ሐቢባ፣ ፖሊሲውን ተግባራዊ ለማድረግ ተቋሙ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ሁለት ቢሊዮን ብር በመመደብ ተማሪዎች በተግባር ልምምድ የሚያደርጉባቸው ግብዓቶችን ለማሟላት እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

መደበኛ ሥልጠና ላገኙ ተማሪዎች ከኢንዱስትሪዎች ጋር በማስተሳሰር የሥራ ዕድል እንደሚመቻች የገለጹት ኃላፊዋ፣ ተመርቀው የሚወጡ ሠልጣኞች ሥራ እናጣለን የሚል ሥጋት እንዳያድርባቸው ብለዋል፡፡

የዘንድሮውን የቴክኒክና ሙያ ሥልጠናና ተቋማት የመግቢያ ውጤት በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የአዲስ አበባ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ቢሮ የአካዴሚክ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ታደለ አየነው፣ የመቁረጫ ነጥቡም እንደ አገር ይወሰዳል ብለዋል፡፡

ሥልጠናው የሚሰጠው በማኅበራዊ ሳይንስና በተፈጥሮ ሳይንስ መሆኑን፣ የተፈጥሮ ሳይንስ የመግቢያ ውጤት በደረጃ አምስት የሚገቡት ወንዶች 218 ሴቶች 199 እና ከዚያ በታች፣ የአካል ጉዳተኞች ደግሞ 147 እና ከዚያ በታች ያገኙ መሠልጠን ይችላሉ ብለዋል፡፡

በማኅበራዊ ሳይንስ በደረጃ ሦስትና አራት የሚገቡ ተማሪዎች ደግሞ 148 ያስመዘገቡ ወንዶች መግባት ሲችሉ፣ ሴቶች 146፣ እንዲሁም የአካል ጉዳተኞች 124 የመግቢያ ውጤት ካስመዘገቡ መሠልጠን እንደሚችሉ አቶ እንዳለ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...