ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ 50 በመቶ ያህሉን ገቢ የሚያገኘው፣ ለደንበኞቹ ከሚሰጠው የኢንተርኔት አገልግሎት መሆኑን አስታወቀ፡፡
ኩባንያው ስለገቢው የገለጸው፣ በጂኤስኤም፣ በኤምፔሳና በኢንተርኔት አገልግሎቶቹ ላይ ትልቅ ሥራ እያከናወነ እንደሆነ ኅዳር 6 ቀን 2016 ዓ.ም. የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን በዋና መሥሪያ ቤቱ ለሚዲያዎች በገለጸበትና ተቋሙን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት የተቀላቀሉትን ሚስተር ዊም ቫንሄሌፑትን ከሚዲያ ባለሙያዎች ጋር ትውውቅ ባደረገበት ወቅት ነው፡፡
ከመስከረም ወር 2016 ዓ.ም. ጀምሮ የተሾሙት ዊም ቫንሄሌፑት ዜግነታቸው ቤልጂየማዊ ሲሆን፣ ለ20 ዓመታት ያህል የቴሌኮም ኩባንያዎች ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው መሥራታቸው በዕለቱ ተገልጿል፡፡
‹‹በኢትዮጵያ ፈጣን፣ ጥራት ያለውና አስተማማኝ የኢንተርኔት አገልግሎት ለማቅረብ እየሠራን ነው፤›› ሲሉ አዲሱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተናግረዋል።
ሳፋሪኮም በኢትዮጵያ በቴሌኮም አገልግሎት ከተሰማራ ጊዜ አንስቶ ፈጣን የኢንተርኔትና የስልክ አገልግሎትን አስፋፍቷል ሲሉ ቫንሄሌፑት ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሳፋሪኮም ከአራት ሚሊዮን በላይ ደንበኞች እንዳሉትም አክለዋል።
ኩባንያው በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ከ1.5 ቢሊዮን እስከ ሁለት ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የመሠረተ ልማት አውታሮች ለማስፋፋት ማቀዱን በመግለጫው አስታውቋል።
ይህ መዋዕለ ንዋይ ከ600 ሚሊዮን ዶላር የኔትወርክ ማማዎቹ ጋር ተዳምሮ ሽፋኑን ወደ ሰባት ሺሕ ማማዎች ለማድረስ ያለመ መሆኑን፣ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስረድተዋል፡፡
ሳፋሪኮም በአሁኑ ወቅት ተደራሽነቱን ወደ 26 ትልልቅና መካከለኛ ከተሞች በማስፋፋት 30 በመቶ ያህሉ ሕዝብ ዘንድ መድረሱን ጠቁመዋል።
ከቴሌኮም አገልግሎት ባለፈ በፋይናንስ ዘርፉ ለመሰማራት ባለፈው ነሐሴ ወር ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ የወሰደው ኤምፔሳ ደግሞ 1.2 ሚሊዮን ደንበኞች በማፍራት፣ በአጠቃላይ 287 ሚሊዮን ዶላር ግብይት እንዲኖር ማድረጉንና ከአሥራ ሁለት የአገር ቤት ባንኮች ጋርም አብሮ እየሠራ እንደሆነ ተገልጿል።
ኩባንያው የገነባቸው የቴሌኮም ማማዎች ከሁለት ሺሕ በላይ መድረሳቸውን የተናገሩቱ የሳፋሪኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ በየወሩም 150 ማማዎች እየተገነቡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በመጪዎቹ አሥር ዓመታት ውስጥም ከአሥር ሺሕ እስከ አሥራ ሁለት ሺሕ የቴሌኮም ማማዎች የመገንባት ዕቅድ እንዳለው ተናግረዋል።
ኩባንያው ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ከገባ ጀምሮ በጥሩ ጉዞ ላይ መሆኑን አስታውቀው፣ በአገሪቱ በተለይ በአማራ ክልል ያለው የፀጥታ ችግር የቴሌኮም ማማ ግንባታን እያተስተጓጎለ መሆኑን ገልጸዋል።
ሳፋሪኮም ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ፉክክር ለመግጠም ሳይሆን ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመገንባት፣ በአገሪቱ ውስጥ ጥራት ያለው የቴሌኮም አገልግሎት እንዲስፋፋ ለማድረግ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስረድተዋል።
ኩባንያው በአገሪቱ የሚስተዋለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ሥራውን በተገቢው መንገድ እንዳያከናውን እንዳደረገው ተወስቷል፡፡