Monday, December 11, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ግሎባል ኢንሹራንስ በፖለቲካ አለመረጋጋትና በሽብር ሳቢያ 8.9 ሚሊዮን ብር የጉዳት ካሳ ከፈለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ኩባንያው 67.1 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ አግኝቷል

ግሎባል ኢንሹራንስ ኩባንያ በተጠናቀቀው የ2015 ሒሳብ ዓመት በፖለቲካ አለመረጋጋትና በሽብር ጥቃት (Political Violence and Terrorism) የመድን ፖሊሲዎቹ አማካይነት በሰጠው የዋስትና ሽፋን ከ8.9 ሚሊዮን ብር የጉዳት ካሳ ጥያቄ አጋጥሞት ክፍያ መፈጸሙን አስታወቀ። 

ኢንሹራንስ ኩባንያው የ2015 የሒሳብ ዓመት ይፋ ሪፖርቱ እንደሚያመላክተው፣ ለመጀመሪያ ከፖለቲካ አለመረጋጋትና ለሽብር ጥቃት የመድን ሽፋን የከፈለው ካሳ በሒሳብ ዓመቱ ከከፈለው ጠቅላላ የካሳ ክፍያ ዘጠኝ በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ይይዛል፡፡ በኩባንያው ዓመታዊ ሪፖርት መሠረት በሒሳብ ዓመቱ ለሁሉም የመድን ሽፋን የፈጸመው ካሳ ክፍያ 109 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ታውቋል፡፡ 87 በመቶ የሚሆነው የካሳ ክፍያ ደግሞ ከሞተር ኢንሹራንስ ጋር ለተያያዙ አደጋዎች የተከፈለ ሲሆን፣ ቀሪው አራት በመቶ ወይም 4.5 ሚሊዮን ብር ለሌሎች የመድን ሽፋን ዓይነቶች የተከፈለ የጉዳት ካሳ መሆኑን የኩባንያው መረጃ ያመለክታል።

የግሎባል ኢንሹራንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጥበቡ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የፖለቲካ አለመረጋጋትና የሽብር ጥቃት ዋስትና የገዙ ደንበኞቹ ተሽከርካሪዎች በወለጋና በዝዋይ አካባቢ በደረሰባቸው አደጋ ምክንያት 8.9 ሚሊዮን ብር የጉዳት ካሳ በሒሳብ ዓመቱ ተከፍሏቸዋል።

የኩባንያው ዓመታዊ የካሳ ክፍያ ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ በ69.2 በመቶ እንደጨመረም ታውቋል፡፡ በ2014 የሒሳብ ዓመት ኩባንያው ለካሳ ክፍያ ያዋለው የገንዘብ መጠን  64.4 ሚሊዮን ብር እንደነበረም ሪፖርቱ ያሳያል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ለኩባንያው የካሳ ክፍያ መጠን በዚህን ያህል ደረጃ ለማደጉ አንዱ ምክንያት ባልተጠበቀ ሁኔታ ለፖለቲካ ቫዮለንስ ቴረሪስት የኢንሹራስ ሽፋን ወደ አሥር ሚሊዮን የተጠጋ የካሳ ክፍያ መክፈሉ ነው፡፡ 

ከዋጋ ንረት ጋር በተያያዘ ለተሽከርካሪዎች የሚከፈለው የካሳ ከፍያ መጠን መጨመሩም የካሳ ክፍያ ወጪው መጨመሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ የከፈለው የካሳ ክፍያ ዕድገት ያሳየ ቢሆንም፣ በሒሳብ ዓመቱ ያሰባሰበው የዓረቦን መጠን ከ67 በመቶ በላይ ጭማሪ የታየበት በመሆኑ ከቀዳሚው ዓመት የተሻለ ትርፍ ሊያስመዘግብ ችሏል፡፡ በኩባንያው ዓመታዊ ሪፖርት መሠረት ከሁሉም የመድን ዘርፎች ያሰባሰበው የዓረቦን መጠን 290 ሚሊዮን ብር እንደሆነ የግሎባል ኢንሹራንስ ኩባንያ ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ያሃያ አብደላ አመልክተዋል፡፡ ይህ የዓረቦን መጠን ከቀዳሚው ዓመት አፈጻጸም ጋር ሲታይ የ67 በመቶ ዕድገት የታየበት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡  

በኢንሹራንስ ኩባንያው ሪፖርት መሠረተ በተጠናቀቀው የሒሰብ ዓመት ባንኩ ከጠቅላላው የመድን ሽፋን ከተገኘው ዓረቦን ገቢ ውስጥ 218 ሚሊዮን ብር ከተሽከርካሪ የመድን ሽፋን የተሰባሰበ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህም ከጠቅላላው የዓረቦን ገቢ ከሞተር ኢንሹራንስ የተሰባሰበው 75 በመቶውን ድርሻ መያዙን የቦርድ ሊቀመንበሩ ሪፖርት አመልክቷል፡፡  

ከዓረቦን ገቢ ባሻገር ኩባንያው ከተለያዩ ኢንቨስትመንቶቹ 39.6 ሚሊዮን ብር ገቢ ያገኘ መሆኑን ሲሆን፣ በተለይ የዓረቦን ገቢው ዕድገት ለኩባንያው የትርፍ ምጣኔ ከፍ እንዳደረገው ታውቋል፡፡ 

እንዲህ ያሉ አፈጻጸሞች ኩባንያውን ከታክስ በፊት ያገኘውን የትርፍ መጠን 85.3 ሚሊዮን ብር፣ ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ 67.1 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ አግኝቷል። ይህም ከቀደሚው ዓመት የ19 ሚሊዮን ብር ብልጫ አለው። በሒሳብ ዓመቱ የተገኘው ትርፍም ለኩባንያው ባለአክሲዮኖች የተሻለ ጥቅም ያስገኘ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት አንድ የኩባንያው አክሲዮን ያስገኘው የትርፍ ድርሻ 150 ብር ሆኗል። አንድ የኩባንያው አክሲዮን በ2014 የሒሳብ ዓመት ያስገኘው የትርፍ ድርሻ 145 ብር ነበር፡፡ 

እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ገለጻም፣ በሒሳብ ዓመቱ የኩባንያው የትርፍ ምጣኔ ሊያድግ ከቻለባቸው ምክንያቶች አንዱ የዓረቦን ገቢ ምጣኔን በከፍተኛ ደረጃ ሊያሳድግ በመቻሉ ነው፡፡  

ግሎባል ኢንሹራንስ በኢንዱስትሪው ውስጥ ከ20 ዓመታት በላይ የቆየ ሲሆን፣ በ2015 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ አጠቃላይ የሀብት መጠኑ 821.1 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህም ከቀዳሚው ዓመት በ40 በመቶ ወይም በ234.8 በመቶ ዕድገት ማሳየት የሚመላክት ነው፡፡ 204.1 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ያለው ግሎባል ኢንሹራንስ 196 ሠራተኞች ያሉት ሲሆን ከ22 በላይ ቅርንጫፎች አሉት፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች