የዛሬው መንገድ ከፒያሳ ወደ የካ አባዶ ነው። የድሮ አራዶች መናኸሪያ ከሆነችው ፒያሳ ወደ አዲሱ ሰፊ ሠፈር የሚደረገው ጉዞ፣ ትናንትን በትዝታ ዛሬን በነገ ተስፋ አሰባጥሮ ብዙ ነገሮችን ያሳስበናል። የአሁኑ ጉዞ ተጀምሮ ከመጠናቀቁ በፊት በርካታ ወጎች ይሰለቃሉ፣ ብዙ ሐሳቦች ይንሸራሸራሉ፡፡ አንዱ መንገድ ሲያልቅ ሌላው መንገድ ይጀመራል። ‹‹አንተ እባክህ መስኮቱን ዝጋው…›› ትነጫነጫለች ከሾፌሩ ጀርባ ያለው ወንበር ላይ የተሰየመች ተሳፋሪ። ‹‹እቱ መስኮቱ ነው እንዲህ የሚያስጮህሽ ወይስ ሌላ ነገር ነው…›› እያለ ወያላው መስኮቱን ይዘጋል። ‹‹ብርድ ብመታ ታሳክመኛለህ?›› ሙግት ጀመረች። ‹‹ብርድ የሚባል ነገር የለም፣ ምላስ እንጂ ንፋስ ጥሎን አያውቅም ማነሽ?›› ይላል ግንባሩን ክስክስ አድርጎ አጠገቧ የተቀመጠ ጎልማሳ። ‹‹ካነሳችሁ ላይቀር ሰማይ የሚባልም የለም ዕድሜ ለህዋ ሳይንስ…›› ይላል መሀል መቀመጫ የተቀመጠ ወጣት፡፡ መሀል ወንበር ላይ የተቀመጠች ወይዘሮ ደግሞ፣ ‹‹እንደ በቅሎዋ ሰማዩን ረግጠህ ነው ለካ የለም ብለህ የሳይንስ ሙግት የምታመጣው…›› ስትለው ሳቅ ቢጤ ተሰማ፡፡ ጉዞ የሚጀመረው እንዲህ ነው እንግዲህ!
‹‹እኔ የምለው ግን…›› ይላል ጎልማሳው ወደ ወይዘሮዋና ወጣቱ ዘወር ብሎ። ‹‹በተበከለ አየር ልቀት አየር ንብረቱን እንዲህ መፐዋወዛቸው ሳያንስ፣ በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ሮቦትን ከሰው ልጆች ጋር ለማቀናጀት ሲያስቡ ዝም ብለን ልናይ ነው?›› ከማለቱ አንዱ የሰሞኑ የምሽት ቅዝቃዜ በቁርጥማት አላመጠኝ ባይ፣ ‹‹አስበው ጨርሰዋል፣ ይልቅ በጊዜ ደህና መከላከያ ለብሰን መጠበቅ ነው። እንኳን ከሮቦት ጋር ከታክሲ ተጋፍተን እርስ በርሳችንም ወላልቀን አልቀናል…›› ብላ መጨረሻ ወንበር የተቀመጠች የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የጨዋታው አባሪ ሆና ብቅ አለች። ‹‹ወይ የእኛ ሰው እስኪ እባካችሁ የሮቦት ወሬ ነው ወይስ የሰላም ዕጦታችን ነው የሚቀድመው? በቃ ያልበላንን ዝም ብለን መፎከት?›› አለ በንዴት ከተማሪዋ አጠገብ የተቀመጠ ቁጡ መሳይ ጎልማሳ። ‹‹ይቅርታ ‘መፎከት’ ምን ማለት ነው?›› ብላ ተማሪዋ መጠየቅ። ጎልማሳውም አንገቱን ሰበር አድርጎ፣ ‹‹ይቅርታ በእንግሊዝኛ የማብራራት አቅም ስለሌለኝ ለቀቅ አድርጊኝ። የዘመኑ ተማርን ባዮች የባጥ የቆጡን በጉራማይሌ እየቀየጣችሁ የምታደናብሩን ሳያንስ፣ በገዛ ቋንቋችን ‘ሼም’ ልታስይዙን እንዲህ ያለ ጥያቄ ትጠይቃላችሁ?›› ብሎ መዳፉን አማታ። ምን ያድርገው!
‹‹ኧረ ተረጋጋ እንዲያውም እሷ እግዜር ይስጣትና አለማወቋን አውቃ ጠይቃለች። ካልክስ አሉልህ በየሚዲያው ብቅ እያሉ ምንነቱ የማይታወቅ ነገር እያወሩ ችግራችንን የሚያባብሱት…›› ብሎ መሀል ወንበር የተቀመጠው ብሶቱን ሲናገር፣ ‹‹ኧረ እባካችሁ እንዳመጣልን አናውራ? ላትጨርሱ ሳይንሱን ጀምራችሁ ሮቦቶችን አምታችሁ፣ ስለቋንቋ ያነሳችሁት ምኑ ከምኑ ቢያያዝ ነው?›› ብላ የንፋስ ‹ፎቢያ› ያለባት ወጣት ቱግ አለች። ይኼኔ ከጎኗ፣ ‹‹በቃ ግራ የገባው እኮ ከዚህም በላይ ይቃብዛል። ሰላማችን ተቃውሶ አኗኗሩ ሲጠፋብን ጨዋታስ ላይጠፋን ነው? እንዴት ነው ነገሩ?›› ብሎ ገላመጣትና አረፈው። ‹‹የሰላማችን መቃወስ ብቻ ሳይሆን የንግግርና የወግ ሚዛናችን ጭምር ሳይዛባ አልቀረም መሰል ዘንድሮ…›› ይላል አንዱ ከጥግ በኩል፡፡ ኑሮ ከባድ ሚዛን ሆኖበት ነው!
ሾፌሩ ሙዚቃ ሊከፍት ቴፑን ይጎረጉራል። ወያላው ደግሞ፣ ‹‹እስኪ ቅድም ያስጫንኳቸውን ዘፈኖች ክፈታቸው…›› ብሎ ፍላሽ ያቀብለዋል። ‹‹ካልክስ እስኪ የጥላሁን ገሠሠን ጋብዘን ሾፌር…›› ብሎ ጎልማሳው አንገቱን እየወዘወዘ ከንፈሩን መምጠጥ ያዘ። አፍታ ሳይቆይ ደግሞ፣ ‹‹ምን ጥልቅ አድርጎኝ በሰዎች ነገር ምንስ አግብቶኝ በሰዎች ነገር ብሎ ነበር ድሮ አፈር ልብላለትና…›› እያለ ሊቀጥል ሲል፣ ‹‹አያገባንም እያልን ቆይተን ይኼው አገር ተተራምሳ ለመፍረስ ትንሽ ቀርቷት ዳር ቆመን እያየን ነው…›› ብላ ወይዘሮዋ ጉድ አፈላች። ‹‹በሕግ አምላክ መንግሥት ባለበት አገር ተተራመሰ፣ ፈረሰ ብሎ ማውራት ወንጀል ነው የእኔ እመቤት…›› አላት ጎልማሳው ቆጣ ብሎ። ‹‹እህ ታዲያ ዋሸሁ? ዓይተን እንዳላየን ሰምተን እንዳልሰማን መሆናችን መሰለኝ ያለ ሙያው፣ ያለ አቅሙና ያለ ችሎታው ትንሽ ትልቁ አናታችን ላይ ቁብ እያለ የተበጠበጥነው። አይደለም እንዴ? በሉ እንጂ አርሙኝ?›› ብላ ተሳፋሪዎችን ቃኘች። ድንጋጤ!
‹‹ያልሽው ልክ ቢሆንም፣ ነገር ግን ደግሞ ያገባኛል ይመለከተኛል ባይ ተቆርቋሪም ከመደቆስና ከመዳፈን ሌላ በለስ ሲቀናው አላየንም። ስለዚህ አርፈን ልጆቻችንን ለማሳደግ የጥላሁንን ዓይነት ዜማ ሳንወድ በግድ እናንጎራጉራለን። እኛ ስናንጎራጉር ግን የሞተ ተጎዳ…›› ብሎ መጨረሻ ወንበር አካባቢ ጎልማሳው ፀጉሩን እየዳበሰ አስተያየት ሰጠ። ‹‹ልክ ነው ዕድሜ ለትውልዳችን፣ ከዝም ጭጭ በቀር ሌላ ዕድሜ ማራዘሚያ ዘዴ አለ እንዴ ጎበዝ? ስለዚህ ምን ጥልቅ አድርጎን?›› ብላ ሳትጨርስ ጋቢና የተቀመጠች ጠይም ቆንጆ፣ ‹‹እኮ ምድረ ጉልበተኛ አገር ሊያፈርስ ሲያሴር፣ ወገናችንን ሲድገል፣ የደሃ ጎጆ እያቃጠለ ሲዘርፍ፣ በውሸት ፕሮፓጋንዳ ሲደልል ዝም ይባላል? በቃ ይኼ ሆኖ ቀረ አትንኩኝ ባይነት?›› ብለው ከጎኗ ተቀምጠው የነበሩ አዛውንት በትዝብት አዩዋት። ‹‹ኧረ አንዳንዱንስ እንኳን የትዝብት የአጥፍቶ ጠፊ ዓይንም አላስደነግጠው ብሏል…›› ያ ሰው አሁንም ከጥግ። ምን እንደሚሻል እንጃ!
ከወደ ጋቢና ደግሞ በሌላ ርዕስ አዲስ ጨዋታ ይደመጣል። ከዚህ ቀደም በደንብ የሚተዋወቁ ወዳጅ ቢጤ ናቸው። አንደኛው መምህር ሳይሆን አይቀርም። ‹‹ለመሆኑ አሁንም የምታስተምረው እዚያው ነው ወይስ ቀየሩህ?›› ይጠይቃል የወዲያኛው። ‹‹ተቀይሬ ሌላ ትምህርት ቤት ተመድቤ ነበር። ነገር ግን የኑሮ ጉዳይ አላዋጣ ስላለኝ ነጋዴ ሆኛለሁ…›› ሲለው፣ ‹‹ከመምህርነት ወደ ነጋዴነት ተዘዋወርኩ እያልኩ ነው የምትለኝ እንዴ…›› ከጋቢና ጠያቂው በመደነቅ ተናገረ። ‹‹የኑሮ ውጥኑ አልሆን ብሎ ሲከር፣ ውጥሩ እንዲላላ የላላውን ወጥር ያለውን ገጣሚ መቼም አትረሳውም፡፡ እኔም በዚህ መሠረት ከመምህርነት ወደ ቦንዳ ነጋዴነት ተሸጋግሬያለሁ…›› ሲለው የቀድሞው መምህር፣ ‹‹ጉድ በል የአገሬ ሰው፣ ከዚህ በላይ ስምንተኛው ሺሕ ምን ሊሆን ነው…›› እያሉ በትካዜ አንገታቸውን ደፉ፡፡ ጉድ እኮ ነው!
ከኋላ መቀመጫ የጋቢናው ጭውውት አንድ ሰበዝ ተመዞ በሌላ መንገድ ፈር ይዟል። ‹‹እንደ ድንበር ድንጋይ አንድ ቦታ ላይ ተገትሮ ከመቅረት አማራጮችን ማየት የተሻለ መሆኑን ስለማምን የመምህሩን ውሳኔ እደግፋለሁ…›› ሲል አንደኛው ሌላው ተቀብሎ፣ ‹‹አገር የቁልቁለቱን መንገድ እንደተያያዘች የምረዳው እንዲህ ያለው ውሳኔ በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ሲኖረው ነው…›› ይላል በሐዘን ስሜት፡፡ ‹‹ሰው ሲሠራ ሊሳሳት እንደሚችል በመረዳት አንዳንዴ አማራጭ አለመንፈግ ቢለምድብን እንዴት ጥሩ ነበር?›› ትላለች ያቺ ጠይም። ‹‹እኔ በበኩሌ ከመምህርነት ወደ ቦንዳ ነጋዴነት የተደረገውን ሽግግር አልደግፍም፡፡ ትውልድ የሚቀርፅ ሰው ልባሽ ጨርቅ ተራ ውስጥ ሲገኝ ልቤ ይሰበራል….›› እያለ አንድ ዝምተኛ መሳይ ወጣት ሲናገር ሰማነው። የዘመናችን ነገር ድንቅ ይላል!
ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። አንድ አዛውንት ስልክ እየደዋወሉ ከዘመን ጓኞቻቸው ጋር ለመገናኘት ይወተውታሉ። የአንዱን ዘግተው ወደ አንዱ ሲሞክሩ፣ ‹‹በስተርጅና እስኪ አሁን ‘ቢዚ’ ነን ሲሉ አያፍሩም? ምን መዓት ነው የመጣብኝ ልጄ? ዕድሜያችንን በቀልድ አሳልፈን ስናበቃ በማረፊያችን ሰዓት ተሰብስበን የጥንት የጠዋቱን በማውጊያችን እንዲህ ለእንጀራ ተጠምደን እንረፈው?›› እያሉ አንዴ ሾፌሩን አንዴ ወጣቷን ያያሉ። ያ ከሾፌሩ ጀርባ ፊቱ የማይፈታው፣ ‹‹ያኔማ ምን አለ አባት? ቫት የለ ታክስ የለ፣ በየወሩ የቤት ኪራይ አይጨምር፣ የእህል ዋጋ ሰማይ አልነካ፣ ሁሉም ያለውን ተካፍሎ በፍቅር ይኖር ነበር…›› ብሎ ተግ ሲል፣ ‹‹አሁንስ?›› አሉት የማያውቁትን እንደሚነግራቸው ሁሉ በምፀት እያዩት። ‹‹አሁንማ እንኳን የምናካፍለው የምንጎርሰውም በቅጡ አይገኝ። እየሰሙ አይደለም እንዴ መምህሩ ደመወዙ አልበቃ ብሎት ቦንዳ ነጋዴ ሲሆን…›› ብሎ ያንን ፊቱን ይባስ ከሰከሰው። ምሬት በሉት!
‹‹ምን ነካችሁ ግፉስ እናንተ? የድሮ ሰው እኮ ነው ይኼን ሁሉ ፍዳ ያመጣብን…›› ሲል አንዱ፣ ‹‹የምን ግፍ?›› አለው ጎልማሳው ግንፍል ብሎ። ‹‹እኛ ሺሕ ብሮችን የምንጠየቅበትን በሳንቲም ቤት ጮማና ጠጅ ሲያወራርዱ አልነበር እንዴ…›› ብሎ ሳይጨርስ ጎልማሳው አቋርጦት፣ ‹‹ጡር አትልም ታዲያ? በተለያዩ ምክንያቶች ተሸናሽነን በዓይነ ቁራኛ የምንተያየው አንሶ ደግሞ በዕድሜ ልትለያየን ነው? ስንቱን እንገስፅ እናንተ?›› እያለ ያዙኝ ልቀቁኝ አለ። ‹‹ዝም አትለውም? ደረቅ ጠጅ በቋንጣ ተወራረደ፣ በፍሪዳ ጮማ ታሪክ ተጻፈ ብሎ አባቶቻችንን ከሚወቅስ፣ ፈጣኑ የኢኮኖሚ ዕድገታችን አምሮታችንን ገደበብን ብሎ አይገላገልም? ማንን ፈርቶ ነው? ዘመኑ እኮ የዴሞክራሲ ነው። አህያውን ፈርቶ ዳውላውን? ሆ…ሆ…›› የምትለው ወይዘሮዋ ናት። ‹‹ሌላውን ትተን በየቦታው የለኮስነውን ግጭት በፍጥነት ጨርሰን ፊታችንን ወደ ልማት በማዞር ማደግ ይሻላል፣ ወይስ እየተፋጀንና በድህነት እያከክን ቦንዳ ተራ መዋል ይሻለናል…›› እያለ ወጣቱ ያልታሰበ ጥያቄ ሲያመጣ ታክሲያችን ጉዞዋ አብቅቶ በየፊናችንን ተበታተንን፡፡ መልካም ጉዞ!