Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየኢትዮጵያ ሕዝቦች ወይስ የኢትዮጵያ ሕዝብ? ለምን?

የኢትዮጵያ ሕዝቦች ወይስ የኢትዮጵያ ሕዝብ? ለምን?

ቀን:

በዳዊት አባተ (ዶ/ር)

እኛ ኢትዮጵያዊያን ለብዙ ዘመናት በሁሉም መድረክ የኢትዮጵያ ሕዝብ (በነጠላው) ስንል ኖረን፣ ከ30 ዓመታት ወዲህ ግን የኢትዮጵያ ሕዝቦች ማለት ጀመርን፡፡ በአሁኑ ጊዜ በመጽሐፍም ይሁን በጋዜጣ፣ በመጽሔትም ሆነ በሬዲዮና በቴሌቪዥን የኢትዮጵያ ሕዝቦች ማለት የተለመደ ሆኗል፡፡ ለመሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሚለው አባባል እንዴትና ለምን መጣ?

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሚለው አባባል የመነጨው ሕወሓት/ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘበትና ሕገ መንግሥቱ ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት 1987 ዓ.ም. አንቀጽ ስምንት ‹‹የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው፤›› ይላል፡፡ ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ሁኔታ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝቦች የሚሉትን ቃላት ትርጉም ለብዙዎቻችን እስካሁን ግልጽ አይደለም፡፡     

ከዚያ ወዲህ በነገድ/ዘውግ (ብሔር) የተደራጁ የፖለቲካ ድርጅቶች (ፓርቲዎች) በመላው አገሪቱ ተቋቋሙ፡፡ ዛሬ ከመቶ ያላነሱ የብሔር ፖለቲካ ድርጅቶች ሲኖሩ፣ ሁሉም ለብሔር ጥቅም የቆሙ ናቸው፡፡ አገራዊ የፖለቲካ አመለካከት (ርዕዮተ ዓለም) አላቸው ለማለት ግን አያስደፍርም፡፡ ለእነዚህ የፖለቲካ ቡድኖች የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሚለው አባባል የሚመቻቸው ይመስላል፣ ከድርጅቶቻቸው ዓላማና ህልውና ጋር ያያይዙታል፡፡ የመንግሥት ሥልጣን በተለይም የክልል፣ የዞንና የወረዳ አስተዳደር ለእነዚህ ድርጅቶች ቅርብ ሲሆን፣ የፌዴራል መንግሥቱም ለፖለቲካ አመለካከቱ ስለሚጠቅሙት ድጋፍ ያደርግላቸዋል፡፡

ይህን የፖለቲካ አመለካከት ሕወሓት/ኢሕአዴግ ለምን እንደፈለገው ግልጽ ባይሆንም፣ የብሔሮችን የተዛባ ግንኙነት ለማሰተካከል ነው የሚሉ አሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ለሕወሓት/ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ ለመቆየት የሚበጅ መንገድ ስለሆነ ብቻ ነው ይላሉ፡፡ ስለዚህ የጠባብ ብሔርተኞችን ድጋፍ ማግኘት ከፖለቲካ አመለካከትና ከፌዴራል መንግሥት ሥልጣን ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ይህ የመንግሥት ሥርዓት ኤትኖክራሲ (Ethnocracy) የሚባለው ዓይነት ነው፡፡ ኤትኖክራሲ ከዴሞክራሲ ይለያል፡፡ ዴሞክራሲ ሕዝብ በሕዝብ፣ ለሕዝብ፣ ከሕዝብ ሲሆን ኤትኖክራሲ ግን ብሔር፣ በብሔር፣ ለብሔር፣ ከብሔር የሚለውን መሠረታዊ መርህ የሚከተል ሥርዓት ነው፡፡ ይህም ማለት ኤትኖክራሲ ለዜጎች (ለግለሰብ) ነፃነት፣ ለዴሞክራሲና ለአገር አንድነት ሳይሆን ለነገድ/ዘውግ ጥቅም የቆመ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የምንለውም ይህን ሥርዓት ለመጠበቅና ለማቆየት ካልሆነ ምን ሊሆን ይችላል?

ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብዝኃነት የሚንፀባረቅባትና የሕዝቧም የወደፊት ተስፋ ከብዝኃነት ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቋንቋ፣ ባህልና የተፈጥሮ ሀብት ብዝኃነት መልካም ዕድል የሚሰጥ መሆኑን ጠንቅቀን ባለመረዳትና ሁኔታውን ባለማመቻቸታችን አገራችን አሁን ላለችበት የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ችግሮች ዳርጓታል፡፡

ኢትዮጵያውያን ያሉንን ብዙ ቋንቋዎችና የባህል እሴቶችን በበጎ ጎን በማየትና ዘርፈ ብዙ ጥቅሙን በተግባር ለማዋል ገና ብዙ ይቀረናል፡፡  ከእያንዳንዱ ብሔር ባህልና ቋንቋ የተገኙ ባህላዊ ዕውቀት ለአጠቃላይ አገር ዕድገትና ለመላው ሕዝብ እንደሚበጅ ግልጽ ነው፡፡ ለምሳሌ የቆጮ ምግብ አዘገጃጀት ወይም የሲዳማ ቤት አሠራር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቢያውቀው ጥቅሙ የጎላ ነው፡፡ ከመኖሪያ አካባቢ ብዝኃነት የሚገኘው ዕውቀት ለምሳሌ ቆለኛው ከደገኛው፣ አርሶ አደሩ ከአርብቶ አደሩ፣ ወዘተ. የሚገኙ ተግባራዊ የኑሮ ዘይቤዎች ከብዝኃነት የመነጩና የሚደጋገፉ ናቸው፣ አገራዊ ፋይዳቸውም ከፍተኛ ነው፡፡

የአገራችን የመሬት አቀማመጥ (ቶፖግራፊ) ሰፊ ልዩነትና ሥነ ምኅዳራዊ (ኢኮሎጂ) ብዝኃነት በተፈጥሮ ሀብት የታደለች እንድትሆን አድርጓታል፡፡ የኢትዮጵያ የዕፅዋትና እንስሳት ብዝኃነት፣ ለግብርና አመቺነት፣ ለደን ልማት ተስማሚነት፣ ከባህላዊ ዕውቀት ጋር በትክክል ከተዛመደ ለመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ አስተማማኝ ኑሮና ለሚቀጥለው ትውልድም መሠረት ይጥላል፡፡ የእንስሳትና ዕፅዋት ዘረመል (ጅን) ብዝኃነት ለግብርናና ለኢንዱስትሪ ማዋል ብዙም ያልተጠቀምንበት ሰፊ ዕድል ይጠብቀናል፡፡ ኢትዮጵያ የግብርና ጥበብ ከመነጨባቸው አገሮች አንዷ ናት፡፡ ጤፍን፣ ዳጉሳን፣ ቆጮንና ቡናን ለዓለም አበርክታለች፡፡ ወደፊትም ከብዝኃ ሕይወት ንብረቷ ስፋትና ልዩነት ሌሎችንም የማበርከት ዕድሏ ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህ የተፈጥሮ ሀብት ብዝኃነትን በትክክል መጠቀም መቻል ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብና ለሚቀጥለው ትውልድ የሚመች መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ የኢትዮጵያን የቋንቋና ባህል ብዝኃነትንም ልክ እንደዚህ በበጎ መልኩ ልናየው ይገባል፡፡

ይህ ባለመሆኑና ጉዳዮቻችንን በጠባቡና በአጭሩ ማየት ስለጀመርን የአገራችን የተፈጥሮ ሀብት በጋራ የመጠቀም፣ የመንከባከብና ለትውልድ ማስተላለፍ ኃላፊነት እየደከመ ሄዷል፡፡ ዛሬ የአገራችን ደኖች፣ የዱር እንስሳት፣ የብሔራዊ ፓርኮች በአጠቃላይ ብዝኃ ሕይወት ያለበት ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ደርሷል፡፡ ይሁን እንጂ በማዕከላዊነት የምርምር ውጤትን፣ የገንዘብ ምንጭንና የሰው ኃይልን በማቀናጀት የተሻለ ውጤት ሊገኝ ይችላል፡፡ የተፈጥሮ ሀብታችን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ (የአንድ ሕዝብ) ንብረት በመሆኑ በጋራ በመሥራት አገራችን የተሻለ አጠቃቀምና ልማት እንዲኖራት ያስችላል፡፡ ማወቅ ያለብን የመናገሻ የተፈጥሮ ጫካ፣ የሰሜን ተራራው ዋሊያ፣ የባሌው ቀበሮ፣ የጣናና የጫሞ ሐይቆች የዓሳ ዘር የሁሉም ኢትዮጵያዊ ንብረት ነው፣ በአካባቢው ለሚኖረው ብሔር (ነገድ) ብቻ የተሰጠ አይደለም፡፡  

በአጠቃላይ አንድ ሕዝብ ነን ብሎ መቀበል በራሱ የመቀራረብና የአብሮነት ስሜት ስለሚፈጥር፣ ለቋንቋና ለባህል ዕድገትም ሆነ ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና አጠቃቀም መሠረት ነው፡፡ ይህችን ትንሽ ለውጥ በማድረግ ብቻ ችግሩ ሁሉ ይፈታል ባይባልም፣ ሥነ ልቦናዊ ፋይዳው ጥቅም ያስከትላል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎት የሰብዓዊ መብቶች መከበር፣ የዜጎች ነፃነትና ዴሞክራሲ መስፈን ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ከተመቻቸና ሥር ከሰደደ አገራዊ የሆነ የፖለቲካ ምኅዳር ስለሚፈጠርና ስለሚፀና፣ የንጉሣዊ ሥርዓት ለሚፈልጉትም ይሁን የኮሙዩኒስት ሥርዓት ለሚሹ ሁሉ በእኩልነት ያስተናግዳል፡፡ መንግሥትም በሕዝብ ፍላጎት መሠረት ይመጣል/ይሄዳል፣ የዴሞክራሲ ሥርዓትም ከትውልድ ትውልድ እየጠነከረ ይሄዳል፡፡

አሁን ያለው ሁኔታ ዜጎች እንደልባቸው የሚንቀሳቀሱባት፣ የሚሠሩባትና  የሚኖሩባት አገር አላደረጋትም፡፡ ኢትዮጵያ ሕዝብ ስለተባለ በአገሪቱ የሚገኙ ቋንቋዎችን፣ ባህሎችን፣ መንከባከብና ከማሳደግ የሚከለክል አንዳችም ጉዳይ የለም፡፡ እንደሚታወቀው ልማትና ዕደገት የሚመጣው ሀብታም በገንዘቡ፣ ደሃ በጉልበቱ፣ የተማረ ደግሞ በዕውቀቱ፣ በፈለጉት ቦታና አካባቢ የሚኖሩባትና የሚሠሩባት አገር ስትሆን ነው፡፡ መዋዕለ ንዋይ አፍስሰው በተለይም በግብርናና በአገሮ ኢንዱስትሪ ለመሥራት ሁኔታዎች አመቺ እንዳልሆኑ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡

በዛሬይቱ አትዮጵያ አንዱ ክልል ከአዋሳኙ (ከጎረቤቱ) ክልል በደንበር (በወሰን) አለመግባባት እየተፈጠረ ግጭትና ጦርነት የተለመደ መሆኑ ያሳዝናል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ በወሰን፣ በግጦሽ መሬት፣ ወዘተ. ከአዋሳኝ ብሔር የማይጣላ  ማግኘት ያስቸግራል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የእኔ ብሔር ክልል ሊሆን ይገባል ወይም የዞን/ወረዳ አስተዳደር ደረጃ ለምን አይሰጠንም የሚሉ ጥያቄዎች እየጨመሩ መጥተዋል፡፡ ይህ ዓይነት ጥያቄ መቼ ሊቆም እንደሚችል መገመት ያስቸግራል፡፡ ይህን ሁሉ እየተገነዘብን አሁንም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ማለት የቀጠልንበት ምክንያት ለብዙዎች ግልጽ አይደለም፡፡ የብሔር ተኮር ፖለቲካ (ኤትኖክራሲ) አመለካከት በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል መራራቅ፣ የሰላም መጥፋትና የኢኮኖሚ ችግሮች ምክንያትነት አለመቀበል ይመስላል፡፡

አሁን ያለንበት አገራዊ ችግሮች አመጣጥና ወዴት እንደሚወስደን መገመት ከባድ አይደለም፡፡ ዜጎች ከመኖሪያ አካባቢያቸው መፈናቀል ለተፈናቃዮች ችግርና ሰቆቃ ከማስተከተሉም በላይ የአብሮነትን እሴቶችን ይንዳል፡፡ የወጣቱ ሥራ አጥነትና በአገሩ ተስፋ መቁረጥ አስከፊውን ስደት እንደ አማራጭ እንዲወስድ ያስገድደዋል፣ በግጭቶችም ውስጥ ዋና ተዋናይ ያደርገዋል፡፡ ዜጎች በሰላምና በመግባባት መኖር ካለቻሉና የወደፊት ብሩህ ተስፋ ከጠፋ ወደ ከፋ ችግር የሚወስድን መንገድ እንደመረጥን ይቆጠራል፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከአንድነትና ዴሞክራሲ ውጪ የተሻለ አማራጭ የለውም፡፡ የሰላም ዕጦት እየበዛ  ጦርነት እየተስፋፋ ከሄደ መፈናቀል፣ ስደት፣ ሥራ አጥነትና የኑሮ ውድነት ችግሮች እየባሱ ይሄዳሉ፡፡ የጋራ አገራዊ እሴቶቻችንን አጥብበንና አሳጥረን ማየት አሁን ላለንበት የፖለቲካ ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ችግሮች እንደዳረገን አያጠራጥርም፡፡

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ስንል የአንድነት፣ የመተባበር፣ የተፈጥሮ ሀብትን በጋራ የመጠቀምና የአብሮነት ስሜትን ስለሚሸረሽር የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚለው ይሻለናል፡፡ ከጋራ ታሪካዊ፣ ባህላዊና የተፈጥሮ ሀብታችን በተጨማሪ አንድ ሕዝብ የሚያሰኙን ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ ዛሬ ሁላችንም 120 ሚሊዮን እንሆናለን፡፡ በአንድ የአገር ወሰን፣ በአንድ ሕገ መንግሥት፣ በአንድ ሰንደቅ ዓላማ፣ በአንድ የአገር መዝሙርና በአንድ ፓስፖርት የምንኖር ስለሆነ አንድ ሕዝብ ነን፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሚለውን አቁመን የኢትዮጵያ ሕዝብ (በነጠላ) ማለት ብንጀምር ከገባንበት የፖለቲካ፣ ኤኮኖሚና ማኅበራዊ ችግር ለመውጣት አንድ ትንሽ ዕርምጃ ይሆናል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው   dawitabatetassew@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...