በሸዋንግዛው ሥዩም
የኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ የዘመናዊነትና ዕድገት መሻት ትልቅ ማደናቀፊያ ተጋርጦበታል፡፡ ይህ መሰናክል ረዥም ጥላውን ያጠላበት የአገሪቱን መጪ ዕድል በሚወስነው የትምህርት ሥርዓት ላይ ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ ይፋ የተደረገው የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ወይም በስፋት “ማትሪክ” በመባል የሚታወቀው ውጤት ትኩረት የሚሹ ክፍተቶችን ፍንትው አድርጎ አሳይቷል፡፡
ያለ ምንም ጥርጥር የማትሪክ ውጤት ግልጽ የማንቂያ ደወል ነው፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው (845‚000) ተማሪዎች ለፈተና የተቀመጡ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ማለፊያ ነጥብ ያስመዘገቡት 27,267 ወይም 3.2 በመቶ ብቻ ናቸው፡፡ ከዚህም በላይ አሳሳቢው ነገር ከ3,106 ትምህርት ቤቶች መካከል ምንም ተማሪዎችን ያላሳለፉት 42.8 በመቶ መሆናቸው ነው፡፡ ምንም እንኳ አንዳንድ ከዚህ የተለየ ውጤት ያስመዘገቡ ቢኖሩም ጥቂቶችና አልፎ አልፎ የተመዘገቡ ናቸው፡፡
ተማሪዎቻቸው ሙሉ በሙሉ የማለፊያ ነጥብ ያስመዘገቡ አምስት ትምህርት ቤቶች ብቻ ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ውስጥ አራቱ በመላ አገሪቱ ተሠራጭተው የሚገኙ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ናቸው፡፡ በተጨማሪም አምስት ሌሎች ትምህርት ቤቶች 94.5 በመቶ ተማሪዎቻቸውን ማሳለፍ የቻሉ ሲሆን፣ እነዚህም ያው አዳሪ ትምህርት ቤቶች ናቸው፡፡
ይህ ክስተት በእዚህ ዓመት ብቻ የታየ አይደለም፡፡ ዓምና አገር አቀፉን ፈተና ከወሰዱ 896,520 ተማሪዎች መካከል ከ50 ማለፊያ ነጥብ ያስመዘገቡት 3.3 በመቶ ብቻ ነበሩ፡፡ ይህም ግማሽ ያህሉ ብቻ ዩኒቨርሲቲ እንዲደለደሉ አድርጓል፡፡ ባለፉት ቅርብ ዓመታት የኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የማስፋፊያ ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ አሁን እየተመናመነ የመጣው የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ የሚያስመዘግቡ ተማሪዎች ቁጥር በእነዚህ ተቋማት ላይ ተግዳሮት ደቅኗል፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር ይህን እየሰፋ የመጣውን ልዩነት በማየት ለእዚህ የሚሆን ዕርምጃ እንደሚወስድ ገልጿል፡፡ ያንንም ተከትሎ፣ ወደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ መቁረጫ ነጥብ ላይ ማሻሻያ አድርጓል 30 በመቶ፡፡ ምንም እንኳ ይህ ውሳኔ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም የእሳት ማጥፋት ሥራ እንጂ፣ ሰፊ የሆነውን ችግር ግምት ውስጥ ያስገባ የመፍትሔ ዕርምጃ አይደለም፡፡
ትኩረቱ መሆን ያለበት መንስዔው ላይ ነው፡፡ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ኃላፊዎች ይህንኑ ለማድረግ ያላቸውን ፍላጎት በትምህርቱ ዘርፍ በመካሄድ ላይ ያሉ ሥራዎችን በማመልከት ይገልጻሉ፡፡ ከዚህም መካከል በቴክኖሎጂ ታግዞ እየተሰጠ ያለው መልቀቂያና በውጤቱ ላይ እየታየ ያለው ግልጽነት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ነገር ግን ጎላ ብሎ የሚታየው መረጃ ቴክኖሎጂን እንደ ዋና የተማሪዎችን ክንዋኔ ምዘና መቆጣጠሪያ መሣሪያ መጠቀም ላይ ነው፡፡ ምንም እንኳ ቴክኖሎጂ አጋዥ ሚና መጫወት የሚችል ቢሆንም ለሁሉም ችግሮች መፍትሔ ግን አይሆንም፡፡ ከእዚህ በተጨማሪ የአዕምሮ ቅኝትና የባህል ለውጥ ማድረግ አስፈላጊ ይሆናል፡፡
ወጣቶች፣ በትምህርት ዋጋ ማመንና በመማር፣ በማስተማሩ ሒደት ንቁ ሚና ሊወስዱ ይገባል፡፡ ከሽምደዳና መልሶ ከማስተጋባት ይልቅ ብልህነትን፣ በማሰብና ፈጠራን በማበረታታት ላይ ማተኮር ይገባል፡፡
በኢትዮጵያ ትምህርትን ለልማት መሣሪያነት ለመጠቀም ያለው ፍላጎት አዲስ አይደለም፡፡ አገሪቱ በታሪክ ትምህርትን ከድህነትና ከኋላቀርነት ለመውጣት ያለውን ኃይል ዕውቅና ሰጥታ ቆይታለች፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴ በአንድ ወቅት ራሳቸው የትምህርት ሚኒስትር ነበሩ፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የከፍተኛ ትምህርት መስፋፋት በትምህርት ላይ ያለው እምነት የሚታይ ነው፡፡
ሆኖም ከትምህርት የተገኘው ጥቅም የተጠበቀውን ያህል አይደለም፡፡ ምንም እንኳ አገሪቱ ዘመናዊ ትምህርትን ካስጀመረች ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ፣ ቢሆንም አሁንም ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ተርታ ትመደባለች ኢኮኖሚዋም የውጭ ዕርዳታን እንደ ትከሻ ወስዶታል፡፡ ዕድገት የታየባቸው ወቅቶችም የተቆራረጡ ሲሆን፣ አገሪቱ ጎላ ያለ የልማት ሽግግር ርቋታል፡፡ ነገሩ ትምህርት እምርታዊ ለውጥን ለማምጣት የሚሳነው ሆኖ አይደለም፡፡
በዓለም ዙሪያ በርካታ አገሮች በተመረጠ አኳኋን በትምህርት ላይ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ ዕጣቸውን ማሳመር ችለዋል፡፡ በዚህም የምሥራቅ እስያ አገሮች ታምራት የተሰኘው ጎላ ብሎ ይወጣል፡፡ እንደ ደቡብ ኮሪያ፣ ታይዋንና ሲንጋፖር ያሉ አገሮች ትምህርትን በመጠቀም እንደ ኮከብ ተመዝግበዋል፡፡ በቅርቡ የታየው የቻይና መነሳትም በትምህርት ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡
የኢትዮጵያው ተግዳሮት ከአቀራረብ ጋር የተዛመደ ነው፡፡ ትምህርትን ከማዛመድና አዳዲስ ዘዴዎችን ከመጠቀም ይልቅ ምዕራባዊያኑ በተምሳሌትነት መውሰዱ ውስንነት ሳይሆን አልቀረም፡፡ የትምህርቱም ትኩረት አካዳሚያዊና ሚዛኑን ለጠበቀ የሰው ኃይል ወሳኝ የሆነውን የቴክኒክና ሙያ ትምህርትን የገፋ ሆኖ ቆይቷል፡፡
በኢትዮጵያ ትምህርት ስኬት አካዳሚያዊ ቦታ ከማግኘትና kምስክር ወረቀት ጋር አንድ ተደርጎ ተወስዶ ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ውስን ዕይታ እውነተኛና ተግባር ላይ ሊውል የሚችል ዕውቀት፣ ዕውቅና አይሰጥም፡፡ ለእውነተኛ የማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ዕምርታ የትምህርቱ ሥርዓት ብልህነትን ማስረፅን ቅድሚያ መስጠት ይገባዋል፡፡
የመማር ዕውቀትን የመገብየት ክህሎትን አፅንኦት መስጠት ከጊዜ ወደ ጊዜ ተለዋዋጭ በሆነው ዓለም ወሳኝ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነቶቹን ክህሎቶችን ብዙ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ መለካትና መመዘን የሚቻል ሲሆን፣ ውጤቶቹ ከአገሮች ብልፅግና ጤናማነትና የአካባቢ ጥራት ጋር ይጣመራሉ፡፡
ኢትዮጵያ በአዲሱ የትምህርት ዓመት መጀመርያ እንደ መገኘቷ በበርካታ መቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ትምህርት ለመጀመር በመዘጋጀት ላይ ናቸው፡፡ ይህም ወቅት ለውጥ ለማድረግ ጊዜው ነው፡፡ መጪው ጊዜ አገሪቱ የትምህርት ሥልቷን መልሳ ለማጤን ባላት ችሎታ ላይ ይመሠረታል፡፡ ይህም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በትምህርቱ ዘርፍ በመጠቀም ላይ ብቻ የተመሠረተ ሳይሆን፣ የአዕምሮ ቅኝትና የባህል ለውጥ ማድረግንም ይሻል፡፡ መንገዱ፣ ቴክኖሎጂንና ሥርዓተ ትምህርትን ያማከለና ከአገሪቱ መሻት ጋር የተስማማ ሊሆን ይገባል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ከፍተኛ አማካሪ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው swsm02@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡