Friday, June 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊከታሪፍ በላይ መክፈል እንደ ሕጋዊ የተቆጠረበት የትራንስፖርት አገልግሎት

ከታሪፍ በላይ መክፈል እንደ ሕጋዊ የተቆጠረበት የትራንስፖርት አገልግሎት

ቀን:

የሰዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ከትራንስፖርት ጋር ጥብቅ የሆነ ቁርኝት አለው። ለረዥሙም ለአጭሩም መንገድ እኩል ተሠልፎ የታክሲ መምጣትን የሚጠባበቅ ሰውም እየተበራከተ መጥቷል።

ረዥም ሠልፍ ቆሞ መጠበቅ፣ ሠልፍ በሌለበት አካባቢ ደግሞ ተጋፍቶ መግባት፣ በግፊያው ወቅት የእጅ ስልክን ጨምሮ ሌሎች ንብረቶችን በሌቦች መመንተፍ፣ ታክሲ ሲታጣ ከሥራ አርፍዶ መግባት፣ አምሽቶ ወደ ቤት መመለስና የመሳሰሉት ችግሮች የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የዕለት ተዕለት እሮሮዎች ናቸው።

ይህንን ሁሉ ውጣ ውረድ አልፈው ከተሳፈሩ በኃላ ደግሞ ከረዳት ጋር ሌላ ጭቅጭቅ አለ፡፡ አንዳንዶች ውኃ በማያነሳ ምክንያት ከሕግ አግባብ ውጪ በራሳቸው ታሪፍ በማውጣት አስቀድመው፣ ‹‹ይኼንን ያህል ትከፍላላችሁ!›› በማለት ተስማምተው ምርጫ ያጣውን ኅብረተሰብ ሲበዘብዙ ይታያሉ።

- Advertisement -

ሌሎች ደግሞ ከተሳፈሩ በኋላ እንዲሁ ሰበብ እየፈለጉ ከተመን ውጪ ያስከፍላሉ። መብታቸውን ለማስከበር የሚከራከሩ ሰዎች በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ እነሱም ቢሆኑ ከጎናቸው በተቀመጠ ተሳፋሪ በሚደርስባቸው ግልምጫ ወይም ተግሳፅ ተሸንፈው የተጠየቁትን ከፍለው ሲወርዱ ይስተዋላል።

በተለይ ደግሞ የአዲስ አበባ መንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ከጥቅምት 20 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ አደረኩት ያለውን የታሪፍ ጭማሪ መነሻ በማድረግ ብዙዎች አግባብ ያልሆነ ወይም ከወጣው የዋጋ ተመን ውጪ ክፈሉ እየተባሉ እንደሆነ ይናገራሉ።

የታሪፍ ማሻሻያ ተደርጓል በሚል ሽፋን በሕግ አግባብ ከወጣው ታሪፍ ውጪ በሁለትና በሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት ከአምስት ብርና ከዚያ በላይ ያላግባብ ክፍያ የሚጠይቁ አሽከርካሪዎች ስለመኖራቸው ተጠቃሚዎች ይናገራሉ።

ወጣት ሻምበል ቢሆነኝ ከሳሪስ ወደ ስታዲየም ለሥራ ዘወትር ተመላላሽ ነው፡፡ የሚኒባስ ታክሲ ትራንስፖርት ላይ የተደረገው ጭማሪ ዘወትር ለሚመላለስ ሰው ከባድ እየሆነ በመምጣቱ፣ ፊቱን ሃይገር ወይም ቅጥቅጥ ወደሚባሉት የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከሪካሪዎች እንዲያዞር አድርገውታል፡፡ በእነዚህም ቢሆን የሚያወጣው ወጪ ከወርኃዊ ገቢው ጋር ሲሠላ ብዙውን እያወጣ ያለው ለትራንስፖርት እንደሆነ ይናገራል።

አዲሱ ታሪፍ ከመውጣቱ በፊት በቅጥቅጥ አምስት ብር ይከፍል እንደነበር ተናግሮ፣ በአሁኑ ወቅት ግን በእጥፍ ጨምሮ አሥር ብር እንደሚያወጣ ተናግሯል፡፡

ረዳቶች ታሪፍ ጨምሯል ብለው ተጨማሪ ገንዘብ ሲጠይቁ እንጂ፣ ‹‹ከየት እስከ የት በስንት ኪሎ ሜትር ጨመረ?›› የሚለው ላይ ብዙም ዕውቀት እንደሌለው የተናገረው ወጣቱ፣ ነገር ግን በሄደበት ሁሉ ጨምሯል በማለት ከዕጥፍ ያልተናነሰ ክፍያ እንደሚያወጣ ብሶቱን ገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ መንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ከጥቅምት 20 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ የታሪፍ ጭማሪ ማድረጉን ተከትሎ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችን አስመልክቶ ሪፖርተር የቢሮውን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ወ/ሮ ዕፀገነት አበበ አነጋግሯል።

ዳይሬክተሯ እንደለገጹት፣ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ከነዳጅ ችርቻሮ ዋጋ መጨመር ጋር ተያይዞ የታሪፍ ማሻሻያ ሊደረግ ይገባል በሚል ያነሱትን ጥያቄ መነሻ በማድረግ ጭማሪ ተደርጓል፡፡ ለዚህም ሰፊ ጥናት መደረጉንና የተደረገውን ጥናት በመመርኮዝ የታሪፍ ጭማሪ መደረጉን አክለዋል።

የታሪፍ ጭማሪ ስለመደረጉ ለኅብረተሰቡ በበራሪ ጽሑፎችና በልዩ ልዩ የመገናኛ ብዙኃን በኩል መረጃውን እያደረሱ እንደሆነ ተናግረው፣ ለአገልግሎት ሰጪዎችም ቢሆን በወጣላቸው ታሪፍ መሠረት ኅብረተሰቡን እንዳገለግሉ የማስተማርና የአገልግሎት ሰጪነት መንፈስን እንዲላበሱ ለማድረግ ከቅጣት በፊት ትምህርት እየሰጡ እንደሚገኙ አብራርተዋል።

አዲስ በተሻሻለው ታሪፍ መሠረት አንድ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ በስንት ኪሎ ሜትር ስንት መክፈል እንዳለበት በተመለከተ፣ ሚኒባስ በሚባሉት ተሽከርካሪዎች ቀደም ሲል በ2.5 ኪሎ ሜትር ባሉት አጭር ርቀቶች አራት ብር ያስከፍል የነበረው፣ በተመሳሳይ ኪሎ ሜትር ላይ የ50 ሳንቲም ጭማሪ በማድረግ 4 ብር ከ50 ሳንቲም ብቻ ሲሆን፣ ከ20 እስከ 30 ኪሎ ሜትር ባሉት ርቀቶች ደግሞ ቀደም ሲል 41 ብር የነበረው የ10 ብር ከ50 ሳንቲም ጭማሪ በማድረግ 51 ብር ከ50 ሳንቲም መሆኑን አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል ሀይገር ወይም ቅጥቅጥ እየተባሉ በሚጠሩት ላይ ደግሞ እስከ 8 ኪሎ ሜትር ባለው አጭር ርቀት 5 ብር የነበረው የ2 ብር ጭማሪ በማድረግ ወደ ሰባት ብር ከፍ ያለ ሲሆን፣ ከ24 እስከ 28 ኪሎ ሜትር ባለው ረዥም በተባለው ርቀት ላይ ደግሞ የ7ብር ጭማሪ በማድረግ ከ18 ብር ወደ 25 ብር ማድጉን ወ/ሮ ዕፀገነት አብራርተዋል።

ቢሮው ክትትል እያደረገ እንደሆነ በአሁኑ ወቅትም ትክክለኛውን አዲሱን የዋጋ ተመን በማስተዋወቅ ላይ እንደሆኑ ዳይሬክተሯ አውስተዋል።

ለአገልግሎት ሰጪዎች ደግሞ አዲሱን የዋጋ ተመን ዝርዝር የያዘ የከተማዋ ትራንስፖርት ቢሮ ማኅተም ያረፈበት ወረቀት ለተሳፋሪዎች በሚታይና ግልጽ በሆነ ቦታ ላይ እንዲያስቀምጡ አስገዳጅ ሁኔታዎች መኖራቸውን አክለዋል፡፡

ኅብረተሰቡም አገልግሎት ላገኘበት መክፈል ያለበት ከረዳቱ ጋር ተጨቃጭቆና ተከራክሮ ወይም ረዳቱ ባወጣለት ዋጋ ሳይሆን፣ ወረቀት ላይ ያለውን የዋጋ ዝርዝር በማየት ብቻ ሊሆን ይገባል ያሉት ወ/ሮ ዕፀገነት፣ ነገር ግን ይህንን ሳያደርግና ከወጣው የዋጋ ጭማሪ ውጪ ሲያስከፍል የተገኘ አሽከርካሪ እስከ አንድ ሺሕ ብር ቅጣት እንደሚከተለው ጠቁመዋል፡፡

ሒሳብ ተቀብሎ አንድ ብርም ሆነ ሃምሳ ሳንቲም ሳይመልስ የቀረ አሽከርካሪ ተመሳሳይ ቅጣት እንዲከፍል ይገደዳል። ተሳፋሪዎችም ቢሆኑ የዋጋ ዝርዝሩን የያዘውን ወረቀት ያላስቀመጠ አሽከርካሪ ሲያጋጥማቸው ‹‹ሒሳብ አልከፍልም›› የማለት መብት እንዳላቸው ጠቁመዋል።

ተገልጋዮች ከታሪፍ በላይ እናስከፍላለን የሚሉና በራሳቸው ተመን በማውጣት አስቀድመው ተመኑን እየተናገሩ የሚያስገቡ አሽከርካሪዎች ሲያጋጥማቸው፣ በተለያዩ መንገዶች ጥቆማቸውን ማድረስ እንደሚችሉ አሳውቀዋል።

ከእነዚህም መካከል ወደ ‹‹9417›› ነፃ የስልክ መስመር በመጠቀም ጥቆማ መስጠት እንደሚችሉ ተናግረው፣ ይህ ካልሆነ ደግሞ በቅርብ በሚገኝ የትራንስፖርት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤትና በቅርብ ለሚገኝ የትራፊክ ፖሊስ ጥቆማና ቅሬታቸውን ማቅረብ ይችላሉ ብለዋል።

እስካሁን ከተገልጋዮች በ9417 በደረሰ ጥቆማ አስተማሪ የሆነ ዕርምጃ እየተወሰደ መሆኑን፣ እንደ አዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ በየትኛውም አካባቢ አሥር ብር የሚያስከፍል ታሪፍ እንዳልወጣ፣ ሆኖም አሥር ብር lሚያስከፍሉ አገልግሎት ሰጪዎች የተጠየቁትን ገንዘብ ከፍለው የሚወርዱ ተገልጋዮች መበራከታቸውን ጠቁመዋል።

መንግሥት ከሚያደርገው ክትትልና ቁጥጥር በላይ ኅብረተሰቡ መብቱን ጠያቂ መሆን ይኖርበታል ሲሉ የተናገሩት ዳይሬክተሯ፣ ተሳፋሪው መክፈል ያለበት በሒሳብ ተስማምቶ ሳይሆን በሕጉ መሠረት በወጣው ተመን እንደሆነ ተናግረዋል።

የድንገተኛ ፍተሻ ሲደረግ እንኳን ኅብረተሰቡ የከፈለውን ሒሳብ ለመናገር ፈቃደኛ እየሆነ እንዳልሆነ፣ ይህ ደግሞ በአጥፊዎች ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ አንዱ እንቅፋት ነው መሆኑን ዕፀገነት አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...