መስኮት ቀዶ ገባ፣
ንፋስና ውርጩ፤
ለንጋት አዜሙ፣
ወፎቹ ተንጫጩ፡፡
ተነፋፍቀው የኖሩ፣
ተኳርፈው ያደሩ፤
ለወፎቹ ዜማ፣ ግጥም ያወርዳሉ፤
ለቀዘቀዘ ልብ፣ ሙቀት ይረጫሉ፤
ይተቃቀፋሉ፡፡
አንቺ የለሽበትም፡፡
ከጎረቤት ደጃፍ፣ ቡና ይወቀጣል፤
‹‹ቡና ጠጡ›› እያለ፣
እንደመወርወሪያ፣
በመንደሩ መሀል፣ ሕፃን ልጅ ይሮጣል፡፡
እሱን ተከትለው፤
የመንደሩ ሴቶች፣
ሐሜት አንጠልጥለው፤
ይሽቀዳደማሉ፤
ለነጋው አዲስ ቀን
ንድፍ ያስቀምጣሉ፡፡
አንቺ የለሽበትም፡፡
ደግሞ ቀኑ ጋመ፣ . . . .
አዳሜ ተነሳ፣
ከትናንት ገንፍሎ፣
እንደልሙጥ ሽሮ፣
መግላሊቱን ጥሎ፤
ተስፋ አንጠልጥሎ፤
ሊረግም – ሊመርቅ
ሊጥል ወይ ሊወድቅ፤
ሊያለቅስ ወይም ሊስቅ፤
በናፍቆት – ሊተያይ፤
ተጣልቶ – ሊለያይ፣ . . . .
አሮጌ ትላንቱን፣ ጎጆው እየጣለ፤
አዲስ ቀኑን ሊያትም፣ አደባባይ ዋለ፡፡
አንቺ የለሽበትም፡፡
ደግሞ አመሻሽ ላይ፣ . . . .
ተራራው አናት ላይ፣
ሠዓሊው ተፈጥሮ፣
አድማስን ወጥሮ፣
ቀለማት ደርድሮ፤
አንዳንዴ በተስፋ፣
ቢጫ እያበዛ፣ ቀይ እያሳነሰ፤
አንዳንዴ በምሬት፣
ቀዩን እያበዛ፣ ቢጫ እየቀነሰ፤
ተቅላሎት ሲሸምን፣ ፍም እያባዘተ፣
የደከመውን ቀን፣ አባብሎ ሲያስተኛ፣ ውበት እየጋተ፡፡
ደግሞ መለስ ብሎ፣
በልቤ የያዝኩትን፣ ማጣት አስተውሎ፣
በረዥም ቡሩሹ፣ ካድማስ ወዲያ በኩል፣ ጨለማን አጥቅሶ፤
ከሰል ሲያስመስለው፣ ሲሠራ ያዋለውን፣ ሲያፈርሰው መልሶ፤
ለጥበብ ምትሃት፣ ልባቸው የገበረ፤
ሰዎች ተሰብስበው፣ ያደንቁ ነበረ፡፡
አንቺ የለሽበትም፡፡
አንቺ የለሽበትም፡፡
አላገኘሁሽም፡፡
ቢሆንም አውቃለሁ፣ . . .
የለሽም አልልም እፈልግሻለሁ፡፡
(ግጥምና ሕይወት ማኅበዊ ትስስር ገጽ፣ በድሉ ዋቅጅራ፣ ግንቦት 2012)