የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን የፕሬዚዳንት ማሟያ ምርጫ ቅዳሜ ኅዳር 8 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ በአፍሪካ ኅብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ እንደሚከናወን ተገለጸ፡፡
በማሟያ ምርጫው ላይ ለመካፈል የዓለም ቦክስ ማኅበር ፕሬዚዳንትና ዋና ጸሐፊውን ጨምሮ ከ47 በላይ አገሮች በጠቅላላ ጉባዔው ላይ እንደሚካፈሉ የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡
ሰኞ ኅዳር 3 ቀን 2016 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጠው የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን፣ በጉባዔው የሚሳተፉ አገሮች ወደ አዲስ አበባ እየገቡ እንደሆነና አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡
በጋዜጣዊ መግለጫው የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢያሱ ወሰን ዕጩ ሆነው ስለቀረቡበት ሒደትና፣ አጠቃላይ የምርጫው ጉዳይ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
በዚህም መሠረት መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ቀድሞ ሊደረግ ከነበረበት ዱባይና ደቡብ አፍሪካ ወደ አዲስ አበባ ሊዘዋወር የቻለበትን ምክንያትም ማብራሪያ ተሰጥቶበታል፡፡
እንደ ዕጩ ፕሬዚዳንቱ ማብራሪያም፣ ምርጫው በአዲስ አበባ ከተማ እንዲከናወን የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዳይሬክተሮች ቦርድ ውሳኔ በመስጠቱ መዛወሩና ኢትዮጵያም ሙሉ ወጪ በመሸፈኗ መሆኑ ተብራርቷል፡፡
ከዚህም ባሻገር ዕጩ ፕሬዚዳንቱ ምርጫውን ቢያሸንፉ በአፍሪካ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ቦክስ ላይ ሊተገብሩ ስለሚችሉት ጉዳዮች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
እንደ አቶ ኢያሱ አስተያየት ከሆነ ምርጫውን እንደሚያሸንፉ ሙሉ እምነት እንዳላቸው አንስተው፣ አኅጉር አቀፍ ውድድሮች እንዲበራከቱ ማድረግና ስፖርቱ ከትምህርት ቤት ጀምሮ እንዲዘወተር ማድረግ ዋና ግባቸው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር አቶ ኢያሱ ምርጫውን ማሸነፍ ከቻሉ የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ከዓለም አቀፉ ቦክስ ማኅበር ጋር ያለውን ግንኙነት እንደሚያጠናክሩና አፍሪካ በኦሊምፒክ ላይ ያላት ተሳትፎ እንዲሰፋ የማድረግ ዕቅድ እንዳላቸው አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያዊው ዕጩ የኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሆነው መመረጥ የሚችሉ ከሆነ፣ የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን መቀመጫው አዲስ አበባ እንደሚሆን የተገለጸ ሲሆን፣ ከዓለም አቀፉ ቦክስ ማኅበር ጋር በመነጋገር ስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራ በአዲስ አበባ ለማስገንባት ውጥን እንዳላቸው ጠቅሰዋል፡፡
ግንባታውን ለማከናወን ከዓለም አቀፉ ቦክስ ማኅበር እስከ 10 ሚሊዮን ዶላር እንደሚመደብላቸው የጠቀሱት አቶ ኢያሱ፣ በተለምዶ ትንሿ ስታዲየም የምትባለው ቦታ ላይ ግንባታውን ለማድረግ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር መወያየታቸውን ጠቁመዋል፡፡
ቅዳሜ ኅዳር 8 ቀን 2016 ዓ.ም. በሚደረገው የማሟያ ምርጫ ከአቶ ኢያሱ ጋር የካሜሮኑ በርትራንድ ሜንዱጋና የሞሮኮ መሐመድ ኤልካቦሪ ይወዳደራሉ፡፡ ምርጫውን በአብላጫ ድምፅ ያሸነፉ የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት በመሆን ለአራት ዓመታት ይመራሉ፡፡