Sunday, July 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየውጭ የፋይናንስ ተቋማት በተከለለ ዞን ውስጥ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚፈቅድ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን...

የውጭ የፋይናንስ ተቋማት በተከለለ ዞን ውስጥ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚፈቅድ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን አዋጅ ቀረበ

ቀን:

  • ማንኛውም የመሬት አስተዳደር ሕግ በኢኮኖሚ ዞኖች ይዞታ ላይ ተፈጻሚነት አይኖረውም
  • የፌዴራልም ሆነ የክልል መዋቅሮች ያለ ፈቃድ ወደ ዞኖቹ መግባት አይችሉም

የውጭ አገር የፋይናንስ ተቋማት በኢትዮጵያ በሚቋቋሙ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ ገብተው አገልግሎት እንዲያቀርቡ የሚፈቅድ ድንጋጌን ያካተተ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበ ሲሆን፣ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ ለመወያየት ረቂቅ ሰነዱን ለአባላቱ አሠራጭቷል።

ከረቂቅ አዋጁ ድንጋጌዎች መካከል መሠረታዊ የፖሊሲ ለውጦች ከተንፀባረቁባቸው አንዱ የውጭ አገር የፋይናንስ ተቋማት በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ ገብተው አገልግሎት እንዲያቀርቡ የሚፈቅደው አንቀጽ ተጠቃሽ ነው።

በዚህም መሠረት በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 33 ንዑስ አንቀጽ አንድ ላይ ‹‹የውጭና የአገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት በልዩ ኢኮኖሚ ዞን አገልግሎት የማቅረብ መብት አላቸው፤›› የሚል ድንጋጌ ተካቶ ቀርቧል።

በልዩ ኢኮኖሚ ዞን ውስጥ በፋይናንስ አገልግሎት ላይ የሚሠማሩ የውጭ አገርና የአገር ውስጥ ተቋማት የሚመረጡበትን መሥፈርት ደረጃ፣ የአሠራርና የፈቃድ አሰጣጥ ሁኔታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሚያወጣው መመርያ እንደሚወሰን ረቂቁ ያመለክታል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የልዩ ኢኮኖሚ ዞንን ሳቢነት፣ ተወዳዳሪነትና ውጤታማነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ራሱን የቻለ የፋይናንስና የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሪፎርም የማካሄድ፣ የአሠራር ሥርዓት የመዘርጋት ኃላፊነት ተጥሎበታል። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከላይ የተገለጸውን ኃላፊነት ሲወጣም፣ በተለየ ሁኔታ ከግንዛቤ ሊያስገባቸው ይገባል ያላቸውን መሠረታዊ ነጥቦች ረቂቅ አዋጁ በጥቅሉ አስቀምጧል። 

በዚህም መሠረት ብሔራዊ ባንክ፣ ከኢንቨስትመንትና ወጪ ንግድ የተገኘ ገንዘብ ወደ ውጭ ማስተላለፍን፣ የውጭ አገር ገንዘብ የባንክ አካውንት መክፈትን፣ በልዩ ኢኮኖሚ ዞን ውስጥ ለግብይት የሚያገለግሉ የገንዘብ ዓይነቶችንና መሰል ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት ይጠበቅበታል። 

በተጨማሪም ፣ የኢንቨስትመንቱን ልዩ ባህርይ የውጭ ንግድ የማሳደግ ብሔራዊ ትልምን፣ የኢንዱስትሪዎችን የግብዓት ፍላጎትና መሰል ጉዳዮችን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በልዩ ኢኮኖሚ ዞን ውስጥ የሚገኙ ባለሀብቶች ከኢንቨስትመንት ሥራቸው የሚያገኙትን የውጭ ምንዛሪ ይዘው የሚቆዩበትና የሚጠቀሙበት፣ በጉምሩክ ክልል ውስጥ ተፈጻሚ ከሚደረገው አሠራር የተሻለ ጥቅም የሚሰጥ ሥርዓትን የሚገዛ መመርያ እንደሚያወጣ ረቂቅ አዋጁ ያመለክታል።

የልዩ የኢኮኖሚ ዞን ሥርዓት ለውጭ ኢንቨስትመንቶች ሰፊ የመሳተፍ ዕድልን የሚሰጥ ሆኖ እንደሚደራጅና ለውጭ ኢንቨስትመንት ዝግ የሆኑ ዘርፎች እንደ ሁኔታው በልዩ ኢኮኖሚ ዞን ውስጥ ሊፈቀድ እንደሚችል የሚጠቁም ድንጋጌ በረቂቁ ታካቷል።

‹‹የልዩ ኢኮኖሚ ዞን ሥርዓት ሁሉን አቀፍ በሆነ አንድ ሕግና አስተዳደር ሥር መከናወን አለበት›› የሚል መርህ የተቀመጠ ሲሆን፣ በዚህ መርህ መሠረትም በረቂቅ አዋጁ ሥልጣን ከሚሰጠው መንግሥታዊ አካል ውጪ ሌላ ድርጅት ወይም የማንኛውም መንግሥታዊ መዋቅር ጣልቃ ገብነትነትን ይከለክላል፡፡

በአጠቃላይ ልዩ የኢኮኖሚ ዞንንና የልዩ ኢኮኖሚ ዞን ተጠቃሚነትን በተመለከተ፣ ረቂቅ አዋጁ ሙሉ ሥልጣን የሚሰጠው ለኢንቨስትመንት ቦርድና ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ብቻ ነው።

በዚህም መሠረት ማንኛውም ሰው ወይም ተቋም ማለትም ኢንቨስተሮች፣ ሠራተኞች፣ ነዋሪዎች፣ አገልግሎት ሰጪ ሦስተኛ ወገኖች፣ የአንድ መስኮት አገልግሎት ሰጪዎች፣ የክልል መንግሥታት ተወካዮችና የፌዴራል መንግሥት ተቋማት የኢኮኖሚ ዞን ተጠቃሚነት ደረጃን የሚይዙት ከኢንቨስትመንት ኮሚሽኑ ፈቃድ ሲያገኙ ብቻ ይሆናል።

ይህንን ለማጠናከርም፣ ከፀጥታ አካላት ውጪ ማንኛውም የፌዴራል፣ የክልል ወይም የአካባቢ አስተዳደር አካል ወይም ሰው ካልተፈቀደለት በስተቀር ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን መግባት ወይም በዞኑ ማናቸውም ሥራ ውስጥ ጣልቃ መግባት እንደማይችል የሚደነግግ አንቀጽ በረቂቅ አዋጁ ተቀምጧል።

የልዩ ኢኮኖሚ ዞን መሬት ልማትና አጠቃቀም ጋር የተያያዙ ሁሉም ሕጎች ወይም ደረጃዎች በረቂቅ አዋጁ በተቀመጡ ድንጋጌዎችና ይህንን ለማስፈጸም በሚወጣ ደንብ ወይም መመርያ ብቻ እንደሚመራ ረቂቅ አዋጁ ያመለክታል።

በዚህም መሠረት የመሬት ይዞታን፣ የከተማ ወይም የገጠር መሬት አጠቃቀምንና የጨረታ ሥርዓትን የሚመለከቱ ማናቸውም ሌሎች የሕግ ወይም አስተዳደራዊ ሥርዓቶች በልዩ ኢኮኖሚ ዞን የሚገኝ መሬትን በተመለከተ ተፈጻሚነት እንደማይኖራቸው ተመልክቷል። 

በተጨማሪም የሕንፃዎች፣ የመሠረተ ልማቶች፣ የተያያዥ መዋቅሮችን ልማትና ግንባታን የሚመለከቱ ሌሎች የሕግ ድንጋጌዎች ቢኖሩም እንኳ፣ በልዩ ኢኮኖሚ ዞን ውስጥ የሚካሄዱ የሕንፃ የመሠረተ ልማትና ተመሳሳይ መዋቅሮች ልማትና ግንባታ ሥራ በልዩ ኢኮኖሚ ዞን ላይ ተፈጻሚነት እንዳማይኖራቸው ረቂቁ ያመለክታል።

በመሆኑም የዲዛይን ማፅደቅ፣ የግንባታ ፈቃድና የመጠቀሚያ ፈቃድ አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል በኢንቨስትመንት ኮሚሽኑ እንደሚፈቀዱ የረቂቁ ድንጋጌዎች ያመለክታሉ።

በሌላ በኩል የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አልሚ፣ አስተዳዳሪና ድርጅቶች ከመንግሥት የሚያገኟቸው አነስተኛ ማበረታቻዎችን የመወሰን ሥልጣን በዘርፉ ዕውቀት ለሌለው መንግሥታዊ ተቋማት መስጠት የራሱ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው ከቀደሙ የአገሪቱ ተሞክሮዎች መጤኑን የሚገልጸው የረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ ሰነድ፣ ይህንን ጉድለት ለመድፈን በመንግሥት የሚሰጡ ማበረታቻዎችን ቢያንስ በጥቅል ለይቶ ማስቀመጥ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ መሠረታዊ የሚባሉ ጥቅል ማበረታቻዎች ተዘርዝረው በረቂቅ አዋጁ እንዲመላከቱ መደረጉን ያስረዳል።

ከተዘረዘሩት ማበረታቻዎች መካከል፣ ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የሚገቡና ከልዩ ኢኮኖሚ ዞን የሚወጡ ዕቃዎች ከቀረጥና ግብር ክፍያ ነፃ እንዲሆኑ፣ ከጉምሩክ ክልል ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የጉምሩክ ቁጥጥር ክልል የሚገቡ ዕቃዎችና አገልግሎቶች ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ እንዲሆኑ፣ እንዲሁም ከሌሎች ቀጥተኛ ያልሆኑ የአገር ውስጥ ታክሶች ሙሉ ለሙሉ ነፃ የመሆን መብት እንዲሰጣቸው በረቂቁ አዋጁ ተዘርዝሮ ቀርቧል።

ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የሚገቡ የግንባታ ዕቃዎች ላይ የጉምሩክ ቀረጥና ታክስ እንዳይከፍልባቸው፣ በተመሳሳይ ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የሚገቡ የካፒታል ዕቃዎች ከጉምሩክ ቀረጥና ቀጥተኛ ያልሆኑ ግብሮች ነፃ የመሆን መብቶችን ረቂቅ አዋጁ ይፈቅዳል። 

የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አልሚ ባለሀብቶችና በዞኖቹ ለሚቀጠሩ የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ሠራተኞችም የታክስ ማበረታቻዎችን እንዲያገኙ ይፈቅዳል። 

በዚህም መሠረት የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አልሚና ተሳታፊ ድርጅቶች ባለ አክሲዮኖች የሚያገኙት የትርፍ ድርሻ ከገቢ ግብር ነፃ እንዲሆን፣ በድርጅቶቹ የሚቀጠሩ የውጭ አገር ሠራተኞች ደግሞ ድርጅቱ የንግድ ፈቃድ ካገኘበት ጊዜ አንስቶ ለአምስት ተከታታይ ዓመታት ከደመወዝ ገቢ ግብር ነፃ የመሆን መብት እንዲያገኙ በረቂቅ አዋጁ ተዘርዝሮ ቀርቧል።

በማንኛውም የልዩ ኢኮኖሚ ዞን ሥራ ላይ የተሰማራ የውጭ ባለሀብት ግለሰብ ወይም በውጭ አገር የሚኖር ኢትዮጵያዊ ወይም የውጭ አገር ዜግነት ያለው ተቀጣሪ ወደ ኢትዮጵያ ለዚሁ ዓላማ የገባ እንደሆነ የግል መገልገያ ዕቃዎችን ያለ ቀረጥና ሌሎች ክፍያዎች እንዲያስገባ የፈቀደ ሲሆን፣ የሚገቡት የግል መገልገያ ዕቃዎች ዓይነትም በጥቅሉ አስቀምጧል።

ልዩ የኢኮኖሚ ዞን አልሚ ፈቃድ ለማግኘት የሚጠየቀው ዝቅተኛ የካፒታል መጠን አምስት ቢሊዮን ብር እንደሚሆንና በአንድ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን አልሚ ጠያቂነት ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ተብሎ የሚሰየም ይዞታ ከ75 ሔክታር ሊያንስ እንደማይችልም ረቂቁ ያመለክታል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመጪዎቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ በዚህ ረቂቅ አዋጅ ላይ እንደሚወያይበት ሪፖርተር ለማወቅ ችሏል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...