የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ለአንድ ወር ከነዳጅ ሥርጭት ውጪ እንዲሆኑ ዕግድ ጥሎባቸው የነበሩ 40 ማደያዎችን፣ ዕገዳውን በማንሳት በመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የነዳጅ ሥምሪት አገልግሎት እንዲጀምሩ ወሰነ፡፡
ባለሥልጣኑ፣ አብዛኞቹ ነዳጅ ማደያዎች ከኤሌክትሪክስ ሽያጭ አማራጮች ውጪ መሸጣቸውን ለአንድ ወር አደረኩት ባለው የማጣራት ሒደት መሠረት፣ በአዲስ አበባና በሸገር ከተሞች የሚገኙ 40 ማደያዎችን ለአንድ ወር በማገድ፣ 57 ማደያዎችን ደግሞ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ባለፈው ሳምንት ሰኞ ጥቅምት 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ውሳኔ ማሳለፉ የሚታወስ ነው፡፡
ሆኖም ከበርካታ ማደያዎች ተቃውሞ የገጠመውና ባለሥልጣኑም ከኢትዮ ቴሌኮም በድጋሚ ለማጣራት ሲሞክርበት የነበረውን ውሳኔ፣ በተላለፈ በሳምንቱ ከትናንት በስቲያ ሰኞ ኅዳር 3 ቀን 2016 ዓ.ም. አንድ ማደያ በመጨመር 41 ማደያዎች ከዕገዳው ዕገዳቸው ተነስቶ በመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መታለፋቸውን ከባለሥልጣኑ በወጣ ደብዳቤ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ሪፖርተር የተመለከተው በባለሥልጣኑ የነዳጅ ሥርጭት ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክተሩ በአቶ ደሬሳ ኮቱ ተፈርሞ የወጣው ዕግዱ የተነሳበት ደብዳቤ እንደሚገልጻው፣ ዕርምጃውን ‹‹ከዕገዳ ወደ መጨረሻ ማስጠንቀቂያ›› ይቀይረዋል፡፡
ማደያዎቹ ለስምንት ቀናት ታግደው መቆየታቸውንና ዕገዳው እስኪነሳ የተቀጡትን ተስምንት ቀናት ቅጣት ያስተምራል ተብሎ በመታሰቡ፣ በዕገዳው ምክንያት በከተሞቹ ሊፈጠር የሚችል የነዳጅ እጥረት ምልክት በመታየቱ፣ እንዲሁም ማደያዎቹና ኩባንያዎቻቸው የመጠኑ ‹‹ማነስና መብዛት እንጂ ችግሩ መኖሩን ያመኑ በመሆናቸው›› ዕገዳውን ማንሳቱን ባለሥልጣኑ የጻፈው ደብዳቤ ይገልጻል፡፡
የሚወሰደው ዕርምጃ መረጃዎችን ለማጣራት በቀጣይነትም እንደሚቀጥል የሚያስረዳው ደብዳቤ፣ ኩባንያዎች በሥራቸው ለሚገኙ ማደያዎች የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንዲሰጡና ለባለሥልጣኑ እንዲያሳውቁም ያዛል፡፡
ከታገዱት ማደያዎች አንደኛው የነበረው በአዲስ አበባ መቻሬ ሜዳ የሚገኘው የኖክ ኢትዮጵያ ማደያ ባለቤትና ሥራ አስኪያጇ ወ/ሮ አርሴማ ሐጎስ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ዕገዳውንም ሆነ ማስጠንቀቂያውን እንደማያምኑበት ባለሥልጣኑ ኦዲት ባደረገበት ጊዜ ያካሄዱት የነዳጅ ሽያጭ መቶ በመቶ የሚሆነውን በኤሌክትሮኒክስ አማራጮቹ የሸጡ መሆኑን በራስ መተማመን የገለጹ ሲሆን፣ ‹‹ምሥጋና እንጂ ቅጣትም ሆነ ማስጠንቀቂያ አይገባኝም›› ይላሉ፡፡
የወ/ሮ አርሴማና ሌሎች የተወሰኑ የማደያዎች መረጃን የባለሥልጣኑ ኃላፊዎች ከኢትዮጵያ ቴሌኮም ጋር በድጋሚ በማመሳከር ዕገዳው የተነሳበት ውሳኔ ከመተላለፉ በፊት ባለፈው ቅዳሜ ኅዳር 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ነዳጅ ይጫንላቸው የነበረ ሲሆን፣ ከሁለት ቀን በኋላ ባለሥልጣኑ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ከሰጣቸው ማደያዎች ጋር አብሮ አካቷቸዋል፡፡
የኩባንያውን ውሳኔ እየጠበቀ መሆኑንና ከኩባንያው መልስ በኋላ ባለሥልጣኑ አሁንም በዚህ ውሳኔ (በማስጠንቀቂያ) የሚፀና ከሆነ ግን ወደ ዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ ‹‹ምናልባትም ከዚያ በላይ›› ሊሄዱ እንደሚችሉ ወ/ሮ አርሴማ አስረድተዋል፡፡
የማስጠንቀቂያውን ደብዳቤ የጻፉት አቶ ደሬሳ ኮቱ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የተወሰኑ ማደያዎች የመረጃ መጣረስ አለ በሚል ቅሬታ አቅርበው እንደነበር ያስረዱ ሲሆን፣ ባለሥልጣኑ ግን ሁሉንም ነገር ከግምት በማስገባት እንዲሠራና፣ ለማደያዎች ‹‹ቅጣት እንዲኖር ለማሳየት›› ዕርምጃው እንደተወሰደ ያስረዳሉ፡፡
‹‹መረጃዎቹ ባይሟሉም፣ ድርጊቶቹን የሚያሳዩ ሁኔታዎች ስላሉ ዕርምጃ መውሰዱ አስፈላጊ ነው በሚል ዕርምጃ ወስደናል፤›› ሲሉ የገለጹት አቶ ደሬሳ፣ ምንም ሳናጠፋ ነው ዕርምጃ የተወሰደው ለዚህም ወደ ዕንባ ጠባቂ ተቋም እደሄዳለን ስላሉት ማደያዎች ሲመልሱ፣ ‹‹እነሱ መጀመርያም የቁጥር ስህተት እንጂ ጥፋቱ እንዳለ አምነው ነው አረጋግጠንና አስልተን የሄድነው፤›› ብለዋል፡፡
በቁጥር ውስን የሆኑ ማደያዎች የስምና የልዩ ቁጥር ስህተት በመፈጠሩ የተካተቱና በሌሎች ማደያዎች ግን ምንም የመረጃ ክፍተት እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ ሆኖም ግን ስህተት ተፈጥሮ የተካተቱም ሆነ ሌሎች ማደያዎች ‹‹ተመልሰው እዚያው ጥፋት ውስጥ ናቸው፤›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
የኢትዮጵያ ነዳጅ አዳዮች ማኅበርም ውሳኔው እንዳሳዘነው፣ እንደ ማኅበር ለንግድ ሚኒስቴርና ለባለሥልጣኑ ደብዳቤ እንደሚጽፉ የማኅበሩ የቦርድ አመራር አባል ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ‹‹ካፈርኩ አይመልሰኝ ዓይነት ውሳኔ ነው የተወሰነው›› ያሉት የማኅበሩ አመራር አባል ‹‹ባለሥልጣኑ የወሰነውን ሕገወጥ ውሳኔ ለዕንባ ጠባቂ ተቋም በአቤቱታ እናቀርባለን፤›› ብለዋል፡፡