Sunday, December 10, 2023

የመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት በአፍሪካ ቀንድ ላይ የሚያስከትለው ተፅዕኖ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

እ.ኤ.አ. በ1973 የተቀሰቀሰው የዓረቦችና የእስራኤል ጦርነት ለኢትዮጵያው የመጨረሻ ንጉሠ ነገሥት የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት አንዱ መውደቂያ ምክንያት እንደሆነ ታሪክ ያወሳል፡፡ እስራኤሎች የ‹‹ዮም ኪፖር›› ዓረቦች ደግሞ የ‹‹ረመዳን›› ጦርነት ብለው የሚጠሩት የመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ የብዙ አገሮችን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መሠረት ያናጋ የታሪክ አጋጣሚ ነበር ይባላል፡፡ ጦርነቱ በወቅቱ የግብፅ መሪ አንዋር ሳዳትና የሶሪያ መሪ ሀፌዝ አላሳድ ከስድስት ዓመታት ቀደም ብሎ በስድስቱ ቀናት ጦርነት ወቅት፣ በእስራኤል የደረሰባቸውን ሽንፈት ለመበቀልና የተነጠቋቸውን ግዛቶች ለማስመለስ በሚል በእስራኤል ላይ በጋራ የከፈቱት ጦርነት ነበር፡፡

በጦርነቱ መጀመሪያ ላይ በግብፅና በሶሪያ ጦር ጣምራ ጥቃት እስራኤሎች ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ቢሆንም፣ ነገር ግን ከዚያ ጉዳት አገግመው ጦርነቱን በድል ለመወጣት እንደቻሉ ይነገራል፡፡ የዚህ የጦርነት ውጤት ያስከፋቸው የዓረብ አገሮች ደግሞ፣ እስራኤሎችና ለእስራኤል አጋዥ ናቸው ያሏቸውን ምዕራባውያን አገሮች በኢኮኖሚ ለመቅጣት ተነሱ፡፡ በሳዑዲ ዓረቢያ መሪነት የዓረብ አገሮች የነዳጅ ምርት ማቋረጥ ዕቀባ እንደጣሉ ይነገራል፡፡ ይህ የዓረብ አገሮች ተባብረው የጣሉት የነዳጅ ዕቀባ ደግሞ ከአዲስ አበባ ጎዳናዎች ጀምሮ በዓለም ትልልቅ ከተሞች ተፅዕኖው መታየቱ ነው የሚነገረው፡፡

የመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት በአፍሪካ ቀንድ ላይ የሚያስከትለው ተፅዕኖ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

የዓረቦችና የእስራኤል የዚያን ጊዜው ግጭት ባስከተለው የነዳጅ ዋጋ መናር የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መፈተኑ ይነገራል፡፡ የንጉሡን መንግሥት ያብረከረኩ የሥራ ማቆም አድማዎች፣ የደመወዝ ይጨመርልን ጥያቄዎችና ኑሮ ተወደደብን የሚሉ የአደባባይ ትዕይንተ ሕዝቦች ከዚያን ጊዜው የመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት ጋር የተቆራኙ እንደነበሩም ይወሳል፡፡ የንጉሡን መንግሥት በማዳከም የሚጠቀሱት የአራት ቀናት የእንቅስቃሴ ዓድማዎችና የታክሲ ሾፌሮች ተቃውሞ አገራዊ መነሻ ቢኖራቸውም፣ በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ተፅዕኖ የተነሳ የተባባሱ የፖለቲካ ምስቅልቅሎች መሆናቸው ነው የሚነገረው፡፡

በብዙ የፖለቲካ ኃያሲያን እንደሚነገረው የመካከለኛው ምሥራቅ ቀውስ፣ ኢትዮጵያ ለምትገኝበት ለአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ተፅዕኖው ቅርብ ነው፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚፈጠር ችግር በአፍሪካ ቀንድ ላይ የሚያሳርፈው ተፅዕኖ ቀላል አለመሆኑ ይነገራል፡፡ ይህ ደግሞ እ.ኤ.አ. በ1973 ጦርነት ብቻ ሳይሆን፣ ዛሬም ድረስ የሚስተዋል ሀቅ መሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ከሰሞኑ እንደ ቲክቶክ ባሉ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ብዙዎች ያጋሩት በሐረር ከተማ የታየ እስራኤልን የሚያወግዝ ሰላማዊ ሠልፍ እንደ ምሳሌ መጠቀስ የሚቻል መሆኑ ነው፡፡ በእስራኤልና በሐማስ መካከል የሚደረገው ጦርነት በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ዜጎች ዘንድ የፈጠረው የስሜት ውጥረት ቀላል አለመሆኑ ይነገራል፡፡ ሐረር አንደኛ መንገድ ላይ የተሰባሰቡ ወጣቶች ‹‹ዳውን ዳውን እስራኤል›› እያሉ የውግዘት ሠልፍ ሲያካሂዱ መታየታቸው፣ የመካከለኛው ምሥራቅ ወቅታዊ ግጭት ባስከተለው ተፅዕኖ መሆኑ ይነገራል፡፡ ከሰላማዊ ሠልፍ በመለስ በዜጎች መካከል አንዱን ደግፎ ሌላውን ወገን ተቃውሞ የሚደረገው ክርክርና ሙግትም ቢሆን፣ አንዳንዴ ያልተጠበቀ ውጤት ሊኖረው የሚችል የመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት ወላፈን መሆኑ ይወሳል፡፡

የእስራኤልና የሐማስ ጦርነት በተለይ የጋዛ ሰርጥን እንዳልነበረ ማውደሙ እየተነገረ ነው፡፡ እስካሁን ከ10 ሺሕ በላይ ፍልስጤሞች ያለቁበትና ከ1,400 በላይ እስራኤሎች የሞቱበት ግጭቱ የመብረድ ምልክት አለማሳየቱ ይስተዋላል፡፡

የእስራኤልና የሐማስ አንድ ወር ያለፈው ጦርነት በዚሁ ተባብሶ ከቀጠለ በሒደት በአፍሪካ ቀንድ ላይ ሊያመጣ የሚችለው ተፅዕኖ ከእስካሁኑ የሰፋ እንደሚሆን ነው የሚገመተው፡፡ በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር አቶ ዑስማን መሐመድ፣ የመካከለኛው ምሥራቅ ግጭትን በቅርበት መከታተልና ከጉዳዩ በስተጀርባ ያሉ አሻጥሮችን በጥንቃቄ መመርመር አስፈላጊ እንደሆነ ያሳስባሉ፡፡   

‹‹ኢትዮጵያን መካከለኛው ምሥራቅ ከሚባለው ቀጣና ነጥሎ ማየት ይከብዳል፤›› የሚሉት መምህሩ፣ ጦርነቱ ብዙ ዓይነት የጎንዮሽ ተፅዕኖ በኢትዮጵያ ላይ ይዞ የሚመጣ መሆኑን ነው የሚገልጹት፡፡

‹‹ዓለም አቀፍ ገበያን በማናጋት በቀጥታ የኢኮኖሚ ተፅዕኖ ይዞ ይመጣል፡፡ የእስራኤልና የፍልስጤም ጦርነት አያገባኝም ማለት፣ ቦሌ ላይ ተቀምጠህ ሳር ቤት ያለው ችግር አይመለከተኝም እንደ ማለት ነው፡፡ ወደድንም ጠላንም የእስራኤልና የፍልስጤም ቀውስ እስከቀጠለ ድረስ በአንድ ወይ በሌላ መንገድ በኢትዮጵያ ውስጥ ተፅዕኖው መታየቱ የማይቀር ነው፤›› ይላል፡፡

የወቅቱ የእስራኤልና የፍልስጤም ጦርነት የፖለቲካም ሆነ የርዕዮተ ዓለም ፍላጎት ያላቸው ኃይሎችን ከጀርባ ያሠለፈ ነው ብለው፣ ‹‹እንደ ኢራን ያሉ አገሮች ለምሳሌ በዚህ ጦርነት የአይዲዎሎጂም የፖለቲካም ፍላጎት አላቸው፡፡ አሜሪካና አውሮፓዎችም በዚህ ጦርነት የራሳቸውን ተፅዕኖ እያደረጉ ይገኛል፡፡ የዓረብ አገሮች በዚህ ጦርነት ወደ አንድ አቅጣጫ ተሰባስበው የመጡበት ሁኔታም ይታያል፡፡ እነዚህና ሌሎችም በጦርነቱ የራሳቸውን ፍላጎት ለማስፈጸም ከጀርባ የተሠለፉ አገሮች ከመካከለኛው ምሥራቅ አልፈው፣ በአፍሪካ ቀንድና በሌሎች አካባቢዎች ተፅዕኖ መፍጠራቸው የማይቀር ነው የሚሆነው፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡

የእስራኤልና የሐማስ ግጭት ዓለም አቀፍ አጀንዳ መሆኑን የሚጠቅሱት አቶ ዑስማን፣ ‹‹ጉዳዩ እንደ ሰንሰለት ቀለበቶች የተሳሰረ፣ ጂኦ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የንግድና ልማት እንቅስቃሴዎችን የሚነካ ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ያለው ነው፤›› ይላሉ፡፡ ‹‹ሐማስ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካም ሆነ በወታደራዊ አቅም ከማይችላት እስራኤል ጋር ወደ ጦርነት ለመግባት እንዴት ተነሳሳ የሚለው ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ እስራኤል ሐማስን መቆጣጠር አቅቷት ነው ወይ ወደ እዚህ አውዳሚ ጦርነት የገባችው?›› የሚለው ጥያቄ በቅጡ መታየት እንዳለበት የጠቆሙት መምህሩ፣ ‹‹ይህ ጦርነት በአሁኑ ወቅት ለምን ተከሰተ? ከሚለው በስተጀርባ ያሉ ድብቅ ፍላጎቶችን መመርመር ለኢትዮጵያ እጅግ ጠቃሚ ነው፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

የእስራኤልና የሐማስ ወቅታዊው ጦርነት ተባብሶ መቀጠል በሒደት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ላይ ሊያደርስ ስለሚችለው ተፅዕኖ የተጠየቁት በቀድሞ መንግሥት በደኅንነት ተቋም ምክትል ሚኒስትር ሆነው የሠሩትና በአምባሳደርነትም ያገለገሉት አስማማው ቀለሙ (ዶ/ር)፣ ዓረቦቹ ወደ ኢኮኖሚ ማዕቀብ ሊገቡ እንደሚችሉ ይገምታሉ፡፡ ‹‹ዓረቦቹ ያላቸውን የፖለቲካ መሣሪያ ወደ መጠቀም ይገባሉ፡፡ ለዚህ ትልቁ መሣሪያቸው ደግሞ ነዳጅ በመሆኑ፣ ወደ ነዳጅ ማዕቀብ ከገቡ የዓለም ነዳጅ ዋጋ መወደዱ የማይቀር ይሆናል፤›› ይላሉ፡፡

አስማማው (ዶ/ር) አክለው ሲናገሩም፣ ‹‹ጦርነቱ እስከቀጠለ የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ኢራቅ፣ ሶሪያ፣ ኢራን እያለ እንደ የመን ባሉ አገሮች ላይ ጫና ማሳደሯ የማይቀር ይሆናል፡፡ ሐማስን ደጋፊ ናቸው በሚሏቸው ኃይሎች ላይ ምዕራባውያኑ ከማዕቀብ እስከ አየር ድብደባ ሊያደርሱ ይችላሉ፡፡ ይህ ደግሞ የመካከለኛው ምሥራቅ ቀውስን የበለጠ ያወሳስበዋል፡፡ ሌላው ደግሞ ጦርነቱ እየተባባሰ ከሄደ እየተመናመኑ የነበሩ ዓለም አቀፍ የሽብር ቡድኖች የመደራጀት ዕድል ያገኛሉ፡፡ ከአውሮፕላን እስከ መርከብ ጠለፋ፣ ዕገታ፣ ኤምባሲዎችና የጦር ተቋማትን ዒላማ ያደረጉ የሽብር ጥቃቶች ሊባባሱ ይችላሉ፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡ እሳቸው የመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት እስከ ቀጠለ ድረስ በምሥራቅ አፍሪካም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች የሽብር ቡድኖች እንቅስቃሴ መጠናከር እንደሚያሠጋ ነው ያሰመሩበት፡፡

የእስራኤልና የፍልስጤሞች ወቅታዊው ጦርነት በሶማሊኛ ተናጋሪ አካባቢዎች (ኢትዮጵያን ጨምሮ ጂቡቲ፣ ሶማሌላንድና ሶማሊያ) የፈጠረውን ተፅዕኖ በመገናኛ ብዙኃን ከሚያስተጋባው ስሜት በመነሳት እንዲያብራራ የተጠየቀው ጋዜጠኛ እስማኤል ቡርጋቦ በበኩሉ፣ ከባድ ቁጣና የሐዘን ስሜት እንደሚንፀባረቅ ተናግሯል፡፡

‹‹በጋዛ ሰርጥ የቀጠለው የእስራኤል ዕርምጃ ፍልስጤማውያንን ለዕልቂት እየዳረገ ነው የሚል ስሜት ይንፀባረቃል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ ሌላ ዓለም አቀፍ አካል ይህን ዕልቂት ለማስቆም አልቻሉም የሚለው ወቀሳም በሰፊው እየተንፀባረቀ ነው፡፡ ፍልስጤማውያን ከባድ ጥቃት እየደረሰባቸው ነው የሚል ከፍተኛ ሐዘኔታና የፍትሕ ጥያቄ ቢስተጋባም፣ ነገር ግን ምንም ማድረግ ያለ መቻልና የተስፋ ቢስነት ስሜት ጎን ለጎን ይስተጋባል፤›› ይላል፡፡

የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዛ አብዲባሬን የመሳሰሉ ባለሥልጣናት ከሰሞኑ የሰጡትን አስተያየት እንደ ምሳሌ ያነሳው ጋዜጠኛው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐማስን ‹‹የነፃነት ታጋይ እንጂ፣ አሸባሪ ቡድን አይደለም›› ማለታቸው፣ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኖ መሰንበቱን አክሎ ይገልጻል፡፡ ይህንን መሰል ስሜት ደግሞ በምሥራቅ አፍሪካ በተለይም እሱ በሚከታተላቸው የሶማሊኛ ቋንቋ መገናኛ አውታሮች በሰፊው የሚንፀባረቅ ሐሳብ እንደሆነ ነው ያመለከተው፡፡

የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር የተናገሩት አስተያየት ከባድ ውዝግብ ያስነሳ ሲሆን፣ አንዳንድ ወገኖች ሰውየው በሽብር አደጋ፣ በግጭትና በረሃብ ለሚረግፉ ሶማሊያውያን ቅድሚያ ቢሰጡ የተሻለ እንደሆነ የአፀፋ ምላሽ ሲሰጡ ታይቷል፡፡ ከዚህ አለፍ ያሉ ደግሞ እ.ኤ.አ. ከ2021 ወዲህ ብቻ አሜሪካ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰብዓዊ ዕርዳታ ለሚሹ ዜጎች ወደ 2.5 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጓን፣ ከዚህ ውስጥ ደግሞ 1.3 ቢሊዮን ዶላር ድጋፉን ሶማሊያ መውሰዷን በመጥቀስ የሶማሊያ ባለሥልጣናት እስራኤልና ምዕራባውያን አጋሮቿን ለመወንጀል የሞራል ድፍረት ሊኖራቸው እንደማይገባ የአፀፋ ምላሽ ሲሰጡ ነበር፡፡ 

አንዳንድ ወገኖች የሚገምቱት የእስራኤልና የሐማስ ግጭት በተለያዩ አገሮች ዜጎች መካከል የሚፈጥረው የስሜት ልዩነት ግጭቱ እስከቀጠለ ድረስ የማይገመት ውጤት ሊፈጥር እንደሚችል ነው፡፡ እስራኤልና ፍልስጤም የሚወዛገቡበት የመካከለኛው ምሥራቅ ምድር በሦስቱም ጥንታዊ እምነቶች ማለትም በአይሁድ፣ በክርስትናና በእስልምና የተለየ ቅድስና የሚሰጠው ቦታ መሆኑን ለዚህ እንደ ቁልፍ ምክንያትነት ያስቀምጡታል፡፡

ሦስቱንም ጥንታዊ ሃይማኖቶች ቀድማ በማስተናገድ ከዓለም የምትጠቀሰዋና በሃይማኖቶች መቻቻል ባህል ለዓለም ምሳሌ ናት የምትባለዋ ኢትዮጵያም ቢሆን፣ የእስራኤልና የፍልስጤም ግጭት ሊፈጥረው በሚችለው ሃይማኖትን መሠረት ባደረገ የመከፋፈል ተፅዕኖ ውስጥ ልትገባ እንደምትችል ነው የሚገመተው፡፡    

የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ መምህር አቶ ዑስማን መሐመድ፣ ‹‹የመካከለኛው ምሥራቅ ቀውስ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ በተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች መካከል የነበረው ተቻችሎ የመኖር ስሜት በሒደት በመገፋፋት እየተተካ እንዲሄድ ሊያደርግ ይችላል፤›› በማለት ሥጋታቸውን ይጋራሉ፡፡ የዚህ ሐሳብ ጋር የሚስማማው ጋዜጠኛ ኢስማኤል በበኩሉ፣ ግጭቱ ሃይማኖት ሳይመርጥ ሙስሊሞችን፣ አይሁዶችንም ሆነ ክርስቲያኖችን ሰለባ እያደረገ ቢሆንም እንኳን፣ ይህንን በጥንቃቄ አጢኖ ሚዛናዊ አቋም ለመውሰድ ሰዎች እንደሚቸገሩ ነው የሚናገረው፡፡ ‹‹ፍልስጤም ውስጥ እኮ ክርስቲያኖች አሉ፡፡ ጦርነቱ ግን ክርስቲያን ከሙስሊም ሳይለይ ነው እየገደለ ያለው፤›› ይላል፡፡

‹‹እስራኤልና ፍልስጤም በተጋጩ ቁጥር ወዲያው ወላፈኑ ይገርፈዋል፤›› የሚባለው ኢትዮጵያ የምትገኝበት የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና፣ በመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳይ ሁሌም ሲፈተን መኖሩን ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ በእስራኤልና በዓረቦች መካከል ግጭት በተፈጠረ ቁጥር ብቻ ሳይሆን፣ ሰላም ተፈጠረ በተባለ ወቅትም ቢሆን የአፍሪካ ቀንድ ከመካከለኛው ምሥራቅ ተፅዕኖ ተላቆ እንደማያውቅ ብዙዎች በማስረጃ ይሞግታሉ፡፡

በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሥልጣን ዘመን በአማቻቸው ጄርድ ኩሽነር ይመራ የነበረው ‹‹ዲል ኦፍ ዘ ሴንቸሪ›› በተባለው የሰላም ጥረት ወቅት ይህ ጎልቶ መታየቱን በምሳሌነት ያወሱታል፡፡ በዓረቦችና በእስራኤሎች መካከል ግንኙነትን ማሻሻልን ግብ አድርጎ የነበረው ይህ የሰላም ጥረት እስራኤል ከሞሮኮ፣ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ከባህሬንና ከሱዳን ጋር በተፈራረመችው ‹አብረሃም አኮርድ› በተባለ የግንኙነት ማሻሻያ ስምምነት ነበር የተጠናቀቀው፡፡ አሜሪካ ይህ የሰላም ጥረቷ በዓለም አገሮች በተለይ በዓረቡ ዓለም ተቀባይነት እንዲያገኝ በሚል ብዙ ዲፕሎማሲያዊ ግፊት ስታደርግ ቆይታለች፡፡

ሱዳንን ከእስራኤል ጋር ስምምነት ያፈራረመችው አሜሪካ፣ በጊዜው ኢትዮጵያ በምትገነባው ታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ ከሱዳንና ከግብፅ ጋር የሚደረገውን የሦስትዮሽ ድርድርም ትመራ እንደነበር ያስታውሱታል፡፡ አሜሪካ ለጀመረችው ዓረቦችን ከእስራኤል ጋር የማስታረቅ ጥረት ግብፆቹና ሱዳኖች ላሳዩት ድጋፍ ውለታ መዋል የፈለገችው አሜሪካ፣ በህዳሴው ግድብ ድርድር ላይ የኢትዮጵያን ጥቅም በመደፍጠጥ ብድር ለመመለስ ጥረት ማድረጓን በርካቶች ይገልጻሉ፡፡  

የአልጄዚራው ከፍተኛ የፖለቲካ ተንታኝ ማርዋን ቢሻራ እ.ኤ.አ. መጋቢት 2020፣ ‹‹The toxic fallout of the ‘deal of the century’›› በሚል ርዕስ ባስነበበው ሰፊ ዘገባ የግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱል ፋታ አልሲሲ የትራምፕን የመካከለኛው ምሥራቅ የሰላም ዕቅድ በመደገፋቸው የተነሳ፣ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ድርድር ላይ የአሜሪካ መንግሥት ኢትዮጵያውያንን የሚጫን አቋም እያንፀባረቀ ነው በማለት ነበር የወቅቱን ሁኔታ የገለጸው፡፡

በዓረቦችና በእስራኤሎች መካከል ግጭትም ሆነ ሌላ የተለየ ሁኔታ በተፈጠረ ቁጥር ተፅዕኖ የሚያርፍበት የአፍሪካ ቀንድ በየመንና በሶሪያ በተካሄዱ ጦርነቶች ወቅት ይህንን እንዳየ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ የዓረቡ ዓለምን ባዳረሰው የፀደይ አብዮት ወቅትም ሆነ በኢራቅ ጦርነቶች ወቅት ቀጣናው የመካከለኛው ምሥራቅ ወላፈንን ቀምሶታል ይላሉ፡፡ እንደ አይኤስና አልቃይዳ ያሉ የሽብር ቡድኖች በመካከለኛው ምሥራቅ በተንሰራፉ ወቅት፣ እንደ አልሸባብ ያሉ የሽብር ርዕዮተ ዓለም ተጋሪ ቡድኖችን ቀጣናው በማፍራት ችግሩን መጋራቱን ያስታውሳሉ፡፡

በቅርብ ጊዜ በቻይና አሸማጋይነት በተደረገ ስምምነት በረድ የማለት አዝማሚያ ቢያሳይም፣ ዘመናትን በተሻገረው ‹‹ሺዓ›› እና ‹‹ሱኒ›› የሚል የሃይማኖት ርዕዮተ ዓለማዊ ልዩነትን መሠረት ባደረገው በኢራንና በሳዑዲ ዓረቢያ መካከል ሲካሄድ በቆየው ውዝግብ የተነሳም፣ የአፍሪካ ቀንድ ብዙ መፈተኑ ይነገራል፡፡ ከኢራንና ከሳዑዲ ዓረቢያ የሃይማኖት ርዕዮተ ዓለም ፍትጊያ በዘለዓለም ቀጣናውን የከፈለው የሳዑዲና የኳታር ውዝግብም የአፍሪካ ቀንድ መፈተኑ ይነገራል፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች መካከል የሚፈጠር ፀብም ሆነ ዕርቅ በተለየ መንገድ ኢትዮጵያ የምትገኝበትን ምሥራቅ አፍሪካንም ሲነካ መቆየቱን ነው ብዙ ተንታኞች የሚናገሩት፡፡

የወቅቱን የሱዳን ጦርነት ምሳሌ የሚያደርጉት እነዚህ ወገኖች የጄኔራል አብዱልፈታ አል ቡርሃንና የጄኔራል መሐመድ ሀምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) ኃይሎች የእርስ በእርስ ግጭት፣ በቀጥታ የሳዑዲና የዓረብ ኤምሬትስ የእጅ አዙር ጦርነት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

የመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳይ አጥኚ በሆነው ታላል መሐመድ “How Sudan Became a Saudi-UAE Proxy War” በሚል ርዕስ በቀረበው የፎሬን ፖሊሲ መጽሔት ትንተና ላይ፣ ከአል ቡርሃን ጀርባ የቆሙት ሳዑዲዎችና ከሄሜቲ ጎን የተሠለፉት የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በእጅ አዙር ጦርነት ሱዳንን እንዳንኮታኮቷት በሰፊው ይዘረዝራል፡፡

የአቡዳቢው ፕሬዚዳንት መሐመድ ቢን ዛይድ እያስተማሩ ካሳደጉት ታናሻቸው ከሳዑዲው ልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን ጋር የፈጠሩት በመካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካ ላይ የበላይ የመሆን ሽኩቻ ሱዳንን እንደበላት በዘገባው ተመልክቷል፡፡ የገልፍ አገሮች ምክር ቤት በሚባለው ማኅበር በኩል የኢኮኖሚ ውህደት እንዲፈጠርና የጋራ መገበያያ እንዲጀመር የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ እ.ኤ.አ. በ 2009 ካቀረበችው ዕቅድ ጀምሮ በየመን ጦርነት፣ በቀይ ባህር ፖለቲካ፣ በኳታርና ኢራን፣ እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ላይ ባራመዱት ልዩነት ግንኙነታቸው የሻከረው ሁለቱ አገሮች በስተመጨረሻ ሱዳንን የጦር ዓውድማቸው እንዳደረጉ ነው ይህ ዘገባ የተረከው፡፡

ከዚህ በመነሳት ከዓረቦችና ከእስራኤሎች ግጭት በዘለለ በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች መካከል የሚኖር የግንኙነት መስተጋብር፣ የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካን ሲበይን መኖሩን ነው በርካታ ምሁራን የሚናገሩት፡፡

‹‹ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ›› በ2012 ዓ.ም. ‹‹ዴሞክራሲያዊ የለውጥ ዕርምጃዎች፣ አንድምታዎችና አማራጮቻቸው በኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ ከአካባቢ አገሮች ጋር ያላት ግንኙነትና የዓባይ ውኃ ጉዳይ›› በሚል ርዕስ ባቀረበው ቅጽ 3 ጥናታዊ ዕትም ላይ፣ የኢትዮጵያና የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ግንኙነትን የሚወስኑ ጠቃሚ ጉዳዮች የተፈተሸበት ጽሑፍ ይገኛል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ምሁሩ አስናቀ ከፋለ (ዶ/ር)፣ ‹‹የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ከጎረቤትና ከዓረብ ባህረ ሰላጤ አገሮች ጋር ያላት ግንኙነት›› በሚለው ምዕራፍ ሥር፣ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን የሚበይኑ የጂኦ ፖለቲካ ጉዳዮች በአምስት ክፍሎች ተዘርዝረዋል፡፡

የመጀመሪያው የቀጣናው አገሮች ሉዓላዊ ድንበሮች በተገቢው መንገድ (በስምምነት) የተካለሉ አለመሆናቸው ጉዳይ ተብሎ ተቀምጧል፡፡ ኢትዮጵያን በተመለከተ ከኬንያ ጋር ከምትጋራው ድንበር ውጪ በሌሎች አቅጣጫዎች ድንበሯ ገና ያልተካለለ በመሆኑ ለግጭት ስትዳረግ መኖሯን በምሳሌነት ያነሳል፡፡

ሁለተኛው የቀጣናው ጂኦ ፖለቲካ ወሳኝ ጉዳይ ከየትኛውም የዓለም ክፍል በላይ የመገንጠል ጥያቄና ግጭቶች የሚስተናገድበት ቀጣና መሆኑ ነው ይላል፡፡ በኤርትራና በደቡብ ሱዳን ለ30 ዓመታት የዘለቁ የመገንጠል ጦርነቶችን ማሳያ በማድረግ፣ ይኼው ታሪክ በሌሎች የቀጣናው አካባቢዎችም ሲደጋገም መታየቱን ያነሳል፡፡

ሦስተኛው ቀጣናው ለኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት እጅግ ከፍ ያለ ሥልታዊ ጠቀሜታ ያለው የመሆኑ ጉዳይ ተብሎ ተመልክቷል፡፡ የአውሮፓና የእስያ አኅጉር ንግድ ልውውጥ ወሳኝ መሸጋገሪያ የሆነው የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ለግጭት፣ ለሽብርና ለባህር ውንብድና ባለው ተጋላጭነት የተነሳ የብዙ ኃያላን አገሮች ትኩረት ያረፈበት መሆኑንም ያወሳል፡፡ ኃያላኑ የራሳቸውን ጂኦ ፖለቲካዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ ጦር ለማስፈር መሽቀዳደማቸው ደግሞ፣ ይህንን ለኢትዮጵያ ሥልታዊ ጠቀሜታ ያለውን ቀጣና ውጥረት ውስጥ ከቶታል ይላል፡፡

አራተኛው የቀጣናውን ጂኦ ፖለቲካ የሚበይን ጉዳይ ደግሞ ድንበር ዘለል የሽብር አደጋ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ ከኒውዮርኩ የአሜሪካ ጥቃት ቀደም ብሎ ሱዳን አልቃይዳን በማስጠለል የምትከሰስ አገር እንደነበረች ያስታውሳል፡፡ አሜሪካ መራሹ ዓለም አቀፍ የፀረ ሽብር ዘመቻ ከታወጀ በኋላ ደግሞ ሶማሊያ የሽብርተኞች መናኸሪያ በመሆን ስትወነጀል ቆይታለች፡፡ የዚህ ድንበር ዘለል ሽብር አደጋ ሰለባ የሆኑት እንደ ኢትዮጵያ፣ ኬንያና ኡጋንዳ ያሉ አገሮች ደግሞ የዓለም አቀፉ ፀረ ሽብር ዘመቻ አጋር በመሆን ሲካፈሉ ቆይተዋል፡፡

አምስተኛው ድንበር አቋራጭ የተፈጥሮ ሀብቶች አጠቃቀም ጉዳይ መሆኑ ተቀምጧል፡፡ የኢትዮጵያ ታላላቅ ወንዞች ድንበር ተሻግረው ወደ ጎረቤት አገሮች የሚፈሱ የጋራ የተፈጥሮ ሀብቶች ቢሆኑም፣ ከእነዚህ አገሮች ጋር ይህ ነው የሚባል በጋራ የመጠቀም፣ መግባባትና ስምምነት መፍጠር አለመቻሉ ቀጣናውን ተፅዕኖ አሳድሮበት መቆየቱን ያስረዳል፡፡ ቀይ ባህርንም የጋራ ቀጣናዊ ሀብት ሲል ይጠቅሰዋል፡፡

ጥናቱ በዓረብ ባህረ ሰላጤ አገሮች መካከል ያለው ግጭትና የፖለቲካ ውጥረት የሥጋት ምንጭ ነው በሚል ሐሳብ ነው ሐተታውን የሚያጠቃልለው፡፡

ከሰሞኑ ‹‹ከዕዳ ወደ ምንዳ›› በሚል ርዕስ በተከታታይ እየቀረቡ ባሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ገለጻዎች ላይ ይኼው ዕሳቤ በተለየ መንገድ ሲነገር ተደምጧል፡፡ በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲና የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ውስጥ ትልቅ ቦታ ስለተሰጠው ጉዳይ በሰፊው ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ምሥራቅ አፍሪካ ቀንድና ቀይ ባህርን በትኩረት ማንሳታቸው ይታወቃል፡፡

‹‹የቀይ ባህርና የዓባይ ጉዳይን የዘነጋ ፖሊሲ ለኢትዮጵያ ምኗም አይደለም፤›› ያሉት ዓብይ (ዶ/ር)፣ ‹‹የአፍሪካ ቀንድና የቀጣናውን ሰላማዊ ሁኔታና መስተጋብር ፖሊሲያችን ከግምት ያስገባ መሆን አለበት፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ባላው በመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳይም ሆነ በሌሎች ዓለም አቀፍ አጀንዳዎች ላይ ገለልተኝነት የተከተለ አቋም ስታራምድ እንደቆየች የሚያስታውሱት አስማማው (ዶ/ር)፣ ይህን አቋሟንም የአፍሪካ አገሮች የጋራ አቋም ስታደርግ መቆየቷን ያወሳሉ፡፡ ‹‹እነ ከተማ ይፍሩና ምናሴ ኃይሌ (ዶ/ር) የመሳሰሉ ጠንካራ የውጭ ጉዳይ ባለሥልጣናት በነበሩበት ወቅት እንዲህ ዓይነት አሳሳቢ ዓለም አቀፍ ጉዳይ ሲከሰት ወዲያውኑ የዲፕሎማቲክ ልዑክ ወደ አፍሪካ አገሮች የመላክ ልማድ ነበር፡፡ ገለልተኛ የሆነ አቋም በአፍሪካ ኅብረት ደረጃ የማራመድን አስፈላጊነትን ለአፍሪካ አገሮች ለማሳመን ነበር ይህ የሚሠራው፡፡ የአፍሪካ አገሮች በኢትዮጵያ አነሳሽነት የጋራ አቋም መያዛቸው ከዓረቦችም ሆነ ከምዕራባዊያኑ ጫና እንዳያርፍባቸው ሲያደርግ ነው የቆየው፤›› በማለትም ያስረዳሉ፡፡

አሁን ገለልተኛ አቋም ብትይዝም ኢትዮጵያ ይህንን ተነሳሽነት ስትመራ እንደማትታይ የተናገሩት አስማማው (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር የጋራ አቋም ብትይዝ ተጠቃሚ ትሆናለች ነው ያሉት::

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -