በዓለም አቀፍ ደረጃ መሥፈርት መሠረት የአንድ ከተማ የአየር ጥራት ደረጃ ከአምስት ሚክሮ ግራም ፐር ሜትር ኪዩብ መብለጥ የለበትም፡፡ ከተጠቀሰው ደረጃ በላይ ሆኖ ከተገኘ ግን ለአየር መበከል አስተዋጽኦ ከሚያደርጉ ጋዞችና ብናኝ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ልዩ ዓይነት የጤና ችግሮች እንደሚከሰቱ በአየር ጥራት ዙሪያ የሚንቀሳቀሰው C-40 የተባለው ዓለም አቀፍ ድርጀት የምሥራቅ አፍሪካ የቴክኒክና ጥራት አማካሪ ይገልጻሉ፡፡
አዲስ አበባን ጨምሮ ከሰባት የአፍሪካ ከተሞች የተውጣጡ የተግባቦትና የአየር ጥራት ባለሙያዎች ተሳታፊ የሆኑበትና ለሁለት ቀናት የተካሄደውን ዓውደ ጥናት አስመልክቶ አማካሪው አቶ ጥበቡ አሰፋ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከሚከሰቱት የጤና ችግሮች መካከል በዋናነት ምት (ስትሮክ)፣ ጭንቀት፣ የመተንፈሻ አካላትና የልብ በሽታዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡
የአዲስ አበባ የአየር ጥራት ከዓለም አቀፉ ደረጃ ከሦስት እስከ አራት እጥፍ እንደሚበልጥ ወይም ከ15 እስከ 20 ሚክሮ ግራም ፐር ሜትር ኪዩብ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም የአየሩን ጥራት ደረጃ ከዓለም አቀፍ ደረጃ ጋር ለማጣጣምና ለማቀራረብ የሚያስችል ተግባር እየተከናወነ መሆኑን፣ ለዚህም ስኬታማነት C-40 የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግና የአየር ጥራት መከታተያ መሣሪያዎችን በማቅረብ ረገድ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አስረድተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የአየር ጥራትንና የብክለት መጠንን በየሰዓቱና በየጊዜው እየመዘገቡ ለኮምፒዩተር የሚያስተላልፉ መሣሪያዎች በተለያዩ አሥር ቦታዎች ላይ ተተክለዋል ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዲዳ ድሪባ ናቸው፡፡
እንደ ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ መሣሪያዎቹ የተተከሉት ክፍለ ከተሞችን ማዕከል ባደረገ፣ የትራንስፖርትና የሕዝብ እንቅስቃሴዎች የሚበዛባቸውን አካባቢዎች ባገናዘበ መልክ ነው፡፡
መሣሪያዎቹን ያቀረበው C-40 የተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት መሆኑንና በአገር ውስጥና በውጭ አገር ባለሙያዎች መተከሉን ያስታወሱት ሥራ አስኪያጁ፣ አዲስ አበባ የድርጅቱ አባል መሆኗ ባለሥልጣኑ በአየር ንብረት ዙሪያ ፕሮጀክት ቀርጾ ለተግባራዊነቱ ማስፈጸሚያ የሚሆን የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያገኝ አስችሎታል ብለዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ የአካባቢ ብክለትን ለመቆጣጠርና የግንዛቤ ሥራ ለማከናወን የሚጠቅሙ ቴክኖሎጂዎችን በቅርበት ለማግኘት ጥሩ አጋጣሚ እንደተፈጠረላቸውም አክለዋል፡፡
ለአየር ብክለት መንስዔዎች ከአሮጌ ተሽከርካሪዎች፣ ከኢንዱስትሪ፣ በየሜዳው ከሚቃጠሉ ደረቅ ቆሻሻዎችና ከሌሎችም የሚወጡ ልቀቶች እንደሚገኙበት ገልጸው፣ ከኢንዱስትሪና ከሚቃጠለው ደረቅ ቆሻሻ የሚመነጨው ጢስ ይህን ያህል የከፋ ችግር እንደማያስከትሉ አስረድተዋል፡፡
እንደ አቶ ዲዳ፣ ከኢንዱስትሪ የሚወጣው ብክለት ለከፋ ችግር የማይዳርገው በከተማዋ የኢንዱስትሪዎቹ ቁጥር አነስተኛና የሚቋቋሙትም በዓለም አቀፍ ደረጃ የወጣውን ደረጃ ጠብቀው በመሆኑ ነው፡፡
የሚፈለገውን ጥንቃቄ ሳያሟሉ ከተገኙና የሚያወጡትም በካይ ነገር ከደረጃ በላይ ሆኖ ከተገኘ የገንዘብ መቀጫና እስከ ማሸግ ድረስ የሚዘልቅ ቅጣት እንደሚጣልባቸው ገልጸዋል፡፡
ከአሮጌ ተሽከርካሪዎች የሚለቀቀው በካይ ነገር ከተቀመጠው ደረጃ ጋር የማይመጣጠን መሆኑን፣ ይህን የሚቆጣጠር መመርያ በመረቀቅ ላይ እንደሚገኝና በረቂቁ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እንደሚኖር ተናግረዋል፡፡
አሮጌ ተሽከርካሪዎችን በአዲስ መተካት፣ አለበለዚያ ያለአገልግሎት እንዲቀመጡ ከተሳካም የሚያወጡትን በካይ ነገር የሚቀንስ ቴክኖሎጂ እንዲገጠምላቸው ማድረግ አማራጭ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከጥቅምት 27 እስከ 29 ቀን 2016 ዓ.ም. በጌትፋም ሆቴል በተካሄደውና ከአዲስ አበባ፣ ናይሮብ፣ ሌጎስ፣ ፍሪታውን፣ ጆሃንስበርግ፣ ደርባንና ሸዋኔ (ፕሪቶሪያ) ከተሞች የተውጣጡ ባለሙያዎች ተሳታፊ የሆኑበት የዚህ ዓውደ ጥናት የትኩረት አቅጣጫ በግንዛቤ ማጎልበቻ፣ በመረጃና በተሞክሮ ልምድ ልውውጦች፣ የአየር ጥራት መረጃን በመተንተንና ተግባቦት በማድረግ ላይ ያለመ ነው፡፡
ዓለም አቀፉ ድርጅት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር በመተባበር ባካሄደው በዚሁ ሥልጠና ሰባቱ ከተሞች ሊሳተፉ የቻሉት በአየር ጥራት ላይ ለመሥራት ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው መሆኑ በመረጋገጡ ነው፡፡
C-40 የተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት የተቋቋመው፣ የዓለም የሙቀት መጠን ከአንድ ነጥብ አምስት ሴንቲግሬድ በላይ እንዳይወጣ የተደረሰበትን ስምምነት ተግባራዊ ለሚያደርጉ አገሮች ተገቢውን የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ በመስጠት እንዲተባበራቸው በማሰብ ነው፡፡
እ.ኤ.አ. በ2015 ፈረንሳይ በተካሄደው የአየር ንብረት ዓለም አቀፍ ጉባዔ ላይ የተደረሰበትን ይህንኑ ስምምነት የፈረሙት 100 አገሮች ሲሆኑ፣ ከእነዚህም ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ ናት፡፡